Print this page
Saturday, 17 November 2012 10:58

ለትምህርት ስርዓታችን ህልውና ከፖለቲካዊ ብልጠት ይልቅ ብልህነት ያሻል

Written by  የተከበሩ አቶ ሙሼ ሰሙ
Rate this item
(15 votes)

ትምህርት ዜጎችን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ በመቅረጽ ለራሳቸው፣ ለማህበረሰባቸውና ለሃገራቸው ጠቃሚ ዜጋ እንዲሆኑ የሚያግዝ የእውቀት ማሸጋገርያ ስልት ነው፡፡ የትምህርት መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ መጣል ከጀመረ ከመቶ ዓመታት በላይ የተቆጠረ ሲሆን ከሁለተኛው አለም ጦርነት በፊት ትምህርት የሚሰጠው በመንግስትና በሃይማኖት ተቋማት ዙርያ ለአስተዳደራዊ ክህሎት፣ ለቀኖናና ለሃይማኖት እውቀት ሲባል እንደነበረ እ.ኤ.አ 2004 ላይ ዮኔስኮ የትምህርት ስርዓትን አስመልክቶ ባዘጋጀው ኮንፍረንስ ላይ የወጡ ዘገባዎች ይገልጻሉ፡፡ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የአፄ ሃይለ ስላሴ ስርዓት ዘመናዊ ትምህርትን በተደራጀ መልኩ በትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲሰጡ ሁኔታዎችን ያመቻቸ ቢሆንም የትምህርት ቤቶች እድገት ከማህበረሰቡም ሆነ ከሃይማኖት ተቋማት በገጠመው ተጽእኖ ምክንያት የመስፋፋቱ እድል አዝጋሚ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የትምህርት ስርዓቱን ለማሻሻል የተደረጉ ተከታታይ ጥረቶችም በወቅቱ ከተከሰተው ኢኮኖሚያዊ ቀውስና ድርቅ ጋር ተዳብለው ለአፄው ስርዓት ውድቀት ምክንያት ሊሆን ችሏል፡፡

ለደርግ በወቅቱ የነበረው አጣዳፊ ጉዳይ አብዮቱ በመሆኑ በመማርና ማስተማር ላይ የነበሩትን መምህራንና ተማሪዎች በነቂስ አሰልፎ አብዮቱን ለማስተዋወቅ በሚል ሰበብ ወደ እድገት በሕብረት የዕውቅትና የስራ ዘመቻ አዘመተ፡፡ ከብዙ ጥረት በኋላ እራሱን በጥቂቱም ቢሆን ማጎልበት የጀመረው የትምህርት ስርዓት ከባድ ፈተና ውስጥ ወደቀ፡፡ ከየመንግስት መስርያ ቤቱና ተቋማቱ ሁሉም ዓይነት ባለሙያዎች በወረንጦ እየተለቀሙ የማስተማር ሂደቱን በግድ እንዲቀላቀሉ ተደረገ፡፡ እዚህ ላይ የመምህርነትን ሙያ በፍቅር ሳይሆን በተጽእኖ እንዲቀበሉ የተገደዱ ግለሰቦች ምን ዓይነት ትውልድ ሊቀርጹ እንደሚችሉ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
አብዮቱን ለማስተዋወቅ በሚለው መፈክር ስር ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ ከተመሙት መምህራንና ተማሪዎች መካከል በርካታዎቹ በማያውቁት ሃገርና መሬት ላይ የበሽታና የተፈጥሮ ቁጣ ሰለባ ሆነው እንደወጡ፣ በዛው ቀሩ፡፡
ከተረፉትም መካከል በቁጥር ቀላል የማይባሉት ዘማቾች በሁለት ጎራ ተከፍለው በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር መፈክር ስር ተዋደቁ፡፡ በአጠቃላይ በርካታ መምህራን እውቀታቸውንና የአሰራር ክህሎታቸውን ለትውልድ ሳያስተላልፉ በየጫካውና በየጥሻው ወደቁ፣ ቀሪዎቹም ተስፋ ቆርጠው ተሰደዱ፡፡
