Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Monday, 05 November 2012 08:12

የቅኝ አገዛዝ መዘዝና የሩዋንዳ እልቂት ተዋናይዋ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በአውሮፓ የቅኝ አገዛዝ ታሪክ ውስጥ እንግሊዝ በከፋፍለህ ግዛ፣ ፈረንሳይ ደግሞ በአዋህደህ ወይም አመሳስለህ ግዛ ዘይቤያቸው ይታወቃሉ፡፡ የንጉሰነገስት ዳግማዊ ሊዎፖልዷ ቤልጅየም የቅኝ አገዛዝ ዘይቤ ግን ከእንግሊዝም ሆነ ከፈረንሳይ የአገዛዝ ዘይቤ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ የቤልጅየምን ቅኝ አገዛዝ ዘይቤ የሚገልፀው አስከፊ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ አገዛዝ ብቻ ነው፡፡ የአገዛዙን አስከፊነት ለመግለጽ ግን ቃል ተፈልጐ አይገኝለትም፡፡ እንደደሌሎቹ የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ሁሉ ቤልጅየምም ቅኝ አገዛዟ ለጨለማዋ አህጉር የስልጣኔና የእድገት ብርሀን ለማብራትና ያልሰለጠኑትን አፍሪካውያን ለማሰልጠን ነው ብላ አጥብቃ ትሟገት ነበር፡፡ ለዚህ ሙግቷ ማስረጃ ይሆናት ዘንድም በዋና ከተማዋ በብራሰልስ፣ አሁን የአውሮፓ ህብረት የኮሚሽኑና የካውንስሉ ዋና ጽህፈት ቤቶች አጠገብ በሚገኝ አንድ ትልቅ አደባባይ መናፈሻ ውስጥ አንድ ሀውልት አቁማለች፡፡

በዚህ ሀውልት ስር የተፃፈው ጽሁፍም “ያልሠለጠኑትን ማሰልጠን” ይላል፡፡ ሀውልቱ የሚያሳየው ግን እርቃናቸውን የሆኑ፣ እጃቸው የኋሊት የፊጢኝ የታሰሩና በአንገታቸው ላይ በታላቅ የእንጨት ቀንበር በአሰቃቂ ሁኔታ ተጠፍረው በአንድ አውሮፓዊ ረጅም ጅራፍ እየተገረፉ የሚነዱ አፍሪካውያንን ምስል ቅርጽ ነው፡፡ 
ብሩንዲያውያንና ሩዋንዳውያን በቤልጅየም ቅኝ አገዛዝ ስር ከተቀበሉት ተነግሮ የማያልቅ አሰቃቂ ግፍ አንዱ በሀውልቱ ላይ የተቀረፀውን ይመስል ነበር፡፡ ሌላኛው የሚገለፀው በህዝቦቹ ላይ በፈጠሩት የዘር ልዩነት ነው፡፡
ማንም እንደሚያውቀው ከቅኝ አገዛዝ በፊት በሩዋንዳ የሚገኙት የሁቱና የቱትሲ ብሔረሠብ አባላት ለአመታት በአንድነትና በሠላም አብረው ኖረዋል፡፡ ሁቱዎች የሀገሪቱን 85 በመቶ የህዝብ ቁጥር በመወከል ብዙሀን ሲሆኑ አስራ አራት በመቶ የሚሆኑት አናሳዎቹ ቱትሲዎች ናቸው፡፡ ከቱትሲዎች ያነሱት ቀሪዎቹ ደግሞ የትዋ ጐሳ አባላት ናቸው፡፡
ከመጀመሪያው እስከ ቅኝ ግዛት ዘመናቸው መገባደጃ አካባቢ ቤልጅየሞች ብዙሁኑ ሁቱዎች በተቀሩት አናሳዎች ላይ በሁሉም ዘርፍ የበላይ እንዲሆኑ አድርገዋቸው ነበር፡፡ የነፃነት ጥያቄ መነሳት ሲጀምር ግን የቆየውን አሰራራቸውን በመቀየር አናሳዎቹን ቱትሲዎች በብዙሀኑ ሁቱዎች ላይ የበላይ እንዲሆኑ አደረጉ፡፡ እናም በአገዛዛቸው ዘመን ለተፈጠሩ ማናቸውም ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ሁሉ አንዱ ሌላውን እንዲወቅስ እንዲያወግዝና በተለይም በከፍተኛ የጥላቻ ስሜት እንዲያየው በማድረግ የመጀመሪያውን ጭፍን የዘር ጥላቻና ከፍተኛ የጠላትነት ስሜት በሁቱና በቱትሲ ህዝቦች ላይ መዝራት ቻሉ፡፡
