Saturday, 10 November 2012 15:10

ማሸነፍም መሸነፍም እንደ አሜሪካ ምርጫ!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(6 votes)

የኦባማ ማሸነፍና የኢህአዴግ 1ለ5 ስትራቴጂ ሚስታቸውን የሚወዱ መሪዎች እንፈልጋለን!በምርጫ 99 በመቶ ማሸነፍ ከመሸነፍ እኩል ነው!ከሁሉም በፊት መወያየት ያለብን የኢቴቪ ደባል ሆኖ ስለገባው የቻይና ኮሙኒስት መንግስት የቴሊቪዥን ጣቢያ /ሲሲቲቪ/ ነው፡፡ እንዴ --- እኔ እኮ እንዲህ አልመሰለኝም ነበር፡፡ ባለፈው ሰሞን  የቻይና ቴሊቪዥን ሃላፊዎች ከኢቴቪ ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት መፈራረማቸውን ስሰማ ትከሻዬን የከበደኝ ለካ ለዚህ ነው፡፡ በቃ ደስ አላለኝም ነበር፡፡ እናንተ ነገሩ ቀልድ እንዳይመስላችሁ - ቻይና በአጭር ጊዜ ውስጥ አፍሪካን በሙሉ ኮሙኒስት ካላደረገች ታዘቡኝ፡፡ አረ አያያዟ አያምርም! ኢህአዴግማ ደስታው ነው - በሰበቡ የኮሙኒስትነት አራራውን ይወጣብናል! /እንኳን ዘንቦብሽ --/  እኔ ግን ተናግሬአለሁ---አንድ ቀን አማን ነው ብለን ከእንቅልፋችን ስንነሳ እቺ ምስኪን አገር ኮሙኒስት ሆና እንዳትጠብቀን፡፡

የኢህአዴግን ባህል የማያውቁ የዋህ ዜጎች “እንዴ እኛ ሳንፈቅድ?” ሊሉ እንደሚችሉ እገምታለሁ /ሰውየው “ሚስትህ አረገዘች ወይ?” ቢሉት “ማንን ወንድ ብላ” አለ!/ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የአሁኑ የተቃዋሚ ፓርቲ ሊ/መንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ያሉትን አልሰማችሁም? “ኢህአዴግ አስር ዓመት ሙሉ ሶሻሊስት ነኝ ሲል ቆይቶ ድንገት ተነስቶ “ነጭ ካፒታሊዝም” ተከታይ ነኝ አለኝ” ብለው ክህደት እንደተፈፀመባቸው ተናግረዋል እኮ፡፡ ስለዚህ እንደሳቸው “ሰርፕራይዝድ” እንዳትሆኑ! ወዳጆቼ--- የስነልቦና ዝግጅት ማድረግ እኮ ቀላል በረከት አይደለም፡፡ እንደው ሌላው ቢቀር ድንገት ፌንት ከማድረግ ይታደጋል፡፡ እኔ የምለው--- ባለፈው ሳምንት ሲሲቲቪ በኢቴቪ ያሰራጨውን ዜና ሰማችሁልኝ? አንደኛው የቻይና ዳያስፖራዎች ወደ አገራቸው እየተመለሱ ነው የሚል ነበር፡፡ ሁለተኛው ዜና ደግሞ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ 18ኛ ጉባኤውን እያካሄደ መሆኑን የሚገልፅ ነው፡፡ ባይገርማችሁ ---- ሁሉ ነገሩ ከኢህአዴግ ጉባኤ ጋር አንድ እኮ ነው /ማን ይሆን የኮረጀው?