Print this page
Sunday, 31 July 2011 12:49

እኔ ጨረቃዋን ሳሳየው እሱ ጣቴን ይመለከታል..

Written by  መሐመድ አደም
Rate this item
(0 votes)

ሐምሌ 16/2003 ዓ.ም ታትሞ በወጣው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ..በአደባባይ ሙግት የተረቱበትን፤ በጦማር ምን ያደርጉታል?.. በሚል ርዕስ የቀረበውን የአቶ ዘሩባቤል አሰፋን ጽሁፍ አነበብኩት፡፡ ጽሁፋቸውን ሳነብብ፤ የነገር አያያዛቸው ..እኔ ጨረቃዋን ሳሳየው፤ እርሱ ጣቴን ይመለከታል.. ቢያሰኘኝም፤ ሀሳብን - ከፀሃፊው መለየት ተስኗቸው ..ስሜት እና ግምት.. ወሰድ መለስ ሲያደርጋቸው ብመለከትም አስተያየታቸውን እጅ ነስቼ እቀበላለሁ፡፡

የፕሬስ ነፃነት በተከበረበት፤ የሃሳብ ገበያ የሆኑ ፕሬሶች ባሉበት ሀገር ስንኖር እኔም እርስዎም ከዚህ ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ ስለዚህ እንኳንስ ክቡር የማዕዘን ድንጋይ በሚሆን ፍትህን በሚመለከት ጉዳይ ላይ፤ ..በስፒል ጭንቅላት ምን ያህል መላዕክት ሊደንሱ ይችላሉ?.. በሚል ጥያቄ ዙሪያ አስተያየት ማቅረብ - የሚያስተናግደው ከተገኘ - ነውር አይደለም፡፡ በፍርድ ቤት ታይቶ ውሳኔ ባገኘ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠትማ ፍጹም ተገቢ ነው፡፡ በህይወትና ንብረታችን ላይ ፍርድ የመስጠት ሥልጣን የተሰጣቸውን ፍርድ ቤቶች አሰራር ማየትና መወያየት ካልቻልን፤ ግድፈቶች ካሉ እንዲታረሙ ካልጣርን የዲሞክራሲ ስርዓት የሚገባቸው ዜጎች ልንሆን አንችልም፡፡ ስለዚህ አስተያየቴን እሰጣለሁ፡፡ እርስዎም በሼል ጉዳይ ብቻ ሣይሆን ለሀገር በሚጠቅሙ ሌሎች አጀንዳዎች ላይ አስተያየት ቢሰጡ እወዳለሁ፡፡ ግን ውይይታችን፤ አሁን እንዳደረጉት፤ ሀሳብን - ከሃሳቡ ባለቤት ባይቀላቅል ጥሩ ነው፡፡ በተረፈ የውይይት አጀንዳ ባደረግነው ጉዳይ መነጋገራችንም ሆነ መከራከራችን ትርፍ እንጂ kþú‰ የለውም፡፡ እንግዲህ ወደ ዋናው ጉዳይ ልመለስ፡፡
ዋናው ጉዳይ
አቶ ዘሩባቤል ለፅሁፋቸው በመረጡት ርዕስ ውስጥ ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮችን አያለሁ፡፡  የመጀመሪያ ..የአደባባይ ሙግት.. ያሉት የሀሳብ ነፃነትን ይጠቅሳል፡፡ በፍርድ ..የተረቱበትን በጦማር ምን ያደርጉታል?.. የሚለው ደግሞ የፍትህን፤ የዳኝነት ነፃነትን ጉዳይ ያሳስባል፡፡ የኔ አስተያየትም በእነዚሁ ነጥቦች ላይ የሚያጠነጥን ይሆናል፡፡
አቶ ዘሩባቤል አሰፋ፤ በሼል እና በአቶ ኃይሉ መካካል የተካሄደውን ክርክር መርምሮ ውሳኔ በሰጠው ፍርድ ቤት ብይን ላይ አስተያየት መፃፌ አላስደሰታቸውም፡፡ የፅሁፌንም ዓላማ በአደባባይ ሙግት የተረቱበትን ነገር በጦማር ለመቀየር ማሰብ አድርገው ወስደውታል፡፡ በዚሁ መነሻም አስተያየት ፅፈዋል፡፡
ስለዚህ የእኔና የአቶ ዘሩባቤል አስተያየት እና አቋም የተለያየ ሆኗል፡፡ በዚህ ብንለያይም ይህን ልዩነታችንን በነፃነት - በአደባባይ የመግለፅ መብት አንድ ያደርገናል፡፡ ስለዚህ ከልዩነታችን ባሻገር ሁለታችንም በጋራ ልንቆምላቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡ እነርሱም፤ ነፃነት፤ ፍትህ፤ ዴሞክራሲያዊ ወዘተ ናቸው፡፡
