Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 September 2012 11:24

የአጥንት ህክምና በኢትዮጵያ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

“አብዛኛው በሽተኛ ባህላዊ ሃኪሞችጋ ተውጦ ይቀራል”

በኢትዮጵያ የአጥንት ህክምና ራሱን ችሎ መሰጠት ከጀመረበት እና ሥልጠናውም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዲፓርትመንት ተቋቁሞለት ባለሙያዎችን ማፍራት ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ የህክምናው ፍላጐት እና ህክምናው በሚሰጥባቸው የጤና ተቋማት ላይ የሚፈጠረው ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ በአንጻሩ የህክምና አሰጣጡ እና በሙያው የሰለጠኑ ባለሙያዎች ቁጥር ከፍላጐቱ ጋር ያለው ልዩነት እጅግም ሲጠብ አይታይም፡፡ ያም ሆኖ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው በህክምና ዘርፉ የሚያሰለጥኑ ተቋማት እና በሙያው መሰልጠን የሚፈልጉ ተማሪዎች ቁጥር እያደገ መምጣት፣ ህክምናውን የሚያግዙ መሳሪያዎች እና ህክምናውን የሚሰጡ የግል ሆስፒታሎች መፈጠር ለአጥንት ህክምና የተስፋ ጊዜ እየመጣ መሆኑን ያሳያል፡፡

በመላው ኢትዮጵያ በዘመናዊ ሐኪሞች እና በሕክምናቸው ላይ ህዝቡ ያለው እምነት ዝቅተኛ ስለመሆኑ ብዙ ጥናቶች እና ምልከታዎች ያረጋግጣሉ፡፡

በማናቸውም የህይወት ዘርፎች ህዝቡ የሥልጣኔ ቀደምትነት ቢኖረውም፤ በልማድ እና በባህል ይዞ ያቆያቸውን እምነቶቹን ትቶ ወደ ዘመናዊነትን እንዲመጣ ማድረግ ፈታኝ ሂደት ነው፡፡ በአጥንት ህክምናም የታየው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ህዝቡ የሚያጋጥሙትን የአጥንት እና የመገጣጠሚያ ችግሮች ሐኪም ዘንድ ሄዶ ከመፍታት ይልቅ በወጌሻዎች ታሽቶ እና ባህላዊ መድኃኒቶችን ተጠቅሞ መዳንን ይመርጣል፡፡

“አብዛኛው በሽተኛ ሆስፒታል ይመጣል ማለት አንችልም” ይላሉ የድሬዳዋው ድል ጮራ ሆስፒታል የአጥንት ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ማንያዘዋል፣ ደሴ በድሬዳዋ እና በዙሪያው ህብረተሰቡ ከህክምና መስጫ ተቋማት ይልቅ ለባህላዊ ሐኪሞች ያለውን አመኔታ ሲያስረዱ፡፡ “አብዛኛው በሽተኛ ባህላዊ ሐኪሞች ጋር ተውጦ ይቀራል፡፡” በሽተኞች ወይም አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች የሆስፒታልን ደጃፍ የሚረግጡት ችግሮቻቸው ከተባባሱ እና መዳን አስቸጋሪ የሚሆንበት ደረጃ ላይ ከደረሱ በኋላ መሆኑንም ያነጋገርናቸው ሐኪሞች ይናገራሉ፡፡

ያም ሆኖ ግን አሁን በያካባቢው እየተስፋፉ ባሉት የህክምና ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎቶች በተለያዩ መንገዶች እየተዋወቁ በመምጣታቸው እና በሌሎችም ምክንያቶች የህክምና ፈላጊው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡

ባለሙያዎች ለመረዳት እንደቻልነው፤ የአገልግሎቱ ፈላጊዎች ብዛት ከዓመት ዓመት ከፍ እያለ ነው፤ የአጥንት ህክምና ክፍሉ አርሲ እና ባሌን ጨምሮ በዙሪያው ለሚኖሩ ወደ 3.5 ሚሊዮን ለሚደርሱ ሰዎች አገልግሎት እንደሚሠጥ የሚነገርለት የአሠላ ሪፈራል ሆስፒታል የአጥንት ህክምና ባለሙያ ዶ/ር ቃኘው ውብሸት በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፤ “ሰው ከባህላዊ የወጌሻ ህክምና ወደ ዘመናዊ ህክምና እየመጣ ነው፡፡ ዘመናዊውን ህክምና የሚፈልጉት ተገልጋዮች ቁጥር የጨመረው ለህዝቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሠርቶ ሳይሆን በአጥንት ህክምናው በሚታዩ ውጤቶች አማካኝነት ነው፡፡”