/ ወደ ሌላ አጀንዳ ከማለፌ በፊት አንድ ጥያቄ ጣል ላድርግ - የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን አሁንም የህዝብ ንብረት ነው ወይስ ---? /ለጠቅላላ እውቀት ያህል ነው!/  አሁን ወደ ዋናው ወጋችን መግባት እንችላለን፡፡ የዛሬ ወጌን የምጀምረው “ኮንግራ” ብዬ ነው - ኦባማ ዳግም በማሸነፋቸው! (ምርጫው ጦቢያ ቢሆን ኖሮ “ኮንግራ”ም አይቻልም ነበር) በነገራችሁ ላይ እኔ እኮ ኦባማን እንጂ ፓርቲያቸውን ብዙም አልወደውም (መለስን እንጂ ኢህአዴግን ብዙም እንደማልወደው ማለት ነው) እኔ የምለው --- የኦባማ ፓርቲ ምን ልሁን ብሎ ነው ምልክቱን “አህያ” ያደረገው? /ምልክትስ ማለት ንብ ነው!/ እነዚህ አሜሪካኖች ግን የምርጫ ምልክት መምረጥ አያውቁበትም፡፡ የሪፐብሊካኖች  ምልክትም እኮ “ዝሆን” ነው /የባሰ አለና አገርህን አትልቀቅ!/  ትዝ ይላችኋል--- እዚህ አገር  አንዷ የግል ተወዳዳሪ  “ምልክቴ ኮንዶም ነው” ብላ ነበር /የዲኬቲ ማስታወቂያ አስመሰለችው እኮ!/ ለነገሩ ኦባማ ምልክታቸው ምንም ይሁን ምን ምርጫውን በድል ተወጥተዋል፡፡ ደጋፊዎቻቸው በትዊተር ላይ Four more years in the White House! በማለት በኦባማ መመረጥ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀውላቸዋል፡፡ ወይ አሜሪካ! ተዓምረኛ አገር እኮ ናት! የዛሬ አራት ዓመት ጥቁር ተመረጠ ተብሎ ጉድ ተባለ! አሁን ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ጥቁር ተመረጠና ለሁለተኛ ጊዜ ጉድ እየተባለ ነው፡፡ ባለዝሆን ምልክቱ ሮምኒም “ለዛሬ አልተሳካልዎትም” ተብለው ተሸኝተዋል፡፡ ደግነቱ እሳቸውም ሽንፈታቸውን በፀጋ ተቀብለዋል፡፡ ደስ የሚለው ደግሞ እንደኛ ፖለቲከኞች ተጭበረበረ ብለው አልተነጫነጩም፡፡ /ሳይጭበረበር?/ ምን እንደናፈቀኝ ታውቃላችሁ? ልክ እንደሰሞኑ የአሜሪካ ምርጫ አንዳች ኮሽታ ሳይሰማ በጦቢያ ምድር ምርጫ ሲካሄድ ማየት! /ሲያምርህ ይቅር እንዳትሉኝ!/  እኔ የምለው ግን --- ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ያን ያህል ከባድ ነው እንዴ? /ቁርጠኝነቱ ካለ እኮ ይቻላል/ ዋናው ችግር ምን መሰላችሁ? ሁሉም ተፎካካሪ ገና የምርጫ ውድድር ሳይጀመር የአራት ኪሎን ቤተመንግስት ብቻ እያለመ እኮ ነው! /ስልጣን መመኘት ኀጢያት ነው አልወጣኝም!