እጅግ አስከፊ የነበረው የቤልጅየም ቅኝ አገዛዝ አብቅቶ፣ ሩዋንዳ ነፃነቷን ስትቀዳጅ መላ ሩዋንዳውያን በመካከላቸው የተፈጠረውን ጭፍን የዘር ጥላቻና የጠላትነት ስሜት ትተው፣ በአዲስ የነፃነት ስሜት እንደ በፊቱ በአንድነትና በመቻቻል በጋራ መኖር ይጀምራሉ የሚል ግምት ነበር፡፡ ሆኖም ከግምትነት አላለፈም፡፡ በአሳዛኝ ሁኔታ ሁሉም ሩዋንዳውያን ሁቱና ትቱሲዎች፤ ቅኝ ገዥዎች በአዕምሯቸው ውስጥ የዘሩባቸውን ጭፍን የዘር ጥላቻና የጠላትነት ስሜት ይበልጡኑ እያረሙና እየኮተኮቱ በሚገባ እንዲያድግና እጅግ ጠንቀኛ የሆነውን የጥፋትና የእልቂት ፍሬ እንዲያፈራ አደረጉት፡፡ ለበርካታ አመታትም ለዚህ የጥፋትና የእልቂት ፍሬ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐቻቸዉን ህይወትና አካል ያለ አንዳች ስስት ገበሩለት፡፡
ሩዋንዳውያን በየጊዜው በዘር ተከፋፍለው የሚያካሂዱትን የእርስ በርስ ፍጅት እንዲያቆሙና ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ለማድረግ፣ የአለም አቀፉ ማህበረሠብ፣ የውጭና አገር በቀል የእርዳታና የሲቪል ማህበረሠብ ተቋማት በርካታና ተደጋጋሚ ጥረቶች ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡
ጊዜያዊና ለአጭር ጊዜ ብቻ የዘለቀ የትንፋሽ መሠብሰቢያ ጊዜ ከማግኘት የዘለለ ዘላቂ መፍትሄ ማስገኘት ግን አልተቻለም፡፡ ሆኖም ተስፋ ቆርጦ ነገር አለሙን ሁሉ እርግፍ አድርጐ የተወው አልነበረም፡፡
በቡታሬ ከተማ ይንቀሳቀስ የነበረውን የሩዋንዳውያን የሰላምና የልማት ራስ አገዝ ሀገር በቀል ድርጅት እንቅስቃሴን መታዘብ የቻሉት ደግሞ በሁቱና ቱትሲዎች መካከል ዘላቂ ሰላም በቅርብ ርቀት ላይ ይታየናል በሚል ብሩህ ተስፋ ሰንቀው የበኩላቸውን እንቅስቃሴ ያጧጡፉ ነበር፡፡
በግምት 77ሺ500 ሩዋንዳውያን ይኖሩባት የነበረችው ቡታሬ የሩዋንዳ ሶስተኛዋ ትልቅ ከተማ ነች፡፡ በዚህች ከተማ የልማትና የማህበራዊ አገልግሎቶችን ለነዋሪው በመስጠት ሥራ ከተሠማሩት አለም አቀፍና ሀገር በቀል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ “የሩዋንዳውያን የሰላምና የልማት ራስ አገዝ” ድርጅት አንዱ ነበር፡፡ ድርጅቱ ከሚሠጠው የልማትና የማህበረሠብ አገልግሎት በተጨማሪ ሁቱና ቱትሲዎች የእርስ በርስ ጭፍን ጥላቻቸውንና በነፍስ የመፈላለግ የጠላትነት ስሜታቸውን በማስወገድ፣ እንዴት በሰላምና በመቻቻል በጋራ መኖር እንዳለባቸው ከፍተኛ ቅስቀሳና ትምህርት ይሰጥ ነበር፡፡
በአብዛኛው በወጣቶችና በሁለቱም ብሔረሰቦች አባላት የተመሠረተው ይህ ሀገር በቀል ምግባረ ሠናይ ድርጅት፤ መላው አባላቱ ሰርተውና ጥረው ደከመኝ ማለትን ጨርሶ የማያውቁ ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዷ ግን ከሁሉም የተለየች ነበረች፡፡ ይህቺ ሴት ድፍን የቡታሬ ከተማ ነዋሪ፣ ዘርና ጾታ ሳይለይ ካይን ያውጣሽ የሚላትና ከሁሉም አብልጦ ከልቡ የሚወዳት የራስ አገዛዝ ድርጅት የስኬት ተምሳሌት ነበረች፡፡ ይህች የቡታሬ ከተማ ተወዳጅና ብርቅዬ ልጅ ዘሯ ከሁቱ ብሔረሠብ የሚመዘዘው ፓውሊን ንይራማስሁኮ ነበረች፡፡
