Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 03 November 2012 13:20

የኢትዮጵያ ፓትርያርክ አሿሿም ተጨማሪ ሕግ ሊወጣለት ነው

Written by 
Rate this item
(11 votes)

ስድስተኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ይመርጣል ተብሎ የተጠበቀው የቤተክርስትያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ የጥቅምት ምልአተ ጉባኤ ምርጫውን ሳያከናውን የተጠናቀቀ ሲሆን ቀጣዩ ፓትርያርክ ከመመረጣቸው በፊት ባለው ሕግ ላይ ተጨማሪ ሕግ ያስፈልጋል በመባሉ ይህንኑ የሚያዘጋጅ የሊቃነ ጳጳሳት ቡድን ተቋቁሟል፡፡ ቡድኑ ሕጉን አርቅቆ ለሕዳር 30 ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁእ አቡነ ናትናኤል በሚመሩት ቡድን ውስጥ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣ ብፁእ አቡነ ሳሙኤል፣ ብፁእ አቡነ አብርሃም፣ ብፁእ አቡነ ሉቃስ፣ ብፁእ አቡነ አብርሃም፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ብፁእ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ብፁእ አቡነ ዳንኤል እና ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የሚገኙበት ሲሆን ቡድኑ ከአቃቤ መንበሩ ጋር እንደ ቋሚ ሲኖዶስ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡

 


አራተኛው የቤተክርስትያኒቱ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በስደት ከሚኖሩበት አሜሪካ ወደ መንበሩ ይመለሳሉ የሚል ሀሳብ ቢቀርብም የሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ ሳያፀድቀው ቀርቷል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስን የጥቅምት ምልዓተ ጉባኤ መጠናቀቅ አስመልክቶ በወጣው ባለ አስራ ሰባት ነጥብ መግለጫ፣ አቡነ መርቆሬዎስ በውጭ ሀገር ካለው “ስደተኛ ሲኖዶስ” ጋር የሰላም ንግግሩ እንደሚቀጥል አረጋግጧል፡፡
ይኸው ውሳኔ ተነቦ እንዳበቃ አንድ ሊቀጳጳስ ጋዜጠኞች ሳይሄዱ መናገር እንፈልጋለን ቢሉም ባለመፈቀዱ፣ በምትኩ የደቡብ ወሎ ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ ብፁእ አቡነ ቄርሎስ “ቅዱስ ሲኖዶስ ፀረ ሙስና እንቅስቃሴን አስመልክቶ ያደረገው ወሳኝ ጉባኤ በቂ ሽፋን አልተሰጠውም” ብለዋል፡፡ ጋዜጠኞችም የሲኖዶሱ ምልዓቱ ጉባኤ ባለበት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲሰጡ ቢጠይቁም ቀሪ ስብሰባ አለ በመባሉ ሳይሰጥ ቀርቷል፡፡ በምትኩ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ እና የከፋሸካ እና ቤንጂ ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁእ አቡነ ሕዝቅኤል፤ በሌላ ክፍል መግለጫ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡
አቡነ ሕዝቅኤል በመግለጫቸው፤ አሜሪካ ካለው ስደተኛ ሲኖዶስ ጋር ድርድሩ መቀጠሉን አውስተው፤ አቡነ መርቆሬዎስ ቤተክህነት ግቢ የሚገኘውን የጳጳሳት መኖሪያ ጨምሮ በመረጡት ስፍራ ሙሉ እንክብካቤ እየተደረገላቸው መኖር እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡ የአዲስ ፓትርያርክ ሹመትን አስመልክቶ ከአዲስ አድማስ ጋር ልዩ ቃለምልልስ ያደረጉት አቡነ ሕዝቅኤል፤ የመርቆሬዎስን ወደ ፓትርያርክነት መመለስ በተመለከተ ሲናገሩ፤ “አምስተኛ ፓትርያርክ ካልን በኋላ አራተኛ አንልም፤ ስለዚህ ሕጉ ተረቆ ከፀደቀ በኋላ ስድስተኛ ፓትርያርክ ይመረጣል” ብለዋል፡፡
ከሲኖዶሱ ፅሕፈት ቤትም ሆነ ከመንበረ ፓትርያርክ ባይረጋገጥም የሲዳማ፣ ቡርጂና ጌዲኦ ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣ የልማትና ክርስትያናዊ ኮሚሽን የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ የቅድስት ሃገር ኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በፓትርያርክነት የመመረጥ ሰፊ ዕድል እንዳላቸው ተነግሯል፡፡ በስም መጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ሊቀጳጳስ፤ በሲኖዶሱ አባላት መካከል ጵጵስና የሌለው መነኩሴ ሊመረጥ እየታሰበ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል ለአስተዳደር አመቺ ባለመሆኑ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአራት እንዲከፈል ሲኖዶሱ ወስኗል፡፡
በተያያዘ ዜና የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ሸኖዳ ሳልሳዊ አምና ከሞቱ ወዲህ 118ኛ ፓትርያርኳን ለመምረጥ ከቀረቡት እጩዎች መካከል፣ ሦስቱ የመጨረሻ እጩዎች የታወቁ ሲሆኑ ከሦስቱ ማን ፓትርያርክ እንደሚሆን ለመለየት ነገ በካይሮው ቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል በሚደረግ የእጣ ማውጣት ሥነሥርአት ተተኪውን ፓትርያርክ እንደሚለይ ታውቋል፡፡
ፓትርያርክ ለመምረጥ ድምፅ ከሰጡ 2400 ሰዎች መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ተወካዮችም እንዳሉበት ተጠባባቂ ፓትርያርክ ፓጆሚዮስ ተናግረዋል፡፡ ለመጨረሻው ዙር ካለፉት እጩዎች ሁለቱ ጳጳሳት ሲሆኑ አንዱ መነኩሴ እንደሆኑ ታውቋል፡፡ በነገው እጣ ከእስክንድርያው መነኩሴ የ70 ዓመቱ አባ ሩፋኤል አቫ ሚና፣ ከ54 ዓመቱ ጳጳስ አቡነ ሩፋኤል እና ከ60 ዓመቱ ጳጳስ አቡነ ቴዎድሮስ መካከል ፓትርያርኩ ተመርጦ እሁድ ሕዳር 9 ቀን 2005 ዓ.ም በዓለ ሲመቱ ይከበራል፡፡
ምርጫውን ለመታዘብ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ልኡካን የሆኑ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ስፍራው አቅንተዋል፡፡ ከልዑካን ቡድኑ አባላት መካከል አቡነ ገብርኤል፣ አቡነ ማትያስ፣ አቡነ አረጋዊ፣ አቡነ እንጦንስ እና አቡነ ኢሳይያስ ይገኙበታል፡፡



Read 10251 times