በወጌሻ ህክምና የሚፈጠሩት ውስብስብ ችግሮች በታካሚዎች ላይ ከሚያደርሱት ጉዳት እና በዘመናዊ የህክምና መስጫዎቹም ላይ ከሚፈጥሩት ጫና አኳያ የግንዛቤው ማደግ መልካም ሆኖ ሳለ፤ ይህንን ባህላዊ ህክምና ሸሽተው እና ዘመናዊውን ፈውስ ሽተው ወደ ጤና ተቋማት ለሚመጡት ታካሚዎች በሀገሪቱ ያለው የአጥንት ህክምና አገልግሎት ምን ያህል በቂ ዝግጅት አለው ብለን ስንጠይቅ፣ በተለይ ቅኝት ባደረግንባቸው አካባቢዎች የተመለከትነው የአገልግሎቱን የሚያበረታታ ጅምርነት ነው፡፡

“በአገር ደረጃ ያለው የአጥንት ህክምና እድገት እንጭጭ የሚባል ነው፡፡ ህክምናው ገና በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ ጓዳ ውስጥ ያለ ነው፡፡ በአገሪቱ ያሉት የአጥንት ሕክምና ባለሙያዎች በጣም ጥቂት ናቸው፤ በአብዛኛው ህዝብ ባህላዊ የወጌሻ ህክምና ላይ ነው ያለው፡፡ ዘመናዊ የአጥንት ህክምና ገና እየታወቀ ያለ ነው፡፡ ከተጀመረበት ጊዜ ይልቅ አሁን አሁን እየታየ ባለው ውጤት የህዝቡም ግንዛቤ እየተለወጠ መጥቷል፡፡” በማለት ለውጡ ግን አዝጋሚ እና አለም ከደረሰበት የህክምናው ደረጃ ጋር  ሲነፃፀር በጣም ገና መሆኑን ዶ/ር ቃኘው ይናገራሉ፡፡

በተዘዋወርንባቸው አምስት የሀገሪቱ ክፍሎች ባየናቸው የአጥንት ሕክምና የሚሰጡ ሆስፒታሎች ውስጥ ያገኘናቸው ሐኪሞች በሙሉ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ነዋሪዎች በብቸኝነት አገልግሎት የሚሰጡ የአጥንት ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ የደሴ ሪፈራል ሆስፒታልን በምሳሌነት ማየት እንችላለን፡፡ የሆስፒታሉ ተገልጋዮች ከአፋር፣ ከወሎ፣ ከሸዋ ሮቢት እና ከሌሎችም የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚመጡ ሲሆን ሀኪም ቤቱ እስከ 7 ሚሊዮን ለሚደርሱ ሰዎች አገልግሎት የሚሠጥ ነው፡፡

ከደሴ ሆስፒታል በተጨማሪ አንድ የግል ሆስፒታል ውስጥ የአጥንት ህክምና መሠጠቱ የሪፈራል ሆስፒታሉን ጫና ይቀንስለት እንጂ፣ ሆስፒታሉ የሚሰጠው አገልግሎት ከህክምናው ፈላጊው ጋር አይነፃፀርም፡፡ ይህንን ጫና ከሚያባብሱት ምክንያቶች ዋነኛው ደግሞ ይህንን ሁሉ ህዝብ እንዲያገለግል የተመደበው የአጥንት ሐኪም “አንድ ለእናቱ” መሆኑ ነው፡፡ በሶዶ፣ በድሬዳዋ፣ በሰላ እና በወሊሶም ያየነው ይሄንኑ ነው፣ አንድ የአጥንት ቀዶ ሐኪም ለሚሊዮኖች፡፡

የባለሙያ እጥረት በመላው ሐገሪቱ የሚታይ ችግር ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአጥንት ህክምና የትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ተዘራ ጫካ በጽሑፎቻቸው እንዳመለከቱት፤ በተለያዩ የአጥንት ህክምና ንኡሳን ዘርፎች የሰለጠኑ ባለሙያዎች ቁጥር ዝቅተኛነት በአጠቃላይ የህክምና አገልግሎቱ ከሚያጋጥሙት ዋነኛ ችግሮች ቀዳሚው ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአጥንት ህክምና የትምህርት ክፍል ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስካለፉት ሁለት ዓመታት ድረስ ለማስተማር የሚቀበላቸው እጩ ሐኪሞች ቁጥር ከሦስት እና ከአራት አይዘሉም ነበር፡፡ በመሆኑም በየዓመቱ ወደ መላው ሀገሪቱ አካባቢዎች በባለሙያነት የሚሰማሩት ተመራቂዎች አንድ ሁለት ቢሆኑ ነው፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት ያፈራቸው ባለሙያዎችም 46 ብቻ መሆናቸውን የዶ/ር ተዘራ ጽሑፍ ያሳያል፡፡ ይሔ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ከመጣው ፍላጐት ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