የሩዋንዳውያን የሰላምና የልማት ራስ አገዝ ድርጅት በሚንቀሳቀስበት የተለያዩ አካባቢዎች የቅድሚያ ትኩረቱ በገጠር የሚኖሩ አርሶ አደሮች ናቸው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የድርጅቱን እንቅስቃሴዎች በግንባር ቀደምትነት የሚያስተባብሩና የሚመሩ አይታክቴ አባላት አሉት፡፡ እነዚህ አባላት በህዝቡ ዘንድ ዘር ከጾታ ሳይለይ የሚወደዱና የሚከበሩ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ አንዳቸውም የቡታሬዋን ፓውሊን ንይራማሱሁኮን መወዳደር የሚችሉ አልነበሩም፡፡ እሷ ፈረንጆቹ “Extraordinary” የሚሏት አይነት ነበረች፡፡
ፓውሊን ንይራማሱሁኮ፤ ዘወትር አዳዲስ ሀሳቦችን የምታፈልቅ፣ ከፍተኛ ህዝብ የማስተባበርና የማነቃነቅ ችሎታ ያላት፣ ስለ ህዝቦች ሰላምና ልማት ዘወትር ከመጨነቅና ስለ እነሱም ከማውራት ሌላ ቋንቋና ወሬ ያላት የማትመስል፣ መላ ህይወቷን ለህዝቦቿ አሳልፋ የሰጠችና ለግል ህይወቷ ጨርሶ የማትጨነቅ እጅግ አስገራሚ “የህዝብ ልጅ” ነበረች፡፡
ፓውሊን በተፈጥሮ የታደለችው ሌላም ፀጋ ነበራት፡፡ በአንደበተ ርቱዕነት በድፍን ሩዋንዳ “እከሌ ያክላታል” የማትባል አስደናቂ ተናጋሪ ነበረች፡፡ ተወልዳ ባደገችበት የቡታሬ ከተማ የገጠር አካባቢዎች አርሶ አደሮችን ሰብስባ፣ የሁቱና የቱትሲ ብሔረሰቦች የእርስ በርስ ግጭትና ጥላቻን እያወገዘች፣ በሰላምና በአንድነት ተቻችለው እንዴት መኖር እንደሚቻልና እንዳለባቸውም ጭምር፣ በዚያ ወፍራም ቃና ባለው አስገምጋሚ ድምጿ፣ ልክ እንደ መድረክ ላይ ተዋናይ ከወዲያ ወዲህ እየተንጐማለለች ስታስረዳ ያያትንና ያዳመጣትን ሁሉ አፍ ታስከፍት ነበር፡፡
የቡታሬ ከተማ ነዋሪዎች በተለይ ደግሞ ሁቱዎቹ ለዚህች ልጅ ያላቸው ከበሬታና ፍቅር ልክ የለሽ በመሆኑ፣ ሁሉም ልክ እንደራሳቸው ልጅ አድርገው በመቁጠር፣ አምላካቸውን እሷን ስለሰጣቸው ዘወትር ተመስገን ይሉት ነበር፡፡
ፓውሊን ንይራማሱሁኮ፤ ባለትዳርና የልጆች እናት ብትሆንም ነገረ ስራዋ ሁሉ ይህንን የሚያረጋግጥ ጨርሶ አልነበረም፡፡ ቀኑን ሙሉ በህብረተሰብ ልማት ስራ ላይ ተጠምዳ ስለምትውል፣ ለቤተሰቧ ብዙም ጊዜ አልነበራትም፡፡ ያላትን ሁለትና ሶስት ሰአታትም ቢሆን ከባለቤቷ ይልቅ የጓደኛ ያህል ከምትቀርበው ወንድ ልጇ ጋር ነበር የምታሳልፈው፡፡ እናትና ልጅ በቤታቸው ውስጥ የሚያደርጉትን ውይይት ከባሏ በቀር ሌላ ማንም ሰው ሰምቷቸው አያውቅም፡፡ እንደ ተአምር በሚቆጠር አጋጣሚ ይህን እድል ያገኘ ሰው ሌላኛዋን ፓውሊን ንይራማሱሁኮን ማየትና መታዘብ ይችላል፡፡
