Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 10 November 2012 15:24

ጃኪ ቻን ለልጁ ቤሳቤስቲን እንደማያወርስ ተናገረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

‹‹ጎበዝ ከሆነ የራሱን ሃብት ያፈራል›› ብሏልዝነኛው የሆሊውድ ተዋናይ ጃኪ ቻን ለብቸኛ ልጁ ለጄይስ ቤሳቤስቲን እንደማያወርስ መናገሩን ‹‹ሰለብርቲ ኔትዎርዝ›› ዘገበ፡፡ ከአባቱ ጋር የተቀማጠለ ኑሮ እየመራ የሚገኘው የ30 ዓመቱ ጄይሲ፤ ድምፃዊና ተዋናይ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም ሊሳካለት አልቻለም ተብሏል፡፡ ሆኖም አባቱ በህይወት ዘመኑ ያፈራውን 130 ሚ. ዶላር የሚገመት ሃብት ሲሞት መቶ በመቶ ለበጎ አድራጎት እንደሚለግስ ገልጿል፡፡ ሰሞኑን በቤጂንግ የተዘጋጀለትን ልዩ ሽልማት ሲቀበል ንግግር ያደረገው ጃኪ ቻን፤ ለልጁ ቤሳቤስቲን እንደማያወርስ ያስታወቀ ሲሆን ቀደም ሲል ከሃብቱ ግማሹን ለበጎ አድራጎት፣ ግማሹን ደግሞ ለቤተሰቡ ለማውረስ የነበረውን እቅድ መሰረዙን ገልጿል፡፡

‹‹ልጄ ጎበዝ ከሆነ በሙያው የራሱን ሃብት ያፈራል፤ ካልሆነ ግን የእኔን ገንዘብ እንደ ቀልድ ማባከን የለበትም›› ያለው የ58 ዓመቱ ጃኪ ቻን ፤ ልጄ በውትድርና ሰልጥኖ ከፍተኛ  የህይወት ልምድ እንዲያገኝ ባለማድረጌ ቆጭቶኛል ብሏል፡፡ የጃኪ ቻን ብቸኛ ልጅ  ጄይሲ እ.ኤ.አ ከ2004 ዓ.ም ወዲህ ከ20 በላይ ፊልሞች ቢሰራም በገቢም ሆነ በትወና አልተሳካለትም፡፡ ዘንድሮ ‹‹ደብል ትራብል› የሚል ፊልም ሰርቶ 9ሺ ዶላር ብቻ በማስገባት፣ በቦክስ ኦፊስ  ታሪክ የመጨረሻውን አነስተኛ ገቢ እንዳስመዘገበ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አባት እና ልጅ  ከሁለት ዓመት በፊት “1911” በሚል ፊልም በጋራ ቢተውኑም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ እንደ ጃኪ ቻን ሁሉ በህይወት ዘመናቸው ያፈሩትን ሃብት ሙሉ በሙሉ ለበጎ  አድራጎት ለመስጠት  ቃል ከገቡ ታዋቂ የአለማችን ሰዎች መካከል ቢሊዬነሮቹ ዋረን በፌት እና ቢል ጌትስ ይገኙበታል፡፡ እነዚሁ ቢሊዬነሮች ሃብታቸውን ለበጎ አድራጎት እንደሚሰጡ ከመግለፃቸውም ባሻገር ሌሎች ሃብታሞችም የእነሱን ፈለግ እንዲከተሉ እየወተወቱ ነው፡፡ይህ በዚህ እንዳለ ጃኪ ቻን በፀሃፊነት፣ በዲያሬክተርነትና በፕሮዱዩሰርነት የሰራው “ቻይኒዝ ዞድያክ” የተባለ ፊልም ከወር በኋላ ለእይታ የሚበቃ ሲሆን፤ ፊልሙ የመጨረሻ የአክሽን ፊልም ስራው እንደሆነና  ከአሁን በኋላ በሌሎች የፊልም ዘውጎች ለመስራት እንደሚፈልግ ጃኪ ቻን ተናግሯል፡፡

Read 3632 times