ከጥቂት ዓመት የዘመቻ ውጣ ውረድ በኋላ በነፍስ ተርፈው የተመለሱት ተማሪዎችና መምህራን የመማር ማስተማር ሂደቱን ሲቀላቀሉ ትምህርት ቤቶችና ክፍሎቻቸው በአዲሱ ትውልድ ተሞልተውና በእጅጉ ተጨናንቀው ጠበቋቸው፡፡ በማያባራ ዘመቻ፣ ግድያ፣ አፈናና ጦርነት ተተብትቦ እራሱን ፋታ የተነሳው ደርግ፤ በቂ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባትና መምህራንን ለማብቃት ጊዜ አልነበረውም፡፡ በዚህም ምክንያት መምህር አልነበሩም፡፡ ትምህርት ቤቶችና ለመማር ማስተማር ሂደቱ በሚያስፈልጉ ግብአቶችና ቁሳቁሶች አልተሟሉም፡፡ የትምህርት ስርዓቱ በአጠቃላይ እርቃኑን እንደቀረ ነበር፡፡ ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓተ ውድቀት አንድ ተብሎ ተጀመረ፡፡
የትምህርትና የእውቀት ዓምድ የሆኑት ክህሎት፣ ጥራት፣ ብቃትና በራስ መተማመን ለብዛትና ለይድረስ ይድረስ ዘመቻ ዋጋ እንዲከፍሉ ተፈረደባቸው፡፡ ተማሪዎች በእውቀት ይበለጽጉና በክህሎት ይዳብሩ ዘንድ በትምህርት ቤት ውስጥ ማሳለፍ የሚገባቸው የትምህርት ሰዓት ቢታወቅም የትምህርት ሰዓቱ በግማሽ ተቀንሶ ተማሪዎች በሶስት ሽፍት እንዲማሩ ተወሰነ፡፡ የቤተ ሙከራ፣ የመስክና የላይብራሪ ሰዓቶች እንደዋዛ እየታጠፉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በሶስት ዓመት እንዲያጠናቅቁ ተደረገ፡፡ ራስ ሳይጠና ጉተና እንዲሉ የአዲሱ ትውልድ አካል የሆነውን ተማሪ የሚፈጥረው መምህር በጫና፣ በውክቢያና በለብ ለብ የመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ተረግዞ፣ ተጸንሶ፣ ተወለደ፡፡ በዚህ መልኩ የተቀረጹት መምህራንም ሆነ ተማሪዎች በአጠቃላይ የትምህርት ስርዓቱ፣ የእውቀትና የፈጠራ መለኪያ ሆኑ፡፡
“ መማር መብት ነው፡፡” የሚለው ደርግ፤ መማር መብት መሆኑን ከመረጋገጡ በፊት የትምህርት ስርዓቱን፣ ተማሪውንና መምህራኑን ለአብዮቱ ስርየት ሲል ጭዳ አደረጋቸው፡፡ ቀጥሎም ጥራትን በመግደል ቁጥርንና ብዛትን መለኪያ መስፈርቱ በማድረግ የቁልቁለት ጉዞውን ተያያዘው፡፡ ስንት ተማሪ ወደ ትምህርት ቤት ሄደ ማለትን እንጂ ስንት ተማሪ ትምህርቱን ጨረሰ ማለትን ዘነጋ፡፡ ስንት ተማሪ ትምህርት ቤት ደርሶ ተመለሰ ማለትን እንጂ ስንት ተማሪ ተገቢውን ትምህርት ወስዶ በእውቀት በለጸገ፣ ብቁ ሆነ ማለትን ረሳ፡፡
ደርግ በዚህ ሁኔታ ያስረከበን የትምህርት ስርዓት፣ ከቁጥርና ከማዳረስ ልክፍት ተላቆ የደረሰበትን ሂደት በሚመለከት ካለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ተነስቼ ድክመቶቹንና ውጤቱን በጽሁፌ ማጠናቀቅያ ላይ የምመለስበት ይሆናል፡፡ ቅድሚያ መሰረታዊ ወደምለው አጠቃለይ ዝንባሌ ላምራ፡፡
ሕዝብ የሃገሩ ባለቤት ነው እንጂ የማንኛውም ፍልስፍና ማስፈጸሚ መሳርያ አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ ሕዝቦችን የምንረዳበት መንገድ ርዕየተ ዓለማችንና ፍልስፋናችንን ከግብ ለማድረስና ምን ያህል ነባራዊ እንደሆነ ለማረጋገጥ ከሚኖራቸው ሚና አኳያ ከሆነ የገዢና የተገዢ መርሆና ቀንበር ገና ያለተሰበረ መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ ለዚህ እንደምሳሌ የማነሳው የኢትዮጵያን የትምህርት ስርዓት ነው፡፡
