Saturday, 28 July 2012 11:47

ታይፎይድ መንስኤ!

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(5 votes)

ምግብና ንፅህናው ያልተጠበቀ ውሃ

የንፁህ ውሃ አቅርቦት ችግር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለተለያዩ የጤና ችግሮች ይዳርገናል፡፡ የምንጠጣውም ሆነ ምግባችን የሚዘጋጅበት ውሃ ንፅናው ያልተጠበቀ ከሆነ፣ በተበከለ ውሃ አማካኝነት ለሚከሰቱት ውሃ ወለድ በሽታዎች መጋለጣችን አይቀሬ ነው፡፡ ነፍሳችንን ለማሰንበት ወደሆዳችን የምንልከው ምግብና የምንጠጣው ውሃ ከአሜባና ቫይረስ ወለድ ከሆነው መለስተኛ ተቅማጥ ጀምሮ የጨጓራ አልሰርን እስከሚያመጣው ባክቴሪያ ድረስ የሚደርሱ ጉዳቶችን ያስከትልብናል፡፡

ከእነዚህ በተበከለ ምግብና ንፅህናው ባልተጠበቀ የመጠጥ ውሃ አማካኝነት ከሚከሰቱት የጤና ችግሮች አንዱ የታይፎይድ ህመም ነው፡፡ ለዓይን ንፁህ የሚመስሉ ምግቦችና መጠጦች እንደዚሁም የመመገቢያና የመጠጫ ዕቃዎች የታይፎይድ በሽታ አምጪ የሆኑ ባክቴሪያዎችን በብዛት ሊይዙ ይችላሉ፡፡የታይፎይድ በሽታ አምጪ ባክቴሪያ፣ በአንድ አሜሪካዊ የእንስሳት ሐኪም እ.ኤ.አ በ1985 ዓ.ም ተገኘ፡፡ ባክቴሪያውም ባገኘው ተመራማሪ ስም (Salmonella Typhi) ሳልሞኔላ ታይፉይ የሚል መጠሪያ ተሰጠው፡፡

ባክቴሪያው በአፍ አማካኝነት ወደ ሰውነታችን ውስጥ የሚገባ ሲሆን በሽታውን ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው ሰው ለማስተላለፍም ጥቂት ጀርሞች በቂ ናቸው፡፡ የተለመደው የታይፎይድ መተላለፊያ መንገዱ በባክቴሪያው የተበከለ ምግብ መመገብና ንፅህናው ያልተጠበቀ ውሃን መጠጣት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በታይፎይድ ከታመመ ሰው፤ ወይንም ባክቴሪያው በሰውነቱ ውስጥ ካለው ሰው ጋር የሚደረግ ንኪኪ ማለትም መጨባበጥና የጨበጡበትን እጅ ሳይታጠቡ ምግብ መመገብ፣ በሽታው ከሚተላለፍባቸው መንገዶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የታይፎይድ ህመመተኛ የሆነ ሰው ዓይነምድር ባክቴሪያውን በከፍተኛ መጠን ይይዛል፡፡

ህመምተኛው የሚጠቀምበት የመፀዳጃ ቤት ንፅህናው ያልተጠበቀ መሆኑና ራሱም ህመምተኛው ከመፀዳጃ ቤት መልስ እጆቹን በውሃና በሳሙና ሙልጭ አድርጐ የመታጠብ ልምድ ከሌለው ንኪኪ የሚፈጥርባቸውን የመመገቢያ ዕቃዎች፣ ምግቦችና መጠጦች እንደዚሁም የሚጨብጣቸውን ሰዎች ሁሉ ሊበክል ይችላል፡፡ ከአይነምድር ባሻገር አክታ፣ የተውከት ፈሳሽና ሽንት በሽታውን ያስተላልፋሉ፡፡

በአንድ ቤት፣ ብዙ ሰዎች በሚኖሩበት ካምፕ፣ ት/ቤትና መሰል ሥፍራዎች ውስጥ አንድ ሰው በታይፎይድ ከተያዘ ወረርሺኝ የመቀስቀስ ብቃቱ ከፍተኛ የሚሆነውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ታይፎይድን የሚያመጣው ባክቴሪያ ቅዝቃዜና ሙቀትን ተቋቁሞ ተቀባይ እስከሚያገኝ ድረስ የመቆየት አቅሙም ከፍተኛ ነው፡፡

የታይፎይድ ባክቴሪያ በተመረዘ ምግብና ንፅህናው ባልተጠበቀ ውሃ እንዲሁም በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር በሚኖር ንኪኪ አማካኝነት ወደ ውስጣችን ከገባ በኋላ የቀጭኑ አንጀት የመጨረሻ ክፍል ላይ ሲደርስ ግድግዳውን ቦርቡሮ ከደም ጋር ይቀላቀላል፡፡ በመቀጠልም ለቫይረሱ መራቢያ የሚያመቸውን ቦታ በመምረጥ ይገባና መራባቱን ይቀጥላል፡፡

