Saturday, 10 November 2012 14:08

የደከሙ ባትሪዎችና…‘ቻርጅ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

ደህና ሰንብቱልኛማ! ምነው ዳገት ሳልወጣ ልቢቷ ምቷ ፈጠነብኝሳ!እናማ…እንዲህ ካልን በኋላ ዋናው ጥያቄ ምን መሰላችሁ…“እነኚህን የደከሙ ባትሪዎች ሁሉ ‘ቻርጅ’ የማድረግ ኃላፊነቱን የሚወስድ አቅሙ ያለውና፣ ከሁሉም በላይ የእውነት ታማኝና የምር ገለልተኛ ሰውና ተቋም አለ ወይ?” የሚለው ነው፡፡ ስሙኝማ…ደጋገመን እንደምንለው ከልብ ከሳቅን ይኸው ስንት ኦሎምፒክ እንዳለፈን የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ በ‘ስንትና ስንት ነገሮቻችን’ እየተሳሳቅን ድብርትን እናባርር እንዳልነበር ሁሉ… የምንስቅባቸው ጉዳዮች አዳዲስ ‘ዴፊኒሽኖች’ (አንዳንዴም ሌላው ዓለም የማይገኙ እንደ ቀይ ቀበሮ “የእኛ ብቻ” የሆኑ ‘ዴፊኒሽኖች’) እየተሰጣቸው…ከማልቀስ ይሻላል ብለን፣ የከተሜዎቹን ቋንቋ ለመዋስ፣ በ‘ፉገራ ለመሳቅ’ ተገደናል፡፡እናማ…‘ቻርጅ’ መደረግ የሚገባቸው የደከሙ ባትሪዎች በሙሉ ይዘርዘሩልንና ሬፌሬንደም ይካሄድ (ቂ…ቂ…ቂ…) ልክ ነዋ… ‘ቻርጅ’ ለማድረግም ቅደም ተከተል ያስፈልግ የለ!እናማ…ምን አይነት እጸ ፋሪስ ቢያስነኩን ነው በናፍቆት የምንጠብቀው! የዚህ ነገር መደጋገም የሆኑ የደከሙና ‘ቻርጅ’ መደረግ ያለባቸው ባትሪዎች ያሉ አይመስላችሁም!ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…“በናፍቆት ሲጠበቅ የነበረው…” የምትባል ጨዋታ አልበዛችባሁም! ነገሩ ክፋት የለውም፡፡

ግን ነገርዬው እኮ እንኳን በናፍቆት ሲጠበቅ መኖሩን ማንም አያውቀውም እኮ፡፡ “በናፍቆት ሲጠበቅ የነበረው በእንትና እንትና ተጽፎ ዳይሬክት የተደረገው ፊልም…” ምናምን ይባላል፡፡ ችግሩ ምን መሰላችሁ…መጀመሪያ ‘እንትና እንትና’ የተባለው ጸሀፊና ዳይሬክተር ከዛ በፊት የሠራው ነገር ስላልነበር ልናውቀው የምንችልበት መንገድ የለም፡፡ የዚሀ አይነት ጠያቂዎችም መላሾችም ከፍተኛ ‘ቻርጅ’ የሚያስፈልጋቸው ‘ውሀ ሊያዡ’ በቋፍ ያሉ ባትሪዎች ያሏቸው ነው የሚመስለኝ፡፡ ስሙኝማ…የማወቅና ፈላስፋ ምናምን የመሆንን ነገር ስናነሳ…አለ አይደለ…አንዳንድ ጊዜ ሚዲያዎች ላይ የምንሰማቸው ነገሮች…ምን አለፋችሁ…የተረፈች ተስፋ ብትኖረን እንኳን እሷኑ አሽቀንጥረን እንድንጥል የሚያደርጉ ናቸው፡፡ “እንደው በአንተ እይታ ሰው ወደዚች ዓለም የመጣው ለምን ይመስልሀል?” ስትል ቤተዘመድ “ነጋ ጠባ አማንፑር ነኝ የምትለው እንደዛ የሚባል ዘመድ አለን እንዴ?” እያሉ የሚዘባበቱባት ‘ጥይት ኢንተርቪወር’ ትጠይቃለች፡፡“በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው የጠየቅሽኝ፡፡ ሁልጊዜ ይህን ጥያቄ መቼ ነው የምጠየቀው እል ነበር፡፡ ምን መሰለሽ…እ…እ…ዋናው ነገር ወደዚች ዓለም የመጣሁበት ዓላማዬ ምንድነው ብለሽ ራስሽን መጠየቅ አለብሽ፡፡” በቃ መልሱ አለቀ! አሪፍ አይደል!እኔ የምለው፣ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የምናቃቸው ነገሮች መአት እንደሆኑ የሚነግሩን ሴሎቻችን ባትሪ በጣም፣ እጅግ በጣም ደክሞብናል፡፡ ‘አዋቂዎች’ በዛን… ‘ፈላስፎች’ በዛን… “ይቺ አገር ዋጋ የላትም…” የምንል ኖስትራዳመሶች በዛን…ኦሾዎች፣ ሳርተሮች…ሲግመንድ ፍሮዶች በዛን! ምን አለፋችሁ…አለማወቅ “ይቅርታ የማይደረግለት ኃጢአት…” እንዳልሆነ የሚነገሩንን ሴሎቻችን ባትሪ ‘ቻርጅ’ ይደረግልንማ!እናማ…‘ቻርጅ’ መደረግ ያለባቸው ብዙ የደከሙ ባትሪዎች አሉ፡፡“ዋጋውን ለመቆጣጠር ጥረት ይደረጋል…” “አስበልጠው የሚሸጡ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር ጥረት ተጀምሯል…” “አግልግሎቱ እንዳይቆራረጥ ለማድረግ ጥረት ተጀምሯል…”  “እንትንን በዩኔስኮ በቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት ተጀምሯል…” ብቻ ምን አለፋችሁ… እዚህ አገር ሁልጊዜም ‘ጥረት የተጀመረባቸው’  (ወደፊትም የሚጀምርባቸው  ብሎ መጨመር ይቻላል) ነገሮች መአት ናቸው፡፡ መጀመር ሳይሆን መጠናቀቅ የሚባል ነገር እንዳለ የሚነግሩን ሴሎቻችን ባትሪ ስለደከመ ‘ቻርጅ’ ይደረግልንማ!ደህና ወሬ መስማት የሚፈልገው የሰውነታችን ክፍል ‘ቻርጅ ይደረግልንማ!እናማ… “ዜና…” እየተባለ የምንሰማው ለስንት ዘመን የሰለቸን  ‘የግብርና ኤክስፐርቱ የመስኖ እርሻ ጠቃሚነቱን’ ስለማብሰራቸው…የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኛው ‘ንጽህናው ያልተጠበቀ አካባቢ ለበሽታ እንደሚዳርግ ማስተማሩን’…ምናምን ሆነና “ከዚህስ እንትና እኮ የእንትናን ሚስት መኪናዋን ሁሉ እስክትሸጥ ድረስ በፍቅር አንሳፈፋት…” አይነት ወሬ ዞርና! ሀሳብ አለን…የናፈቁን የዜና አይነቶች ስላሉ በስፖንሰርም ድጋፍ ቢሆንም ይተላለፉልንማ! (መቼም ዘንድሮ ስፖንሰር ከተገኘ ምንም ነገር የሚሆንባት አገር ሆናላችኋለች!)እናላችሁ…ደህና ወሬ መስማት የሚፈልገው የሰውነታችን ክፍል ባትሪ ሳይደክምብን አልቀረም፡፡ “ምን አዲስ ነገር አለ?” የምንባባለው እኮ “ወደቀ፣ ተሰበረ” አይነት ርዕሰ ዜናዎች መስማት በጣም ስለተላመድን  “ተኝተን እስክንነሳ ማን ምን ሆኖ ይሆን?” የሚለውን ለማረጋገጥ ነው፡፡ በቃ… አገር እንዲህ ሲሆንስ! ስሙኝማ…ዘንድሮ ‘ኔጌቲቭ’ የሆኑ ዜናዎች አልበዙባችሁም…ስለ መከደዳት፣ ስለ መካሰስ፣ ስለ መሸዋወድ፣ ስለ መነጣጠቅ…ብቻ የምትሰሙት ነገር ሁሉ ጭለማ አይነት ነገር ነው፡፡ ይሄ… አለ አይደል… ‘እርስ በእርሱ የሚተሳሰበው’… ‘የምሽት እንግዳን እግር አጥቦ መኝታና ምግብ የሚሰጠውን’…  ‘አንዲት እንጀራ እንኳን ብትተርፈው ከሦስት ጎረቤቶቹ ጋር ተካፍሎ የሚቃመሰውን’ ህዝብ ወዴት ሄዶ ነው እኛን የምንመስል ጄኔሬሽኖች የመጣነው ያሰኛል፡፡ የምር እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…“ይሄን ያህል ጭልም ያለ ነገር የሰፈረብን ለምንድነው?” አትሉም! ሁሉንም ነገር ገና በሚገባ መርምረን ሳናውቀው በአሉታዊ የምናየው ለምን እንደሆነ አይገርማችሁም! እናላችሁ…‘ቻርጅ’ መደረግ ያለባቸው ብዙ የደከሙ ባትሪዎች፡፡ ነገሮችን በአዎንታዊ ዓይንና “ሊሆን ይችላል…” በሚል አይነት የማየት ባትሪያችን ደክሞብናል፡፡ የአእምሯችን ‘አዎንታዊ ሴሎች’ ያሉበት ቦታ ‘ቻርጅ’ የሚደረጉበት ዘዴ ይፈጠርልንማ! በተለያዩ ቦታዎች ስትሄዱ ነገሬ ብላችሁልኝ እንደሆነ በየማግስቱ በየግድግዳው ላይ የሚለጠፈው ህግ ብዛት! እኔ የምለው…አንዳንዱ መሥሪያ ቤት “እንዲህ ማድረግ ክልክል ነው…” “በእንዲሀ አይነት ቀናት ውስጥ ያለብህን ፍራንክ ቁጭ ባታደርግ…” ውርድ ከራሳችን አይነት ጡንቻ ለማሳየት የሚጣደፉትን ያህል “ለመላ ሠራተኛው የአራት ወር ደሞዝ በቦነስ ይሰጣል…” “ጤፍ ለሚፈልጉ ሠራተኞች መሥሪያ ቤቱ የዋጋውን ስድሳ በመቶ እርዳታ ያደርጋል…” አይነት ‘በምድር የሚያስመሰግን፣ በሰማይ ቤት የሚያስቀድስ’ ነገር ለማደረግ የማይጣደፉትሳ!የምር እኮ፣ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… የብዙ ነገሮች ባትሪዎቻችን ደክመዋል፣ የባሰባቸው ደግሞ ጭርሱን አብቅቶላቸዋል፡፡ታዲያማ…‘ቀይ ባለስልጣን’  ወይም ‘አረንጓዴ ቦተሊከኛ’ ድንበራችንን አልፎ ሲገባ “እንዲህማ ልታደርጉኝ አትችሉም…”  የምንልበት ባትሪ አልቆብናል፡፡ እንደ ውሳኔዎች ብዛት የሚወስኑብን ሲበዙ “ኧረ በዛ፣ በዛ…” የምንልበት “ያልተጻፈ ህግ ለእኔ ብቻ ልታወጣ አትችልም…” የምንልበት   “ስልጣን ማገልገያ እንጂ መበቀያ አይደለም…” የምንልበት ባትሪያችን ስለ ደከመ ‘ቻርጅ’ ይደረግልንማ፡፡ ስሙኝማ…አንድ አነስ ያለች ሱቅ ላይ “ሞባይል ቻርጅ እናደርጋለን…” የሚል ማስታወቂያ አለ፡፡ ከዚህ ጽሁፍ በላይ ምን ይል መሰላችሁ… “ሁሉም ነገር ቻርጅ እናደርጋለን፡፡” ይህኛው ምን ማለት እንደሆነ ባይገባንም ያጣነው ሁሉንም ‘ቻርጅ’ የሚያደርግልን ነው፡፡(ጠረጴዛ ላይ ያለው ሳህናችን ባዶ ቢሆንም ጣራ ላይ ያለው ዲሻችን በፒሳ ማስታወቂያ ስለሚያጠግበን ዕድለኞች ነን!)እኔ የምለው…ይቺ ሳንዲ የሚሏት ‘የተፈጥሮ ቁጣ’ በጥብጣ ኤሌክትሪክ የጠፋባቸው ጊዜ ሞባይላቸውንና ላፕቶፖቻቸውን ቻርጅ ማድረጊያ ልዩ ድንኳኖች መዘጋጀታቸው…“አይ አገር፣ አይ አገር…” አላሰኛችሁም! ይቺን ሰሞንማ ይሄንን ክፉ ነጋሪዎች  ሪሞት ኮንቶሮላችሁን እነሱ ናቸው የያዙት የሚላቸውን ምርጫ ዘመቻ ስናይ የምር ሆድ ባሰን፡፡ የምር…በየ‘ኢሌክሽኑ’ ጊዜ ብቅ የሚሉትን ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች’ የረጅም ጊዜ እረፍት ሰጥተናቸው… “መቼ ነው እኛም እንዲህ አይነት ደረጃ ላይ የምንደርሰው?” አያሰኛችሁም! እንዴት ሰነበታችሁሳ!

Read 3707 times