Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 11 August 2012 11:03

በድሬዳዋ የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ብናኝ ለጤና ጠንቅ ሆኗል መንግስት ለህብረተሰቡ ጤና ደንታ ቢስ ሆኗል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የመተንፈሻ አካላት ላይ የሚከሰተው የጤና ችግር ዋንኛው ሲሆን የአይን በሽታ እና ከንፅህና ጉድለት የሚከሰቱ የሆድ በሽታ ችግሮችም ተጠቃሽ ናቸው     (የአካባቢው ነዋሪዎች)

ብናኙ ስለአስከተለው የጤና ችግር ሪፖርት ያደረገልን አካል የለም….  (አቶ ያሬድ ታደሰ የፍብሪካው ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስኪያጅ)

በተደጋጋሚ አሳውቀናል፤ በአጭር ጊዜ ካላስተካከሉ ፋብሪካውን እስከ ማስቆም የሚደርስ እርምጃ እንወስዳለን፡፡  (የድሬዳዋ ጤና ቢሮ) “የምንበላውና የምንጠጣው ሲሚንቶ ነው፡፡ ልብስ አጥበን ማድረቅ፣ እህል አስጥተን ማስፈጨት አንችልም፡፡ የቤት ጽዳቱን ጉዳይ ተይው፡፡ በየሰዓቱ ብታፀጂውም ተመልሶ ያው ነው፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ አዋራው በጤናችን ላይ የሚያስከትለው ችግር ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች በተለይም ህፃናት አብዛኛዎቹ የአይን በሽተኞች ናቸው፡፡

ከእኔም ልጆች ሁለቱ በየጊዜው ይታመሙብኛል፤ በተለያዩ ጊዜያት ለፋብሪካው ሃላፊዎችም ሆነ ለቀበሌና ዞን መስተዳድሮች ብንናገርም ሰሚ አላገኘንም፡፡ ድሃን ማን ይሰማዋል? ከተማ መሀል ይህን ሁሉ አዋራ የሚለቅ የሲሚንቶ ፋብሪካ ከፍቶ ሕዝቡን እንዲጨርስ የፈቀዱትስ እነሱው አይደሉ?” ይህን ያሉን ወ/ሮ ሃይዳ ሚፍታህ ይባላሉ፡፡ በድሬዳዋ ከተማ ሽመንተሪ በሚባለው ሰፈር ላለፉት 10 ዓመታት ኖረዋል፡፡ የአምስት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ሃይዳ ከወለዷቸው ልጆች መካከል ሁለቱ የሐኪም ቤት ደንበኛ እንዳደረጉዋቸው ይናገራሉ፡፡

ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዘ የጤና ችግር ላለበት የሰባት ዓመቱ ወንድ ልጃቸውና በዓይን ህመም ሣቢያ በየጊዜው ወደ ድል ጮራ ሆስፒታል ለምታመላልሳቸው የሶስት ዓመቷ ሴት ልጃቸው የጤና ችግር መንስኤው በአቅራቢያቸው የሚገኘው የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከፋብሪካው የሚለቀቀው ብናኝ በእሳቸው፣ በህፃናት ልጆቻቸውና በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ እያደረሰ ያለውን የጤና ችግር ለሚመለከታቸው ሁሉ ቢያሳውቁም መፍትሔ እንዳላገኙ ይናገራሉ፡፡ “የፋብሪካው የሥራ ኃላፊዎች ስለሚያገኙት ገንዘብ እንጂ ስለእኛ ጤና ለደቂቃዎች ማሰብ የፈለጉ አይመስለኝም፡፡ መንግስትም ቢሆን ከፋብሪካው ስለሚያገኘው ገቢና ግብር እንጂ በነዋሪው ላይ እያደረሰ ስላለው ችግር ሰሚ ጆሮ የለውም፡፡ እኛ ታዲያ ወደየት እንሂድ? ለማንስ ነው አቤት የምንለው?” የወ/ሮ ሐይዳ ቅሬታ ነው፡፡

ይህንኑ የወ/ሮ ሃይዳን ቅሬታ አብዱራህማን ጀሎ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ይጋሯቸዋል፡፡

“በመሃል ከተማ ህፃናትና አረጋውያን በሚኖሩበት አካባቢ ላይ ይህንን ያህል ብናኝ የሚለቅ ፋብሪካ እንዲሰራ መፍቀድ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አይገባኝም፡፡ ይህ ለእኔ የሚያመለክተኝ መንግስት ለዜጐቹና ለህብረተሰቡ ደንታ ቢስ መሆኑን ነው” ብለዋል፡፡