በዚህ ሁኔታ በከፍተኛ ቁጥር የተራባው ባክቴሪያ ተመልሶ በደም መሰራጨት እስከሚቀጥልበት ጊዜ ድረስ ታማሚው ምንም ዓይነት የህመም ስሜትና የበሽታ ምልክቶች ሳይታዩበት ይቆያል፡፡ የታይፎይድ ምልክቶች መታየት የሚጀምሩት ባክቴሪያው በሰውነት ውስጥ ከገባ ከስምንት እስከ አስራ ሁለት ቀናት ውስጥ ነው፡፡

ትኩሳት፣ የምግብ ፍላጐት ማጣት፣ ማስመለስና ተቅማጥ በታይፎይድ በሽታ የተያዘ ሰው የሚያሳያቸው ምልክቶች ናቸው፡፡ ህመምተኛው እነዚህ ምልክቶች በታዩበት ጊዜ ወደ ሐኪም ዘንድ ሄዶ ለበሽታው መድሃኒት ካላገኘ ምልክቶቹ እየጨመሩና እየቀጠሉ ይሄዳሉ፡፡

ቀስ በቀስ የሚጨምር ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት ራስ ምታት፣ ቁርጥማት፣ ድካም፣ የሆድ መነፋትና የሆድ ህመም፣ የጉሮሮ ህመም… በሽተኛው በቀጣይነት ከሚያሳያቸው ምልክቶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በሽታው በከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ቅዠትና ራስን መሣትም ሊያስከትል ይችላል፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ ህክምናን ለማግኘት ካልቻለም የመሞት ዕድሉ ይጨምራል፡፡

በወቅቱ ትክክለኛውን ህክምና ያገኙ የታይፎይድ ህሙማን፤ የመሞት ዕድላቸው አንድ ፐርሰንት ብቻ ሲሆን ህክምና ያላገኙ ህሙማን ግን 10 ፐርሰንት ሊደርስ ይችላል፡፡

ታይፎይድ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በብዛት ከመከሰቱ አንፃር ቀላል ህመም ተደርጐ የሚታሰብ ቢሆንም የሚያደርሰው ችግር እና የሚያስከትለው የጤና መዘዝ ግን ቀላል አይደለም፡፡

በጊዜው ህክምና ያላገኘ ታይፎይድ፤ የአንጀት ግድግዳ ተበስቶ አደገኛ ህመም እንዲፈጠር በማድረግ ለአንጀት መድማትና ለሞት ሊዳርግ ይችላል፡፡ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን፣ የአጥንትና የመገጣጠሚያ ኢንፌክሽን፣ የሳምባ ምች፣ የሀሞት ቧንቧ ኢንፌክሽንና የጣፊያ መፈንዳት በታይፎይድ ህመም አምጪ ባክቴሪያዎች ሰበብ ሊከሰት የሚችል ትልቅ የጤና ችግር ነው፡፡ በተመረዘ ምግብና ንፅህናውን ባልጠበቀ ውሃ አማካኝነት የሚተላለፈውን ይህንኑ በሽታ በቀላሉና ብዙ ወጪን በማይጠይቅ መንገድ ልንከላከለው እንችላለን፡፡

የምንጠጣውን ውሃ ንፅህና መጠበቅ፣ ከመፀዳጃ ቤት መልስና ምግብ ከማዘጋጀታችንና ከመመገባችን በፊት እጆቻችንን በንፁህ ውሃና ሣሙና መታጠብ በተለይ በከተማ አካባቢ የሚኖሩ ህብረተሰቦችን ብዙ ዋጋ የማይጠይቅ የበሽታ መከላከያ ዘዴ ነው፡፡

ሆቴሎችና የምግብ መሸጫ ሥፍራዎች ስለምግብ አዘጋጆቹ የጤና ሁኔታና የንጽህና አጠባበቅ ሊጨነቁና ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓታቸው ላይም እንደዚሁ ሊጠነቀቁ ይገባል፡፡

በአንድ ሆቴል ውስጥ የምግብ አዘጋጆች ከሆኑ ሰዎች መካከል አንዱ በምግብና ውሃ አማካኝነት ሊተላለፉ ከሚችሉ በሽታዎች (ኢንፌክሽኖች) የአንዱ ተሸካሚ ቢሆን በሆቴሉ ተመጋቢ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ለታይፎይድ የተጋለጡ ይሆናሉ፡፡

ስለዚህም ሆቴል ቤቶች፤ የሰራተኞቻቸውን ጤንነትና ንፅህና በሚገባ መጠበቅ፣ የሚመለከታቸው አካላትም ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ፣ በዚህ መልክ የሚመጣውን የታይፎይድ ችግር ማስወገድ ይቻላል፡፡

በያዝነው የክረምት ወር የምንጠቀምበትን የመጠጥ ውሃ ሊበክሉ የሚችሉ ታይፎይድ አምጪ ባክቴሪያዎችን ጨምሮ ሌሎች በሽታዎችን የማስተላለፍ አቅሙ ከፍተኛ ነው፡ ስለዚህም ለመጠጥ የምንጠቀምበትን ውሃ አፍልቶ በማቀዝቀዝ፣ መጠጣቱ ወይም አክሞ መጠቀሙ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው፡፡

 

 

Read 11700 times Last modified on Saturday, 28 July 2012 11:52