ሁለታችንም፤ ሀሳባችንን በነፃነት መግለፅ የቻልነው፤ የሃሳብ ነፃነት የተከበረበት ስርዓት በመኖሩ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ዕድል ማግኘት የሚቻለውም በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ነው፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች እኔና አቶ ዘሩባቤል መለያየት የለብንም፡፡ እኔም አቶ ዘሩባቤልም ለዚህ ስርዓት ዘብ የመቆም ኃላፊነት አለብን፡፡
ታዲያ ፀሐፊው እንደ ገለፁት ..በአደባባይ ሙግት የተረቱበትን በጦማር ምንም ማድረግ የማይቻለው.. በዲሞክራሲያዊና የህግ የበላይነት በተከበርበት ስርዓት ነው፡፡ ስለዚህ ለፍትህና ለዴሞክራሲ ነገር እኔም እርሳቸውም፣ በጥቅሉ የዚህች አገር ዜጎች፤ በጋራ መቆም አለብን፡፡ ይህን የማድረግ የምንችለውም፤ የምንጠላውን ሀሳብ የመግለፅ ዕድል በመቀበል ነው፡፡  
ይህን ሀሳቤን የሞንታኝ ቃል ይበልጥ ይገልጠዋል፡፡ ሞንታኝ እንዲህ አለ፤ ..አንተ የምትለውን አልደግፍም፡፡ ሆኖም ይህን የማልደግፈውን ሀሳብህን እንዳትናገር የሚከለክልህ ኃይል ቢመጣ ከአንተ ጎን እሰለፋለሁ፡፡.. እንግዲህ እኔም እርስዎም እንዲህ ያለ አቋም መያዝ ይኖርብናል፡፡ ይህን ማድረግ ሲሳነን ወይም የነፃነትን ዋጋ በምንጠላው ሰው እና ሀሳብ በለወጥናት ጊዜ፤ ..ይህን ሃሳብ እንዴት ታነሳለህ.. ማለት በጀመርን ሰዓት ነጻነት ትጠፋለች፡፡ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት ልዩ ናት፡፡ ፍትህና ተጠያቂነት እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ አላት፡፡ ይህች ነፃነት የምትኖረውም የህግ የበላይነት ወይም ፍትህ በሰፈነበት ሀገር ስለሆነ፤ ስለ ፍትህ በነፃነት (በጦማር) መነጋገራችንን መጥላት ወይም ማውገዝ የለብዎትም፡፡ ..በአደባባይ ሙግት የተረቱበትን ነገር በጦማር ምንም ማድረግ የማይቻለውም.. በእንዲህ ዓይነት ስርዓት ውስጥ ነው፡፡ ይህ ስርዓት ሲጠፋ ነገሮች የሚወሰኑት በሙግት ወይም በነፃ በዳኝነት መሆኑ ቀርቶ፤ በቀላጤ ይሆናል፡፡ ያኔ ..በአደባባይ ሙግት.. ሳይሆን፤ በኃይል (_YT) መረታት ይመጣል፡፡
ከዚህ አደጋ ለመጠበቅ ወይም በ..ፍርድ አደባባይ በተካሄደ ሙግት የተወሰነን ጉዳይ በጦማር ወይም በቀላጤ የማይለወጥበት ፍትሃዊ ስርዓት እንዲኖር፤ የዳኝነት ነፃነት የተከበረበት ወይም የህግ የበላይነት ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲፀና ነቅተን እንጠ ብቅ፡፡ ይህ ስራችን በነፃነት ከመነጋገር ይጀምራል፡፡ ታዲያ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት፤ ፍ/ቤቶች በአደባባይ ሙግት በሰጡት ውሳኔ ላይ አስተያየት መስጠት ይቻላል፡፡ የፍርድ ቤቶች የዳኝነት ነፃነት ተቋማቱን ከህዝብ አስተያየት ነፃ አያወጣቸውም፡፡ ስለዚህ በሼል ኢትዮጵያ እና በአቶ ኃይሉ መካከል የተነሳውን ክርክር በማዳመጥ የሀገራችን ፍ/ቤት በሰጡት ውሳኔ ላይ አስተያየት መፃፌ የሚነቀፍ አይደለም፡፡ እንዲህ ማድረግም፤ ..በአደባባይ ሙግት በፍ/ቤት የተወሰነን ጉዳይ በጦማር.. ለመለወጥ መፈለግን አያመለክትም፡፡