ፓውሊን ምሽት ላይ ከመኖሪያ ቤቷ ሳሎን ላይ ካለውና የግብጽ ስሪት ከሆነው ትልቅ ሶፋ ላይ አረፍ እንዳለች፣ ወዲያውኑ ልጇ የብርቱካን አሊያም የማንጐ ጭማቂ ያቀርብላትና፣ በጀርባዋ ዞሮ አንገቷ ስር፣ ትከሻዋንና የውስጥ እግሮቿን በሁለት እጆቹ እያሻሸ “እሺ እማዬ! How is your day?” በማለት የምሽቱን ጨዋታቸውን ይጀምርላታል፡፡ “ኦው! ዛሬ ድንቅ ቀን ነበር፡፡ ለወረዳው ህዝብ ካቀረብነው የጓሮ አትክልት ዘር ውስጥ አብዛኛውን የወሰዱት የኛ ሰዎች ናቸው፡፡ በረሮዎቹ ዛሬ ምን እንደነካቸው አይታወቅም! የመጡት ጥቂት ብቻ ነበሩ፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ በጣም ዘግይተው ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት ዘሮቹን ሙሉ በሙሉ ግፍፍ አድርገው የወሰዱት በረሮዎቹ ነበሩ፡፡ እንዴት እንደበሸቅሁ አትጠይቀኝ፡፡ ደግነቱ የሰጠኋቸው ዘሮች ሙሉ በሙሉ የተበላሹና ጊዜያቸው ያለፈባቸው ናቸው፡፡” እያለች ታስረዳዋለች፡፡
“ግን እማዬ፤ በረሮዎቹን የምንገላገላቸውና ሩዋንዳ “ኮክሮች ፍሪ” ሀገር የምትሆነው መቼ ይመስልሻል?” ልጇ በጉጉት አይን እያያት ይጠይቃል፡፡ ፓውሊንም አንገቷን ወደ ግራና ቀኝ እያወዛወዘችና አይኗን ቦዘዝ አድርጋ ጣሪያው ላይ በመስቀል “well! አሁን ጊዜውን መገመት አይቻልም፡፡ እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻለው ግን ኮክሮቾቹን (በረሮዎቹን) ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መገላገላችን የማይቀር መሆኑን ነው፡፡” በማለት መለሰችለት፡፡ ወዲያው ከተቀመጠችበት ሶፋ ላይ ድንገት ቱር ብላ ተነሳችና፣ ልጇ ያቀረበላትን የማንጐ ጭማቂ ባንድ ትንፋሽ ገጭ ገጭ አድርጋ ጠጥታ ከጨረሰች በኋላ፣ የግራ እጇን ጥብቅ አድርጋ ጨብጣ በመያዝ “ስማ አቡሽ! ኮክሮቾችን ሳያስቡት አንገታቸውን እንቅ አድርገን ይዘን ወደመጡበት እንዲመለሱ ቪክቶሪያ ሀይቅ ውስጥ ከመክተታችን በፊት፣ ያ ነጭና ጥቁር አይናቸው ተጐልጉሎ ወጥቶ እየተቁለጨለጨ ምህረት ሲለምን ማየት በጣም ደስ አይልም?” በማለት ጠየቀችው፡፡ ልጇ አልመለሰላትም፤ ግን ፊቱ ሁሉ ጥርስ ብቻ የሆነ እስኪመስል ድረስ ፈገግ አለ፡፡
ልጇን ምን አይነት ነገሮች እየነገረች እንዳሳደገችውና ምን አይነት ልጅም እንዳደረገችው በሚገባ ታውቃለች፡፡ እናም ለሚሰጣት መልስ ግድ አልነበራትም፡፡ እንዲህ በመሰለው ሁኔታ እናትና ልጅ ዘወትር የሚወያዩት “ስለሁቱና ቱትሲ” ጉዳይ ነው፡፡ ፓውሊን ንይራማሱሁኮ፤ የኛዎቹ እያለች የምታወራው ስለራሷ የሁቱ ብሔረሰብ አባላት ሲሆን “ኮክሮች” የምትላቸው ደግሞ አናሳዎቹን ቱትሲዎችን ነበር፡፡ ከኮክሮች የፀዳች ሩዋንዳን መፍጠርና “ኮክሮቾችን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መገላገል” እያሉ የሚያወሩት ደግሞ ምን ማለታቸው እንደሆነ ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይደለም፡፡
እንግዲህ ልብ አድርጉ፡፡ ማንም የውጭ ሰው አዳምጧቸው የማያውቀው ውይይታቸው ይህን የሚመስል ነበር፡፡ እስከ 1991 ዓ.ም ድረስ ማንም አይቶትም ሆነ ሰምቶት የማያውቀው የፓውሊን ንይራማስሁኮ አንዱ ገጽታና ማንነትም ይህ ነበር፡፡
