Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 03 November 2012 12:44

የምርጫው ውጤት መቼ ይታወቃል? በዚያው ምሽት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ተፎካካሪዎች እናሸንፋለን እያሉ ነው
ባራክ ኦባማ በዋሺንግተን የድል መድረክ እያዘጋጁ ነው
ሚት ሮምኒ፣ ሚኒስትሮችን የሚመርጥ ቡድን አዋቅረዋል
የ4 አመቷን ሕፃን ያስለቀሰ የምርጫ ዘመቻ
ባራክ ኦባማና ሚት ሮምኒ ሰለቹኝ ብላ ምርር ብላ ታለቅሳለች - ሥማቸውን በሬድዮ ስትሰማ።
በርካታ ሬዲዮ ጣቢያዎችን የሚያካትተው ኤንፒአር ይቅርታ ጠይቋል - እኛም ሰልችቶናል በማለት።
ስልክ ያልተደወለለት የኦሃዮ ነዋሪ የለም ማለት ይቻላል።

የመራጮቹ ቁጥር ወደ 6 ሚሊዮን ቢሆን ነው። የሚት ሮምኒ የምርጫ ዘመቻ መሪዎች እንደሚሉት፤ ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ መራጮችን በስልክ አነጋግረዋል። የኦባማ የምርጫ ዘመቻ ቡድንም እንዲሁ ብዙዎቹን በስልክ አነጋግሯል። የቴሌቪዢንና የሬድዮ የምርጫ ዘመቻ ዘገባዎችንና እረፍት የሚነሱ የማስታወቂያዎች ውርጅብኝ ያነሰ ይመስል፤ የስልክ ጥሪ ሲጨመርበት ብስጭትጭት ብለው ስልኩን የሚዘጉ ጥቂቶች አይደሉም። አቢጌል ኢቫንስ ገና የ4 አመት ሕፃን ብትሆንም፤ የብዙዎችን ምሬት ትጋራለች።
በቲቪና በሬድዮ፣ ለወራት ያህል የባራክ ኦባማና የሚት ሮምኒ ስሞችን ስትሰማ የከረመችው አቢጌል፤ ሰሞኑን ከምትታገሰው በላይ ሆኖባት ተንገሸገሸች። ግን ምን ታድርግ? የምርጫው እለት ሲቃረብ፣ የማስታወቂያውና የዘገባው ብዛት ጭራሽ ብሶበታል። “በቃኝ” አለች ኢቢጌል። ገና የተፎካካሪዎችን ስም ስትሰማ ምርር ብላ ታለቅሳለች - “ብሮንኮ ባማና ሚት ሮምኒ ሰለቹኝ” እያለች። በርካታ ሬድዮ ጣቢያዎችን ያቀፈው ኤንፒአር ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዘና የሚያደርግ መግለጫ፣ አቢጌልንና ሌሎችንም ይቅርታ እንጠይቃለን ብሏል። ማን ያልሰለቸው አለ? እኛም ሰልችቶናል የሚለው ኤንፒአር፤ ምርጫው ጥቂት ቀን ነው የቀረው፤ ትንሽ ታገሱን ሲል አድማጮቹን ጠይቋል።
መቼስ ማር ሲበዛ ይመራል ይባል የለ! እኛ የሚቀመስ ማር አጥተን በምኞት እናልማለን። በግጭትና በእስር ያበደ የፖለቲካ ምረጫ ተመልሶ እንዳይመጣ እየፈራን፤ ፉክክር በሌለው የፖለቲካ ምርጫ ደግሞ እየተሰላቸን፤ የአሜሪካው አይነት የተሟሟቀና ጨዋ ፉክክር እንመኛለን። እስቲ የተሟሟቀ ሰላማዊ የምርጫ ዘመቻ ሰለቸን ለማለት ያብቃን። ለማንኛውም፤ በርካታ የኦሃዮ፣ የኮሎራዶ፣ የፍሎሪዳ ነዋሪዎች ለወራት የዘለቀው የምርጫ ዘመቻ አማሯቸዋል - እንደ አቢጌል።
ከቴሌቪዥንና ከሬድዮ የምርጫ ዘመቻው በተጨማሪ፤ የስልክ ጥሪም እረፍት አይሰጥም። አንዳንዶቹማ፤ ቢያንስ ቢያንስ የቤታቸውን ስልክ ነቅለውታል - በሞባይል ብቻ ለመጠቀም። ብዙዎቹ ግን፣ ነገሩ ቢሰለቻቸውም፣ በስነስርዓት የስልክ ጥሪውን ተቀብለው ያነረጋግራሉ። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ የሌላው ተፎካካሪ ቡድን ይደውላል። ነገ ከነገወዲያም እንደዚሁ እየደወሉ የጥያቄ ዶፍ ያወርድብዎታል። በመራጭነት ተመዝግበዋል? ከምርጫው እለት በፊት ድምፅ ቢሰጡስ? የት እንደሚመርጡ ያውቃሉ? ድምፅዎን ለማን ለመስጠት አሰቡ? የኦባማ እቅዶችን ሰምተዋል? የሚት ሮምኒን እቅዶች ሰምተዋል? ...