እንኳን እኔ፤ ..ምስክርነታቸው የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሀብትነትን ለማቀዳጀት አግባብነትና ብቃት የለውም.. ያሏቸው፤ ካወጡት መመሪያና ከአሰራራቸው ተቃራኒ የሆነ ውሳኔ የተወሰነባቸው መስተዳድሮችም ምንም ማድረግ እንዳልቻሉ እርስዎ ምስክር ነዎት፡፡ እና የኔ ጦማር ምን ያመጣል? ግን የፍትህ ሞገስ የሆነው ህዝብ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ፖሊሲ አውጭዎች ያዩት ይሆናል፡፡ የፍ/ቤት ውሳኔን ተቀብሎ፣ የህግ የበላይነትን አክብሮ የሚያድር መንግስት አስፈላጊ ነው፡፡ እንኳንስ በጦማር፤ በሥልጣንና በሹመት ፍርድ እንዲለወጥ ማድረግ ባልፈልግም፤ የፍ/ቤት ውሳኔ ከመንግስት መመሪያ ተቃራኒ ሲሆን መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ ስለዚህ፤ በተሰጠው ውሳኔ እንደ ዜጋ አስተያየት ማቅረቤን ከመብትም ከንቁ ዜጋ ተግባርም ሊቆጥሩት ይገባል፡፡
እንደሚያውቁት ..የቤቱ እና የቦታው ህጋዊ ባለ ይዞታ ማነው?.. የሚል ጥያቄ ምላሽ  የሚያገኘው፤ እርስዎ ..ብቃት እና አግባብነት ያለው.. ማስረጃ በሆነው የቦታ ካርታ ነው፡፡ ሆኖም እንዲህ ያለ ማስረጃ አልተገኘም፡፡ የመስተዳድር መስሪያ ቤቶች በሼልም ሆነ በአቶ ኃይሉ ማህደር የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር አላገኙም፡፡ ሆኖም ችግሩ አሁን አከራካሪ  በሆነው ቦታ ብቻ አይደለም፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመላ ሀገሪቱ እንዲህ ያለ ሰነድ የሌላቸው በርካታ ቤቶችና ቦታዎች አሉ፡፡ ችሎት ቀርበው እንዲያስረዱ የተጠሩት የመስተዳድሩ ኃላፊዎች ..በአዲስ አበባ መስተዳድር ውስጥ የቦታ ካርታ የሌላቸው 80 ሺህ ባለ ይዞታዎች አሉ.. ብለዋል፡፡
ከእነሱ በተጨማሪ፤ ባለፈው ወር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ..ፊት ለፊት.. የተሰኘ ፕሮግራም ቀርበው የነበሩት የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ችግሩ ሀገር አቀፍ መሆኑን ገልጸው ..ከአፄ ኃ/ስላሴ ዘመን ጀምሮ ሲንከባለሉ የመጡ ሰነድ አልባ ይዞታዎች አሉ፡፡ ይህ ለከተሞች ዕድገት እና ልማት እንቅፋት ፈጥሯል፡፡ እናም ለዚህ ችግር የመጨረሻ እልባት መስጠት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መንግስት የወሰደው እርምጃ የውሃና የመብራት ወዘተ አገልግሎት ክፍያ ሰነዶችን በስሙ ሲከፍል የቆየ ሰው የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ እንዲያገኝ ማድረግ ነው የሚል ውሳኔ ላይ ደርሰን መመሪያ ወጥቷል፡፡ በዚሁ መሰረት ተግባራዊ እየተደረገ ነው.. ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ታዲያ ጋዜጠኛው፤ እንደርስዎ ..እንዴት እንደዚህ ይደረጋል?.. አለ፡፡ የሚኒስትሩ ምላሽ አጭር ነበር፡፡ ..ሌላ አማራጭ የለንም.. የሚል፡፡ በችሎት የቀረቡት የሥራ ኃላፊዎችም ያሉት ይህንኑ ነው፡፡