ወጣቷ የሽመንተሪ ነዋሪ ትዕግስት በፍቃዱም የዚሁ ብሶት ተጋሪ ነች “ሽመንተሪ ኖረሽ ለብሰሽ ማጌጥና መዘነጥ የለም፡፡ ፀጉራችንን ተሰርተን በማግስቱ መታጠብ ግድ ነው፡፡ አዋራው ወፍጮ ቤት የዋለች ሴት አስመስሎን ቁጭ ይላል፡፡ ካለመነጽር መሄድ፣ ነጣ ያሉ ልብሶችን መልበስ የማይታሰቡ ነገሮች ናቸው፡፡ የብናኝ ልቀቱ በምሽት የከፋ ነው፡፡ ግን ይህ ነገር እስከመቼ ነው የሚቀጥለው፡፡ ፋብሪካውን ሃይ የሚልና ህብረተሰቡን ሊጐዳ በማይችል መልኩ ምርቱን እንዲያመርት ማድረግ የሚችል አካል የለም ማለት ነው?” ትዕግስት ትጠይቃለች

እነዚህን ቅሬታዎች የሰማነው በ”water aid Ethiopia” ሥር የሚገኘው የ”Wash movement” በከተማዋ ልዩ ልዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ስለ ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ ስለ ግል ንፅህና አጠባበቅ፣ ስለ ቆሻሻ አወጋገድና ንፅህና ከጤና ጋር ያለውን ትስስር አስመልክቶ ዘገባ ለማዘጋጀት እንድንችል ባደረገልን ድጋፍ መሠረት ሰሞኑን ወደ ሥፍራው በተጓዝንበት ወቅት ነበር፡፡

ይህንን የነዋሪዎቹን ቅሬታ ይዘን ወደ ፋብሪካው ሄድን፡፡ የፋብሪካው የሥራ ኃላፊዎች ወደ ውስጥ ገብተን ለማነጋገርና መረጃዎችን ለመሰብሰብ እንድንችል ፍቃድ ቢሰጡንም፣ በያዝናቸው የምስል መቅረጫ (ካሜራዎች) የፋብሪካውን የውስጥ ገጽታም ሆነ የሃላፊውን ፎቶግራፎች ለማንሳት እንደማንችል ነግረውናል፡፡ የፋብሪካው ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ታደሰ የአካባቢው ነዋሪዎች የሚያነሱትን ቅሬታ አስመልክተው ሲናገሩ፤ የፋብሪካው ብናኝ ሽመንተሪ፣ ጐሮ፣ ሳቢያንና ጀርባ በተባሉ ሰፈሮች ላይ ይደርሳል ተብሎ እንደሚታሰብ ገልፀው፤ ከአካባቢው ነዋሪዎች ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ከዚህ ቀደም ቅሬታዎች ቀርበውላቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ የፋብሪካው ብናኝ አስከተለ ስለተባለው የጤና ችግር ዝርዝር ሪፖርት ከየትኛውም አካል እንዳልደረሳቸው አቶ ያሬድ ተናግረዋል፡፡ የፋብሪካው ልቀት መቆጣጠሪያ ሲስተም (ASP) በቀጥታ ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የሚገናኝ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ያሬድ፤ የሃይል መዋዠቅ በሚያጋጥምበት ወቅት ከፍተኛ የአቧራ ልቀት ሊኖር እንደሚችል ገልፀዋል፡፡

ብናኙ ያስከተለውን የጤና ችግር የሚያመለክቱ ቅሬታዎች ወደ ፋብሪካው ከመምጣታቸው በፊት ፋብሪካው ልቀቱን የሚቆጣጠርበትን መንገድ የማስተካከሉን ሥራ ለመሥራት ዕቅድ ይዘው እንደነበር የተናገሩት አቶ ያሬድ፤ የአዲሱ ፋብሪካ ግንባታ ግን ዕቅዳቸውን እንዳያሳኩ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡

“በ1.8 ቢሊዮን ብር ወጪ በቀን ከ40-45ሺ ኩንታል ሲሚንቶ የማምረት አቅም ያለው አዲስ የሲሚንቶ ፋብሪካ በመገንባት ላይ ነን፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን ይህንን የፋብሪካ ግንባታ አስቁመን ማስተካከሉ ከባድ ነው፡፡ በመጪዎቹ ሁለት እና ሶስት ወራት አዲሱ ፋብሪካ ግንባታው ተጠናቆ ሥራ ስለሚጀምር ያን ጊዜ የዚህኛውን ፋብሪካ ሥራ በማስቆም ወደማስተካከሉ ሥራ እንገባለን” ብለዋል፡፡