ዜጎች በትምህርት አማካኝነት ከማንኛውም ፍልስፍና ወይም ርዕዮተ ዓለም አላስፈላጊ ተጽእኖ ነጻ እንዲወጡና ከብዙ ፍልስፍናዎችና ርዕዮተ-ዓለሞች መካከል የሚያምኑበትንና የሚጠቅማቸውን መምረጥ የሚችሉ በማድረግ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ነው፡፡ አምባገነን ስርዓቶች ሰዎች ማሰብ የሚገባቸው ገዢዎቻቸው የሚያውቁትንና የገባቸውን ወይም የሚሰጧቸውንና የሚፈቅዱላቸውን ብቻ እንዲሆን ስለሚሹ በዜጎች አስተሳሰብ ላይ ያልተገባ ተጽእኖ በማሳደር እንደሚሊተሪ ሬጅመንት አድርገው ሊያሰልፉቸው ይፈልጋሉ፡፡
“በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ፣ መሠረታዊ ጥያቄዎች” በሚል ርእስ ነሐሴ 1992 ዓ.ም. ኢህአዴግ ያሳተመውን የፍልስፋና መጽሔት ከገጽ 91-117 ያተተውን በጥሞና እናንብብ፡፡
“ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሣሠብ ልዕልናን ማረጋገጥ ማለት አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል በተናጠል ብቻውን ሆኖ፣ ስለአንድ ጥያቄ ሲያስብ በውስጡ ያለው መሠረታዊ እምነት አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ስለሆነ ዞሮ ዞሮ ወደ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አቋም ሊደርስ የሚችልበት ሁኔታ መፈጠር ማለት ነው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሣሠብ ወደ ሁሉም አቅጣጫ ሠርጾ በመግባቱ የተነሣ ሰው በየግሉ ሲያስብ ከሱ ውጭ ሊያስብ የማይችልበት ደረጃ ላይ ማድረስ ማለት ነው፡፡ …አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ የአስተሣሠብ ልዕልናን ለመፍጠር የዜጐችን አስተሣሠብ በመቅረጽ ላይ ጠንካራ ሚናን የሚጫወቱ መዋቅሮች መኖር አለባቸው፡፡ … አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ የአስተሣሠብ ልዕልናን በማረጋገጥ ላይ ትምህርት ቤቶች ወሣኝ ሚና መጫወት አለባቸው፡፡ … ይህ ደግሞ በቋሚ አካዳሚያዊ ትምህርት ብቻ ሣይሆን በሚሰጥ የሲቪክስ፣ የሕገ-መንግሥት ወዘተ ትምህርት በዕለታዊ የትምህርት ቤቶች አሠራር ወዘተ የሚገለጽ ነው፡፡”
የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፖለቲካዊ ፍልስፍናው ልሳን የሆነው ይህ ህትመት፤ ግልጽ በሆነና በማያሻማ ቋንቋ ያብራራው ፍልስፍና የዜጎች የአስተሳሰብ ነጻነትን የሚጻረር ከመሆኑም በላይ እራሱን መለኮታዊነትና ፍጹማዊ አድርጎ ከመሳሉም በላይ አንዳችም ዴሞክራሲያዊ ቅርጽም ሆነ ይዘት ያልተቀላቀበት ፍልስፍና መሆኑን በራሱ ጊዜ ያረጋገጠ ነው፡፡ እንደ ኢህአዴግ እምነት የሰው ልጅ ላስብና ልመራመር ማለቱና መሞከሩ ከንቱ ጭንቀትና ልፋት ነው፡፡ ስለሆነም ዞሮ ዞሮ መዳረሻው አብዮታዊ ዴሞክራሲ በመሆኑ ከወዲሁ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ አብዮታዊ ዴሞክራሲ እንዲዋሃደው ማድረግ ከድካምና ከኪሳራ እንደሚድን ጽሑፉ ሲገልጸው እንዲህ ሲል ያውጃል “አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ የአስተሣሠብ ልዕልናን በማረጋገጥ ላይ ትምህርት ቤቶች ወሣኝ ሚና መጫወት አለባቸው፡፡” ከዚህ አብዮታዊ ፍልሰፍናና ሃሳብ ውስጥ አንጥረን ማውጣት የምንችለው ነገር ቢኖር እንደ ኢህአዴግ ፍላጎትና እምነት የትምህርት ስርዓቱ መቀረጽ ያለበት ይህንኑ ኢህአዴጋዊ እውነታ ለማረጋገጥና የአስተሳሰቡን የበላይነቱን ሊጭን በሚያስች መልኩ የተደራጀ እንደሆነ ነው፡፡ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በሕገ-መንግስቱ ውስጥ በማያሻማ መልኩ በተረጋገጠበትና በነጻነትና የማሰብ መብት እውቅና ባገኝበት ሃገር ውስጥ የትምህርት ስርዓቱን የአንድ ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም አገልጋይ ለማድረግ ማሰብና ማቀድ ከባድ ዴሞክራሲያዊ ኪሳራ ከመሆኑም በላይ በመጻፍ ነጻነት ላይ ቅድመ ሳንሱር ከሚያደርግ አስተሳሰብ በላይ በእጅጉ የከፋ ነው፡፡
ይህንን ፍላጎት በተግባር ለመፈተሽ ሕገ-መንግስቱ ባይፈቅድም ኢህአዴግ ግን እምነቱ ለማስፈፀም የመረጠው አቋራጭ መንገድ ቅድመ ትምሀርትም ላይም ሆነ ድህረ ትምህርት ላይ ያሉ ተማሪዎችን ከምዝገባ ወረቀት ጋር የአባልነት ፎርም በመስጠት ስውር የሃሳብ የበላይነትን በሌሎች ላይ ማረጋገጥን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ትምህርትም ሆነ ስራ በእውቀት ሳይሆን ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ በሚኖር ታማኝነት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት እያስጨበጠ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የሃሳብ የበላይነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ሃሳቦች ፍጭት ሳያደርጉበት የተጫነ ሃሳብ፣ በአስተሳሰብ ነጻነት ያልዳበረና ተገዢ አዕምሮ ከመሆን አይዘልም፡፡
መሰረታዊ የትምህርት ስርዓቱን ፈተና ከርዕዮተ ዓለም አኳያ በዚህ ደረጃ በጥቂቱ ከፈተሽን በመግቢያዬ ላይ ወደ አነሳሁት ሃሳብ ልመለስ፡፡
የኢትዮጵያን የትምህርት ስርዓት ተብትበውና ቀስፈው የያዙት ችግሮች ከደርግ ጋር ተዳብለው ስር እየሰደዱ ቆይተው፣ ዛሬም በኢህአዴግ ውስጥ በመሸጋገር ማጣፊያ እንዳጠራቸው ቀጥለዋል ፡፡ የመማር ማስተማር ሂደቱ በደርግ ስርዓት የለከፈው የማጥራት ሳይሆን በማብዛት፣ በማዳረስ ላይ የመተማመን በሽታ ዛሬም ኢህአዴግን ቀስፎ እንደያዘው ይገኛል፡፡ ሃገርን ለማበልጸግ፣ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲን ለማስፈን የነቃና የበቃ ትውልድ በሚሊዮኖች ማብቃት አስፈላጊ ነው፡፡ ትምህርት መብት ስለሆነ ዜጎች በሙሉ በአንደኛ ደረጃ ላይ እንዲማሩ እድሉ መመቻቸቱ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ትምህርት