እናም አቶ ዘሩባቤል፤ ..ከ1968-2000 ዓ.ም የቦታ ኪራይና የቤት ግብር የከፈሉ መሆኑን.. የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ኃላፊዎች አቶ ኃይሉ ህጋዊ ባለቤት መሆናቸውን መስክረዋል.. ማለቴን ጠቅሰው አስተያየቴን ሲተቹ፤ ..የአቶ ኃይሉን ባለመብትነት ለማረጋገጥ ሙግት ገጥመዋል.. ብለዋል፡፡ አያይዘውም፤ ሆኖም ..ይህ ሙግት የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለመብትነት በህግ አግባብ እንዴት እንደሚቋቋም መገንዘብ የተሳነው ነው፤ የንብረት ባለቤትነት እንደ መና ዳቦ ከሰማይ አይወርድም.. ብለዋል፡፡ ግን ለ79 ሺህ ሰዎች የሰራ ህግ በአንድ ሰው ሲለወጥ የፍትህ ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡
እርግጥ ነው፤ እርስዎ የያዙት አቋም የፌደራል ፍ/ቤቶች የያዙት አቋም ነው፡፡ የእርስዎ ቀላል ነው፡፡ ችግሩ፤ የአንድ መንግስት ሁለት አካላት፤ የተለያየ አቋም ይዘው መፋጠጣቸው ነው፡፡ እንግዲህ የእኔ ጥያቄዬ እዚህ ላይ ነው፡፡
እንደሚያውቁት¿ ሁሉም የመንግስት አካላት በህግ የተወሰነ ስልጣን ያላቸው ናቸው፡፡ በህግ በተቀነበበው ቅፅር ተወስነውም ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በመርምር-መዝን (check and balance) መርህ እየተጠባበቁ ስሙር ሆነው ይሰራሉ፡፡ እንጂ እንዲህ እንደ አሁኑ፤ በቴሌ እና በመንገድ ስራዎች ዓመል፤ አንዱ የገነባውን ሌላው ማፍረስ የለበትም፡፡ እንዲህ ሲሆን ቀውስ ይመጣል፡፡ በ መንግስት ውስጥ መንግስት (a state with in a state) የሚባል ዓይነት ቀውስ ይከሰታል፡፡
ፍርድ ቤቶች በህግ አውጭው አካል የወጣን ህግ በነፃ ህሊና እየተረጎሙ ፍርድ መስጠታቸውን ትተው ህግ ማውጣት ውስጥ አይገቡም፡፡ የአንድ የመንግስት አካላት ከሆኑት አንዱ፤ ..ካርታ ወይም ደብተር በሌለበት ሁኔታ፤ የውሃ እና የመብራት ክፍያ ሰነዶችን በማየት ባለቤትነትን እወስናለሁ.. ሲል፤ ሌላኛው እርስዎ እንደ ጠቀሱት ..የቦታ እና የቤት ግብርን በስሜ ገብሬያለሁ ማለት የባለቤትነት ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም.. አለ፡፡ እዚህ ውስጥ ችግር አይታይዎትም? እኔ ያነሳሁት ይህን በችግር የተሳከረ አሰራር ነው፡፡
ይህ አሰራር በዜጎች መካከል ልዩነት ይፈጥራል፡፡ ..ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው.. የሚለውን ህገ መንግስታዊ መርህም ይጎዳል፡፡ በሌላ በኩል፤ የፍርድ ቤቶችን ውሳኔ የሚያስፈጽመው አካል ያወጣውን መመሪያ የሚቃረን ተግባር ውስጥ ይገባል፡፡ በዚህ ጊዜ፤ አስፈፃሚው አካል፤ የፍርድ ቤት ነፃነትን አክብሮ ለመሄድ ሲል ከ..ህሊናው.. ጋር የሚጋጭን፣ በዜጎች መካከል መድሎን የሚፈጥር ወይም ..ኢ- ፍትሃዊ.. አድርጎ የሚያየውን ውሳኔ ዝም ብሎ ያፈፅማል? ወይስ ..ለእኔ አስተዳደራዊ ችግሮች ትኩረት ያልሰጠ የፍ/ቤት ነፃነት ይበጣ..