በፋብሪካው የልቀት ሁኔታ ላይ ጥናት ማስጠናታቸውን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ የልቀት መጠኑ በየጊዜው እንደሚለያይና በተወሰኑ ሰዓታት ማለትም የሃይል መዋዠቅ በማይኖርባቸው ጊዜያት ከሚጠበቅበት በታች፣ የሃይል መዋዠቁ በሚኖርበት ጊዜ ደግሞ ከሚጠበቅበት በላይ ልቀት እንደሚኖር ገልፀዋል፡፡ “በብናኝ መልክ የሚወጣው እኮ ለእኛ ምርታችን ነው፤ ልናስቀረው ብንችል አትራፊዎቹ እኛ ነበርን፤ ግን ቀደም ሲል ፋብሪካው የተሰራበት ሁኔታ ይህንን እንዳናደርግ አግዶናል ሲሉም አክለዋል፡፡

በፋብሪካው ቅጥር ግቢ በተገኘንበት ወቅት ፋብሪካው በሥራ ላይ ስለነበረና ወደ አየር የሚለቀው ብናኝና የተቃጠለ ጋዝ ለእይታ በጣም ቅርብ ስለነበር ሁኔታውን ፎቶግራፍ ለማንሳት ጠይቀን ተከልክለናል፡፡

የነዋሪዎቹን ቅሬታና የሥራ አስኪያጁን ምላሽ ይዘን የከተማዋ የጤና ቢሮ በጉዳዩ ላይ የሚለውን ለመስማት ወደዚያው አመራን፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ተወካይ ኃላፊ አቶ ካሣሁን ኃ/ጊዮርጊስ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡

“ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ለህብረተሰቡ ጤና ትልቅ ጠንቅ ሆኗል” ሲሉ የጀመሩት አቶ ካሳሁን፤ ፋብሪካው በህብረተሰቡ ጤና ላይ እያስከተለ ያለውን የጤና ችግር አስመልክቶ ለፋብሪካው ሃላፊዎች በተደጋጋሚ ማሳወቃቸውን ገልፀዋል፡፡

ከፋብሪካው በሚወጣው ብናኝ መነሻነት ስለሚመጡ በሽታዎችም ሲናገሩም፤ የመተንፈሻ አካላት ላይ የሚከሰተው የጤና ችግር ዋንኛው ሲሆን የአይን በሽታ እና ከንፅህና ጉድለት የሚከሰቱ የሆድ በሽታ ችግሮችም ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡ በተለይ ህፃናት በእነዚህ በሽታዎች ለመጠቃት በጣም ቅርብ መሆናቸውንና ችግሩ በቀላሉ የማይታይ እንደሆነም አቶ ካሳሁን ተናግረዋል፡፡

ከድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ ህዝብ መካከል ቢያንስ የሶስት ቀበሌ ነዋሪዎች በዚህ ለጤና ጥሩ ባልሆነ አካባቢ ውስጥ እንዲኖሩ መገደዳቸውን የተናሩት ኃላፊው፤ በቀበሌ 01፣ 02 እና 03 ውስጥ የሚኖረው ከ80ሺ በላይ ህዝብ የችግሩ ቀጥተኛ ተጠቂ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ ስለችግሩ ከፋብሪካው የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ማድረጋቸውን የጠቆሙት አቶ ካሳሁን፤ ከፋብሪካው ሃላፊዎች በኩል ችግሩን የማስተካከልና የጤና ጠንቅ የሆኑትን ነገሮች በማስወገድ ረገድ ቀና ምላሽ ባለመታየቱ በቅርቡ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

የጊዜ ገደብ በማስቀመጥም አቧራና ብናኝ ኬሚካሎችን ወደ ውስጥ ለማስቀረት የሚችሉ መሣሪያዎችን እንዲገጥሙ ግዴታ ማስገባታቸውን ገልፀዋል

በገቡት ግዴታ መሠረት የማይፈጽሙ ከሆነ ግን ፋብሪካውን እስከማስቆም የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስዱም አቶ ካሳሁን ተናግረዋል፡፡ ወደ ኢንቨስትመንቱ ዘርፍ በቀጣይ የሚገቡ ባለሃብቶች ሁሉ የአካባቢ ጥበቃና የህብረተሰቡን የጤና ችግር ለማስወገድ የሚችሉበትን መንገድ ካላሟሉ በስተቀር ወደ ኢንቨስትመንቱ እንዳይገቡ ማድረግ አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑን አቶ ካሳሁን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

 

 

Read 3772 times Last modified on Saturday, 11 August 2012 11:22