ገና ከጅምሩ ብቁ ዜጋን መፍጠር ካዳገተው፣ እውቀት፣ ፈጠራ፣ ጥበብና ክህሎትን ማቀዳጀት ከተሳነው፣ ትምህርት ከጊዜ ማሳለፊያነት ወይም ከመሃይምነት ለመላቀቅ ከሚሰጠው መሰረተ-ትምህርት ያለፈ ሚና አይኖረውም፡፡ ትምህርት መልካም አስተዳደርን ከማስፈንና እድገትንና ልማትን ከማሳለጥ አኳያ የሚኖረው ሚና ሲፈተሸ “መቁጠር” ሌላ “ማወቅ ወይም “መካን” ሌላ መሆኑ በቅጡ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ኢትዮጵያ ስላሏት ታላላቅ ሃብቶች ሲናገሩ “ሕዝቦቿ አይነተኛ ሃብቷ” እንደሆኑ ሲገልጹ ማዳመጥ የተለመደ ነው፡፡ ሕዝብን ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው አኳያ የመመዘንና የመተንተን አስተምህሮት ትውልድ የቆጠረ አስተምህሮት ነው፡፡ ይህንን ሕዝብን ከኢኮኖሚያዊ መስፈርትና ጠቀሜታ አኳያ መተንተን በእጅጉ ያዘመነው የኔዎሊብራሊዝም አመለካከት ነው፡፡ በኔዎሊብራሊዝም ፍልስፍና ሰብአዊ ፍጡርን ጨምሮ ሁሉ ነገር የሚሰፈረውና የሚለካው በብዛቱና በኢኮኖሚያዊ ጥቅሙና ፍጆታው ነው፡፡ ልኬቶቹም ዜጎች ምን ያህል ያመርታሉ? ምን ያህል ያሸጣሉ ወይም ምን ያህል ይገዛሉና ይጠቀማሉ ናቸው፡፡
ከላይ ያነሳሁት ዝንባሌ ኢህአዴግ የሚከተለው የፖለቲካ ፍልስፍና አይነተኛ መዘወርያ ቁልፍ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ኢህአዴግ ሕዝብን ሃብት ነው ሲል ከብዛታችን ተነስቶ እንደሆነ ለመረዳት ፖሊሲዎቹን ማንበብ በቂ መልስ ነው፡፡ ኢህአዴግ በቁጥሩ ትልቅ የሆነውን የአርሶ አደሩን መደብ ሁነኛ አጋሩ ለማድረግ ሲባትል የኖረው በሌላ ምክንያ አልነበረም፤ በነጻ አውጭነት ዘመኑ መሳርያ አንግቦ ደርግን በመፋለም ሁነኛ መሳርያ ሆኖ ስላገለገለው ጭምር ነው፡፡ አዲሱን የትምህርት ስርዓት ሲዘረጋ ጀምሮ ከጥራት ይልቅ ትኩረት የሰጠው ለማዳረስና ለብዛት የሆነው በሌላ ምክንያት ሳይሆን ከኢትየጵያ ሕዝብ ውስጥ ከግማሽ በላይ እንደሆነ የሚነገርለትን ወጣት ትውልድ በአስተማርኩህ ስም ባለውለታ በማድረግ የስልጣን ዘመኑ መሰንበቻና አጋር ለማድረግ ነው፡፡
ኢህአዴግ በስልጣን ላይ ለመሰንበት ካለው ጉጉት አኳያ፣ መሰረታዊና ዘለቄታ ያለው ለውጥ የሚያመጣ አሰራርን መከተል አይሻም፡፡ እንደሚታወቀው በኢህአዴግ ዘንድ በብዛት ላይ ማተኮርን እንጂ ብዛትና ጥራትን በማዋሃድ ዘለቄታን ማረጋገጥ መወጣት ያቃተው ፈተናው ነው፡፡ ብዙሃንን በብዛት ማሰባሰብን እንጂ ብዙሃኑን በጥራት እንዴት ለለውጥና ለውጤት ማብቃት እንደሚቻል በፕሮግራሙ፣ በፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚ ፍልስፍና ውስጥ ማጣቀስ አይቻልም፡፡ የትምህርቱ ጥራት፣ የስራው ጠቀሜታ፣ አይነትና ቀጣይነት ከግምት ውስጥ ሳይገባ ሚሊዮኖች ማስተማር፣ ሚሊዮኖች ስራ ማስያዝ በሚል ዘመቻና መፈክር ስር ሁሉን ነገር በሚሊዮኖችና በሚሊዮኖች ለማድረግ መመኘት መገለጫ ባህርይው ነው፡፡ ለሚሊዮኖች ሊዳረስ የማይችልን ሃገራዊ ሃብት ለሚሊዮኖች በማርከፍከፍ እዚህ ግባ የማይባል “ውጤት” ማስመዝገብ ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት የድርጅቱ ሁነኛ ተግባሩ ሆኖ ቆይቷል፡፡ እንደሚታወቀው እንኳን የሰው ልጅን ይቅርና ቁሳቁስንም ቢሆን በሚሊዮኖች በብቃትና በጥራት ማቅረብ አጠቃላይ ሃገራዊ ሃብታቸው በተትረፈረፈ ሃገራትም ቢሆን እጅግ እጅግ አዳጋች ተግባር ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ለሚሊዮኖች ሁሉን ነገር ለማዳረስ መሻት አንድ ነገር ሆኖ ሳለ ጥራትና ብቃትን ለሚሊዮኖች ማረጋገጥ ግን ከፍተኛ ሃብትን እንደሚጠይቅ ከወዲሁ መረዳትና ቁሳዊ ሃብት ሁሉ አላቂ መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡
ጥራት፣ ብቃትና ክህሎት ሃብትን እንደሚወልዱ ተረድቶ በአስር ሚሊዮኖች ትምህርትን ለማዳረስ ከተጀመረው ውሎ ከማይገባ አሰራረር ተላቆ፣ ውሎ ለሚያድር አንጻራዊ ጥራት መስራት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ውሎ አድሮ በሚሊዮኖች የተጀመረው ሁሉ ባክኖና ተዝረክርኮ መቅረቱ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በፊት አስቦና አስተውሎ በአቅም ልክ መራመድ ውጤታማነት ከማረጋገጡም በላይ ዘለቄታ ያለው መፍትሔ መሆኑን መጨበጥ እጅግ የላቀም ብልሐት ነው፡፡ እስኪ ከላይ የተቀስነውን የጥራትና የብዛት ወይም የማዳረስ ችግር ከኢህአዴግን የትምህርት ፖሊሲ ተነስተን በቁጥር እንፈትሽ፡፡ ከ70 ዓመት ረጅም ጉዞ በኋላ ዛሬ የትምህርት ስርዓታችን በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኛል የሚለውን በዩኔስኮ ዩ. ኤስ. አይ. ዳታ ሪፖርት ላይ ተመርኩዘን እንመልከት፡፡ የኢትዮጵያ ትምህርት ወጭ ከአጠቃላይ ሃገራዊ ምርት አኳያ 4.6 ፐርሰንት ነው፡፡ ይህ ማለት መረጃ መስጠት ከቻሉ 168 ሃገራት ውስጥ ኢትዮጵያ 68ኛ ተርታ ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ አቅም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በእውቀት የበለጸጉ ብቁ ዜጋዎች መፍጠር መቻል አለመቻልን ለጊዜው ትተን ቁጥሩን ብቻ እንመልከት፡፡ በአጠቃላይ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቅበላ በቁጥር 8,269,663 ሲሆን ከ 176 ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ 1ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡በአጠቃላይ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቅበላ በቁጥር 2,140,751 ሲሆን ከ171 ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ በ4ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ እነዚህ አውነታዎች ከትምህርት ቅበላ አኳያ የተሰራውን ስራ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በጥሬው አመርቂ ወጤት ነው ብሎ መቀበል ይቻላል፡፡ እስቲ ቁጥሮቹን የትምህርት ስርዓቱን ከተቀላቀሉት ምን ያህሉ አጠናቀዋል ከሚል ሌላ ንጽጽር በመነሳት እንፈትሻቸው፡፡
