Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Monday, 05 November 2012 09:09

ሉሲዎች እንደተጠበቁት አልሆኑም

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በኢኳቶርያል ጊኒ አዘጋጅነት መካሄድ ከጀመረ ሳምንት ባለፈው 8ኛው የአፍሪካ ሴቶች ሻምፒዮንሺፕ ላይ በሞት ምድብ የሚገኘው የኢትየጵያ የሴቶች ብሄራዊ ቡድን በምድቡ የመጀመርያ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈቶች ከገጠመው በኋላ ለግማሽ ፍፃሜ ሳይደርስ ቀረ፡፡ ሉሲዎች የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታቸውን ከካሜሮን ጋር መርሃግብሩን ለመፈፀም ያደርጋሉ፡፡ ሉሲዎች ባለፈው ሰኞ ከአይቮሪኮስት አቻቸው ጋር ባደረጉት የምድቡ የመጀመርያ ጨዋታቸው 5ለ0 ሲሸነፉ ከትናንት በስቲያ ሁለተኛ ግጥሚያቸውን ከናይጄርያ ጋር አድርገው 3ለ0 ተረትተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በሁለቱ ጨዋታዎች ያለምንም ነጥብ በ8 የግብ እዳ የምድቡን መጨረሻ ደረጃ በመያዙ የማለፍ ዕድሉ የተከናወነ ይሆናል፡፡


ባለፈው ሰኞ የተካሄደው የኢትዮጵያ እና የኮትዲቯር ጨዋታ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ሜዳው በመበላሸቱ በአግባቡ ለመጫወት ምቹ አልነበረም፡፡ ሉሲዎች በሜዳው ውሃ መቋጠር የሚታወቁበትን የአጨዋወት ስልት ለመተግበር አልቻሉም ነበር፡፡
ሉሲዎች በኮትዲቯር ቡድን ለደረሰባቸው ሽንፈት በግብ ጠባቂ እና በተከላከይ መስመር የነበረው ድክመት ምክንያት ነበር፡፡ በመጀመርያው ግማሽ ጨዋታ በተጀመረ በ36ኛው ሴኮንድ እና በዘጠነኛው ደቂቃ 2 ጎሎች ገባባቸው፡ኮትዲቯሮች ከእረፍት መልስ ተጨማሪ ሶስት ጎሎችን በማግባት የኢትዮጵያን አጀማመር በ5ለ0 ውጤት አበላሽተውታል፡፡
በዚያው እለት በሌላ የምድቡ ጨዋታ ናይጄርያ ካሜሮንን 2ለ1 አሸንፋለች፡፡ ሐሙስ እለት በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ ካሜሮን 4ለ1 በሆነ ውጤት ኮትዲቯርን ስታሸንፍ የሰባት ጊዜ የውድደሩ አሸናፊ ናይጄሪያ 3ለ0 በሆነ ውጤት ኢትዮጵያን በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፏን አረጋግጣለች፡፡
በምድብ አንድ የመጀመርያ ጨዋታዎች ኢኳቶሪያል ጊኒ ደቡብ አፍሪካን፤ ዲ.ኮንጎ ሴኔጋልን በተመሳሳይ አንድ ለዜሮ አሸንፈዋል፡፡ ረቡዕ በተደረገው የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታዎች ደግሞ ደቡብ አፍሪካ 1ለ0 ሴኔጋል ስታሸንፍ ኢኳቶሪያል ጊኒ ደግሞ ዲ.ኮንጎ 6ለ0 ረታለች፡፡
የየምድቦቹ የመጨረሻ ጨዋታዎች ከመካሄዳቸው በፊት ከምድብ1 ሴኔጋል ከምድብ 2 ኢትዮጵያ መውደቃቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ምድብ አንድን በሁለት ጨዋታዎች በሰበሰበችው 6 ነጥብ የምትመራው አዘጋጇ ኢኳቶርያል ጊኒ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፏን ከምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ በፊት ስታረጋግጥ ከምድቡ ሁለተኛውን አላፊ ቡድን ለመለየት እኩል 3 ነጥብ ያላቸው ደቡብ አፍሪካና ዲ ሪፖብሊክ ኮንጎ ይፋጠጣሉ፡፡ በምድብ 2 ናይጄርያ 6 ነጥቦች አስመዝግባ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ከሶስተኛው የምድብ ጨዋታ በፊት መግባቷን ስታውቅ ሁለተኛውን አላፊ ለመለየት በሚደረገው ትንቅንቅ ኮትዲቯር ከናይጄርያ እንዲሁም ካሜሮን ከኢትዮጵያ ወሳኝ ግጥሚያዎች ይኖራቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ሻምፒዮናው ብቁ ተፎካካሪ እንደሚሆን ተጠብቆ ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡ ለዚህም ሁለት ችግሮች በምክንያትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ በመጀመርያ የብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች በሰው ሜዳ እና ደጋፊ ፊት ሲጫወቱ መደናገጥ ማሳየታቸው ነው፡፡ የአየር ሁኔታን ለመላመድ የሚያስችል በቂ ዝግጅት በጥናት አለመደረጉ ደግሞ ሌላው ችግር ነው፡፡
በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፏቸው ከፍተኛ ልምድ ያገኙት ሉሲዎች በቀጣይነት ስኬታማ እንዲሆኑ በስፋት መስራት ያስፈልጋል፡፡ በብሄራዊ ቡድኑ ላለፉት 8 እና 10 ዓመታት የተጫወቱ የሴቶች እግር ኳስ ወርቃማ ትውልድ አባላትን ከዚህ አፍሪካ ዋንጫ በኋላ ስለሚያጣ ለእነሱ ተተኪ እንደሚያስፈልጋቸው በማሰብ ለለውጥ መንቀሳቀስ የሁሉ ባለድረሻ አካላት ሃላፊነት ነው፡፡

Read 4120 times