Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Monday, 05 November 2012 07:53

የምትሠራበት መጋዝ ደነዝ ከሆነ አንተም ደነዝ ነህ!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ብዙ ዕውነት ሲቆይ ተረት ይሆናል!
ከዕለታት በአንደኛው የዱሮ ዘመን፤ የአንድ የፖለቲካ ድርጅት አባላት፤ ድርጅታቸውን ይተዉና ወደ መንግሥት ይገባሉ፡፡ በመንግሥት ሥር አንድ አለቃ ተመድቦላቸው እየነቁ፣ እየበቁ፣ እየተደራጁ ኑሮ ይጀምራሉ፡፡
በመካከል አንደኛው ወደ ኪውባ ለከፍተኛ የንቃት ትምህርት ይላካል፡፡ ተምሮ ሲመለስ አንድ አዲስ ክስተት ያጋጥመዋል! የቡድናቸው ኃላፊ ታስሮ ይጠብቀዋል! በጣም ይደነግጥና ለቡድኑ አባላት፤
“ያ ሰብሳቢያችን (በዛሬው ቋንቋ ጠርናፊያችን) የት ሄደ?” ሲል ይጠይቃል፡፡
“ውይ ታሰረኮ!” ይላል አንደኛ የቡድን አባል፡፡

ከኪዩባ የመጣው ጓድ ምን መመለስ ወይም ማለት እንዳለበት ግራ ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም፤ “ደግ አረጉለት!” እንዳይል ገና የራሱ ዕጣ ፈንታ አልታወቀም፡፡ “ለምን? እንዴት?” እንዳይል መንግስትን መጋፋት ሊሆንበት ሆነ፡፡ 
ስለዚህ፤
“አቤት የአብዮታችን ፍጥነት?!” አለ፡፡
ዋሉ አደረና ሁሉም የቡድኑ አባላት ተያይዘው ወህኒ ወረዱ፡፡
ወህኒ ቤት ከለመዱ ከሰነበቱ በኋላ አንድ ላይ ሰብሰብ ብለው እንደመቅሩስ ሲወያዩ፤ አንደኛው አባል ያንን ከኪውባ የመጣ ጓደኛውን፤
“አሁንስ? የአብዮታችን ፍጥነት ምን ይመስላል?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ኪውቤውም፤
“ኧረ ተወኝ! አሁንማ አንደኛውን ጀት ሆኖልሃል! ሁላችንንም ይዞን በሯል!!” ሲል መለሰ፡፡
***
ያመኑትን ክዶ ማተብ መበጠስ መጥፎ ነው፡፡ የማያምኑበት ቦታ ገብቶ መቧቸርም ክፉ አባዜ ነው፤ “የቤት ጣጣ አለብኝ” እንደሚሉት ሰዎች መሆንን ያስከትላል፡፡ ምንም ያፈሩት ነገር ሳይኖር “ቤት ያፈራውን ትበላለህ” እንደሚሉት የታይታ ሰዎች መሆንም አባዜው ለብዙ ይተርፋል፡፡ “ሳይገሉ ጐፈሬ ሳያረግጡ ወሬም” ዕውነቱ የተጋለጠ ለታ ያጋልጣልና ውርደቱ አይቀሬ ነው፡፡
ይህንን ዕውነታ በአገር ጉዳይ መንዝሮ ማየት፤ ወመቴን ከአለሌ፣ ጨውን ካሞሌ፣ ቱሪስትን ከፒስኮር፣ ናዚን ከናዜራ… ለይቶ ለማየት ይጠቅማል፡፡
“ያለንበት ዘመን ሐሰተሃ ወዳጅና፣ ዕውነተኛ ጠላት ያለበት ሊሆን ይችላልና ተጠንቀቅ” ይላል አንድ ፈላስፋ፡፡ የአፍጋኒስታን ሰዎች፤
“ሰው ሶስት ነገሮችን መፍራት አለበት” ይላሉ፡፡
“ምን ምን?” ሲባሉ
“የኮብራ መርዝ
የነብር ጥርስና
የአፍጋን በቀል!”
ብለው ይመልሳሉ፡፡
ከበቀለኝነት ይሰውረን!!
አበው ከዘፈኖች ሁሉ ድንቅ፤
“ያልነበርኩበትን አሳየኝ
ያላየሁት ሠፈር ውሰደኝ…”