1ኛ ደረጃ ትምህርት መማር ከሚገባቸው ውስጥ ለትምህርት የበቁት አጠቃላይ የዜጎች ቁጥር 40.6 ፐርሰንት ሲሆን ከ176 ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ በ172ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
ለ2ኛ ደረጃ የሴቶች ትምህርት ቅበላ 39.7 ፐርሰንት ሲሆን በዚህ ስሌት መሰረት ኢትዮጵያ ከ176 ሃገራት መካከል 150ኛ ተርታ ላይ ትገኛለች፡፡ በአጠቃላይ ወደ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ከገቡት ተማሪዎች መካከል ትምህርታቸውን አጠናቀው የሚወጡት ተማሪዎች ቁጥር በፐርሰንት 55 ሲሆን ከ148 ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ 107ኛ ተርታ ላይ ትገኛለች፡፡
1ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚጨርሱ ወንዶች በፐርሰንት 61 ሲሆኑ ከ145 ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ 97ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ፡፡
1ኛ ደረጃ ትምህርት የሚጨርሱ ሴት ተማሪዎች በፐርሰንት 49 ሲሆኑ ከ145 ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ 103ኛ ተርታ ላይ ትገኛለች፡፡
በትምህርት ቤት የመቆየት አቅምን በሚመለከት አስከ 5ኛ ከፍል ድረስ የሚዘልቁ ሴት ተማረዎች በፐርሰንት 22.96 ሲሆኑ ከ83 ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ 75ኛ ደረጃን ተቀዳጅታለች፡፡
በትምህርት ቤት የመቆየት አቅም አስከ 5ኛ ክፍል ድረስ በወንድ ተማሪዎች ዘንድ በፐርሰንት 15.62 ሲሆን ከ83 ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ 76ኛ ተርታ ላይ ትገኛለች፡፡
በትምህርት ቤት የመቆየት አቅም እስከ 5ኛ ክፍል አጠቃላይ ወንድና ሴት ድምር በፐርሰንት 18.2 ሲሆን ከ83 ሃገራት መካከል 76ኛ ናት፡፡
ከላይ በቀረበው ሪፖርት መሰረት፤ ተማሪዎችን በብዛት ለማዳረስ ሲባል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በማስመዝገብ ላይ የታየው የኢህአዴግ ትጋት ከበርካታ ሃገራት መካከል ሲወዳደር በአንደኛ ደረጃ ሊያስያስቀምጠው የሚችል ቢመስልም ተማሪዎች ትምህርት ቤት ከገቡ በኋላ ትምህርታቸውን ጨርሰው ለታቀደላቸው ዓላማና ግብ መብቃታቸውን ከማረጋገጥ አኳያ ግን በመቶዎቹ ወደ ታች ያሽቆለቁላል፡፡ ይህ እንግዲህ ብዛትና ማዳረስን ከዘመቻ ጋር በማዋሃድ የሚካሄድ የትምህርት ስርዓት የሚገለጥበትን ድክመት በቅጡ የሚጠቁም ነው፡፡ የቀረቡት መረጃዎች ትኩረት የሚሰጡት በቁጥር ላይ ብቻ በመሆኑ ትምህርት ጀምረው ያላጠናቀቁ ተማሪዎች ላይ የፈሰሰውን መዋእለ ንዋይ መጠንና ዋጋ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው፡፡ ከዚህም በላይ መረጃው ለማሳያነት ሲባል በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ላይ ያተኮረ በመሆኑ በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ የተማሪዎች ቅበላና ትምህርትን ከማጠናቀቅ አኳያ የሚፈጠሩ ምስቅልቅሎችን የሚያንጸባርቅ አይደለም፡፡
