Saturday, 03 November 2012 15:07

ቫይረስ አመጣሹ ጉንፋን

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(4 votes)

ጉንፋን ራይኖ ቫይረስ በተባለ ቫይረስ መነሻነት የሚከሰትና በአየር ማስተላለፊያ አካላቶቻችን ላይ ጥቃት በማድረስ ለህመም የሚዳርግ በሽታ ነው፡፡ የአየር ማስተላለፊያ አካላቶቻችን በቫይረሱ ጥቃት በሚደርስባቸው ጊዜ እንደልብ አየር ማስወጣትና ማስገባት ይሳናቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከዋና ዋና የመተንፈሻ አካለቶቻችን በተጨማሪ እንደጆሮ፣ አይንና የብሮንካይ አካባቢዎችም በቫይረሱ ሊጠቁና የህመም ስሜት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ የጉንፋን አምጪ ቫይረሱ በአብዛኛው የሚያጠቃው የላይኛውን የመተንፈሻ አካላቶቻችንን ነው፡፡ ስለዚህም የህመም ስሜቱም ከታችኛው ይልቅ በላይኛው አካላታችን ላይ በርትቶ ይታያል፡፡ 

የጉንፋን በሽታ አምጪ ቫይረስ ወደ ሰውነታችን ውስጥ ከገባ በኋላ በአፍንጫችን ውስጥ ባሉ የአየር መተላለፊያ ንጣፎች ላይ ያርፋል፡፡ 
እዚያው ሆኖ መባዛት ይጀምርና ሴሎችን መበከልና ማጥቃቱን ይያያዛል፡፡ ሴሎቹ ሲሞቱ ቫይረሱ በይበልጥ ራሱን እያበዛ ወደ ውስጠኛው የመተንፈሻ አካላችን መዛመቱን ይቀጥላል፡፡ በጉንፋን ከተያዘ ሰው የምትገኝ በጣም ጥቂቷ ቫይረስ ራሷን ለማባዛትና ሌላውን ሰው በጉንፋን በሽታ ለማስያዝ በቂ ነች፡፡ ቫይረሱ በህይወት ለመቆየትና ተባዝቶ በሽታውን ለማስተላለፍ የሚችለው ህይወት ባላቸው ሴሎች ውስጥ መቆየት ሲችል ብቻ ነው፡፡ ቀዝቃዛና ነፋሻማ አየር ለጉንፋን ቫይረስ ተስማሚ ነው፡፡ በጉንፋን የተያዘ ሰው በሚስልበት ወይም በሚያስነጥስበት ወቅት በሚወጡ ቫይረሶች አማካኝነትና በቫይረሱ በተበከለ እጃችን አፍንጫችንን ስንነካ ቫይረሱ ሊተላለፍብን ይችላል፡፡
የጉንፋን በሽታ አምጪ ቫይረሱ (ራይኖ ቫይረስ) ከ150 በላይ ዓይነቶች አሉት፡፡
ከእነዚህ ዓይነቶች ውስጥ የመተንፈሻ አካላት ላይ ጥቃት በማድረስ የጉንፋን በሽታ እንዲከሰት ዋንኛውን ሚና የሚጫወተው አር ኤን ኤ የተባለው ቫይረስ ነው፡፡
የጉንፋን ቫይረሱ ብዙውን ጊዜ ራሱን በቀላሉ የሚያባዛ ከመሆኑም በላይ በመተንፈሻ አካላቶች ውስጥ ያሉትን ሴሎች በመጉዳት በቀላሉ የጉንፋን በሽታ እንዲከሰት ያደርጋል፡፡ የጉንፋን በሽታ አምጪ ቫይረሶች ስትሬይኖች በሰውነታችን ውስጥ ለመራባት ምቹ ሁኔታን በሚያገኙበት ወቅት ይራባሉ፡፡ እንደበሽታ አምጪ ቫይረስነታቸው የጉንፋን በሽታ አምጪ ቫይረሶች የተለያዩ ዓይነት ስትሬይኖች አላቸው፡፡
