Saturday, 28 April 2012 14:27

ሲጋራና መዘዙ!

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

ሲጋራ ማጨስ ለሞት መንስኤ ሊሆኑ ለሚችሉ በሽታዎች ይዳርጋል፡፡ በሲጋራ ማጨስ ምክንያት ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች መካከል ካንሰር፣ የሳንባ፣ የጉሮሮ፣ የቆዳ፣ የማህፀን የደም ግፊት መጨመር፣ የልብ ህመም፣ ጋንግሪን፣ የአንጐል በሽታ፣ የዓይን ሞራ ግርዶሽ፣ ስንፈተ ወሲብ፣ የቆዳ መጨማደድ፣ የፀጉር መመለጥ፣ የጥርስ መበስበስ፣ የጨጓራ ህመምና የማስታወስ ችሎታ መቀነስ ይጠቀሳሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም በአለም አቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ በዓለማችን ከሲጋራ ማጤስ ጋር በተያያዙ ችግሮች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በኤችአይቪ ኤድስ፣ በመንገድ ትራፊክ አደጋ፣ በአደንዛዥ እፅ፣ በግድያ ወንጀሎችና ራስን በማጥፋት ከሚሞቱ ሰዎች አጠቃላይ ድምር ይበልጣል፡፡

በአለማችን በየዓመቱ አምስት ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ሲጋራ በማጨስ ምክንያት በሚከሰቱ የጤና ችግሮች የሚሞቱ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ስድስት መቶ ሺህ የሚሆኑት እራሳቸው ሲጋራ የማያጨሱ ሆነው ከአጫሾች በሚመጣ ጭስ ምክንያት ለጤና መታወክ የሚዳረጉና የሚሞቱ ናቸው፡፡ በታዳጊ አገሮች ውስጥ ያለ ዕድሜ የሚከሰተውን ከፍተኛ የሞት መጠንና ህመምተኛነት በማባባስ ረገድ ትምባሆ ወይንም ሲጋራ ማጨስ ቁልፍ ሚና እንዳለው ያመለከተው ጥናቱ፤ የሲጋራ አጫሾች ቁጥር በአደጉት አገራት እየቀነሰ መምጣቱንና በአንፃሩ ደግሞ በታዳጊ አገራት በከፍተኛ መጠን በመጨመር ላይ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

በህዝባዊ ሥፍራዎች ሲጋራ ማጨስ በህግ መከልከሉ፤ ከፍተኛ ታክስ በሲጋራ ምርቶች ላይ መጣሉ፣ የሲጋራ ማስታወቂያዎች እንዳይሰራ መከልከሉና የሲጋራን የጤና ጠንቅነት ለዜጐች በስፋት ማስተማር ባደጉ አገራት ላይ የሚገኙ የሲጋራ አጫሾች ቁጥር በእጅጉ እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በታዳጊ አገሮች የሚገኙ የሲጋራ አጫሾች ቁጥር እንዲጨምር ካደረጉት ምክንያቶች መካከል የየአገሮቹ የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የገቢ አቅማቸው እያደገ መምጣት፣ ግዙፎቹ የትምባሆ አምራች ኩባንያዎች ፊታቸውን ወደ ታዳጊ አገራት ማዞራቸው፣ የዜጐች ግንዛቤ አናሣ መሆኑና በትምባሆ ምርቶች ግብይትና አጠቃቀም ላይ ገዳቢ ህጐች አለመኖራቸው ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ከሚኖሩ ሰዎች መካከል 1.3 ቢሊዮን የሚደርሱት የትምባሆ ተጠቃሚዎች (ሲጋራ አጫሾች) መሆናቸውን የሚያመለክተው የአለም ጤና ድርጅት ጥናት፤ ከዓለም አገሮች በትምባሆ ተጠቃሚዎች ቁጥር ቻይና የመሪነት ቦታውን እንደምትይዝና 350 ሚሊዮን የሚደርሱት ዜጐቿ የሲጋራ ሱሰኞች መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡ እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም በአገራችን የተደረገ ጥናት፤ ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ዜጐቿ ውስጥ 6.9% የሚሆኑ ወንዶችና 0.5% የሚሆኑ ሴቶች የትምባሆ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን አመላክቷል፡፡

የሀገራችን አመታዊ የሲጋራ ፍላጐት 4.4 ቢሊዮን ፍሬ መድረሱንም ይኸው ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡

ሲጋራ ከሚያስከትላቸው ዘርፈ ብዙ የጤና ችግሮች ሌላ ለኢኮኖሚያዊ፣ ለማህበራዊና አካባቢያዊ ጉዳቶች ያጋልጣል፡፡ ሲጋራ ማጨስ የአጫሹን የዕለት ወጪ በመጨመር ከሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በተጨማሪ የሲጋራ አጫሹ ጤና ሲታወክ ለህክምና የሚወጣው ገንዘብ የአጫሹን አቅም የሚፈታተን ከመሆኑ ሌላ በአገሪቱ የጤና በጀት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሣድራል፡፡ ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች በአፋቸውና በልብሣቸው ጠረን ምክንያት በትዳር ጓደኛቸው፣ በቤተሰባቸውና በማህበረሰቡ ዘንድ ዝቅተኛ ግምት እንዲሰጣቸው ማድረጉ ሲጋራ ማጨስ የሚያስከትለው ማህበራዊ ጉዳት ነው፡፡ ሲጋራ በአካባቢ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ስንመለከት የትምባሆ ተክል የሚያስፈልገው ፀረ ተባይ ኬሚካሎችና ማዳበሪያዎች ለመሬት እጅግ አደገኞች ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከተጨሱ በኋላ በግድየለሽነት በየቦታው የሚጣሉት ቁራጭ ሲጋራዎች (ቁሬ) የአካባቢን ንፅህና ያጓድላሉ፡፡ ለሲጋራ መጠቅለያና ፓኬቶች መስሪያ የሚያስፈልገው የወረቀት መጠን ደግሞ የሲጋራ ምርት ለደን መጨፍጨፍ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ለማየት እንችላለን፡፡ ለምሣሌ 300 ፍሬ ሲጋራዎችን ለመጠቅለል የምንጠቀምበትን ወረቀት ለማግኘት አንድ ዛፍ ተቆርጦ ለወረቀትነት መዋል ይኖርበታል፡፡

የአለም ጤና ድርጅት (WHO) ትምባሆ ያለ ዕድሜ የሚከሰተውን ከፍተኛ የሞት መጠንና ሕመምተኛነት በማባባስ ረገድ ያለውን ቁልፍ ሚና በማረጋገጥ፣ የትምባሆ መቆጣጠሪያ ህጋዊ ማዕቀፍን (FCTC) አውጥቷል፡፡ ይህ ማዕቀፍ የሲጋራ ተጠቃሚነትን በእጅጉ ለመቀነስ፣ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመግታት፣ ድንበር ተሻጋሪ የትምባሆ ማስታወቂያዎችንና የፕሮሞሽን ስራዎችን እንዲሁም በኮንትሮባንድ የሚካሄደውን የትምባሆ ንግድ ለመቆጣጠር የሚያስችል ነው፡፡ ይህንን ህጋዊ ማዕቀፍ 172 የዓለማችን አገሮች በፓርላማ ደረጃ ተቀብለው አፅድቀውታል፡፡ ማዕቀፉን ካልተቀበሉና ካላፀደቁት አገራት መካከል ሰባቱ አፍሪካዊ አገሮች ሲሆኑ አገራችን ኢትዮጵያም አንዷ ናት፡፡ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ሞዛምቢክ ሞሮኮ፣ ዙምባቡዌና ማላዊ ቀሪዎቹ ስድስት አገራት ናቸው፡፡

አገሪቱ ይህንኑ “የትምባሆ መቆጣጠሪያ ሕጋዊ ማዕቀፍ” ተቀብላ እንድታፀድቅ ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት የተለያዩ ግፊቶችና ማግባባቶች ቢደረጉም እስከ አሁን ድረስ የህግ ማዕቀፍ አልፀደቀም፡፡

የዚህ ህጋዊ ማዕቀፍ መፅደቅ በህዝባዊ ሥፍራዎች ሲጋራ እንዳይጨስና የትምባሆ ማስታወቂያዎችና ፕሮሞሽኖች ላይ እገዳ ማድረግ እንዲሁም በሲጋራ ፓኬቶች ላይ ጐላ ያለ የሲጋራን ጉዳት የሚገልፅ ማስጠንቀቂያ እንዲፃፍ ማስገደድ፣ በትምባሆ ላይ ከፍተኛ ታክስ የመጣል  እርምጃዎች እንዲወሰዱ ያስገድዳል፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን የህግ ማዕቀፍ የምትደግፍ መሆኑን በማረጋገጥ እ.ኤ.አ በ2004 ዓ.ም ብትፈርምም የህግ ማዕቀፉን ካፀደቁት 172 የአለማችን አገሮች መካከል አልተቀላቀለችም፡፡

 

 

Read 10395 times Last modified on Saturday, 28 April 2012 14:36