የእናትና ልጁን የዘወትር ውይይት ያዳመጠ ሠው፤ ፓውሊንን ህዝብ ሰብስባ ስለ ጋራ ልማትና ተቻችሎ መኖር ነውና ልዩ መታወቂያዋ የሆነውን ያን አስገራሚ ንግግር ስታደርግ ቢያያትና ቢሠማት አንድም ያየበትን አይንና የሰማበትን የገዛ ጆሮውን መጠራጠሩ አሊያም በሴትየዋ ተለዋጭ ባህርይ ክፉኛ መደንገጡ አይቀሬ ነው፡፡
አሳዛኝና እድግ አስደንጋጭ የሆነው እውነት ግን ትክክለኛውና እውነተኛው የፓውሊን ንይራማሱሁኮ ማንነት ይህ መሆኑ ነው፡፡ ፓውሊን ንይራማሱሁኮ ገና “ውሪ” ሳለች ጀምሮ አባቷ በልቧና በአዕምሮዋ ውስጥ በቀላሉ እንዳይፋቅ አድርጐ የተከለባትን ወደር የለሽና ጭፍን የቱትሲ ጥላቻና አደገኛ የጠላትነት ስሜት በንቁ ስሜት ተንከባክባ በማሳደግ፣ በከፍተኛ ጥንቃቄ ከሰው አይንና ጆሮ ሸሽጋ ያስቀመጠችው በከፍተኛ ባተሌነት፣ የህዝብ ፍቅርና ተቆርቋሪነት የህዝብ ሰላምና ልማት ስራ ውስጥ በመቅበር ነበር፡፡
ቱትሲዎችን ሲያይ ከጥላቻው የተነሳ አፍንጫውን የሚነስረው አባቷ፤ ገና ከህፃንነቷ ጀምሮ እሷንና ወንድሞቿን እየሰበሰበ “ሞት የሚጋልበው ፈጣኑን ግመል ነው፡፡ ስለዚህ ሁሌም ቢሆን ተረጋጉ፡፡ የሚገድላችሁ ወደ እናንተ የተተኮሰው ጥይት ሳይሆን እጣ ፈንታችሁ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ አትፍሩ፡፡ ውሻ ነብር የሚሆነው በሠፈሩ ብቻ ነው፡፡ ይህን አትርሱ፡፡ የሰው ልጅ ሆድና ልብ ከአንድ አህጉር ይሠፋል፡፡ የልባችሁን በልባችሁና በሆዳችሁ ብቻ ያዙት፡፡ የእናንተ ቀዳሚም ሆነ ተከታይ የሌላቸው ዋነኛ ጠላቶቻችሁ ኮክሮቾች ብቻ ናቸው፡፡ ፍየሎች በአነር መንጋ መካከል መኖር እንደማይችሉት ሁሉ እናንተም በኮክሮቾች መካከል መኖር አትችሉም፡፡ ኮክሮቾች ጨርሰው መጥፋት አለባቸው፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ልናጠፋቸው ስንሄድ ቀድመው እንዳይሸሹ፣ ስለታሙን ሳንጃችንን በገንፎው መሀል ደብቀን መያዝና በፍቅር ልባቸውን መማረክ መቻል አለብን፡፡” በማለት ጭፍን የጥላቻና የጠላትነት ስሜቱን ሳይሰለች ያስተምራቸው ነበር፡፡
ፓውሊን ንይራማሱሁኮም በጐልማሳነት እድሜዋ መሆን የቻለችው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ያባቷ ልጅ፡፡ በቱትሲዎች ላይ ያላትን ወደር የለሽ ጭፍን ጥላቻ ልክ አባቷ እንዳስተማራት በልቧና በሆዷ በመያዝ፣ ጊዜው ደርሶ ልታጠፋቸው ስትሄድ ቀድመው እንዳይሸሿት ባለ መንታ ስለት ጩቤዋን ገንፎው ውስጥ ደብቃ አስቀመጠችው፡፡ ለዋነኛ ጠላቶቿ ለቱትሲዎች እንዲበሉት ያቀረበችላቸው ገንፎ ደግሞ የደቂቃ እረፍት ሳያምራት በከፍተኛ ስኬትና ብቃት የምታከናውነው የሰላምና የልማት አገልግሎት ነበር፡፡ በዚህ ባተሌነቷ መካከልም ትንሿ እንሽላሊት አዞ ለመሆን ከሁሉም የላቀ ተስፋ ታደርጋለች እንደሚባለው፣ “ኮክሮች” የምትላቸውን ጠላቶቸን ቱትሲዎችን በቀላሉ ቅርጥፍ አድርጋ መብላት የምትችል አዞ እስከምትሆን ድረስ አድፍጣ ታደባ ነበር፡፡ እስከ 1991 ዓ.ም ድረስም የቆየችው እንዲሁ እንደተባተለችና እንዳደባች ነበር፡፡
