Saturday, 21 April 2012 16:02

ሳውና ባዝ እና የጤና ፋይዳዎቹ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

በ19ኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ አካባቢ በፊንላንዶች እንደተጀመረ የሚነገርለትና መጠሪያ ቃሉንም ከዛው ያገኘው ሳውና ባዝ፤ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ መንገድ በጋለ አለት ላይ ውሃ በማፍሰስና እንፋሎት እንዲፈጠር በማድረግ በእንፋሎቱ ገላን የማጽዳት ተግባር ነው፡፡ አምስት የሳውና ባዝ አይነቶች በስፋት ይታወቃሉ፡፡ እነዚህም ድራይ፣ ስቲም፣ ኢንፍራሬድ ዌት እና ስሞክ ይባላሉ፡፡ እነዚህ የሣውና ባዝ አይነቶች እንደስማቸው ሁሉ የተለያዩ አገልግሎቶች አሏቸው፡፡ በሰውነታችን ውስጥ የሚያስከትሉትም ለውጥና የሚሰጡትም ጠቀሜታ እንደዚሁ የተለያየ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል በስፋት የሚታወቀውና አገልግሎት ላይ የዋለው ኢንፍራሬድ ሳውና ባዝ የተባለው ዓይነት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሳውና ባዝ ከሰውነታችን ውስጥ መርዛም ነገሮችን በማስወገድ ጤናማና ንፁህ ቆዳ እንዲኖረን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት እንደቅንጦት ይታይ የነበረውና ለሠርግና ለአንዳንድ ፕሮግራሞች ብቻ ጥቂት ሰዎች ይጠቀሙበት የነበረው ሳውና ባዝ፤ ዛሬ የበርካታ የከተማችን ሴቶችና ወንዶች ራሳቸውን ለማስዋብና ቆዳቸውን ለመንከባከብ እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡ በእርግጥ ሳውና ባዝ (በእንፋሎት ገላን ማጽዳት) በአንዳንድ የአገሪቱ ክልሎች ለሚኖሩ ህዝቦች የተለመደና ለዓመታት ሲገለገሉ የኖሩበት የተፈጥሮ የህክምና ዘዴ ነው፡፡ ሆኖም ግን በከተማ ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች ዘንድ ከውበት መጠበቂያነት የዘለለ አገልግሎት እንዳለው እምብዛም ሳይታወቅ ቆይቷል፡፡

ሳውና ባዝ በቆዳችን ላይ ያሉትን ቀዳዳዎች ክፍተት ስለሚጨምር፣ ከሰውነታችን በሚወጣው ላብ አማካኝነት መርዛማ ንጥረ ነገሮችንና ሌሎች ቆሻሻዎች ከደማችን ውስጥ እንዲወገዱ ያደርጋል፡፡

በዚህ መንገድ አላስፈላጊ ነገሮች የተወገዱለት የሰውነታችን ቆዳ፣ ንፁህና ጤናማ በመሆን ለተመልካችም የሚያስደስት ገጽታን እንድንጐናፀፍ ያደርገናል፡፡ የቆዳ መድረቅና ማሳከክ፣ የቆዳ ቁጣ (አለርጂ) ለመሳሰሉ ችግሮችም ሳውና ባዝ ፍቱን መፍትሔ ነው፡፡ የሳውና ባዝ ሌላው ጠቀሜታ ደግሞ ጡንቻዎችን ዘና በማድረግ በመገጣጠሚያ ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን ማስወገድ ነው፡፡ የጡንቻ መሸማቀቅ፣ የመገጣጠሚያ ህመም፣ ሪህና የመሳሰሉ በሽታዎች ከእንፋሎት ውሃው በሚገኘው ሙቀት የህመም ስሜታቸውን ማስታገስና ህመምተኛው እፎይታን ሊያገኝ ይችላል፡፡