ስ.. በሚል የዳኝነት ነጻነትን በመጣስ ውሳኔውን ለማስለወጥ ወይም ህልውናውን ለማስከበር ይንቀሳቀሳል? አሳሳቢው ጉዳይ ይሄ ነው፡፡ ይኸ ጉዳይ ደግሞ ..ጥብቅና ቆምክላቸው.. ያሏቸውን አንድ ግለሰብ የሚመለከት ጉዳይ አይደለም፡፡ ይኸ የስርዓት ጥያቄ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኔ ጭንቀት ሁለት ነው፡፡ በአንድ በኩል፤ የፍርድ ቤቶች ነፃነት መከበር፤ በሌላ በኩል፤ የአስፈፃሚው አካል እና የህግ ተርጓሚው አካል፤ እንደ አንድ አካል መስራት አለመቻል፡፡ በዚህ ጉዳይ መነጋገር አስፈላጊ ነው፡፡
ፍርድ ቤቶች፤ በግልፅ ችሎት በተሰየሙ ዳኞች ፍርድ የሚሰጡት ተጠያቂነታቸውን ለማረጋገጥ ይመስለኛል፡፡ ኃይላቸውም እንደ አስፈፃሚው አካል ሰራዊት የማዘዝ ሥልጣናቸው አይደለም፡፡ የእነሱ ኃይል እና ክብራቸው በህግ የተሰጣቸው ህግን የመተርጎም ስልጣን እና ዝምታው እንኳን የሚያስፈራው የህዝብ ዓይን እና ትዝብት ወይም አመኔታ ነው፡፡ የፍርድ ቤቶች ኃይል የማንንም ህሊና የሚያሸንፍ ሀቅን ተመስርተው የሚሰጡት ዳኝነት ነው፡፡ እልፍ ሰራዊትን ከሚያዝ አስፈፃሚ አካል ትንኮሳ ወይም ጥቃት የሚጠብቃቸው ..ፍትህ ትመነምናለች እንጂ አትበጠስም.. ብሎ የሚታመናቸው ህዝብ ከበሬታ ነው፡፡ ይህ ከበሬታ ሲኖር ዜጎች የፍ/ቤት ተቋማዊ ነጻነት በማንም እንዳይደፈር ለመከላከል ዝግጁ ይሆናሉ፡፡ በተቃራኒው፤ ይህ ከበሬታ እና አመኔታ ሲጠፋ የፍ/ቤቶች ኃይል አብሮ ይጠፋል፡፡ ህዝብም ቸል ይላቸዋል፡፡ የስርዓት ቀውስም ይከተላል፡፡
ዲሞክራሲያዊን እና ህገ መንግስታዊን ስርዓት የሚፈታተን አደጋ ይመጣል፡፡ ስርዓቱን ያስከብራሉ ወይም ይጠብቃሉ የሚባሉት ፍ/ቤቶች ራሳቸው የስርዓቱ ጠንቅ ይሆናሉ፡፡ የጀርመን ታሪክ የሚያስተምረን ይህንኑ ነው፡፡ የጀርመኑ ናዚ ወደ ሥልጣን የመጣው የፍርድ ቤቶችን ነፃነት አክብሮ ለማደር የሞከረው እና ዲሞክራሲያዊ ሊባል የሚችለውን መንግስት አልፈስፍሶ የጣለው በፍርድ ቤት መድረክ ነው፡፡ ስለዚህ የፍትህ ስርዓቱ ጤናማነት፤ የጠቅላላ ህገ መንግስታዊ እና ዲሞክራሲያዊ ስርዓቱን ጤናማነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ እናም የፍ/ቤቶች አሰራር ሁሌም በንቃት መታየት ያለበት ነው፡፡ታዲያ አቶ ዘሩባቤል፤ ..ለአቶ ኃይሉ ጥብቅና ቆመሃል.. ቢሉኝም፤ እኔ የህዝብን ስሜት፣ የአትሌት ኃይሌ ገብረ ስላሴን ሀቀኛ አስተያየት፤ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚደንት ለፓርላማው ባቀረቡት ሪፖርት የጠቀሷቸውን ችግሮች ተንተርሼ፤ በፍትህ ስርዓቱ ላይ ነው አስተያየት ያቀረብኩት፡፡ አቶ ዘሩባቤል ተከታትለው እንደሆነ፤ ባለፈው ወር የፌደራል የሥነ - ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአዘጋጀው አንድ የውይይት መድረክ ..