/ ግን ደግሞ ፕላን “ኤ” እና ፕላን “ቢ” ሲኖር ጥሩ ነው፡፡ አያችሁ --- በቅድመ-ምርጫ “ካላሸነፍኩ ሞቼ እገኛለሁ” ተብሎ ወደ ውድድር ሜዳው ሲገባ በድህረ- ምርጫ ቀውጢ ይፈጠራል፡፡ እንዴ ውጤቱን የሚወስነው እኮ እልህ ሳይሆን “የድምፅ ሳጥን (Ballot)” ብቻ ነው! እናም---  ሮምኒ ዘንድሮ እንዳልተሳካላቸው ሲያውቁ ምን አደረጉ መሰላችሁ? ቶሎ ብለው ስልክ መቱ - ወደ ዋይት ሃውስ፤ ኦባማ ጋ፡፡ ሊሳደቡ፣ ሊያስፈራሩ ወይም ሊያስጠነቅቁ እንዳይመስላችሁ - እሳቸው እቴ! “Congra!” ለማለት ነው እንጂ! “ሚ/ር ፕሬዚዳንት እንኳን ደስ ያለዎት፤ God bless America!” አሉና ስልካቸውን ጠረቀሙ፡፡ ከዚያ በኋላ የሆኑትን የሚያውቁት ፈጣሪና ራሳቸው ሮምኒ ብቻ ናቸው፡፡ ይሄ ማለት ግን አልበሸቁም ወይም አልተንጨረጨሩም ማለት አይደለም፡፡ (እንዴት አይበሽቁ!) ግን ደግሞ እንደ ጦቢያ ፖለቲከኞች እድሜ ልካቸውን ሲበሽቁ ሲቃጠሉ አይኖሩም፡፡ ደግሞም ለአገራቸው ለመስራት የግድ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆን እንደሌለባቸው አሳምረው ያውቃሉ (ቢመረጡ እኮ እሰየው ነበር!) ግን ደግሞ ህዝብ ካልመረጣቸው አልመረጣቸውም ነው፡፡ የአሜሪካና የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ልዩነት እዚህ ጋ ነው፡፡ የአሜሪካዎቹ ህዝብ ሳይመርጣቸው ሲቀር ውሳኔውን ያከብሩለታል፡፡ ሲመርጣቸውም እንዲሁ፡፡ (እንደኛ ቂም መያያዝ የለም!) This is America! ለነገሩ  ሮምኒ ኦባማ ጋ ደውለው “Congra!” ከማለት ውጭ ሌላ ምርጫም የላቸውም ነበር፡፡ እኛ ጋ ግን ብዙ ምርጫ አለን፡፡ ከፈለግን የጐዳና ላይ ነውጥ፤ ከፈለግን ፖለቲከኞችን ሰብስቦ ወህኒ ቤት መክተት፡፡ ከፈለግን ፀረ-ልማትና ፀረ-ሰላም ብለን መፈረጅ ሁሉ መብታችን ነው፡፡ ለምን መሰላችሁ? This is Ethiopia! /ማን ነበር “አገርህ ናት በቃ” ያለው ገጣሚ?/ አያችሁ … ሮምኒ ባይደውሉ፣ ወይም ሊነጫነጩ ቢሞክሩ የአሜሪካ ህዝብ አይምራቸውም … “አፋራም” ይላቸዋል (ወይም ፋራ!) ይሄን ደግሞ ሮምኒ አይፈልጉትም፡፡ አሜሪካውያንም አይፈቅዱትም፡፡ /መታደል እንጂ መታገል አያስፈልግም/ ኦባማም እኮ ዳግም መመረጣቸው ይፋ ከሆነ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ ሮምኒን እና ፓርቲያቸውን አመስግነዋል (ያሸነፈው የተሸነፈውን ሲያመሰግን አልታያችሁም!) በአሜሪካ ግን ይሄም ይቻላል፡፡ አንዴ ሳይሆን በተደጋጋሚ አይተናል፤ ሰምተናል፡፡ (That’s America ብለናል በሆዳችን!) “ከሮምኒ ጋር አውርቼአለሁ፡፡ በምርጫ ዘመቻው ላደረጉት እልህ አስጨራሽ የምረጡኝ ዘመቻ አመስግኜአቸዋለሁ፤ ክፉኛ ታግለንና ተፋጭተን ሊሆን ይችላል፡፡ ያንን ያደረግነው ግን እቺን አገር በጣም ስለምንወዳትና ለመጪው ጊዜዋም በጣም ስለምንጨነቅ ነው” ይሄን ያሉት ኦባማ ናቸው! /ምነው ኢህአዴግ ያለው ቢሆን!