Saturday, 17 November 2012 11:04

“አንተ የተሻልክ ነህ…” ስንት ሚሊዮን ያወጣል?

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በቀደም እዛ ‘ዋናዋ አገር’ የተሸነፉት ሰውዬ ያሸነፏቸውን ሰውዬ ስልክ ደውለው “እንኳን ደስ አለህ…” ያሏቸው ነገር እንዴት ያስቀናል! የምር እኮ…“እንኳን ደስ አለህ፣ አሸንፈኸኛል” የምንባባለው መቼ ነው አያስብላችሁም!
ነገሬ ካላችሁልኝ…እዚህ አገር ብዙዎቻችን በሆነ ነገር ‘የምንበለጠው’ በእኛ ችሎታ ማነስ ወይም የሌላኛው ሰው ከእኛ መሻል ሳይሆን ሌላ ምክንያት ይፈለግለታል፡፡ መሸነፍን፣ መበለጥን ያለመቀበል…አለ አይደል…በ‘ሊግ’ የማይከፋፋል፣ የዝውውር ገንዘብ የሌለበት ‘ናሽናል ስፖርት አይነት ነገር ሆኗል፡፡

እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በፊት ጊዜ የኳስ ቡድናችን ውጪ ሄዶ ‘ተረምርሞ’ ሲመጣ መቼም ቢሆን “አልቻልናቸውም፣ በጨዋታ በልጠው ነው ያሸነፉን…” ሲባል ሰምታችሁ ታውቃላችሁ! ልክ ነዋ…‘አየሩ ይከብደናል’ እንጂ አንበለጥም፡፡ ኮሚክ ነገር ነው… ልክ እኮ የእኛ ልጆች ሜዳ ሲገቡ ማልያቸውን አስወልቀው ‘ኩንታል፣ ኩንታል አየር’ የሚያሸክሟቸው ነበር የሚመስለው፡፡ የኳስ ነገር ከተነሳ…ይሄ ቡድኖቻችንን ለማውረድ በሚያስቸግር ሁኔታ ሽቅብ መስቀል ትንሽ የበዛብን አይመስላችሁም! የዚህ ሰሞን የኳስ ነገር “ሞኝ የያዘው ነገር…” እንዳያስመስልብን ያስፈራል፡፡
ስሙኝማ…የሞኝነት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…አንድ ልጅ ጸጉር ማስተካከያ ቤት ይገባል፤ አስተካካዩ የሚያስተካክለውን ሰው እንዲህ ይለዋል፤ “ይሄ ልጅ እንዴት አይነት ሞኝ እንደሆነ ልነግርህ አልችልም፡፡ ዘላለሙን አይማርም፡፡ እንዴት ሞኝ እንደሆነ አሳይሀለሁ” ይልና ልጁን ይጠራዋል፡፡ ልጁም ቀረብ ይላል፡፡ ጸጉር አስተካካዩ በአንድ እጁ አንድ ብር፣ በሌላኛው እጁ ሀምሳ ሳንቲም ይይዝና “የምትፈልገውን መርጠህ ውሰድ” ይለዋል፡፡ ልጁም ሀምሳ ሳንቲሙን ይዞ ይወጣል፡ ጸጉር አስተካካዩም “አየኸው አይደል እንዴት ሞኝ እንደሆነ! ለመጣው ሰው ሁሉ ነው የማሳየው” ይላል፡፡
ጸጉሩን የተስተካከለው ሰው ጨርሶ ሲወጣ ልጁን ኬክ ቤት ሊገባ ሲል ያቆመውና “አንተ ለምንድነው ብር እያለልህ ሁልጊዜ ሀምሳ ሳንቲሙን የምትወስደው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ልጁ ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ “ብሯን የወሰድኩ ዕለት ጨዋታው ይጠናቀቃል፡፡” አሪፍ አይደል! ያሞኘን እየመሰለን እየተሞኘን ያለነውን ቤቱ ይቁጠረን፡፡
እናላችሁ…የምር የሚገርም ነገር ነው…ብዙዎቻችን በአንድ ነገር ስንበለጥ “በልጠኸኛል፣ አንተ የተሻልክ ነበርክ…” ማለት… አለ አይደል…ኮልት ሽጉጥ እንደ መጠጣት ይመስለናል፡፡ (ማካሮቩ ተለቅ ይላል ልበል! ቂ…ቂ…ቂ….)