1991 ዓ.ም ለፓውሊን ንይራማሱሁኮ የተለየና እጅግ ድንቅ አመት ነበር፡፡ በሩዋንዳውያን የሰላምና የልማት ራስ አገዝ ድርጅት አማካኝነት፣ በቡታሬ ከተማ ስታከናውናቸው የነበሩትን በርካታ ስኬታማ የሰላምና የልማት ማህበራዊ አገልግሎቶች በቅርበትና በትኩረት ሲከታተሉት የነበሩት የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ጁቤናል ሀቢያሪማና፤ መልዕክተኛቸውን በመላክ፣ ወደ ኪጋሊ ቤተመንግስታቸው አስጠሯትና በሚኒስትርነት የካቢኔአቸው አባል ሊያደርጓት እንደሚፈልጉ አሳወቋት፡፡ እሷም ፕሬዚዳንቱን በአክብሮትና በምስጋና ጐንበስ ብላ እጅ ነሳች፡ ከሶስት ቀን በኋላም የሩዋንዳ የቤተሰብና የሴቶች ጉዳይ ሚኒስትር ሆና መሾሟ በይፋ ተገለፀ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮም ትንሿ እንሽላሊት ቀስ በቀስ ወደ ትልቁ አዞነት ማደግ ጀመረች፡፡ “ሁሉም አራዊት በየግዛቱ ያገሳል” እንደሚባለው ፓውሊን ንይራማሱሁኮም በሚኒስትርነት ከተሾመችበት ጊዜ ጀምሮ በስልጣን ክልሏ ላይ ሆና ማግሳት ጀመረች፡፡
ከተሾመችበት የሚኒስትርነት ስራዋና ሃላፊነትዋ ይልቅ ከቀበረችበት የልቧና የሆዷ ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ቆፍራ ይፋ ባወጣችው እጅግ ጽንፈኛ የፀረ - ቱትሲ አቋሟ ፕሬዚዳንት ሃቢያሪማናንና ሌሎች ሁቱ የካቢኔ አባላትን የበለጠ ማስገረምና ማስደነቅ የቻለች ሆና ብቅ አለች፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን የቡታሬ ቱትሲዎች ለፓውሊን ያላቸው ስሜትና አመለካከት ያው እንደቀድሞው ነበር፡፡ ፓውሊን የተባረከችውና ታታሪዋ ልጃቸው ነበረች፡፡ ስለነብር የሚያውቁት አባባልም “አምላክ ነብርን በመፍጠሩ ከምትወቅሰው ይልቅ ለነብሩ ክንፍ ስላልቀጠለለት አመስግነው” የሚለውን ብቻ ነው፡፡ አዲሲቷን ፓውሊን ንይራማሱሁኮን ጨርሰው አላወቋትም እንዲያው ሠይጣን አሳስቷቸው በክፉ ቢገምቷት ነብር ቢሏት ነው፡፡ እርሷ ግን ከነብርም ባለክንፍ በራሪ ነብር ሆና ነበር፡፡
1993 ዓ.ም ተገባዶ አዲሱ አመት 1994 ዓ.ም እንደጀመረ፣ የሁቱና የቱትሲ ብሔረሰቦች ግንኙነት ቀስ በቀስ እየሻከረ፣ አዲስና አደገኛ አዝማሚያም መያዝ ጀመረ፡፡ በየቦታው ግጭቶች እየተፈጠሩ በአስራና በመቶ የሚቆጠሩ ሩዋንዳውያንን ህይወት መቅጠፍ ጀመሩ፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለውም በጀነራል ፖል ካጋሜ የሚመራውና የቱትሲዎች ነው የሚባለው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር አማፂ ቡድን በሁቱዎች የተገነባውን የመንግስት ጦር እያጠቃ ይዞታውን ማስፋት ቀጠለ፡፡
በዚህ ወቅት የቱትሲዎች ጉዳይ የፕሬዳንት ጁቬናል ሀቢያሪማና ካቢኔ ዋነኛ የመወያያ አጀንዳ ሆነ፡፡