በዩኒቨርስቲዎችና በኮሌጆች የሚመደቡ ተማሪዎች በቁጥር ደረጃ በ30 እና በ40 ፐርሰንት የማደጋቸውን ያህል ትምህርታቸውን በቅጡ መማር እያቃታቸው የሚሰናበቱትና ደካማ በሆነ የትምህርትና ምዘና ስርዓትም እየታገዙም ቢሆን በዝቅተኛ ውጤት ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ የሚያቅታቸው ተማሪዎች ቁጥር የትየለሌ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ተስፋን ሰንቀው ከቤታቸውና ከቤተሰቦቻቸው የወጡ ተማሪዎች በሃገሪቱ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ተመድበው በመምህራን እጥረትና ብቃት እጥረት፣ በክትትል ማነስ ምክንያት ተምረው ለማደግ የሰነቁትን ህልም ከግብ ማድረስ እያቃታቸው በመጀመርያ ዓመት ከትምህርታቸው ተባረው ኑራቸውን በአልባሌ መንገድ በየከተማው የሚመሩ ሴት እህቶቻችንን በርካታ መሆናቸውን በተለያዩ መጽሔቶች ለመከታተል በቅተናል፡፡
የመማር ማስተማር ሂደቱ በየትኛውም ደረጃ ቢሆን የግድ የሚላቸው አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች አሉት፡፡ ያልተጨናነቁ ክፍሎች፣ በቂ የአየር ዝውውር ያለባቸውና ለጥናት የተመቹ ላይብረሪዎችና ቤተ ሙከራዎች፣ በቂ መማሪያ መጽሐፍትና ዶክመንቶች፣ በቂ የሚባል የተማሪ እና አስተማሪ ጥምርታ እንዲሁም አስተማማኝ የምዘና ስርዓት ወዘተ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ግብአቶች ባልተሟሉበት ሁኔታ የሚሰጥ ትምህርት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡
በቆርቆሮ በተሰሩ ክፍሎች ውስጥ በቂ የአየር ዝውውር በሌለበት ሁኔታ፣ ክፍሎቹ ሊያስተናግዱ ከሚችሉት በላይ በተማሪ ተጨናንቀውና ተፋፍገው በመቀመጥ በላብ እየተጠመቁ ማስተማርም ሆነ መማር አሊያም ማጥናት የማይሞከር ጉዳይ ነው፡፡ ትምህርቱን ያለ በቂ እውቀት ማጠናቀቅ ቢቻልም እንኳን በተፋፈገና በቂ ባልሆነ የምግብ አቅርቦት እየታገዙ በመማር ስር ለሰደደ በሽታ ሳይጋለጡ ሙሉ ጤንነት ይዞ መውጣት አዳጋች ነው፡፡ መጪው ትውልድ ሃገር ተረካቢ ነው ማለት ብቻ አይበቃም፡፡ በትምህርት የታረቀ፣ ከየት እንደተነሳና ወዴት እንደሚደርስ የሚያውቅ፣ በክህሎትና በእውቀት የተገነባ ማድረግ ያሻል፡፡ ተማሪዎች ተምረው ከጨረሱና መረጃ ከተሰጣቸው በኋላ የተማሩትን አያውቁም በሚል ጥርጣሬ እንደገና ለምዘናና ለፈተና በመዳረግ የትምህርት ስርዓቱን ችግር የተማሪው ማድረግ ጊዜውን በማባከን የትውልዱን ሕይወት ስንኩልና ባዶ ከማድረግ አይተናነስም፡፡ የትምህርት ስርዓቱ መፍጠር የሚገባውን ተጸእኖ በትውልድ ላይ የሚፈጥር እንዲሆን ከብዛት ወደ ጥራት፣ ከብልጠት ወደ ብልሕነትና አስተዋይነት ይሸጋገር፡፡

 

Read 11669 times Last modified on Saturday, 17 November 2012 11:04