እናላችሁ…ለምሳሌ እሱዬው በሆነ ነገር ይወዳደርና በሌላው ተወዳዳሪ ይሸነፋል፡፡ ይሄኔ “ስላሸነፍክ እንኳን ደስ አለህ፣ በሚቀጥለው ጊዜ ይበልጥ ተዘጋጅቼ እመጣለሁ…” ብሎ አበባ ከማበርከት ይልቅ መጀመሪያ የሚያደርገው ነገር ቢኖር ጓዳ ገብቶ ካራ መሳል ነው፡፡ ቤተ ዘመዱ ሁሉ ለልጃቸው መሸነፍ ምክንያቱ የችሎታ ጉዳይ ሳይሆን ሌሎች ነገሮች እንደሆኑ ይነግሯችኋል፡፡
እህቱ ምን ትል መሰላችሁ… “ኮምፕሌክሳም ሁሉ! ድሮም ቢሆን ሳሩም ቅጠሉም የእኔን ወንድም እንደ ተመቀኙት ነው፡፡ ውስጥ ለውስጥ ተስማምተው…” ምናምን ነገር ትልላችኋለች፡፡
ታላቅ ወንድም ሆዬ በበኩሉ… “እኛ ቤተሰብ መሸነፍ ብሎ ነገር የለም፡፡ የአባባ ዘመዶች ቢሰሙ ምን ይላሉ! እስቲ ወንዱ ማን እንደሆነ እናያለን…” አይነት ከነገሩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ፉከራ ይፎክርላችኋል፡፡ (እኔ የምለው ያቺ አንዴ ተተኩሳ በአንድ ሊትር ውሀ ቀዝቀዝ የምትደረገው ‘ጭስ የጠጣች’ ጠብመንጃ አሁንም ጓዳ እንደተሰቀለች ነች እንዴ! ብዙ ጊዜ የሚፎከርብን እሷ ወይም ለእሷ ቅርብ የሆነ ነገር ሲኖር ነዋ!)
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን…አንዳንዱ ሰው በየሚኒባሱ ምናምን ከመሬት ተነስቶ የሚያስፎክረው ምንድነው! መብት ማስከበር አሪፍ ነው…ግን የሁለት ብር ከሰባ መንገድ መሆኑ እየታወቀ “እስቲ ከብር ከአርባ በላይ የሚያስከፍለኝን አያለሁ…” አይነት ‘ጭስ የጠጣች’ ፉከራ አሪፍ አይደለም፡፡ እግረ መንገዴን “ካልከፈለ አውርደህ ጣለው…” እያላችሁ ‘እንቁላል ለሮማ ስንሸጥ’ የኖርን ይመስል የምታስፋራሩን የሚኒባስ ሾፌሮችም ተዉንማ!)
እናላችሁ… የተሸናፊው አጅሬ እናት ምን ይሉ መሰላችሁ…“እነኛ መጫኛ ቀጥ የሚያደርጉ መተተኛ ደብተራ ዘመዶቹ አሁንም አልተዉንም!” በኢትዮዽያ ‘ዲክሺነሪ’ “ጉድ ሠሩኝ…” “በጠላ በጥብጠው ሰጡኝ…” ምናምን ነገር ነው እንጂ ተሸነፍኩ ‘ብሎ አማርኛ’ የለማ! “ጎሽ” ብሎ በአድናቆት ማጨብጨብ እኮ ‘የማይከፈል ዕዳ’ ምናምን ነገር አይደለም፡፡
ስሙኝማ…የጭብጨባን ነገር ካነሳን አይቀር…ሰውየው ንግግር እያደረገ ነበር፡፡ እና ከተሰብሳቢዎቹ አንዱ ሲያጨበጭብ የሰማው መሰለው፡፡ እናላችሁ…ተናጋሪው ሆዬ ምን አለ መሰላችሁ… “አሁን ያጨበጨብከው ሰውዬ፣ አመሰግናለሁ…” ይላል፡፡ ተሰብሳቢው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው …“እያጨበጨብኩ አልነበረም፡ እንቅልፍ እንዳይወስደኝ ጉንጬን እየመታሁ ነበር፡፡” ከልባችን የምናጨበጭበውና እንቅልፍ ስንከላከል የምናጨበጭበው ይለይልንማ!
እናላችሁ…ከድክመት ከመማርና ለሚቀጥለው ዙር ተዘጋጀቶ ከመምጣት ይልቅ ጊዜያችን የሚጠፋው ለመሸነፋችን ምክንያቶች ስንፈበርክ ነው፡፡ ‘ቦተሊካችን’ ተጽፎ አላልቅ ያለ ‘ትራጂክ ኮሜዲ’ ነገር የሆነው እኮ… “አዎ ተሸንፈናል…” የሚል ጠፍቶ ነው፡፡ (ስሙኝማ…በቀደም ጋዜጣ ላይ ያየሁት የ‘ኦፖዚሽን’ ቁጥር ሲገርመኝ ከረመ ነው የምላችሁ፡፡ እኔ የምለው… የእቁብ፣ የአብሮ አደግ፣ ምናምን ስብስቦችን ወደ ‘ሶሺሌ’፣ ‘ኮሚ’ ምናምን ቡድኖች መለወጥ ይቻላል እንዴ! ነው… ወይስ ነገ ደግሞ በ‘ኦፖዚሽን’ ቁጥር ብዛት “ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ምናምነኛ…” ለመባል ነው!) እኔ የምለው…እንዲሁ ትዝ ስላለኝ ላንሳውና…የእኛ ‘ቦተሊከኞች’ ይሄ ‘ሴንሰ ኦፍ ሂዩመር’ ምናምን የሚሉት ነገር የሚኖራቸው መቼ ይሆን! አሀ ሁልጊዜ “ዋ! ሱሪህን ዝቅ አድርጌ እንዳልጠበጥብህ!” አይነት ንግግርና አስተያየት ሰለቸና! አንዷ ሴትዮ ዊንስተን ቸርችልን ግብዣ ላይ “ጌታዬ ጥምብዝ ብለው ሰክረዋል” ትላቸዋለች፡፡ ዊንስተን ቸርችል ምን አሏት መሰላችሁ፡፡ “አንቺ ደግሞ አስቀያሚ ነሽ፡፡ እኔ ግን ስካሩ ጠዋት ይለቀኛል፡፡” አሁን የእኛን ‘ቦተሊከኛ’ “ጥምብዝ ብለው ሰክረዋል…” የሚል ሰው ሊገጥመው የሚችለው…ተዉት ብቻ፡፡እናላችሁ…“እንኳን ደስ አለህ…” ስንባባል እንኳን በፌዝ ነው፡ “እህ አጅሬው… በዚችም በዛችም ብለህ ተሳካልህ አይደል!” ይባላል፡፡ የሚገርመኝ እኮ…“እንኳን ደስ አለህ፣ አሸንፈሀል…” መባባል ምን ዋጋ ያስከፍላልና ነው እንዲህ የምንሸሸው! ሁላችንም እኮ ሽንፈት ከአንዴም ሁልጊዜ ይገጥመናል፡ እንደውም ብዙ ጊዜ በ‘ኖክአውት’ እየተዘረርን “ቡጢው ሳይሆን ሲሰነዝር ተረከዜን አደናቅፎኝ ነው የወደቅሁት…” አይነት ቀሺም ነገር ነው ያለው፡፡ የምር ምክንያት ለመፍጠር የምናጠፋውን ካሎሪ ምናምን እኮ…አለ አይደል… የጎደለንን ነገር ለማስተካከያ ብንጠቀመበት አሪፍ የሚሆን አይመስላችሁም!ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ኪነ ጥበብ አካባቢ ብታዩ “እሱ ከእኔ የተሻለ ትያትር ዕፏል…” “እሷ ከእኔ የተሻለ አልበም አውጥታለች…” “የእሱ ግጥሞች ከእኔ የተሻሉ ናቸው…” “እሷ የተሻለች ተዋናይት ነች…” ማለቱ…ልክ ከሰዶምና ገሞራ የበለጠ ሀጢአት መሥራት እናስመስለዋለን፡፡ እኔ የምለው…ካነሳነው አይቀር እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… ‘ነገርዬው’ ሀጢአት ለመሆን የግድ ሰዶምና ገሞራህ ውስጥ ብቻ ነው እንዴ መፈጸም ያለበት! አሀ…እዚቹ ከተማችን ውስጥ ‘ነገርዬው’ ቅልጥ ብሎ የለ እንዴ! ቀን የለ፣ ማታ የለ፣ አዩኝ አላዩኝ የለ…የበሬ ጥማድ ምስጋን ይግባው፣ ተጣምዶላችሁ ውሎ ያመሻል! ቂ…ቂ…ቂ… ልክ ነዋ፣ ‘ጣኦቱ’ በወርቅ ባይሠራም በተለያየ መልኩ ታገኙታላችሁ፡፡እናላችሁ…አንድ ሰው ከበለጠን “በሚቀጥለው ጊዜ ከእሱ ተሽዬ ካልመጣሁማ…” ከማለት ይልቅ…“ቆይ ለዛ መፅሐፍ ገላጭ ዘመዴ ነግሬ በአራት እግሩ ባላስኬደው!” አይነት ነገር ነው የለመደብን፡፡ ግዴላችሁም… ምስጋና “አንተ የተሻለ ሥራ ሠርተሀል…” ማለት ቫት ያለበት፣ ቲ.ኦ.ቲ. ያለበት፣ የባንክ ወለድ ያለበት፣ የእንትን መዋጮ ያለበት… ነገር የለውም፡፡ “አንተ የተሻልክ ነህ…” ማለት ስንት ሚሊዮን ያወጣል? ቢቸግረን ነው እንዲህ የጠየቅነው፡፡ለመልካም ሥራ የምንነካከስበት ሳይሆን የምንመሰጋገንበትን ጊዜ ያምጣልንማ!
ደህና ሰንበቱልኝማ!

 

Read 14181 times Last modified on Saturday, 17 November 2012 11:15