Print this page
Saturday, 11 August 2012 10:10

ጥርሷን የነከሰች ልጅ፣ ነገር የገባት ሰጐን ናት

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

ነገር የገባት ሰጐን፣ፅናት - የገባት ሰጐን ናት!

(ቁጥር 4)

ማለዳ ነገር የገባት

ጥርሷን የነከሰች ሰጐን፣ ከቲኬም ወዲያ ስም የላት!

ቲኬ ነብስ፣ ያገር እስትንፋስ! አሁንም ጥናቱን ይስጥሽ!

ከልብ የምትሮጭ ሰጐን ነሽ፣ ማራቶን መስክ የሆነልሽ!

በሀቀኛ እግር ወርቅ አሳሽ

በሩቅ አገር ሩቅ - ደራሽ

ዕድሜ ላንቺ ውስጡን አወቅን፣ ቁምነገሩ አንድ ብቻ ነው፡-

መሮጥ፣ ወይም አለመሮጥ

መቆም፤ ወይም ቆርጦ መሮጥ

መሆን ወይም አለመሆን፣ ሁሉንም በፅናት መብለጥ!!

ፅናት - የገባት ሰጐን፣ አገር - የገባት ሰጐን ናት!

ቲኬ ነብስ ያገር እስትንፋስ!

እንዲያ እስክታመሪ ድረስ

እንደምትቦርቅ ግልገል

ሽቅብ - ቁልቁል እንደምትል

እንደዋዛ ያለትንፋሽ፣ እንደልጅነት ሩጫሽ

እንደተማሪ ቤት ጉዞሽ

ሁሉን እያቃለልሽ ሄደሽ

የምሯ ደቂቅ ስትመጣ፣ እንደጥሩዬ እነደህትሽ

እንደወርቅዬ እንዳጋርሽ

“ድልሽን እንደነብር ግልገል፣ በጥርስሽ ጫፍ አንጠልጥለሽ”

ወኔሽን ከጽናት ወልደሽ

እኛን በፌሽታ ገድለሽ፣ ዓለምን በታምር ቀበርሽ!

ቲኬ!

የሯጮቹ አገር ልጅ ነሽ፣ ከወዴት መጣሽ አይባል?

የያሬድ ልጅ ዜማ ጠፋው፣ የማለት ያህል ይጨንቃል!

ወዶም ጠልቶም ማንም ያውቃል

አበሻ እንደሁ እግር አምራች ነው፣ ሲሮጥ አድጐ ሮጦ ‘ሚጥል

አንዴ ሜዳ ሲገባ፣ ዕትብቱን ቆርጦ ሲነሳ

የዕትብቱን መቀበሪያ አገር፣ በባንዲራ ነው እሚያወሳ!

አዲስ የኦሎምፒክ ጀግና፣ ለካ ሁሌም ይወለዳል

ከልጅነት እስከ ዕውቀት ነው፣ ያይበገር ሩጫ ገድል!

ፒዲፒዲስም መልዕክቱን፣ አድርሶ ለወገኖቹ -

እደጃፉ ደርሶ ወድቋል፤

አንቺ ግን ኬላውን አልፈሽ፣ አዲስ ሬኮርድ ይዘሻል!

ባንዲራችንን ለብሰሻል፤

ምን ምን ይል ይሆን ባንዲራ፣ ዓለም ፊት ሲከናነቡት?

ዕንባ ዕንባ ይላል ወርቅ ወርቅ፣ ምነው ቀምሼ ባወኩት?!

በሞቴ ንገሪኝ ቲኬ፣ ምን ምን ይላል ሲለብሱት?!

አየር ላይ ሲያውለበልቡት?

አስቀናሽኝ ለእኔ ወይኔ

ምሥጋን ይግባው ላንቺ ወኔ!

ባንዲራ ለሌለው መጥኔ!!

ባንዲራችንን ለብሰሻል፣ ይሙቅሽ ይመችሽ ቲኬ!!

ፅናት - የገባሽ ሰጐኔ

ነገር የገባሽ ዋኔ

ይሙቅሽ እስቲ ወገኔ!

ጥርሷን - የነከሰች ሰጐን፣ ነገር - የገባት እኮ ናት!

የሰው ፅናት፤ ያጋር ኩራት

የአገር እናት፣ የዓለም አናት!!

አንቺ ነሽ እሷ ማለት!

ላገር ሲባል ምን አይኮን?!

ቲኬ ትምርትሽ ገብቶናል

ጥርሽን ነክሰሽ ድል ፍቀሽ

ሜዳውን ብራና አድርገሽ

ስንቱን ከምጥ ገላገልሺው፣ እንዲህ ብለሽ በእግርሽ ጽፈሽ፡-

…ፅናት ይኑረን እንጂ፣ ጐበዝ የትም እንደርሳለን

ጥናቱን ይስጠን እንጂ፤ ማንንም እንረታለን!

ልቡን ሞልቶ እሚሮጥና፣ ለወግ ብቻ እሚንጠራራ

በቁርጡ ቀን ይለያሉ፣ እንደ ጀግናው ጀብድ ሥራ!

ለካ ዳር ሲደርሱ ኖሯል፤ ይብስ ሀሞት እሚፈለግ

ተፋላሚን አንበርክኮ፣ ባገር በውጭ ለማስደግደግ፡፡

ፍፃሜው ላይ ሲጥ እንዳንል፣ ፅናትን ነው ሙጥኝ ማለት

ጥርስን ነክሶ ሩቅ ሩቅ ማየት

ሰዉን እንደወኔ ድግ፣ ባንዲራን እንደአገር ጥለት

ይዞ ነው ድል ማድረግ ማለት!!

(ለቲኬ ገላና እና ለጀግኖች አትሌቶቻችን

እንዲሁም ልቡን እንደባንዲራ ለሰቀለው የኢትዮጵያ ህዝብ)

ነሐሴ 2004 ዓ.ም

 

 

 

Read 3389 times Last modified on Saturday, 11 August 2012 10:13