Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Wednesday, 04 April 2012 08:21

ለሴቶች - ሰውነት እንዳይላላ አራት መፍትሄዎች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ሆድና ጀርባን፤ ጭንና ዳሌን ለማሳመር -

ሩጫና ቀላል ስፖርቶች

ሰውነት የሚላላው በሁለት ምክንያቶች ነው - አንደኛ፤ በስፖርት እንቅስቃሴ እጥረት ጡንቻዎች ይደክማሉ። ሁለተኛ፤ የሰውነት የስብ መጠን መብዛት ነው። እንደ ሩጫ በመሳሰሉ ስፖርቶች የስብ መጠን ካልተስተካከለ፤ ሺ ጊዜ የጡንቻ ስፖርት መስራት የተሟላ ውጤት አያስገኝም።

ለምሳሌ፤ እጃችንን ወገባችን ላይ አድርገን፤ “በርከክ ብድግ” እያልን ደጋግመን በመሥራት፤ የሆድ ጡንቻዎችችንን ማጠንከር እንችላለን። ነገር ግን፤ ይህን የጡንቻ ስፖርት፤ ከ’ስብ’ ስፖርት ጋር ካላጣመርነው፤ የምንመኘው ሸንቃጣነት ላይ አንደርስም። በቦርጭ የተሸፈነ ጠንካራ የሆድ ጡንቻ ይሆንብናል።

ስለዚህ፤ በሳምንት ቢያንስ ለሶስት ቀን የግማሽ ሰአት የ”ስብ” ስፖርት ያስፈልገናል፤ ለምሳሌ ሩጫ፤ ሶምሶማና “ኤሮቢክስ”። ከዚህ ጋር፤ የሚከተሉትን አራት የጡንቻ ስፖርቶች ስንሰራ፤ ያማረ ውጤት ልናገኝ እንችላለን።

ከክርን በላይ ከብብት በታች

መቼም፤ እንደ ሚያዝያና ግንቦት ወር፤ አየሩ ሞቃት ሲሆን፤ እጅጌ የሌለው ልብስ ያስደስታል። ግን... ግን... የሰውነታችን ውፍረት ባያስደስተንስ? መጨነቅ አያስፈልግም።  ከክርን በላይ፤ ከጀርባ በኩል የሚገኘው የእጃችን ጡንቻ በቀላሉ የሚላላ ቢሆንም፤ በዚያው መጠን በቀላሉ በስፖርት ይስተካከላል።

እንደሌላው አላስፈላጊ የስብ መጠን፤ እዚህም ላይ ሩጫና ተመሳሳይ ስፖርት ያስፈልጋል - ከመጠን ያለፈ የስብ ክምችት ለማስወገድ። ነገር ግን፤ ያማረ ቅርፅ እንዲይዝልን፤ የጡንቻ ስፖርት መስራት አለብን። ቀለል ባለ “ፑሽ አፕ”፤ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ መልካም ለውጥ ማየት ይቻላል።

ወለል ላይ የሚከናወን አይደለም - “ፑሽ አፑ”። መዳፎቻችንን የወንበር ጫፍ ላይ አሳርፈን ነው፤ “ፑሽ አፑ”ን የምንሰራው። በቀስታ 15 ጊዜ መስራት። ይህንኑን ስፖርት ሁለት ወይም ሶስት ዙር መስራት።

ከብብት ስር በጎናችን በኩል የሚፈጠረው የመወፈርና የመላላት ችግር ያን ያህልም የተለየ ነገር የለውም። በ”ፑሽ አፕ” ማጠንከር ይቻላል።

የዳሌና የጭን ውበት

የዳሌና የጭን ውፍረት አስቸጋሪ ነው። ብዙ ሴቶች፤ ገና መወፈር ሲጀምሩ፤ በዳሌና በጭን አካባቢ ነው ለውጥ የሚያዩት። ውፍረቱን ሲቀንሱ ደግሞ፤ ቶሎ የማይቀንሰው የዳሌና የጭን ውፍረት ነው። አላስፈላጊ ስብ ለማስወገድ፤ እንደ ሩጫ እና “ኤሮቢክስ” የመሳሰሉ ስፖርቶች የግድ ያስፈልጋሉ። ከዚሁ ጋር፤ የአራት አቅጣጫ “እመር እርምጃዎች”ን ደጋግሞ መስራት።