የሚለው ነው ይላሉ አሉ፡፡ ያልነበርንበት ደረጃ ለመድረስ አርቆ ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ ያላየነው ሰፈር ለመድረስ አዳዲስ መንገድ መቅደድ፣ አዳዲስ ህልም ማየት፣ አዳዲስ ዕቅድ ማቀድ ይኖርብናል፡፡ ነባሩን ወሬ ይዘን እንዳንደንዝ እንጠንቀቅ! በአሮጌ ህልም ተቀይደን አዲስ ራዕይ አለን ማለት ቅዠት ይሆንብናልና!! ጣራዬ ሰማይ ጥግ ነው ይላል ፈረንጅ The sky is the limit እንደማለት፡፡ ያንን ለማየት መጋረጃውን ገልፆ ፅላቱን የማየት ያህል ጥረትና ድንበር - ዘለልነት ይጠይቃል!!
“እንተኛም ካላችሁ እንገንደሰው
መኝታ እንደሆነ ቀርቷል ካንድ ሰው!”
የሚለውን ዘፈን፤
“አገርህ ናት በቃ
አብረህ አንቀላፋ፤ ወይ አብረሃት ንቃ!!” በሚለው መቀየር ቢያንስ በመርህ ደረጃ አይገደንም ተብሎ ቢታሰብ መልካም ነው!!
“በምናውቀው ስንሰቃይ፣ የማናውቀውንም ፈርተን
በህሊናችን ማቅማማት፣ ወኔያችንንም ተሰልበን…”የሚለውም ሼክስፒራዊ መልዕክት ልብ ካልነው ልብ የሚያስገዛን መርህ ይሆነናል!
በማክቤዝ የመጨረሻ ደቂቃ ልሣን ሼክስፒር የሚለን ብዙ የህይወት መንገዳችነን በመጨረሻዋ ሰዓት አንድንመረምር ወይም እንደዘመኑ እንድንገመግም ያሳስበናል፡፡ እነሆ:-
“የነገ ውሎ፣ የነገ ውሎ፣ የነገ ውሎ
ከቀን ወደቀን ይሳባል፣ በዕድሜ ንፉግ ጀርባ ታዝሎ፡፡
ትላንትናም፣ ከትላንት ወስቲያም
ለጅሎች ጥርጊያ አሳምሮ!
ወደሞት ትቢያ ይሸኛል፣ ዛሬ ፈጥሮ ነገ ቀብሮ!
ጥፊ አንቺ መብራት ጥፊ፣ ጥፊ አንቺ የብርሃን ጭላንጭል
የምትንቀሳቀሽ ጥላ፣ የሰው ህይወት የሰው ዕድል
እንደአልባሌ ተጨዋች
ተወራጭቶ ተፍረክርኮ፣ ተርበትብቶ መድረኩ ላይ
ለብልጭታ ብቻ እሚታይ
ጅል የሞኞች ተረት ነሽ
ቋሚ ትርጉም የሌለብሽ!
(ፀ.ገ.መ)
(Tomorrow and tomorrow and tomorrow,
Creeps in this pety pace to the last
Syllables of the recorded time.
And all our yesterdays have lighted fools
The way to dusty death!
Out out brief candle!
Life is but a walking shadow,
A poor playerዘ that struts and frets his hour upon the stage,
and then is heard no more!
It’s a tale told by an idiot
Full of sound and fury signifying nothing)
ለማናቸውም ፖለቲካዊና ሀገራዊ እንዲሁም አህጉራዊ ጉዞአችን የሚጠቅሙንን መሣሪያዎች ፓርቲያችንን፣ የሰው ኃይላችንን፣ ዕውቀታችንን ወዘተ በአግባቡ ካልተጠቀምንባቸው ካመረርንም ካከረንም፤ ዘራፍ ካልንም ዋይ ዋይ ካልንም፤ ለፀፀት ይዳርጉናል፡፡
ፈረንሣዮች፤
“የምትሠራበት መጋዝ ደነዝ ከሆነ፣ አንተም ደነዝ ነህ!” የሚሉንን በቅጡ እናውጠንጥን!!

Read 5791 times