Saturday, 17 November 2012 12:23

ዳዊት ንጉሡ ረታን እከስሰዋለሁ!

Written by  ጌታሁን ሄራሞ(ኬሚካል ኢንጅነር)
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ሳምንት ዳዊት ንጉሡ ረታ የ”አጥቢያ” እና የ”ኢሕአዴግን እከስሳለሁ” መጽሐፍት “ሂስ” የጀመረውና የጨረሰው ደራሲውን አሌክስን (ዓለማየሁ ገላጋይ) በማድነቅ ነበር፡፡ መግቢያው ላይ ዳዊት ስለ አሌክስ ብቃት ያስቀመጣቸው አባባሎች እነዚህን ይመስላሉ፦ “ለንባብ ከሚያቀርብልን አሪፍ አሪፍ ጽሁፎች…ሃሳቦቹ የተለየ ክብር አለኝ…የታሪክ አዋቂነቱ…ለደራሲው ያለኝ አድናቆት ላቅ ያለ ሆኗል… ወዘተ” እንዲሁም መዝጊያው ላይ ዳዊት አንባቢውን የተሰናበተው “ዓለማየሁ የጊዜአችን ምርጥ ፀሐፊ” በማለት ነበር፡፡
ሂስን በአዎንታዊው ጎን መጀመርና መጨረስ ማሄስ ለምንፈልገው ጭብጥ እውነትነት ዋስትና አይሆንም…ምንም እንኳን አካሄዱ የጨዋ ሃያሲ መርህ ቢሆንም፡፡ ደረጀውን የጠበቀ መሠረታዊ የሂስ ዲስፕሊን ግን ከዚህ ባለፈ ብዙ ምርምርን፣ ድካምንና የጊዜን መስዋዕትነት ይጠይቃል፡፡ ደራሲና ገጣሚ ደረጀ በላይነህ እንደሚለው “ሂስ ጊዜ የሚበላ ጅብ ነው” ፡፡