ጊዜ የማይሰጡ ችግሮች

ዶ/ር ዱዌን አንደርሰን በሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል ዳይሬክተር እና የአጥንት ህክምና ባለሙያ ናቸው፤ በሆስፒታሉ ብቸኛ የአጥንት ቀዶ ሐኪም መሆናቸው የፈጠረባቸውን ጫና ሲገልፁ፤ “በአንድ ቀን እስከ 13 ቀዶ ህክምናዎችን እናደርጋለን፣ ከእነዚህም መሐል አምስቱ ከፍተኛ ሲሆኑ ሌሎቹ አነስተኛ ቀዶ ህክምናዎች ናቸው” ይላሉ፡፡ በሁለት የቀዶ ህክምና መስጫ ጠረጴዛዎች በተመሳሳይ ጊዜ ሁለት ታካሚዎችን የሚያክሙበት ጊዜ መኖሩንም ይናገራሉ፡፡ የድል ጮራው ዶ/ር ማንያዘዋልም አዋዋል ከዚህ አይለይም፡፡ በሳምንት ሃያ እና ሰላሳ ታካሚዎችን በአንድ የአጥንት ህክምና ጤና ረዳት ታግዞ ማከም በእሳቸውም ዘንድ የተለመደ ተግባር ነው፡፡ እንደ ዶ/ር አንደርሰን ያሉት ጫናው የበረታባቸው ሐኪሞች የተጣለባቸውን የሙያ ኃላፊነት ለመወጣት ሲሉ የሻይም ሆነ የምሳ የእረፍት ሰአቶቻቸውን ሥራቸው ላይ በማሳለፍ በሰው ኃይል እጥረት ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን ክፍተት ለመሙላት ይሞክራሉ፡፡

ሆኖም፣ የሐኪሞቹ እጥረት ሳያንስ በአብዛኞቹ አካባቢዎች የሚገኙት ሆስፒታሎች ህክምናቸውን በበቂ ሁኔታ መስጠት የሚችሉባቸው የህክምና መሳሪያዎች አልተሟሉላቸውም፤ “ይህ በአገር አቀፍ ደረጃም ያለ እውነታ ነው፡፡ የአጥንት ህክምና በኢትዮጵያ ከፍተኛ ፍላጐት አለው፡፡ ለዚህ ታላቅ ፍላጐት ተመሳሳይ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የባለሙያም ሆነ የቁሳቁስ አቅርቦት ግን የለም” ይላሉ፤ የአሰላው ዶ/ር ቃኘው ውብሸት፡፡ “የቦታ ጥበት፣ የቁሳቁስ እንደልብ አለመገኘት እና የባለሙያዎች እጥረት አገልግሎት አሠጣጡን አዳጋች አድርጐታል፡፡”

በሆስፒታሎቹ ያሉት በቂ ያልሆኑ አልጋዎች እያንዳንዳቸው በዓመት ከአቅማቸው በላይ ታካሚዎችን ያስተናግዳሉ፡፡

የሌሎች ወሳኝ የህክምና ቁሳቁሶች አቅርቦትም አገልግሎቱን አይመጥንም፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ አያና፣ በወሊሶ ቅዱስ ሉቃስ ሆስፒታል የአጥንት ህክምና ክፍል ኃላፊም፣ የህክምናው መገልገያ ቁሳቁስ እንደ ልብ አለመገኘቱ ህክምናውን በሀገሪቱ ለማዳረስ እንቅፋት መሆኑን በአጽንኦት ይናገራሉ፤፤ ህክምናው በአብዛኛው በአዲስ አበባ ተወስኖ የቆየው ከዚህ የተነሳ መሆኑን ያምናሉ፡፡