ካቢኔው በጉዳዩ ላይ ውይይት በሚያደርግበት ወቅት ከመላው አባላቱ ውስጥ ለቱትሲዎች ችግር ዋነኛውና የማያዳግመው መፍትሔ “ኮክሮቾቹን ቱትሲዎች በሙሉ ገድሎ መጨረስ ነው” የሚል የመፍትሔ ሃሳብ ስታቀርብና ለተግባራዊነቱም ሽንጧን ገትራ ስትሟገትና በጦር አውርድልኝ መሬት በጅራፍ ስትገርፍ የነበረችው ፓውሊን ንይራማሱሁኮ ነበረች፡፡ ይህን እጅግ አደገኛ ምኞቷን በቅርብ ሆኖ ሲያዳምጣት የነበረው ሠይጣንም በጥቅምት ወር 1994 ዓ.ም ላይ የምኞቷን ይዞላት ከተፍ አለ፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ 1994 ዓ.ም ለሩዋንዳውያን በታሪካቸው አይተውት የማያውቁትን መከራ በውስጡ አጭቆ በመያዝ፣ በሩዋንዳ ብቻ ሳይሆን በመላው አለምና የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ በአስከፊነቱ ለዝንተአለም ሲነገር የሚኖር ዘግናኝ ጥቁር ታሪክ የሚያስመዘግቡበት አመት ሆነ፡፡ ለአናሳዎቹ ለቱትሲዎች ደግሞ አውቀውት አልተዘጋጁበትም እንጂ የምጽአት ቀናቸው ነበር፡፡
በዚሁ አመት የጥቅምት ወር ፕሬዚዳንት ሃቢያሪማና ከአማፂው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ጋር በታንዛንያ አደራዳሪነት በተጀመረው የሰላም ስምምነት ቢቀጥሉበትም የቱትሲዎች ጉዳይ የማያዳግም መፍትሔ እንዲያገኝ ይፋ ያልሆነ ውሳኔ አሳልፈው ነበር፡፡ በዚህ መሠረትም የጦር ሃይሉ መሪዎች የካቢኔ አባላት ሚኒስትሮች፣ የሲቪል ማህበረሰብ መሪዎችና የሀይማኖት መሪዎች የሆኑ ጽንፈኛ የሁቱ ብሔርተኞች፣ ፀረ ቱትሲ ቅስቀሳቸውንና “ኢንተርሃዋሜ” እየተባሉ የሚጠሩትን የሁቱ ሚሊሻዎች በቻሉት አቅም ሁሉ ማደራጀትና ማስታጠቅ ጀመሩ፡፡
ፓውሊን ንይራማሱሁኮም ወደ ትውልድ ከተማዋ ቡታሬ ወጣ ገባ በማለት የዘመናት እቅዷና ህልሟ የሆነውን ኮክሮቾችን የማስወገድ ዝግጅት አገባደደች፡፡
በሩዋንዳ ታሪክ እጅግ የተረገመ በተባለለት የህዳር ወር 1994 ዓ.ም በታንዛንያ የሠላም ድርድር ላይ የሠነበቱትን የሩዋንዳውን ፕሬዚዳንት ጁቬናል ሀብያሪማናንና የብሩንዲውን አቻቸውን ፕሬዚዳንት ሲፕሪየን ንታራማራን አሳፍሮ ወደ ኪጋሊ ሲገሰግስ የነበረው አውሮፕላን፣ ዛሬም ድረስ በይፋ ባልተገለፀ ሁኔታ ተመትቶ ወደቀና የሁለቱ ፕሬዚዳንቶች ህይወት አለፈ፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉም ሠይጣኖች ከገሀነም ቤታቸው በመውጣት፣ በቀጥታ ያመሩት ወደ ሩዋንዳ ነበር፡፡ ብዘሀኑ ሁቱዎች ጦር ሰብቀው ዘገር ነቅንቀው ኮክሮች በሚሏቸው አናሳዎቹ ቱትሲዎች ላይ ዘመቱባቸው፡፡
ፍጅቱ እንደተጀመረም ፓውሊን ንይራማሱሁኮ በቀጥታ ያመራችው ወደ ቡታሬ ነበር፡፡ እዛ ሄዳም ያደረገችው አስቀድማ ካደራጀቻቸው በተጨማሪ ሌሎች የሁቱ “ኢንተርሃዋሜ” ሚሊሻዎችን ማደራጀትና ማስታጠቅ ነበር፡፡
ይህን ስራ ለማጠናቀቅ የፈጀባት አራት ቀናት ብቻ ነበር ከዚህ በኋላ የቀረው በጉጉት ስትጠብቀውና ስትሳልበት የነበረው ሥራ ብቻ ነው፡፡ ያደራጀቻቸውን የኢንተርሃዋሜ ሚሊሻዎች ወሳኝ አመራር በመስጠት ኮክሮቾችን በያሉበት እየሄዱ በገንፎው መሀል ለዘመናት ደብቃ አኑራው በነበረው ሳንጃ መፍጀት፡፡ በቃ ይሄው ነው!