በዳኞች፣ በጠበቆች እና በዓቃቢያነ ህግ ዘንድ አሳሳቢ የስነ-ምግባር ችግር አለ.. በማለት፤ ራሳቸው ባለ ጉዳዮቹ አስተያየት ሲሰጡ ነበር፡፡ ይህን በማጤን የሀገራችን የፍትህ ስርዓት ችግሮች ተለይተው እንዲወገዱ የሚያግዝ አስተያየት ሰጠሁ እንጂ ለግለሰብ ጥብቅና አልቆምኩም፡፡ ቀደም ሲልም፤ በአሁኑ ጊዜ በርካታ የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ በመሆናቸው በመጥቀስ፤ እንደ ሼል ያሉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች፤ የፍትህ እና የግብር አስተዳደር ስርዓታቸው ደካማ በሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች ውስጥ አንድ አገር የሚጎዳ ድርጊቶችን ከመፈፀም የማይመለሱ መሆናቸውን በማስረጃ በማስደገፍ፤ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የሚኖርባትን ችግር ለመከላከል ዝግጁ መሆን እንዳለባት ለመግለጽ ሞክሬያለሁ፡፡ የእኔ ጥያቄ፤ ሼል ኢትዮጵያን የቦታ ባለቤት ሊያደርገው የቻለው እና በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት ያገኘው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተገኘ? የሚል ነበር፡፡ ልብ አድርጉ፤ ሼል ኢትዮጵያ የነዳጅ ማደያ ጣቢያ የነበረው በመላ ሃገሪቱ ነበር፡፡ አሁን ይህን ቦታ ለኦይል ሊቢያ ሸጦ ወይም ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ የጋዳፊ ኩባንያ ለሆነው ኦይል ሊቢያ አስተላልፎ፤ የቦታ ባለቤት አድርጎት ከሃገር ወጥቷል፡፡ ታዲያ ሼል ወይም ኦይል ሊቢያ የቦታ ባለቤት የሆነው በካሳንችስ ብቻ አይደለም፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት 42 የማደያ ጣቢያዎች የእርሱ ሆነዋል፡፡ የአቶ ኃይሉ ጉዳይ ፍርድ ቤት ስለቀረበ እየሆነ ያለውን ነገር ለማወቅ ቻልን እንጂ ሌሎቹ 41 ጣቢያዎች በፀጥታ ወይም በጨለማ ከኦይል ሊቢያ እጅ ገብተዋል፡፡
በራሳችን ገንዘብ፣ በራሳችን የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ቤት የምናስገባውን ነዳጅ ከመቸርቸር በቀር፤ ለሃገር የኢኮኖሚ ዕድገት አጋዥ የሚሆን ካፒታል ይዞ ልገባ እንደ ኦይል ሊቢያ ያለ የውጭ ኩባንያ፤ በአዲስ አበባ ውስጥ የዚህ ሁሉ መሬት ባለቤት መሆን የቻለው በምን ተዓምር ነው? አብነት ልስጣችሁ፤ የካሳንችሱ ሼል ብቻ አንድ ሺህ ካሬ ሜትር ገደማ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ሌሎቹም ከዚህ የሚተናነሱ አይሆኑም፡፡ ታዲያ ይኸን ያህል የህዝብ ሀብት ከኦይል ሊቢያ እጅ የገባው በታወቀ፤ የመንግስት እና የህዝብ ጥቅምን ባስከበረ አኳኋን ነው? የሚለው ጥያቄ፤ ኢትዮጵያዊ የሆኑትን አቶ ዘሩባቤልንም ከእኔ እኩል ሊያሳስባቸው ይገባል፡፡ ይሄን ያህል መጠን ያለው የህዝብ ንብረት ግልጽ ባልሆነና በውጭ ሃገር በተከናወነ ሽያጭ ከሼል ወደ ኦይል ሊቢያ እጅ ሲዛወር ጥያቄ ማንሳት፤ ስለ ሁኔታው ማብራሪያ መጠየቅ፤ ለኔ - መብት፤ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ኃላፊዎች ደግሞ ግዴታ ነው፡፡ አቶ ዘሩባቤል የጠቀሱት እና መጋቢት 29/1968 ዓ.