የአሰላ ሪፈራል ሆስፒታልን ደግሞ እንውሰድ፤ የአጥንት ህክምና ክፍሉ አገልግሎት በሚሰጥባቸው አርሲ እና ባሌን ጨምሮ በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች በግልም ሆነ በመንግስት ደረጃ የአጥንት ህክምናን የሚሠጥ ሌላ ሀኪም ቤት የለም፤ በዚህም የተነሳ እራሱን የቻለ ዋርድ ስለሌለው የቀዶ ህክምና ክፍልን ከመሳሰሉ ሌሎች የህክምና ክፍሎች ጋር በሚጋራቸው አልጋዎች ታካሚን መከታተል አዳጋች ነው፡፡

የራሱ አልጋ አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን ራሱን ችሎ ባለመቆሙ እና ከአገልግሎት ፈላጊው ጋር የተመጣጠነ የመኝታ ክፍል እንዲሁም የተለያዩ ውስብስብ እና ዘመናዊ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችሉ ዘመናዊ መሣሪያዎችን አለማግኘቱ የአጥንት ህክምና አሠጣጡ ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽእኖ አሳርፎበታል፡፡

በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ግን አስቀድሞ እንዳልነው፣ የህክምናው ፍላጐት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፤ ስለ አገልግሎቱ መረጃ ከመስማት እና አገልግሎቱም በተለያዩ አካባቢዎች መስፋፋት ከመጀመሩ ባሻገር ፍላጐቱ እንዲጨምር ዋነኛ ምክንያቶች የሆኑት አብዛኞቹ የአጥንት ጤና ችግር መንስዔነት የሚጠቀሱት አደጋዎች ናቸው፡፡

በድሬዳዋ በየዓመቱ ድል ጮራ ሆስፒታል ከሚቀበላቸው 1008 ገደማ አዳዲስ ታካሚዎች 80 በመቶው በሰው ሠራሽ አደጋ ተጐድተው የሚመጡ ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ ተፈጥሯዊ ችግሮች ያሉባቸው ናቸው፡፡

እነዚህን በመላው ኢትዮጵያ በአጥንት ህክምና ላይ ጫና እየፈጠሩ ያሉ የበሽታ መንስዔዎች ስንመለከት በመኪና እና በሌሎች ተሽከርካሪዎች የሚደርሱ አደጋዎችን፣ የመውደቅ አደጋዎች፣ ግጭቶች እና የመሳሰሉትን እናገኛለን፡፡ በድል ጮራ ሆስፒታል የአጥንት ህክምና ክፍል ኃላፊው በዶ/ር ማንያዘዋል ትንታኔ መሠረት በአደጋ ምክንያት ወደ ክፍላቸው የሚመጡ ታካሚዎች ችግሮቻቸው ይህንን ይመስላሉ

የመኪና አደጋ - 45 በመቶ

የመውደቅ አደጋ - 30 በመቶ

ማሽን እና ፀብ - ከ15 እስከ 20 በመቶ ይይዛሉ

 

በደሴ ሆስፒታል ደግሞ ከትራፊክ አደጋ ቀጥሎ ከፍተኛውን ጉዳት እያደረሰ እና በሆስፒታሉም ላይ ጫና እየፈጠረ የሚገኘው የሰዎች አካላዊ ግጭት እና መጐዳዳት ነው፡፡ በወሊሶ በፀብ ተጐድተው ወደ ሆስፒታል የሚመጡት፤ በትራፊክ አደጋ ከሚጐዱት ሁሉ በቁጥር ይበልጣሉ፡፡

በድሬዳዋ እና በዙሪያዋ ሰዎች ሲጋጩ እንደ ሜንጫ ባሉ ስለታማ መሣሪያዎች እርስ በርስ ስለሚጐዳዱ በዚህ መልኩ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ታካሚዎች ቶሎ ቶሎ ማየት የተለመደ ነው፡፡ በአሰላ እና በዙሪያውም ቢሆን በአብዛኛው ለአጥንት ህክምና ፈላጊዎች መብዛት ምክንያት የሚሆኑት በሰዎች የእርስ በርስ ጠብ መንስኤ የሚከሰቱ አደጋዎች ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን መንገዱ በዘመናዊ መልክ መሠራቱን ተከትሎ በባጃጅ እና በመኪና አደጋዎች ምክንያት ለህክምና የሚመጡት ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ መጥቷል፡፡

ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የመንገድ ዝርጋታዎች እና መንገዶቹን ተከትሎ የመጣው የትራፊክ እንቅስቃሴ መጨመር ለትራፊክ አደጋው መብዛት፤ የግንባታዎች መስፋፋት እና የደህንነት ጥንቃቄዎች እኩል አለማደግ፣ ለግንባታ አደጋዎች መብዛት እንዲሁም የእርስ በርስ ግጭቶች ለተጐጂዎች መብዛት ምክንያቶች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ፣ የአጥንት ህክምና በኢትዮጵያ ነገ ዛሬ ሳይባል በባለሙያ እና በቁሳቁስ ተጠናክሮ እንዲስፋፋ የግድ የሚሆንበት ዋነኛ ምክንያት፣ ከላይ የጠቀስናቸው፣ ሆስፒታሎቹ ላይ ጫና የሚፈጥሩ መሠረታዊ ችግሮች በፍጥነት እየተባባሱ እንጂ እየተሻሻሉ ሲመጡ አለመታየታቸው ነው፡፡ ዛሬም ከትናንት በባሰ ሁኔታ በመላ ሀገሪቱ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ይጐዳሉ፤ ይሞታሉ፤ ዛሬም በግንባታ እና በማሽን ሥራዎች ላይ ከደህንነት ጥንቃቄዎች መጓደል የተነሳ ከትናንት በባሰ ሁኔታ ሰዎች ለአደጋ ይጋለጣሉ፤ ዛሬም በተለያዩ ምክንያቶች ሰዎች ተጋጭተው እርስበርስ ይጐዳዳሉ፡፡

ሌላው ይህንን ውጥረት የበዛበት የህክምና አገልግሎት የሚፈጥነው የተጐጂዎች በወጌሻዎች ከተበለሻሹ በኋላ ወደ ሆስፒታሎቹ መምጣታቸው ነው፡፡ በዚህ ከግንዛቤ እጥረት በሚመጣ ችግር ሐኪሞች ይማረራሉ፤ ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ ከወጌሻ መልስ ወደ ሐኪሞቹ የሚሄዱት ምንም ሳይነካኩ ቢተዉ የሚድኑ ችግሮቻቸው ከተወሳሰቡ እና ተስፋ ከቆረጠባቸው በኋላ ነው፡፡ በቀላሉ ይድኑ የነበሩ ችግሮች ተባብሰው ሆስፒታሎች ላይ አላስፈላጊ ጫና ይፈጥራሉ፤ ለዚህም ነው ዶ/ር አንደርሰን የኢትዮጵያ ባህል ተለውጦ ሕዝቡ የአጥንት ቀዶ ሐኪሞችን እንደ ብቸኛ የአጥንት እና የመገጣጠሚያ ችግሮቹ ፈቺ አድርጐ ቢወስዳቸው ታላቅ ስኬት እንደሚሆን የሚናገሩት፡፡

የባለሙያ እና የቁሳቁስ እጥረት ባለበት ሁኔታ እንዲህ ያሉ ችግሮቹን የሚያባብሱ ሁኔታዎች መከሰት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆናል፡፡

ዕድሎች እና ተስፋዎች

“በቁጥርም ሆነ በአስከፊነት እየጨመሩ ካሉት የአደጋ ሰለባዎች እና ሌሎች የአጥንት እና የመገጣጠሚያ ችግሮች አኳያ ሲታይ፣ ሙያውን በመላ ሐገሪቱ የማስፋፋት አስፈላጊነት አያጠራጥርም፡፡ በመስኩ ገና በጅምሩ ላይ ያለው የተሻሻሉ የህክምና ዘዴዎችን የመጠቀም ነገር ሊበረታታ ይገባዋል፡፡”