በዚህ በኩልም የሰጠችው አመራርና የፍጅት አፈፃፀሟ እንከን አልባና እጅግ የተዋጣለት ነበር፡፡ የቡታሬ ቱትሲዎች ለአመታት ለሰላምና ልማት ስትታገልላቸው የነበረችው የሚወዷትና የሚያከብሯት ፓውሊን ንይራማሱሁኮ ያደራጀቻቸውን ሚሊሻዎች አስከትላ በየመንደሮቻቸው ከች ስትል፣ ያው እንደለመደችው የመጣችው ለሠላምና ልማት ነው አሉ እንጂ ልትፈጀን ነው ብለው ጨርሰው አልጠረጠሩም፡፡ እናም ሲያዩዋት መሸሽ እንዳለባቸው ፈጽሞ አላሰቡትም፤ አልፈለጉምም ነበር፡፡
ለእሷ ግን ሰርግና ምላሽ ሆኖላት ነበር፡፡ የቡታሬን ኢንተርሃዋሜ ሚሊሻዎችን እየመራች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩትን ቱትሲዎች ለመግለጽ በሚያስቸግር ሁኔታና ወደር በሌለው ጭካኔ ጨፈጨፈቻቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ እንደግል ጠባቂም እንደ ቀኝ እጅም ሆኖ ያገለግላት የነበረው ወንድ ልጇ ነበር፡፡
ፓውሊን ንይራማሱሁኮ፤ ለሶስት ወራት በዘለቀው ፍጅት በጣም ያስደስታት የነበረው ከወንድ ቱትሲዎች ይልቅ ሴቶችን ማሰቃየት ነው፡፡ ከመግደሏ በፊት ቶርች ማድረግ፣ ከገደል እጅግ እግራቸውን በማሠር መወርወር፣ ከፎቅ ላይ በጭንቅላታቸው እንዲወድቁ በማድረግ መወርወር፣ ውሃ የተሞላ ላስቲክ በአንገት ላይ ማሠርና በውሃ ማፈን፣ የግብጿ ንግስት ክሊዮፓትራ ታደርገዋለች እንደሚባለው የሴቶችን ጡት በስለት መውጋትና መሠንጠቅ ነበር፡፡
ከሁሉም የሚያስገርመው የግድያ ድርጊቷ ደግሞ ቆንጆ የቱትሲ ልጃገረዶችን እየመረጠች በልጇ ማስደፈርና ሲደፈሩም ቁጭ ብላ እያየች መደሠቷ ሲሆን አንዳንዴ ደግሞ ልጇ የቱትሲ ልጃገረዶችን ሲደፍር እርሷ የሚደፈሩትን ልጃገረዶች አንገት በሁለት እጆቿ አንቃ ትገድል ነበር፡፡ እንዲህ ያሉትን አሠቃቂ ፍጅቶች ለሶስት ወራት ሙሉ በቡታሬ ከተማና የገጠር አካባቢዎች እየተዘዋወረች ስትፈጽም ከቆየች በኋላ በፖልካጋሜ የተመራው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ኪጋሊን ሲቆጣጠር፣ በሀምሌ ወር መጨረሻ 1994 ዓ.ም ያንን ልጇን አስከትላ ድንበር በማቋረጥ ወደ ኬንያ ተሠደደች፡፡
ፓውሊን ንይራማሱሁኮ በኬንያ ለሶስት አመታት በስደት ተደብቃ ከቆየች በኋላ ሀምሌ 18 ቀን 1997 ዓ.ም በአለም አቀፉ ወታደራዊ ሀይል ከተደበቀችበት ተይዛ፣ በአሩሻ ታንዛንያ ለተሰየመው የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተላልፋ ተሰጠች፡፡ ከቀረቡበት ክሶች በሰባቱ ጥፋተኛ ሆና በመገኘቷም በእደሜ ልክ ጽኑ እስራት እንድትቀጣ ፍርድ ቤቱ በየነባት፡፡ ያ ሴት ደፋሪ ልጇም ፍርድ ቤት ቀርቦ ልክ እንደ እናቱ የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ተከናነበ፡፡

Read 7948 times