የስልክ ጥሪው ሁልጊዜ ውጤታማ ይሆናል ማለት አይደለም። ለባራክ ኦባማ የምርጫ ዘመቻ የሚያካሂዱ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች በየፊናቸው ይደውላሉ። ግን የስልክ ጥሪ የደረሰው ሰው ሁሉ ለኦባማ ድጋፍ እንዲሰጥ ማግባባት አይቻልም። ከፊሎቹ ሚት ሮምኒን የሚደግፉ ናቸው። ባለቀ ሰዓት ሃሳባቸውን ለማስቀየር መሞከር ከንቱ ድካም ነው። አሁን ዋነኛው ትኩረት በደጋፊዎች ላይ ነው። አንዳንዶቹ ደጋፊዎች፤ ገና ድምፅ ለመስጠት እያመነቱ ሊሆኑ ይችላሉ። ወይም ሌላው ደግሞ በመራጭነት አልተመዘገበ ይሆናል። አልያም፤ በምርጫው እለት ስራ ሊበዛበት ይችላል። እንዲህ የሚያመነታ ሰው ሲገኝ፤ በስልክ ብቻ ቃል ማስገባት በቂ አይደለም። ቤቱ ድረስ ሰው ይላካል።
ሁለቱ ተፎካካሪዎች በየፊናቸው ደጋፊዎቻቸውን ለመቀስቀስና ለመገፋፋት የመጨረሻ ላይ ሩጫ ላይ መሆናቸውን ያውቁታላ። ሶስት ቀናት ብቻ ናቸው የቀሩት። የሮምኒ የምርጫ ዘመቻ ቡድን፤ በአንድ ሳምንት ውስጥ፤ 300ሺ ያህል የኦሃዮ መኖሪያ ቤቶችን አንኳክተናል ይላል። የኦባማ ቡድንም፤ በስልክ ጥሪና በቤት ለቤት ዘመቻ አልሰንፍም። ለዚህም ነው፤ በሳምንት ውስጥ ከኦሃዮ መራጮች መካከል እስካለፈው ሐሙስ እለት 1.3 ሚሊዮን ያህሉ ድምፅ የሰጡት። በርካታ መራጮች እንደሚሉት፤ ከምርጫው እለት በፊት ድምፅ ለመስጠት የወሰኑት፤ ከምርጫ ዘመቻው ለመገላገል ነው።
የምርጫ ውጤቶችን በትክክል መተንበይ
በመላ አገሪቱም ከ22 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እስከ ሃሙስ እለት ድምፅ መስጠታቸውን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ የዲሞክራቲክ ፓርቲው ባራክ ኦባማ በተወሰነ ብልጫ እየመሩ ነው ይላል። በተለይ ደግሞ፤ የምርጫውን ውጤት ይወስናሉ በሚባሉ፤ ኦሃዮ፣ ፍሎሪዳ፣ ዊስኮንሲን፣ ኔቫዳ በመሳሰሉ ግዛቶች የኦባማ ብልጫ ጎላ ያለ መሆኑን ዘገባው ይጠቁማል። ፎክስኒውስ በበኩሉ፤ እስካሁን በተሰጠው ድምፅ በአገራቀፍ ደረጃ ሚት ሮምኒ 52 ለ46 እየመሩ ነው ብሏል። የእነዚህ መረጃዎች ምንጭ ማን ይሆን? ከድምፅ ቆጠራ የተገኘ መረጃ ነው? አይደለም። ታዲያ እንዴት፤ “ኦባማ እየመሩ ነው”፣ “ሮምኒ እየመሩ ነው” ተብሎ ይዘገባል? ድምፅ ሰጥተና ከሚሉ ሰዎች በተሰበሰበ መረጃ በመነሳት ነው።