ይህ በተባባሪ ፕሮፌሰር ተዘራ የቀረበ የይሁንታ ሐሳብ ነው፤ እስካሁን የዘረዘርናቸው የአጥንት እና የመገጣጠሚያ ህክምና ተግዳሮቶች ጠቅላላ የህክምናውን ድባብ የሚያጨልሙ ተደርገው መወሰድ የለባቸውም፡፡ ህክምናው እነዚህን በመሳሰሉ ችግሮች የተከበበ ቢሆንም፤ በተለይ በተዘዋወርንባቸው ሆስፒታሎች ማየት እንደቻልነው፤ በተጨናነቀ ሁኔታም ውስጥ የሚሰጡት የህክምና አገልግሎቶች በአዝግሞትም ቢሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ መጥተዋል፡፡ በየቦታው ያገኘናቸው የጤና ባለሙያዎች ዕውቀታቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን ሳይቆጥቡ፣ ደከመን እንረፍ ሰለቸን እንጥፋ ሳይሉ አገልግሎታቸውን እንደሚሰጡ ተረድተናል፡፡ ይሄ ቀናነት በኢትዮጵያ በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በተሻሻሉ ህክምናዎች ለማቃለል የሚረዳ አንድ ትልቅ ግብአት ነው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሊደረጉ የታሰቡ ማሻሻያዎች ይህንን ግብአት በመንደርደሪያነት መጠቀም ይችላሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የአጥንት ህክምና ትምህርትን በተለያዩ ደረጃዎች የማስፋፋት እንቅስቃሴዎች በዘርፉ የሚሰጡትን አገልግሎቶች በበቂ ሁኔታ ለማዳረስ ተስፋ የሚሰጡ ሁነቶች ናቸው፡፡ ዶ/ር ዘላለም እንደሚሉት፤ ህክምናውን በአገር አቀፍ ደረጃ የማሳደጉ ነገር ብዙ ሊሠራበት የሚገባ ነገር ነው፡፡ “ባለሙያዎችን ማፍራት፣ ያሉንንም ባለሙያዎች በተደራጀ መልኩ በአግባቡ መጠቀም ቢቻል እና የእውቀት ደረጃቸው ከፍ ያሉ ባለሙያዎች ልምዳቸውን የሚያጋሩበት ሁኔታ ቢመቻች መልካም ነው፡፡

ትኩረት ሰጥቶ ከተሠራ የአጥንት ህክምና አስደሳች እና ውጤቱም የሚያረካ የህክምና መስክ ነው”  ሥልጠናውን በማስፋፋት ረገድ የህክምና ተቋማቱ በየአካባቢያቸው ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር እየሠሩ መሆናቸው ለነገ የዘርፉ መጠናከር ከሚኖረው አስተዋጽኦ ባሻገር ተማሪዎች በ”ሬዚደንስ” የህክምና አገልግሎታቸውን እንዲያግዟቸውም ያስችላቸዋል፡፡ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች  ከታየው ጅምር በተጨማሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአጥንት ህክምና የትምህርት ክፍል የታየው ለውጥ ትልቅ ተስፋ የሚያሰንቅ ነው፡፡

ትምህርት ክፍሉ ባሳለፋቸው ሃያ አምስት ዓመታት የሚያስመርቃቸው በሙያው ስፔሻላይዝ ያደረጉ ተማሪዎች ቁጥር አንዴም ሲወርድ አንዴም ሲወጣ የነበረ ቢሆንም አሁን በሀገሪቱ አሉ ተብለው የሚጠሩትን ሐኪሞች ለማፍራት ተችሏል፡፡ የዚህ ዓመት የተማሪዎች ቁጥር ግን በዚህች ሐገር ታሪክ የተመዘገበ ትልቁ ቁጥር ነው፤ ቀድሞ ሦስትም አራትም ተማሪዎችን ያስመርቅ የነበረው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፤ ዘንድሮ 12 ተማሪዎችን ተቀብሎ በዘርፉ ማሠልጠን ጀምሯል፡፡

ሕክምናውን የተሻለ ለማድረግ መንገድ ከሚያመቻቹ ነገሮች አንደኛው ነገር ብለው ሁሉም ያነጋገርናቸው ሐኪሞች የሚስማሙበት፤ በሀገሪቱ ባሉት ባለሙያዎች መካከል የልምድ ልውውጥ መኖሩን እና ሥልጠናዎች እየተበረታቱ እና እየተስፋፉ መምጣታቸውን ነው፡፡ ይሁንና ባለሙያው ብቻውን የቱንም ያህል ሁኔታውን የተሻለ ለማድረግ ቢሞክር የህዝቡ ግንዛቤ እና በፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ ለአጥንት ሕክምና የሚሰጠው ትኩረት እስካልተጠናከረ ድረስ ችግሩ ማቆሚያ አይኖረውም፡፡

በመሆኑም ባለሙያዎች በቅንነት ተቀራርበው በመሥራት እና የእውቀት ሽግግርን በማመቻቸት እንዲሁም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመሞከር ፈቃደኛ በመሆን፤ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላትም ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ የአጥንት ህክምናን በመላዋ ኢትዮጵያ ማስፋፋት እና ማሻሻል እንደሚችሉ እንተማመናለን፡፡ (ከ“ኢትዮጵያን ሶሳይቲ ኦፍ ኦርቶፔዲክስ ኤንድ ትሩማቶሎጂ” ሕትመት የተወሠደ)

 

 

Read 6453 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 11:28