/ አያችሁ--- እዚያ እንደኛ አገር ለሥልጣን መፎካከር በጠላትነት አያፈራርጅም፡፡ ፀረ ሰላም፣ ፀረ ልማት፣ ፀረ አገር፣ ፀረ ወዘተ… አያስብልም፡፡ “የተፎካከርነው፤ ክፉኛ የተፋጨነው አገራችንን ስለምንወዳት ነው” በቃ ይሄን ነው ያሉት ኦባማ፡፡ ምናልባት ይሄ እንዴት ተቻለ ትሉ ይሆናል፡፡ መልሱ ቀላል ነው - አገሪቷ አሜሪካ ናታ! (ኢትዮጵያ አሜሪካን መሆን አለባት አልወጣኝም!) ለነገሩ ብልም እኮ አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ናት፤ አሜሪካም አሜሪካ፡፡ ኦባማ በንግግራቸው መጀመሪያ ያመሰገኑት ህዝባቸውን ነው - አሜሪካውያንን!! Thank you. Thank you. Thank you so much - በማለት፡፡ ግን የመረጣቸውን ብቻ አይደለም፡፡ በኢህአዴግ ቋንቋ በድምፁ የቀጣቸውንም ጭምር አመስግነዋል - “የኦባማንም ሆነ የሮምኒን ምልክት የያዛችሁ ድምፃችሁ ተሰምቷል” ብለዋል - ኦባማ፡፡ እዚያ ሁለት ዓይነት ህዝብ የለማ! (ልማታዊና ኪራይ ሰብሳቢ!) በቃ ህዝብ ህዝብ ነው፡፡ የኦባማን ዲሞክራት ፓርቲ የመረጠም ሆነ የሮሚን ሪፐብሊካን የመረጠ ለውጥ የለውም፡፡ ዲሞክራሲ ማለት ይኼው አይደለ!! በነገራችሁ ላይ እኚህ ኦባማ በአደባባይ ሚስታቸውን እንደሚወዱም ተናግረዋል፡፡ “አንቺ ባትኖሪ ኖሮ የዛሬውን ኦባማ አልሆንም ነበር” ሲሉ ባለቤታቸውን ሚሼልን አድንቀዋል፤ አሞግሰዋል፡፡ የአሜሪካ ህዝብ ሚስታቸውን ስለወደደላቸውም “ኮርቼብሻለሁ” ብለዋል፡፡ ሁለቱ ሴት ልጆቻቸው ሳሻና ማሊያም “እኮራባችኋለሁ!” ተብለዋል - በአባታቸው በኦባማ፡፡ እኔ የምለው ግን … የእኛ መሪዎች ሚስታቸውንና ልጆቻቸውን እንደሚወዱ ነግረውን ያውቃሉ እንዴ? (ኧረ በፍፁም!) የኢህአዴግም የተቃዋሚዎችም መሪዎች እኮ ስለሚስት፣ ስለልጆችና ስለቤተሰብ ትንፍሽ ብለው አያውቁም! (ያፍራሉ እንዴ?)  (እውነቴን እኮ ነው እንዲህ እንደ ኦባማ የትዳር አጋራቸውን እንደሚያፈቅሩና እንደሚያከብሩ፤ ለስኬታቸውም ትልቅ ሚና እንዳላት ቢነግሩን ቀላል ነገር አይመስለኝም፡፡ ቀላል ቢሆንማ አዳሜ ዝም አይልም ነበር፡፡ ወይስ የወንድ ትምክተኝነት ገና አለቀቀንም? (የሥልጣኔ ችግር ይመስለኛል!) አንድ ሃሳብ አለኝ - ማንኛውም የመንግስት ባለስልጣንም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ሚስቱን፣ ልጆቹንና ቤተሰቦቹን እንደሚወድ ለህዝብ እንዲገልፅ የሚያስገድድ ህግና ደንብ ቢወጣስ? (ፍቅር በግዳጅ በሉት!) ነገሩ ቀላል እኮ ነው፡፡ የመንግስት ባለሥልጣናት ሃብታቸውን እንደሚያስመዘግቡት ሁሉ ፍቅራቸውንም ያስመዘግባሉ ማለት ነው - ሌላ ጣጣ ፈንጣጣ የለውም (የፓርቲያችን ባህል አይፈቅድም የሚሉ ባህላቸውን ይለውጡ!) በነገራችሁ ላይ ኦባማ ያሸነፉት ዝም ብሎ በዕድል እንዳይመስላችሁ - ብዙ ታትረውና ተግተው ነው፡፡ ስንት ተናግረውና አሳምነው መሰላችሁ ያሸነፉት፡፡ መቼም ስንት ሺ የምርጫ ሰራዊት እንዳሳለፉ ሳትሰሙ አትቀሩም (ኢህአዴግ የልማት ሰራዊት፣ የጤና ሰራዊት፣ የንግድ ሰራዊት፣ የጥበብ ሰራዊት፣ ወዘተ እንደሚለው) ቢቢሲ ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ፤ በኦሃዮ ግዛት ብቻ ለኦባማ የሚቀሰቅሱ 32ሺ854 የበጐ ፈቃድ አገልጋዮች ነበሩ - በሦስት ሰዓት ሽፍት የሚሰሩ፡፡ የምርጫው ዕለት ደግሞ የኢህአዴግን 1ለ5 የሚመስል ስትራቴጂ ተጠቅመዋል ተብሏል፡፡ ኦባማ ወይም ፓርቲያቸው ግን አይደለም፡፡ ራሱ ህዝቡ ነው - መራጩ! ቀደም ብለው ድምፃቸውን የሰጡ የኦባማ ደጋፊዎች አምስት አምስት ባልንጀሮቻቸውን እጃቸውን ይዘው ወደ ድምፅ መስጪያ ጣቢያ እንደወሰዱ ነው ቢቢሲ የዘገበው፡፡ በኢህአዴግ “ጥርነፋ” እንደሚባለው ግን እንዳይመስላችሁ (ኧረ አይገናኝም!) ኦባማን እየደገፉ ነገር ግን ወደ ምርጫ ጣቢያው ለመሄድ የሰነፉ አሜሪካውያንን እንዲመርጡ የማድረግ ማግባባት እንጂ ሌላ ማስገደድ የለውም (ኢህአዴግ ያስገድዳል አልወጣኝም!) በ2002 ምርጫ ኢህአዴግ እንዳደረገው ቤት ለቤት እያንኳኩ ለምርጫ ማትጋትም ይቻላል፡፡ በስልክም እንዲሁ፡፡ (ቡናና ፈንዲሻ ብቻ ነው የቀረው!) እንዲያም ሆኖ ግን ኦባማ ተፎካካሪያቸውን በ99 ነጥብ ምናምን አልዘረሯቸውም፡፡ (ኢህአዴግ በ2002 ምርጫ እንዳሸነፈው!) ለነገሩ በእንዲህ ያለ ከፍተኛ ልዩነት ማሸነፍ እንኳን በአሜሪካ በሌላውም ዓለም ፋሽኑ አልፎበታል - የፋራ ነው እየተባለ ነው! (ብቻ ፉገራ እንዳይሆን!) አንዴ በአልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ የቀረቡ አሜሪካዊ የፖለቲካ ምሁር፤ የ2002 የአራችንን ምርጫ አንስተው ኢህአዴግን ሲተቹት ሰምቼ ግርም አለኝ (“ቅ” መሆን አለባት ብያለሁ - በሆዴ!) በእንዲህ ዓይነት ሰፊ ልዩነት የሚያሸንፉት አምባገነን መንግስታት ናቸው አሉና እነ ዚምባቡዌን መጥራት ጀመሩ፡፡ ከዚህ በላይ መታገስ ስላቃተኝ አልጀዚራን አጥፍቼ የሆሊውድን ፊልም መኮምኮም ጀመርኩኝ (ለምን ልቃጠል!) ለነገሩ እኮ ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን በዝረራ በማሸነፉ ተጐዳ እንጂ አልተጠቀመም እኮ! አንደኛ ተቃዋሚዎች “አጭበርብሮናል” ብለው “ስመጥሩውን” ፓርቲ አሳጥተውታል፡፡ ሁለተኛ ፓርላማው በኢህአዴጋውያን ብቻ ተሞልቶ ፍዝዝ ድንግዝ ብሏል፡፡ ሦስተኛ ደግሞ “የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል” ለሚለው የተቃዋሚዎች ክስ ጥሩ ማስረጃ ሆናቸው፡፡ ስለዚህ 99 በመቶ ማሸነፍ ከመሸነፍ እኩል ነው ቢባል ያስኬዳል፡፡ ለምን መሰላችሁ? 99 በመቶ ማሸነፍ እኮ አንድም ተቃዋሚ በምርጫው አልተሳተፈም ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ አንድም ሰው በኢህአዴግ ኩርፊያም ሆነ ቅሬታ የለውም እንደማለት ነው፡፡ ይሄ ደግም ከእውነታው የተፋታ ይመስላል፡፡ ህዝቡ ኩርፊያ ባይኖረውም እንኳ ኢህአዴግ በግድ ማስኮረፉ አይቀርም እኮ (ነገረኛ ነው ማለቴ ግን አይደለም!) በቃ ልማታዊ ኪራይ ሰብሳቢ፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ኒዮሊበራሊስት፤ የሰላም ሃይሎች የጥፋት ሃይሎች ወዘተ እያለ ህዝቡን በጐራ መክፈል አመል ስለሆነበት ሁሌም የሚያኮርፍ አይጠፋም፡፡ እናላችሁ … ይሄን አመሉን እርግፍ አድርጐ ካልተወ፣ 99 በመቶ አሸነፍኩ ቢል ጥርጣሬ ውስጥ መግባቱ አይቀርም፡፡ እኔ የምለው ግን … ኢህአዴግ በራሱ ከተማመነ ለምን የፖለቲካ ሜዳውን ለተቃዋሚዎች በሰፊው አይለቅላቸውም (ፆሙን ያደረ ሜዳ ሞልቶ የለም እንዴ?)እኔ የምለው ግን ኦባማ የፈለገ ህዝብ ቢወዳቸው አራት ዓመታቸውን ሲጨርሱ ዋይት ሃውስን ለቀው መውጣት አይቀርላቸውም አይደል … (ወደው ነው!) ያልጨረስኩት ልማት አለ … መንገድ … ኮንዶሚኒየም … ግድብ መገንባት ይቀረኛል ቢሉ ማንም የሚሰማቸው የለም፡፡ ለምን ቢባል … አዲሱ መሪ ይጨርሰዋላ! እንዲህ ያለው ምክንያት የሚሰራው ምናልባት ለልማታዊ መንግስት ብቻ ሳይሆን አይቀርም - ትኩረቱ ልማት ነዋ! ኢህአዴግ አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ለማሰለፍ የ40 ዓመት ሥልጣን ያስፈልገኛል አላለም? ወይም ሃሳቡን ቀይሯል?  የዛሬ ፖለቲካዊ ወጌን የምቋጨው ኦባማ ከተፎካካሪያቸዉ ጋር ስለሚኖራቸው ቀጣይ ግንኙነት በተናገሯት ዓረፍተ ነገር ነው፤ “በቀጣዩቹ ሳምንታት ከሮምኒ ጋር ተቀምጠን እቺን አገር ወደፊት ለማራመድ በምንችልባቸው ጉዳዮች ላይ ለመመካከር በተስፋ እጠብቃለሁ” (እርግጠኛ ነኝ ለአፋቸው ያህል አይደለም!)

Read 3763 times