Saturday, 26 May 2012 09:44

አስታዋሽ ያጡትን ማስታወስ!

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

በተለያዩ በሽታዎች ተይዘው አስታማሚና የቅርብ ርዳታ በማጣታቸው ምክንያት በየቦታው የወደቁና ዝናብና ፀሐይ እየተፈራረቀባቸው ለከፍተኛ ስቃይና ችግር የተዳረጉትን ወገኖች እያነሳ የሚንከባከብና የሚረዳ አንድ ምግባረ ሠናይ ድርጅት መኖሩን ሰማንና ሰሞኑን ወደ ሥፍራው ሄድን፡፡ በሮታሪ ኢንተርናሽናል ሥር የሚገኘው የፍኖተ ሮታሪ በጐ አድራጊ ክለብ ከሥፍራው ለመገኘታችንና ለመጐብኘታችን ምክንያት ነበር፡፡ የክለቡ አባላት በግል ተነሳሽነት ባዋጡት ገንዘብ የገዙትንና ከተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ለምነው ያሰባሰቡትን የተለያዩ የንጽህና መጠበቂያ ዕቃዎች፣ ብርድ ልብሶችና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ለእነዚሁ ወገኖች ለመስጠት በሥፍራው ተገኝተዋል፡፡ የክለቡ አባላት ማህበሩን ሰፋ ባለ መንገድ ለመርዳትና ሌሎች ድጋፎችንም ለማድረግ ቃል ሲገቡ እማኝ ሆነናል፡፡

ከሽሮሜዳ ወደ ሐመር ኖህ ኪዳነ ምህረት ገዳም መሄጃ መንገድ ላይ ማረፊያውን ያደረገውና “የወደቁትን አንሱ” የነዳያን መረጃ ማህበር የተቋቋመው በ1990 ዓ.ም ነው፡፡ ሥንታየሁ አበጀ በተባሉ በከፋ ደዌ ተይዘው ረዳት በማጣታቸው ምክንያት ጐዳና ወድቀው በነበሩና ከበሽታው በተፈወሱ አንድ ግለሰብ የተጀመረው ይኸው ማህበሩ፤ ዛሬ 80 የሚደርሱ ረዳት አልባ ደካሞችንና ህሙማንን እያስታመመና እየተንከባከበ ይገኛል፡፡ በአራት መጠለያ ቤቶች በሚሰጠው በዚህ እርዳታ፤ እስከዛሬ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

ህሙማኑ ከማህበሩ ከሚሠጣቸው የምግብና የመጠለያ አቅርቦት በተጨማሪ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ህሙማን ህክምና የሚያገኙበትን፣ ፀበል መጠመቅ ለሚፈልጉ ህሙማን ደግሞ ይህንኑ እንዲያገኙ በማድረግ ይረዳቸዋል፡፡

ንፁህ ልብስ ለብሰው፣ በንፁህ መኝታ ላይ ተኝተው፤ ንፁህ ምግብ እንዲመገቡ በማድረግ ህሙማኑን የሚንከባከቡ የማህበሩ ቅጥር ሰራተኞችና በጐ አድራጊ ሰዎች አሉ፡፡

አብዛኛዎቹ ህሙማን ራሳቸውን በሚገባ የማያውቁና ተነስተው መፀዳዳት የማይችሉ በመሆናቸው አስታማሚዎች ህሙማኑን የማፀዳዳቱን ተግባር ያለአንዳች መፀየፍና መሰልቸት ሲከውኑት ማየቱ ያስደንቃል፡፡ ከአስራ ሁለት ህሙማን በላይ የተኙበት ክፍል ጽዳትና  የመኝታዎቹን ንጽህና ተመልክተን አንዳችም መጥፎ ጠረን በአካባቢው አለመኖሩን ታዝበን ስንወጣ፣ የህሙማኑን ልብስ ከሚያጥብ ወጣት ጋር ተገናኘን፡፡ ለዓመታት ማየት ተስኖት በዚሁ ድርጅት እርዳታ ሲደረግለት ቆይቶ ዓይኖቹ በህክምናና በፀበል ለማየት በመቻላቸው ምክንያት ቀሪ ህይወቱን ወገኖቹን ለመርዳት ቃል የገባው ወጣት፤ በተለያዩ ነገሮች የተበላሸውንና የቆሸሸውን የህሙማኑን ልብስ ያለመታከት በየጊዜው ያጥባል፡፡ ልዩ ልዩ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችለውን የእጅ ጓንት ለማጠቢያ ይጠቀማል፡፡