አንድ ሰው በአንድ ዓይነት የቫይረስ ስትሬይን የሚያጠቃው ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ሰውየው በቫይረሱ ስትሬይን በሚጠቃበት ጊዜ ሰውነቱ ቫይረሱን የሚከላከል (Anti Body) ማምረት ይጀምራል፡፡
ይህ የመከላከል ኃይሉ የቫይረሱን የጥቃት ሁኔታ ከተከላከለም በኋላ በዚያው በሰውነታችን ውስጥ ይቀመጣል፡፡ ስለዚህም የቫይረሱ ስትሬይን በድጋሚ ጉንፋን የማስያዝ አቅም አይኖረውም፡፡ እናም ሰውየው ቀደም ብሎ ተይዞበት ከነበረው የቫይረስ ስትሬይን ጋር ተመሳሳይ በሆኑ ቫይረሶች የመጠቃት እድል አይኖረውም፡፡ የጉንፋን አምጪ ቫይረሶቹ ዓይነት በርካታ በመሆኑ በሌላ የቫይረስ ስትሬይን የመጠቃትና ጉንፋን የመያዝ ዕድሉ አያቆምም፡፡ የሰዎች በሽታን የመከላከል አቅማቸው (Immune system) የተለያየ ነው፡፡ በአንድ በሽታ ቶሎ የመያዝና ያለመያዝ አቅም፣ በቶሎ የመዳንና ያለመዳን ጉዳይ፣ በሽታውን ወደ ሰዎች የማስተላለፍና ያለማስተላለፍ ችሎታ እንደየሰዎቹ ሁኔታ ይለያያል፡፡ በአንድ የጉንፋን አምጩ ቫይረስ ስትሬይን ቀደም ሲል ተጠቅቶ የዳነ ሰው፣ በሚቀጥለው ጊዜ በተመሳሳይ የቫይረስ ስትሬይን ተጠቅቶ ጉንፋን ከያዘው ሰው ጋር የትኛውንም አይነት ንኪኪ ቢያደርግ በበሽታው የመያዝ ዕድል የለውም፡፡ ምክንያቱም ሰውየው ቀደም ሲል በሽታው በያዘው ወቅት በሰውነቱ ውስጥ የተመረተና ቫይረሱን ለመከላከል የሚችል Anti Body በውስጡ ስለሚኖር ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች እኔ የሰው ጉንፋን አይዘኝም ለሚሉበት ዋንኛ ምክንያቱም ይኸው ነው፡፡
እነዚህ ሰዎች እነሱ ተይዘውበት ከነበረው የቫይረስ ስትሬይን የተለየ ቫይረስ ካለባቸው ሰዎች ጋር ንኪኪ ቢያደርጉ በጉንፋን የመያዛቸው እድል አይቀሬ ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች በጉንፋን በሽታ ለመያዛቸው ምንም ምልክት ሳያሳዩ በጉንፋን በሽታ ታመው ሊድኑ ይችላሉ፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ከሰዎቹ በሽታን የመከላከል አቅም ጋር በተያያዘ ነው፡፡
አንድ ሰው በጉንፋን ቫይረስ ከተጠቃ ከአስር እስከ አስራ ሁለት ሰዓታት ባለው ጊዜ ውስጥ ምልክቶችን ማሳየት ይጀምራል፡፡ በቫይረሱ የተጠቃ ሰው ከሚያሳያቸው የህመም ምልክቶች ውስጥ በተደጋጋሚ ማስነጠስ፣ ከአፍንጫ ቀጠን ያለ ፈሳሽ መውጣት፣ የራስ ምታት፣ በአይን አካባቢ የህመም ስሜት መፈጠር፣ የዓይን እንባ ማዘል፣ የሰውነት ሙቀት መጨመር፣ ብርድ ብርድ የማለትና የማንቀጥቀጥ ስሜቶች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የጉንፋን በሽታ አብዛኛውን ጊዜ ለአንድ ሣምንት ያህል ይቆያል፡፡ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ በሽታው እስከ አንድ ወር ድረስ ሊቆይ ይችላል፡፡ እንደየሰው የመከላከል አቅም የሚለያይ ቢሆንም የጉንፋን በሽታ በወጣቶች ላይ በአማካይ በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ ድረስ ሊከሰት የሚችል ሲሆን በህፃናት ላይ በሽታው በወር አንድ ጊዜ ወይንም በዓመት እስከ አስራ ሁለት ጊዜ ድረስ ሊከሰት እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እድሜያችን እየጨመረ በሄደ መጠን በጉንፋን የመያዝ ዕድላችን እየቀነሰ እንደሚሄድ የሚጠቁሙት መረጃዎች፤ ለዚህ በምክንያትነት የሚያቀርቡት በልጅነት ዕድሜያችን ወቅት በተለያዩ የቫይረስ ስትሬይኖች በተጠቃን ቁጥር ሰውነታችን ቫይረሶቹን የሚከላከል AntiBody በማምረት ሲያከማች በመቆየቱና፣ ይህም በቀላሉ በበሽታው እንዳንጠቃ ማድረጉን ነው፡፡ ስለዚህም ጉንፋን እርጅናን ድጋፍ አድርገው እንደሚከሰቱ ሌሎች በሽታዎች አለመሆኑንም እነዚሁ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በጉንፋን በሽታ የመተላለፊያ መንገዶች ላይ ብዙዎቻችን ያለን ግንዛቤ የተሳሳተ ነው፡፡ አንድ በጉንፋን የተያዘን ሰው ለመሳም እና አጠገቡ ተጠግተን ለመነጋገር በእጅጉ ስንፈራና በሽታው በዚህ ሊተላለፍብን እንደምንችል ስንናገር እንስተዋላለን፡፡
ይሁን እንጂ የበሽታው ዋነኛ መተላለፊያ መንገድ ይኼ አይደለም፡፡ በእርግጥ የጉንፋን በሽታ ከያዘው ሰው ጋር መሳሳምና ቅርበት ላይ ሆኖ ትንፋሽ ለትንፋሽ መለዋወጥ የበሽታው መተላለፊያ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡
ነገር ግን ዋነኛው የጉንፋን በሽታ መተላለፊያ መንገድ እጅ ለእጅ መጨባበጡ ነው፡፡ እንደ ባለሙያዎች ገለፃ ንኪኪ የጉንፋን በሽታ ዋነኛ መተላለፊያ መንገድ ነው፡፡
በጉንፋን በሽታ የተያዘ ሰው በእጁ የአፍንጫውንና አፉን አካባቢዎች ሲነካካ ቆይቶ ቫይረሶቹን በተሸከመ እጁ የሚጨብጠን ከሆነና እኛም በተመሳሳይ መንገድ የአፍንጫ፣ አይንና አፋችን አካባቢዎችን የምንነካካ ከሆነ በሽታው በቀላሉ ሊተላለፍብን ይችላል፡፡ ጉንፋን የተለየ ህክምና የሚደረግለት በሽታ ባይሆንም ከሚያጨናንቁ ሥራዎች ተቆጥቦ እረፍት ማድረግ፣ ፈሳሽ በብዛት መውሰድ፣ የግል ንጽህናን በተለይም በመተንፈሻ አካላት አካባቢ የሚገኙትን በንጽህና መያዝ፣ የሎሚ ጭማቂ ያለበትና ሞቅ ያለ ውሃን በመጠቀም የአፍ ውስጣዊ አካላትን ማጽዳት በሽታው በቶሎ እንዲድን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡
ወደ ህክምና ተቋም በመሄድም የሃኪም ምክርና እርዳታ ማግኘቱ በሽታው የሚያስከትለውን ህመም ሊቀንስና ከበሽታው ፈውስ ሊያስገኝ ይችላል፡፡

Read 7880 times