Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 November 2012 11:36

ስጦታው

Written by 
Rate this item
(7 votes)

አውቶብሱ በሰዎች ጢቅ ብሎ ሞልቷል፡፡ ወጣት፣ ሽማግሌ፣ ወይዛዝርት፣ ባልቴት…በግልም በቡድንም ተሳፍረው እየፈሰሱ ነው - እንደ ዥረት፡፡ የሁሉም መድረሻ ለየቅል ነው - እንደሃሳባቸው፡፡ አውቶብሱ ተሳፋሪዎችን ከወዲህ ወዲያ እያላተመ በልሙጡ አስፋልት ላይ ይከንፋል፡፡ ከአውቶብሱ ተሳፋሪዎች ሁሉ ጐልተው የሚታዩት ሁለቱ ናቸው - የሚያጓጓ የአበባ ዕቅፍ የያዙት ሽማግሌና ዝንጥ ያለችው ድንቡሽቡሽ ወጣት፡፡ ሽማግሌው 60 ዓመት ገደማ ይሆናቸዋል፡፡ ወጣቷ ከ25 ዓመት አይበልጣትም፡፡ አውቶብሱ ላይ ከተሳፈረችበት ቅጽበት አንስቶ ዓይኗን ማዶ የተቀመጡት ሽማግሌ ላይ ጥላለች፡፡ አንዴ ሰውየውን ሌላ ጊዜ ዕቅፍ አበባውን ትክ ብላ ታያለች - በስስት፡፡

አውቶብሱ ለመቆም ፍጥነቱን መቀነስ ሲጀምር የአበባ ዕቅፍ የያዙት ሽማግሌ ከተቀመጡበት ብድግ አሉ ፡፡ 
መውረጃቸው ደርሶ ነው፡፡ ከመውረዳቸው በፊት ግን በቀጥታ ያመሩት ወደ ድምቡሽቡሿ ወጣት ነበር፡፡ አጠገቧ ሲደርሱም ፈገግ አሉና በእጃቸው የያዙትን ዕቅፍ አበባ በከፊል የተጋለጡ ፍም ጭኖቿ ላይ አስቀመጡላት፡፡ ወጣቷ በድንጋጤ የምትለው ጠፍቷት ስትርበተበት ሽማግሌው ተናገሩ “አበቦቹን የወደድሻቸው ስለመሰለኝ ነው፡፡ በእርግጥ ለሚስቴ የገዛሁት ስጦታ ነበር…ግን ለአንቺ በመስጠቴ አይከፋትም…ደሞ አልዋሻትም…እነግራታለሁ” ብለው መልሷን ሳይጠብቁ ከአውቶብሱ ወረዱ፡፡
ወጣቷ በአበቦቹ ብትደሰትም አንዲት የምስጋና ቃል ትንፍሽ ሳትል ሽማግሌው ስላመለጧት ቆጭቷታል፡፡
ወዲያው ዓይኗን በመስኮት ስትልክ ሽማግሌው መንገድ ዳር ላይ ወዳለው ቤ/ክርስቲያን ገብተው አንድ የመቃብር ሃውልት ጋ ቆመው ተመለከተች፡፡
( “chicken soup ” ከሚለው መፅሃፍ ታሪክ መነሻ ሃሳብ ተወስዶ የተፃፈ )

 

Read 3770 times Last modified on Saturday, 17 November 2012 11:59