ማህበሩ ወጣቱን በሠራተኝነት ቀጥሮ ደሞዝ መክፈል ቢጀምርም ወጣቱ ግን ከዚህ ይልቅ ለወገኖቹ እያደረገ ባለው ነገር እጅግ ደስተኛ ነው፡፡

የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ዓይናለም ኃይሌም ያረጋገጡልን ይህንኑ እውነት ነው፡፡

በማህበሩ ውስጥ እርዳታ ሲደረግላቸው ከነበሩ ወገኖች መካከል ሞተው በመንግስትና በቤተክርስቲያናት ሥርዓተ ቀብራቸው የተፈፀመ እንዳሉ ሁሉ፤ ከበሽታቸው አገግመው መጠለያ ቤቱን ለቀው የሄዱና በተለያዩ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ወገኖችም አሉ፡፡ ማህበሩ ከተለያዩ በጐ አድራጊ ወገኖችና ድርጅቶች በሚያገኛቸው እርዳታዎች አገልግሎቱን እየሰጠ መሆኑን የሚናገሩት የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ዓይናለም፤ ይህንኑ አገልግሎቱን ለማስፋፋትና ረዳት አልባና ደካማ ወገኖቹን በይበልጥ ለመርዳት የቦታ ውሱንነት እንቅፋት ሆኖት መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ይህንን ችግሩን የተረዳው መንግስትም 2923 ካሬ ሜትር ቦታ ከሊዝ ነፃ በመስጠት ድጋፉን ማሳየቱን ገልፀዋል፡፡ በተሰጣቸው ቦታ ላይ ረዳት አልባ አረጋውያንና ደካሞችን ለመንከባከብ የሚያስችል መጠለያ ለመገንባት ህዝቡ እንዲረባረብም ጠይቀዋል፡፡

የፍኖተ ሮታሪ ክለብ አባላት በራሳቸው ተነሳሽነት በግል ባዋጡት ገንዘብ የገዙትንና ከተለያዩ ድርጅቶች በእርዳታ ያገኙትን ቁሳቁሶች በመያዝ በሥፍራው ተገኝተው ህሙማኑን ጐብኝተዋል፡፡ የማህበሩ አባላት በቦታው ላይ ባዩት ነገር እጅግ ስሜታቸው መነካቱን ጠቁመው፤ ለዋናው ሮተሪ ኢንተርናሽናል ክለብ ፕሮጀክት ቀርፀው መላካቸውንና ያ እስከሚደርስ ድረስ ጊዜ በማይሰጥ ችግር ውስጥ ያሉ ወገኖቻቸውን ለመርዳት በማሰብ የተለያዩ ሳሙናዎች ፣ ቅባቶች፣ ጥጦች፣ የአዋቂ ዳይፐሮች፣ አልኮል፣ ብርድልብሶች፣ 29ሺህ ብር በሚደርስ ገንዘብ ገዝተው ማምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህ የፍኖተ ሮታሪ ክለብ እርዳታና ድጋፍ ለወደፊቱም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ከጐናቸው እንደሚቆሙም ለማህበሩ ሥራ አመራሮች አረጋግጠውላቸዋል፡፡

በ”የወደቁትን አንሱ” የነዳያን መርጃ ማህበር ውስጥ ካሉ ህሙማን መካከል የአዕምሮ ህመም ያለባቸውና እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ውስጥ ያሉትን ህሙማንም ለማየት ችለናል፡፡ አስታማሚዎቹ እነዚህን ህሙማን ለማስታመምና ለመንከባከብ እጅግ ከባድ ፈተና ሲገጥማቸውም ተመልክተናል፡፡ በግለሰብ ደረጃ የተሰባሰቡና የተደራጁ ሰዎች ለወገኖቻቸው ይህንን ያህል እርዳታና ድጋፍ ሲያደርጉ መንግስት እገዛና ድጋፉን ሊያደርግና ሊያግዛቸው እንደሚገባ እሙን ነው፡፡ በተለይ የህክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውና የአእምሮ ህሙማኑ እጅግ ፈጣንና አጣዳፊ ምላሽ ይፈልጋሉ፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Read 3465 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 10:32