Print this page
Saturday, 03 November 2012 13:04

በድሬዳዋ ከፍተኛ ሹምሽር ይጠበቃል

Written by  መታሠቢያ ካሣዬ /ከድሬዳዋ/
Rate this item
(2 votes)

ባለስልጣናቱ ለአስቸኳይ ስብሰባ አዲስ አበባ ናቸው
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባለስልጣናትና በመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ከፍተኛ ሹምሽር ይጠበቃል፡፡
በከተማዋ የሚገኙ የተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናትና የሥራ ኃላፊዎች ለአስቸኳይ ስብሰባ አዲስ አበባ ተጠርተዋል፡፡
በከተማዋ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀውን ሹምሽር አስመልክቶ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ለአዲስ አድማስ እንደጠቆሙት፤ ሰሞኑን በከተማዋ የተለያዩ የሥራ ዘርፎች ግምገማዎች ሲካሄዱ ሰንብተዋል፡፡ ይህንኑ ተከትሎም ባለስልጣናቱ ለአስቸኳይ ስብሰባ ወደ አዲስ አበባ በመጠራታቸው ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

እንደ ውስጥ አዋቂዎች ጥቆማ፤ ከባለስልጣናቱ መካከል የድሬዳዋ ከተማ ት/ቢሮ፣ የብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ፣ የመሬት ልማት አስተዳደር ባለስልጣንና የውሃና ፍሣሽ ባለስልጣን መ/ቤቶች ሹምሽር ይካሄድባቸዋል ተብሎ ከሚጠበቁ የመንግስት ቢሮዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ስለ ጉዳዩ መረጃ እንዲሰጡን በስልክ የጠየቅናቸው የድሬዳዋ ኢህአዴግ ኮሚቴ ፅ/ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማንደፍሮ፤ ለአስቸኳይ ስብሰባ ከከተማዋ የሥራ ኃላፊዎች ጋር አዲስ አበባ እንደሚገኙና በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት መግለጫ መስጠት እንደማይችሉ ገልፀውልናል፡፡ ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላ መረጃዎችን ይፋ እንደሚያደርጉም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ 
የፌደራል መንግስት የምዕተዓመቱን የልማት ግብ ለማሳካት ያስችሉኛል በማለት፤ የኢንዱስትሪ ማዕከል እንዲሆኑ ከመረጣቸው ከተሞች መካከል አንዷ ድሬዳዋ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ይህንኑ ተከትሎም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከፍተኛ የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት ከተማዋን እየጐበኙ ነው፡፡ ከአንድ አመት ከስድስት ወር በፊት የቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር አቶ መለስ ዜናዊ በቻይና ከአገሪቱ ባለሃብቶች ጋር ውይይት በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የኢንዱስትሪ ዞን እንዲገነቡ ባደረጉት ማግባባት በርካታ የቻይና ባለሃብቶች ወደ ከተማዋ መጥተው የኢንዱስትሪ ዞን ገንብተዋል፡፡
ይህም ድሬዳዋን ከአዲስ አበባ ክልል ወጪ የኢንዱስትሪ መንደር ግንባታ የተካሄደባት የመጀመሪያዋ ከተማ እንድትሆን አስችሏታል፡፡

 

Read 3290 times Last modified on Saturday, 03 November 2012 13:11