በሚዲያዎች እየተዘገቡ የሚገኙት ጥናቶች እነዚህ ብቻ አይደሉም። እጅግ ብዙ ናቸው። ገና እንመርጣል ከሚሉ ሰዎች የሚሰበሰቡ መረጃዎች ላይ በመመስረት የሚደረጉ ጥናቶችና በይፋ የሚዘገቡ ውጤችማ ለቁጥር ያስቸግራሉ። ብዙ ቢሆኑም ግን፤ በጥናት የሚያገኙት ውጤቶች ተቀራራቢ ናቸው። በእርግጥ ከፊሎቹ ጥናቶች የባራክ ኦባማን አሸናፊነት ሲያመላክቱ፤ ከፊሎቹ ደግሞ በተቃራኒው ሚት ሮምኒ እንደሚያሸንፉ ይጠቁማሉ።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ይፋ ከተደረጉት የመራጮች አስተያየት ጥናቶች መካከል 36ቱን ወስደን ብናይ፤ አስሩ የሚት ሮምኒን መሪነት ያሳያሉ። ሃያዎቹ ጥናቶች፤ የባራክ ኦባማን መሪነት ይተነብያሉ። በስድስቱ ጥናቶች ደግሞ፤ ሚት ሮምኒና ባራክ ኦባማ በእኩል ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ይጠቅሳሉ። የሁሉም ጥናቶች አማካይ ሲሰላ፤ የተፎካካሪዎቹ ውጤት እኩል ነው - 47 ለ47።
ታዋቂው የፖለቲካ ምርጫ መሃንዲስ ካርል ሮቭ በበኩላቸው፤ ባለፉት ሰባት ቀናት የተደረጉ 31 ጥናቶችን ይጠቅሳሉ። ከ31 ጥናቶች መካከል፤ ሚት ሮምኒ በ19ኙ ይመራሉ፤ ኦባማ በ7ቱ ይመራሉ። በ5 ጥናቶች ደግሞ የሁለቱ ተፎካካሪዎች ውጤት እኩል ነው። የሁሉም ጥናቶች አማካይ ውጤት ሲሰላ፤ ሮምኒ 48 ለ47 ይመራሉ።
የሆነስ ሆነና፤ ጥናቶቹ የምርጫውን ውጤት በትክክል መተንበይ ይችላሉ። አዎ፤ የጥናቶቹ አማካይ ውጤት፤ የምርጫውን ውጤት ለመተንበይ ያስችላል። ባለፉት ሃምሳ አመታት በአሜሪካ የተካሄዱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች ላይ በተግባር ታይቷል። (በነገራችን ላይ፣ በአገራችን እንዲህ አይነቶቹ ጥናቶች ስለማይካሄዱ ነው፤ በምርጫ 97 ኢህአዴግ አዲስ አበባ ውስጥ በዝረራ ሲሸነፍ ዱብዳ የሆነበት።)
የዘንድሮው የባራክ ኦባማና የሚት ሮምኒ ምርጫ ግን በጣም ተቀራራቢ ስለሆነ አስቸጋሪ ሆናል። የጥናቶቹ ትንበያ አስተማማኝ የሚሆነው፤ ተፎካካሪዎቹ ቢያንስ በ3 ነጥብ ሲበላለጡ ነው። ኦባማና ሮምኒ ግን በእኩል ነጥብ ወይም በአንድ ነጥብ ልዩነት ትንቅንቅ ውስጥ በመግባታቸው፤ ከወዲሁ የአሸናፊውን ማንነት ለመለየት አስቸጋሪ ሆናል። እንዲያም ሆኖ፤ ሁለቱ ተፎካካሪ ቡድኖች የተለያዩ ጥናት ውጤቶችን እየጠቀሱ፤ የየራሳቸውን ድል በልበሙልነት መናገራቸውና መተንበያቸው አልቀረም። የዛሬ አራት አመትኮ፤ ኦባማ ተፎካካሪያቸውን በ10 ነጥብ ይመሩ ነበር። በመጨረሻም በምርጫው እለት፤ በ7 ነጥብ ልዩነት በአሸናፊነት ፕሬዚዳንት ለመሆን በቁ። ምን ዋጋ አለው? በትዝታ ብቻ ማሸነፍ አይቻልም።
የምርጫው ውጤት በማን እና መቼ ይታወቃል?
