Saturday, 21 April 2012 15:57

ፍትሐዊ ጤና - ለዓለም ሕዝብ ሁሉ

Written by  በዶ/ር መንግሥቱ አስናቀ - (ኤም ዲ፣ ኤም ፒ ኢች)
Rate this item
(0 votes)

ጤናችን ያለበት ደረጃ፣ ሁኔታና የሚደረግለት ክብካቤ የመሻሻላችንና የዕድገታችን ዋነኛ አመልካች ከመሆኑም በላይ በኅብረተሰብም ሆነ በአገር ደረጃ ጥሩ ወይም መጥፎ የመሥራታችን መገለጫም ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ በኅብረተሰቡም ውስጥ በጣም ከሚፈለጉና መሠረታዊ ከሆኑ ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ ሆኖ ሰርጿል፡፡ ለዚህ ነው ጤና በሁሉም የዓለማችን ክፍል የሰዎች ዋነኛ ሰብአዊ መብትና መሠረታዊ ፍላጐት የሆነው፡፡ ስለዚህ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የጤና ባለሙያዎች በትምህርትና ጤናማ የአኗኗር ስልት በማስተዋወቅ፣ በሽታና ጉዳት የሚያደርሱ ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት በጥናትና ምርምር ለመከላከል፣ ከበርካታ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የዜጐች ጤና ተሻሽሎ ደስተኛ ሕይወት የሚመሩበትን መንገድ ለማመቻቸት ሌት ተቀን እየጣሩ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ ሚሊዮኖች የጤናን ሁኔታ ለማሻሻል ቢደክሙና ቢጥሩ፣ ቢሊዮን ዶላሮች ወጪ ቢደረጉም፣ መከላከል በሚቻል በሽታዎች፣ ሚሊዮኖች ያለ ዕድሜያቸው እየረገፉና፣ የበሽታና የአካል ጉዳት ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡

የሕዝብ ጤና መሠረታዊ መመሪያ፣ ሁሉም ሰው ጤነኛ የመሆን መብት አለው፤ ፍትህ በነገሠበት ዓለም ሁላችንም ለጤናችን የሚበጀንን የመምረጥ መብት አለን የሚል ነው፡፡ በሕዝብ ጤና ጽሑፎችና ተግባራዊ አሠራር መሠረት ፍትሐዊ ጤና ማለት፣ እያንዳንዱ ሰው ጤነኛ የመሆን ሙሉ አጋጣሚዎች ይኖሩታል፤ እንዲሁም ማንም ሰው በኅብረተሰቡ ውስጥ ባለው ከፍ ወይም ዝቅ ያለ ደረጃ ወይም በሌላ በማኅበረሰቡ በሚወሰን በማንኛውም ሁኔታ የጤና መብቱን አያጣም ወይም አይነፈግም የሚል ነው፡፡

ዛሬ ግን በተለየ አስገራሚ መልኩ የሰዎች ጤና በሚኖሩበት አካባቢ የሚወሰን ሆኗል፡፡ የምዕራቡ ዓለም ሰዎች በአማካይ ከ80 ዓመት በላይ መኖር አለብን ብለው ያስባሉ፡፡

ከሰሃራ በታች ያሉ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ደግሞ ለመኖር የሚያስቡት ከ50 ዓመት ጥቂት ቢዘል ነው፡፡ ጤናና በሽታ ባሉባቸው አገሮች፣ የመኖር ሁኔታ የሚወሰነው በኢኮኖሚው ደረጃ ነው፡፡ የአገሪቷ የኢኮኖሚ ደረጃ ዝቅተኛ ከሆነ የጤና ሁኔታም በዚያው መጠን የደኼየና የተጐሳቆለ ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ኢ-ፍትሐዊ ሁኔታ መፈጠር አልነበረበትም - ትክክልም አይደለም፡፡

ሁሉም ሰው ተመሳሳይ ጤና ኖሮት አይወለድም፡፡ እኩል ያልሆነ ጤና የሚፈጠረው በጤና ደረጃ (ሁኔታ) መለያየት ወይም ለጤና ወሳኝና አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች በተለያዩ የሕዝብ ቡድኖች መካከል እኩል ሳይከፋፈሉ ሲቀሩ ነው፡፡ አንዳንድ የጤና ልዩነቶች በባዮሎጂያዊ (በጽንሰ ሂደት ወቅት በሚፈጠር) ልዩነት፣ ወይም በዚሁ ወቅት በነፃ ምርጫ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ሌላው ደግሞ በውጫዊ (አካባቢያዊ) ተጽእኖና አብዛኛውን ጊዜ ከግለሰቡ ቁጥጥር ውጭ በሆነ ምክንያት የሚከሰት ሊሆን ይችላል፡፡

የመጀመሪያው ዓይነት ፍፁም የማይቀለበስ፣ በሞራልም ሆነ በእምነት ደረጃ የጤና ወሳኞችን መቀየር በፍፁም ስለማይቻል ልዩነቱ ሊቀር አይችልም፡፡ በሁለተኛው መንገድ የጤና እኩልነት የማይኖረው እኩል ባልሆነና በተዛባ የገቢ፣ የቁሳቁስና የአገልግሎት አቅርቦትና ክፍፍል የተነሳ ነው፡፡ ይህ የማያስፈልግና መቅረት ያለበት እንዲሁም የተሳሳተና አግባብነት የሌለው አሠራር ውጤት፣ እኩል ያልሆነ ኢ-ፍትሐዊ የጤና ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡

