Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 03 November 2012 12:44

ቸሻየር ሰርቪስስ ኢትዮጵያ ዛሬ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉን ያከብራል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ባለፉት 50 ዓመታት ከ25ሺህ በላይ የእንቅስቃሴ ችግር የነበረባቸውን ሕፃናት መራመድና መሄድ፣ መማርና መሥራት እንዲችሉ ማድረጉን የገለፀው ቸሻየር ሰርቪስስ ኢትዮጵያ፤ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉን ዛሬ እንደሚያከብር አስታወቀ፡፡
በመናገሻ ከተማ የሚገኘው ድርጅቱ የመሠረት-ማኅበረሰብ ተሃድሶ አገልግሎት በመጀመር ከ1500 በላይ የአካል፣ የአዕምሮና የስሜት ሕዋሳት የዕድገት ጉድለት እንዲሁም ተደራራቢ ጉዳት ለደረሰባቸው ሕፃናት የቤት ለቤት ተሃድሶ በመስጠት የዕለት ተዕለት የሕይወት ክህሎቻቸውን እንዲያዳብሩ ከማስቻሉም በላይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የአካል ጉዳተኛ ሕፃናት እናቶች ነፃ የተሃድሶ አገልግሎት በመስጠት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮቻቸው ለመቅረፍ ልዩ ድጋፎች ማድረጉን አስረድቷል፡፡

ከአራት ዓመት ወዲህ በአገር ውስጥ ካሉ ደጋፊዎች፣ ለጋሽ ድርጅቶችና በጀርመን ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በጐ አድራጊ ግለሰቦች በሚያገኘው ዕርዳታ በመናገሻ፣ በሀዋሳ፣ በሐረር፣ በድሬዳዋ በአዲስ አበባ በከፈታቸው ማዕከላት በድህረ-ልምሻ፣ የእግር መቆልመም፣ የእጅና የእግር መቆረጥና ሌሎች ችግሮችንም በቀዶ-ሕክምናና በፊዚዮ ቴራፒ እያስተካከለ መሆኑን ገልጿል፡፡ 
የፊት ገጽታን በሚያበላሸው ኖማ በሽታ የከንፈር መሰንጠቅ ለደረሰባቸው ወገኖች ከውጭ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሚያስተካክል ሲሆን በአቅም ማነስ ምክንያት ት/ቤት መግባት ላልቻሉ አካል ጉዳተኞች የቀለምና የሙያ ሥልጠና በመስጠት፣ አካል ጉዳተኛ ወጣቶች በራስ አገዝ ማኅበራት ተደራጅተው በገቢ ማስገኛ ሥራዎች እንዲሳተፉ ድጋፍ አድርጓል፡፡
ባለፉት አስር ዓመታት 39 ጊዜ የእግር ጉዞ በማዘጋጀት ከእግር ከጉዞው 4.2 ሚሊዮን ሲያስገኝ፤ ከሀገር ውስጥ በጐ አድራጊዎች ከ12ሚ ብር በላይ፣ ከውጭ አገር ለጋሽ ድርጅቶች ከ64ሚ. ብር በላይ በአጠቃላይ ከ80ሚ. ብር በላይ መሰብሰቡን ጠቅሶ፣ በቀጣይም ለነደፋቸው የአምስት ዓመት መርሐ ግብር ማስፈፀሚያ ከ80 ሚ. ብር በላይ ለማሰባሰብ፣ አሁን ያሉትን ጨምሮ ከ45ሺህ ብር በላይ የአካል ጉዳተኞች አገልግሎት ለመስጠት ማቀዱን አብራርቷል፡፡
ሠው ሠራሽ አካል ልዩ ልዩ የአካል እንቅስቃሴ መርጃ መሳሪያዎችን እያመረተ ለአካል ጉዳተኞች የሚያቀርበው የተሃድሶ ድርጅት፤ በአምስት ዓመት ዕቅዱ ለአገሪቷ መልክአምድር ተስማሚ የሆኑ ከ2 ሺህ 900 በላይ ተሽከርካሪ ወንበሮችና (ዊልቼሮች) የተሻሻለ ሰው ሠራሽ አካልና የአካል ድጋፎች በማምረት የተገልጋዮችን ሕይወት ምቹ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ዓመታዊው የገቢ ማሰባሰቢያ የእግር ጉዞ ኅዳር 1 ቀን 2005 ዓ.ም ከጧቱ 2፡30 ጀምሮ በመናገሻ እንደሚደረግ የጠቀሰው ድርጅቱ፤ እያንዳንዱ ተጓዥ ቢያንስ ከ20-60 ሰዎችን ወክሎ 21ኪ.ሜ (ግማሽ ማራቶን) መሄድ ለማይችሉ አካል ጉዳተኞች ተጉዞ እነሱም በተራቸው መጓዝ እንዲችሉ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጋብዟል፡፡
ቸሻየር ሰርቪስስ ኢትዮጵያ፤ ልዕልት ሰብለና ኮማንደር እስክንድር ደስታ ከእንግሊዛዊው በጐ አድራጐት ካፒቴን ሊዮናርድ ቸሻየር ባገኙት ድጋፍ በ1954 ዓ.ም ያቋቋሙት ድርጅት ነው፡፡

Read 4226 times