እጆች ወገብ ላይ አድርገን በመቆም እንጀምራለን። የግራ እግር ሳይታጠፍ ባለበት ሆኖ፤ የቀኝ እግር ወደ ፊት እመር ብሎ ይራመዳል - ከጉልበት አጠፍ ብሎ። ነገር ግን ባትና ታፋ እስኪገናኝ ድረስ፤ ጉልበታችን መታጠፍ የለበትም። ከዚያ ወደ ጀመርንበት እንመለሳለን። የቀኝ እግር እንደገና ወደ ኋላ ይዘረጋል - (የግራ እግር አጠፍ ብሎ)። ወደ ጀመርንበት እንመለስና፤ የቀኝ እግር ወደ ቀኝ ይዘረጋል (ከጉልበት አጠፍ ብሎ)። ወደ ጀመርንበት ተመልሰን ከቆምን በኋላ፤ በመጨረሻ የግራ እግር ወደ ግራ አቅጣጫ ይዘረጋል (ከጉልበት አጠፍ ብሎ)። እነዚህን 15 ጊዜ መስራት። ይሄ ሁሉ በቀኝ እግር መሪነት የተሰራ ስፖርት ነው። በግራ እግር መሪነት፤ ተመሳሳይ ስፖርት 15 ጊዜ መስራት።

የመጀመሪያው ዙር አለቀ ማለት ነው። ሁለት ወይም ሶስት ዙር መስራት።

ጀርባ ሸክም አይፈልግም

ከጀርባ በኩል፤ የጡት መያዣ ማሰሪያውን የሚያስቸግር፤ የውፍረት ችግር ለማስወገድ፤ ቤት ውስጥ ሊሰራ የሚችል ቀላል ስፖርት አለ። አንድ ወንበርና አንድ በመዳፍ ሊጨበጥ የሚችል ክብደት ብቻ ነው የሚያስፈልገን። ወንበሩን ከግራ ጎናችን አድርገን አጠገቡ እንቆማለን። በቀኝ እጃችን የተወሰነ ያህል ክብደት ያለው እቃ ጨብጠናል። የግራ እግራችንን ጉልበት እና የግራ እጃችንን ወንበሩ ላይ እናሳርፋለን። ጎንበስ ብለናል ማለት ነው። ክብደት የያዝንበትን እጅ ወደ ታች ወደ ወለል ዘርግተናል። በቀስታ የእጃችንን ክርን ወደ ጎን በኩል እያጠፍን እየዘረጋን፤ ክብደቱን በቀስታ እስከ ደረት ድረስ ከፍ ዝቅ እናደርጋለን። 15 ጊዜ እንደግመዋለን።

ከዚያም የቀኝ እግር ጉልበትና የቀኝ እጅ ወንበሩ ላይ አስደግፎ፤ በግራ እጅ በተመሳሳይ መንገድ ክብደቱን 15 ጊዜ ማንሳት። ይህን ስፖርት ሁለት ወይም ሶስት ዙር መድገም ያስፈልጋል።

የሆድ ነገርስ?

ደጋግሞ መሮጥ ነው ዋናው ነገር። ከዚያ ሆዳችንንና ዙሪያውን የበለጠ ጠንከርከር ለማድረግ፤ የተለያዩ ዘዴዎች አሉ። ለምሳሌ ብስክሌት መንዳት ጥሩ ዘዴ ነው። ካልሆነም ግን ቤት ውስጥ የምንሰራቸው ስፖርቶችን መጠቀም እንችላለን።

ወለል ላይ መዳፎቻችንን ሳይሆን ክንዶቻችንን አሳርፈን፤ ሰውነታችንን እንዘረጋለን። እንደ “ፑሽ አፕ” ይመስላል። ግን አይደለም። በእግር ጣቶቻችንና በክንዶቻችን ብቻ ሰውነታችንን እንደደገፍን፤ ጀርባችንን ቀጥ አድረገን ሆዳችንን ወደ ውስጥ አጠንክረን ለ30 ሴኮንድ እንቆያለን። ከቻልንም፤ ለ60 ወይም ለ90 ሴኮንድ ማርዘም እንችላለን። ይህንን 15 ጊዜ ከሰራን በኋላ፤ ሁለተኛ ዙር መድገም።

ሌላኛው ተጨማሪ ዘዴ፤ ወለል ላይ በጀርባ ተኝተን የምንሰራው የሆድ ጡንቻ ስፖርት ነው። እግሮቻችን አጠፍ ብለዋል። መዳፎቻችንን ከጭንቅላታችን ጀርባ አድርገናቸዋል። ከትከሻችን ከፍ እንልና፤ የግራ ክርናችንን ወደ ቀኝ እግር ጉልበታችን አቅጣጫ ለማስጠጋት እንጠመዝዛለን። ትከሻችንን አናሳርፍም። ከወለሉ ከፍ እንዳለ ነው። የቀኝ ክርናችንን በመጠምዘዝ፤ ወደ ግራ እግር ጉልበታችን እናስጠጋለን። በዚህ መንገድ የግራ እና የቀኝ ክርኖቻችንን እያፈራረቅን 15 ጊዜ እንሰራለን። ሁለት ወይም ሶስት ዙር እንደግመዋለን።

 

 

 

Read 3709 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 08:24