ኢ - ፍትሐዊ ጤና በጣም ውስብስብ ጉዳይ ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ወሳኝ የሆኑት  የቅጥርና የሥራ ሁኔታ፣ ትምህርት፣ ተስማሚ መኖሪያ፣ አቅምን ያገናዘበ የኢነርጂ አቅርቦት፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ግንኙነቶች፣ እንክብካቤ፣ የተፈጥሮ ሀብት ክፍፍል፣ የፖለቲካ ስልጣን… ያሉ ነጥቦች በግለሰብና በማኅበረሰብ ጤና ላይ ተጽእኖ መፍጠር ስለሚችሉ፣ እነዚህን ነጥቦች አመለካከታችንን አስፍተንና በጥንቃቄ ልናያቸው ይገባል፡፡ የኅብረተሰቡ ሀብት ከፍ ሲል በተጠቀሱት የማኅበረሰቡ ወሳኝ ነጥቦች አማካይነት እኩል ካልተከፋፈ በዓለም ላይ የሚታዩትን የተለያዩ የጤና ጉድለቶች ለማስተካከል የተለያዩ የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ባለሙያዎችና ተቋማት ትብብርና ቅንጅት ያስፈልጋል፡፡ የተለያዩ ሙያዎች ማኅበር የሆነውና የዓለም ጤናን ማሳደግና መንከባከብ ዓላማውና ተልዕኮው ያደረገው የዓለም ሕዝብ ጤና አጠባበቅ ማኅበራት ፌዴሬሽን (WFPHA) ለእንዲህ ዓይነቱ ተግባር የቆመ ተቋም ነው፡፡

ከፌዴሬሽኑ ዋና ፖሊሲዎችና ዓላማዎች አንዱ፣ ከ1975 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ጀምሮ በየሦስት ዓመቱ የሚያካሂደው የዓለም ሕዝብ የጤና ጉባኤ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ዘንድሮ “ዓለም አቀፍ ፍትሐዊ የሕዝብ ጤና - ምቹ አጋጣሚዎችና ስጋቶች” በሚል ርዕስ 13ኛ ጉባኤውን ከሚያዝያ 15-19 ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኢትዮጵያ ያካሂዳል፡፡ በዚህ ጉባኤ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ በርካታ የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች “ፍትሐዊ ጤና ለሁሉም” ከሚለው ዋነኛ አጀንዳ በተጨማሪ በተለያዩ ጤና ነክ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ - ይወያያሉ፡፡

ጉባኤው በአገር፣ በአህጉርና በዓለም ደረጃ አቀፍ ደረጃ ያሉ ሐሳቦችና ተሞክሮዎችን (ልምዶችን) ለመለዋወጥ ምቹ አጋጣሚዎችን ይፈጥራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለማኅበራዊና ጤና ወሳኝ በሆኑ ነጥቦች ላይ በመወያየት አገሮች ለፍትሐዊ ጤና መጓደል ምክንያት የሆኑ ነጥቦችን ከስረ - መሠረታቸው በማጥፋት፣ ለሁሉም ጤና ምቹ ተስማሚና ጤነኛ መኖሪያ ለመፍጠር የገቡትን ቃል በፍጥነት እንዲያሳድጉ ጥሪ ያስተላልፋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ኮሚሽን ወሳኝ በሆኑ የማኅበራዊ ጤና ጉዳዮች ላይ ከሠራው ሥራ የቀሰምነው ዋነኛ ትምህርት፣ መንግሥታት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጋራ ተባብረው ከሠሩ፣ በአንድ ትውልድ ጊዜ ውስጥ የተዛባውን የጤና አጠባበቅ በመቀልበስ የዜጐችን ሕይወት ማሻሻል እንደምንችል ነው፡፡

ጉባኤው የሚካሄደው በመላው ዓለም ባሉ የተለያዩ የሕዝብ ቡድኖች መካከል የጤና አገልግሎት አሰጣጥ መዛባትና መለያየት እየጨመረና እየሰፋ ባለበት በአሁኑ ወቅት መሆኑ በጣም ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ ምክንያቱም ተሳታፊዎቹ፣ የጤና አቅርቦትና አገልግሎት ለሁሉም ዜጋ በእኩል ደረጃ ያለመስጠት በመላው ዓለም የፈጠረው ጉዳትና ተፅዕኖ ምን ያህል እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች የቀሰሙትን ትምህርትና ልምድ በማንሳት በጥንቃቄ ይወያዩበታል፡፡

ከተለያየ ዘርፍ የመጡት በርካታ ባለሙያዎች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦና ትምህርት፣ በተለያዩ የመንግሥት እርከን ላሉና ሌሎች ባለድርሻ አካላት፣ ፖሊሲ አውጪዎችና የፖሊሲው ፈፃሚዎች፣ እጅግ የዘቀጠውን ጤና ተቀባይነት እስከሚኖረው ደረጃ ድረስ ከፍ እንዲያደርጉበት ያለ ጥርጥር ጥሩ ግብአት ይሆናቸዋል፡፡

ስለዚህ፤ የተሻለ የጤና ሁኔታ ለመፍጠርና በመላው ዓለም ላሉ ሕዝቦች በሙሉ ፍትሐዊ ጤና ማቅረብ እንዲቻል ሁሉም የጉባኤው ተሳታፊዎች ያላችሁን እውቀትና ልምድ በቅንነት እንድታካፍሉ በትህትና እጠይቃለሁ በማለት አስገንዝበዋል፡፡

 

ዶ/ር መንግሥቱ አስናቀ

(ከ1998-2001 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ነበሩ)

 

 

 

Read 2226 times Last modified on Saturday, 21 April 2012 16:01