ሳውና ባዝ አካልና አዕምሮንም ዘና በማድረግ ውጥረትን የማርገብ ተግባርም አለው፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ከእንቅልፍ ማጣት ጋር የተያያዙ ችግሮች ያሉበት ሰው ሳውና ቢጠቀም ችግሩ ሊቃለልለት ይችላል፡፡

ለመታፈን ችግር፣ ለጉሮሮ ህመም፣ ለጉንፋንና ለብሮንካይትስ ሳውና ባዝ (የእንፋሎት መታጠቢያ) ውስጥ የገባ ሰው፣ የሙቀት መጠኑ በመጨመር 39 ድግሪ ሴንቲግሬድ ድረስ ከፍ ሊል እንደሚችል የሚጠቁመው መረጃ፤ ይህ የሰውነት ሙቀት መጨመር በቆዳ አካባቢ ከፍተኛ የደም ዝውውር እንዲኖር ማድረጉንና የላብ መጠንን በመጨመር አላስፈላጊ ነገሮችን ከሰውነታችን ውስጥ የማስወገድ ሥራው እንዲጨምር እንደሚያደርግ ይገልፃል፡፡ እነዚህን አላስፈላጊ ነገሮች ለማስወገድም ሰውነታችን ኃይል መጠቀም ይኖርበታል፡፡ ይህንን ኃይል ለማግኘት ደግሞ በሰውነታችን ውስጥ የተከማቸው ስብ ይቀጣጠላል፡፡ በዚህም ከባድ ሥራን ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ከማድረግ ጋር ተመጣጣኝነት ያለው ስብ ከሰውነታችን ውስጥ እንዲወገድ ያደርጋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ የሰውነታችን ክብደት እየቀነሰ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ ከ15-20 ደቂቃ ሳውና ባዝ መውሰድ ከአንድ እስከ ሁለት ሰዓት ጠንካራ እርምጃ ወይም የአንድ ሰዓት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከማድረግ ጋር ይስተካከላል፡፡

ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የሚነገርለትን ሳውና ባዝ ከጤና አኳያ መውሰድ የማይገባቸው ሰዎች እንዳሉ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

እርጉዞች፣ የልብ ህሙማኖችና ከፍተኛ የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች ሳውና ባዝ ችግር ሊያስከትልባቸው ይችላል፡፡ አብዛኛዎቻችን ለውበታችን የምንጠቀምበት ሣውና ባዝ (የእንፋሎት መታጠቢያ) እነዚህ ሁሉ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡

በከተማችን በቁጥር በርከት ያሉ የሣውና ባዝና የእስቲም አገልገሎት የሚሰጡ ቤቶች ያሉ ሲሆን የአገልግሎት ዋጋቸውም እንደ ቤቶቹ ጥራትና እንደ አካባቢያቸው ይለያያል፡፡ አብዛኛዎቹ የሳውና ባዝ ቤቶች በቦሌ፣ በሃያ ሁለት አካባቢ፣ ቴሌ መድሃኒያለም፣ ሲኤምሲ፣ መገናኛና ሣር ቤት አካባቢ ይገኛሉ፡፡ የፍልውሃዎች ድርጅትም በአዲስ አበባ ከተማ ብቸኛው ተፈጥሮአዊ የሳውና ባዝ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለአንደኛ ማዕረግ  47 ብር፣ ለሁለተኛ ማዕረግ 41 ብር እያስከፈለ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የተለያዩ የግል ሳውና ባዞች ደግሞ ደንበኞቻቸው ለሁለት ሰዓታት በ75 ብር ክፍያ አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋሉ፡፡ ዳጊ፣ አለም ፊትነስ፣ ዴይስፓ፣ ሮዝ፣ ዮሊ ወዘተ… የሣውና ባዝ አገልግሎት ከሚሰጡ የከተማችን የውበት ሣሎኖችና ጂምናዚየሞች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

 

 

Read 10438 times Last modified on Saturday, 21 April 2012 16:07