በእርግጥ የምርጫው ውጤት በይፋ የሚታወቀውና የሚገለፀው፤ ቀስ በቀስ በበርካታ ሳምንታት በበርካታ የመንግስት አካላት ነው - ከምርጫ ጣቢያና ከወረዳ አንስቶ እስከ ግዛትና አገር አቀፍ ደረጃ። አሜሪካዊያን ግን የምርጫውን ውጤት ለማወቅ ሳምንታትን ቀርቶ ቀናትን አይታገሱም። መንግስት እስኪናገር አትጠብቅም። ነፃ የሚዲያ ተቋማት አሉላቸው - ሳይውሉ ሳያድሩ ዜናውን የሚናገሩ። በእርግጥ የአሜሪካ ሚዲያዎች፣ በተወሰነ ደረጃ ከፊሎቹ ወደ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ከፊሎቹ ወደ ሪፐብሊካን ፓርቲ ሊያዘነብሉ ይችላሉ። ነገር ግን፣ ወደ አንዱ አዘነብላለሁ ብሎ የተዛባ ዘገባ እያቀረበ ተአማኒነትን ለማጣት የሚፈልግ ነፃ ሚዲያ የለም። እናም በተለይ በምርጫ ውጤት ላይ የተሳሳተ መረጃ ላለመስጠት ይጠነቀቃሉ። ተጠንቅቀውም የምርጫውን ውጤት በዚያው እለት ምሽት ለማብሰር ይሽቀዳደማሉ። እንዴት?
በተፎካካሪዎቹ መካከል ሰፊ የድጋፍ ልዩነት በሚኖርበት ወቅት፣ ያን ያህልም አያስቸግርም። ቀኑን ሙሉ በምርጫ ጣቢያዎች ደጃፍ ላይ ቆመው መረጃ የሚሰበስቡ ሰራተኞች ነገሩን ይጨርሱታል። መራጮች ለማን ድምፅ እንደሰጡ ፎርም እንዲሞሉ ይደረጋል፤ ኤግዚት ፖል ይሉታል። ። እናም አዝማሚያውን በማየት የአሸናፊውን ማንነት መለየት ይቻላል - ምርጫው ሳይጠናቀቅ። ፉክክሩ ተቀራራቢ ከሆነ ደግሞ፣ ከተለያዩ የምርጫ ወረዳዎች ለናሙና ያህል የድምፅ ቆጠራዎችን በማሰባሰብ ውጤቱን ማስላት ይቻላል። ፉክክሩ አንገት ለአንገት ሲሆን ግን የድምፅ ቆጠራ መረጃዎችን ከአሶሼትድ ፕሬስ ማግኘት ያስፈልጋል። አ
ሶሼትድ ፕሬስ፣ በምርጫው ውጤት ዙሪያ ዋነኛ የመረጃ ምንጭ ለመሆን የቻለው አለምክንያት አይደለም። የድምፅ ቆጠራ ውጤቶችን ለማሰባሰብ በመላ አገሪቱ ከ5000 በላይ ሰራተኞችን ስለሚያሰማራ ነው። ፉክክሩ እጅግ ተቀራራቢ ከሆነ ግን፤ እያንዳንዱ የምርጫ ድምፅ በፖስታ የሚመጣውና የዘገየውም ጨምር ተጣርቶና ተቆጥሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ፤ ሳምንት ይፈጃል። የዛሬ 12 አመት እንደተከሰተው አይነት የጭቅጭቅና የክስ መነሻም ሊሆን ይችላል። ለማንኛውም ተፎካካሪዎቹ ወገኖች፤ በየፊናቸው በሺ የሚቆጠሩ ጠበቆችንና የሕግ አማካሪዎችን በተጠንቀቅ አሰልፈዋል። ጭቅጭቅና ንትርክ ቢፈጠር፤ መፍትሄ የሚገኘው በድንጋይ ወይም በጥይት አይደለማ - የአሜሪካ ፖለቲካ ነዋ።

Read 4524 times