ም የወጣ አንድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት  መመሪያ አለ፡፡ ይህ መመሪያ የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች የመሬት ባለቤት ይሆናሉ አይልም፡፡ ይህ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣው መመሪያ፤ ..አዋጁ ሲታወጅ ለሌላ ሦስተኛ ወገን በኪራይ ተሰጥተው የነበሩት የነዳጅ ማደያ ጣቢያዎች በኩባንያዎቹ ቁጥጥር ሥር ይግቡ.. አላለም፡፡ ለዚህም ነው፤ መንግስት በነዳጅ ማደያ ጣቢያዎችን ይጠቀሙ የነበሩት ኢትዮጵያውያን ግብር እንዲከፍሉ የጠየቀው፡፡ ቦታዎቹ በከተማ ቦታ እና ትርፍ ቤቶች አዋጁ ወደ መንግስት ንብረትነት የተዛወሩ በመሆናቸው፤ መንግስት የቀድሞ ባለርስቶችን ተክቶ ኩባንያዎቹ ከግል ባለርስቶች ጋር ያደረጉት የኪራይ ውል ዘመኑ የተፈመ ከሆነ፤ ስለ ኪራዩ ተገቢው ጥናት እየተደረገ በሚሰጥ ውሳኔ አዲስ ውለታ እንዲደረግ የሚያዝ መመሪያ ነው፡፡ በዚሁ መሰረት ሼል ከባለ ርስቶች ጋር ያደረገው ውል በ1987 ዓ.ም አልቋል፡፡ ይህን ጉዳይ ተከታትሎ ያስፈፀመ አካል ባለመኖሩም፤ ሼል ኢትዮጵያ ያለ አንዳች ውል ወይም ግብር ሳይከፍል ለ15 ዓመታት በዝምታ ሲሰራ አንዳች ጥያቄ ያልተነሳበት እንዴት ነው? ፍርድ ቤቱም ይህ ጉዳይ ሲገለፅለት ..የሚመለከተው አካል ይጠይቅ.. ነበር ያለው፡፡እዚህ ላይ ጥያቄ አለኝ፡፡ ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች ..ዕዳ አለባችሁ ግብር ክፈሉ.. እየተባሉ በጥብቅ በሚጠየቁበትና መንግስት ለግብር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በሚንቀሳቀስበት በዚህ ዘመን፤ ሼል ኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን ሀብትና የውጭ ምንዛሬ ሲነግድና ትርፍ ሲሰበስብ ቆይቶ ግብር ሳይጠየቅ ዝም የተባለው በምን አግባብ ነው? ማለት ተገቢ ነው፡፡ ይህ የፍትህ ጥያቄ ነው፡፡ እንዲሁም፤ አቶ ኃይሉን ..የቦታው ባለቤት አንተ ነህ ግብር ክፈል.. ብሎ ያስከፈላቸው በአንድ መዋቅር ያለ ፍ/ቤት፤ መልሶ ..የቦታው ባለቤት አንተ አይደለህም.. ሲላቸው፤ የፍትህ ጥያቄ ይመጣል፡፡ እንዲህ ያለ፤ በአንድ ጉዳይ በማድረግም- ባለማድረግም መቅጣት ፍትህ እንዳልሆነ አቶ ዘሩባቤል ያውቃሉ፡፡ ይህን ማንሳት የፍትህ ጥያቄ እንጂ ጥብቅና አይደለም፡፡ ሼል ኢትዮጵያ ከነዳጅ አዳዮች ጋር ያደረገውን የነዳጅ እና ቅባት አቅርቦት ውል፤ ለዚያውም በውል እና ማስረጃ ፅ/ቤት ያልተመዘገበን ውል፤ የቦታ ባለቤትነት ማስረጃ አድረጎ መውስድ ተገቢ ነው? ይህ ውል፤ ቦታው የሚገኝበት የመስተዳደር ኃላፊዎች ከሰጡት ምስክርነት ክብደት አለውን?
እናም፤ ሼል ኢትዮጵያ ወይም ..ወራሹ.. የሆነው ኦይል ሊቢያ የቦታው ባለት የሆኑበት አግባብ ትክክል ነውን? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ፀሐፊው አቶ ዘሩባቤል፤ ለአቶ ኃይሉ ጥብቅና ቆመሃል ቢሉኝም፤ የኔ ትኩረት ግለሰብ ሣይሆን ፍትህ ነው፡፡ ለዚህ ነው፤ ..እኔ ጨረቃዋን ሳሳየው እሱ ጣቴን ይመለከታል.. ማለትን የመረጥኩት፡፡ ቸር እንሰንብትሠ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ለዘላለም ይኑር፡፡

Read 3693 times