የዳዊት ሂስ ግን ጊዜ የበላ ጅብን አይመስልም፡፡ በእርግጥ ዳዊት የአጥቢያ ልብ ወለድ ውስጥ የደራሲውን ፍንትው ያለ አቋም ፍለጋ ብዙ የደከመ ይመስላል፡፡ ፍለጋው ያለውጤት በመጠናቀቁ የተከፋው ዳዊት፤ የአሌክስን ክርክር የተበቀለው “ጉንጭ-አልፋ” የሚል ታፔላን በመለጠፍ ነበር ፡፡ ሚዳቋዋ ከአቅሙ በላይ እየፈጠነችበት ከተኩስ ኢላማው ምህዳር በመራቋ የተበሳጨው አዳኝ “ወትሮም ሥጋዋ አይጣፍጥም” በሚል መደምደሚያ ወደ ቤቱ እንደተመለሰው ማለቴ ነው፡፡
አሜሪካዊው ፕሮፌሰር ኖኤል ካሮል ከዘመናችን ምርጥ የሂስ ፍልስፍና ጠበብት ውስጥ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ስለ ሂስ መሰረታዊ ሀሳቦችን በሚያስጨብጠው “On Criticism” መጽሀፋቸው ላይ ደረጃውን የጠበቀ ሂስ ቢያንስ ስድስት መስፈርቶችን ማሟላት እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ በሶስተኛ ደረጃ የተቀመጠው ምደባ (Classification) ነው፡፡ ይህ ለማሄስ የምንደረደረው የጥበብ ውጤት በየትኛው የአስተሳሰብ ጎራ እንደሚመደብ ለማወቅ የምናደርገውን ጥረት ይወክላል፡፡ የደራሲውን የአስተሳሰብ ጎራ ካወቅን በኋላ የጥበብ ሥራው መዳኘት ያለብን በዚያው አውድ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሲታይ የዳዊት ንጉሱ ረታ “ሂስ” በራሱ ከሂስ የሚያመልጥ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡
ለዓለማየሁ ገላጋይ እሳቤ መደብ ማበጀት የተሳነው የዳዊት ንጉሱ ትችት የሚሰለፈው ከዘመናይ የእሳቤ ተርታ ነው፡፡ ዘመናይነት ሁሌም አንድ ገዥ ማጠቃለያ(metanarrative) ፍለጋ ይኳትናልና፡፡ በተቃራኒው የአሌክስ የአጥቢያ መጽሀፍ ግን በዘመናይነት የእሳቤ መነጽር የምትታይ አይደለችም፡፡ ይልቅ የምትመደበው ከድህረ ዘመናዊያኖቹ ተርታ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ድህረ ዘመናይ ሥነጽሁፍን በዘመናይነት ዕይታ ለማሄስ መሞከር ደግሞ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ያሰኛል፡፡
አጥቢያ መጽሐፍ ገና ከጅምሩ የድህረ ዘመናይነት አመለካከትን የምታውጅ ትመስላላች፦አዲስ አበባ ላይ እንደጭጋግ በቀስታ የምንሳፈፍ መሰለኝ…በማለት(ገጽ 1) ፡፡ ድህረ ዘመናይነት እሳቤ የሚያደርገው እንደ እርሱ ነው! ያንሳፍፋል እንጂ የቱ ጋ መሬት መርገጥ እንዳለብን አስረግጦ አይነግረንም፡፡ መውረጃ ፌርማታችንን፣ የመጨረሻ ዕጣችንን መወሰን ያለብን እኛው እራሳችን(አንባቢያን) ነን፡፡
አጥቢያ መጽሀፍ የድህረ ዘመናይነት ሥነ ጽሁፍ መልክ እንዳላት የሚያስረግጡንን ሌሎች ምክንያቶችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በገጽ 15 ላይ ያለውን ሀሳብ እንመልከት፦
“የጽሁፉ ጭብጥ በአራት ኪሎ ፈራሽ መንደር ላይ ያተኮረ ነበር፣ የፀሐፊው መነሻ የመንደሩ መፍረስ የሚያስከትለውን ሰብአዊ ቀውስ ማሳየት ቢሆንም ጽሁፉ እንደ በተሃ ጠጅ ከመድረቅ ይልቅ ወደ ልስላሴ ያደላል …ፀሀፊው የተለሳለሰው በመለዘብ እንዳልሆነ ያስታውቃል፡፡ ምክንያቱም የአራት ኪሎ መፍረስ የሚያስከተለው ሰብኣዊ ቀውስ ከፍተኛ ነው የሚል አቋም ቢኖረውም በሌላ አንፃር መፍረስ የለበትም አይልም፡፡ ታዲያ ምን ይሁን ለሚሉትም ፀሐፊው አማራጭ አይሰጥም፡፡”
አማራጭ አለመስጠት አንባቢን እንደ ማንሳፈፍ ነው፡፡ “እንደ በተሃ ጠጅ ከመድረቅ ይልቅ..” ተብሎ የተቀመጠው ደግሞ ደራሲው ዘመናይ አስተሳሰብን እንደማይከተል ይጠቁማል፡፡ ወደ ልስላሴ ማድላቱ ደግሞ ድህረ ዘመናይ አመለካከትን እንደሚያራምድ ማሳያ ነው፡፡ የድህረ ዘመናዊነት ዕሳቤ እንደ ዘመናዊው ግትርና ደረቅ ሳይሆን ልክ እንደ ታጣፊ አልጋ ቅርጹን እየቀያየረ ከአካባቢው አውድ ጋር በቀላሉ የሚላመድ ነው፡፡
ሌላው የድህረ ዘመናይነት ሥነጽሁፍ ባህርይ ዘልማዳዊ በሆነ ዘዴ፣ ህግና ሥርዓት ጠብቀው የደራሲውን ወጥ ሀሳብ ለመፈለግ የሚሞክሩ አንባቢያንን ማብሸቁ ነው፡፡ ከአምስት ዓመታት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውና የዘመናችን ቁጥር አንድ የድህረ ዘመናይነት ፈላስፋ አሜሪካዊው ራይካርድ ሮሪቲ፤ “Philosophy and the Mirror of Life “ በተሰኘ መጽሀፍ ውስጥ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አዲስ ንድፈ ሀሳብ የሚፈልግ አንባቢ የማታ ማታ ማኩረፉ የማይቀር ስለመሆኑ እንዲህ ሲል ተናግሯል ፦”The reader in search of a new theory on any of the subjects discussed will be disappointed “ እንዲሁም ሲልቪያ ፖክርቭካኮቫ የተባለች ፀሐፊ “Understanding literature” በተሰኘው መጽሀፏ፤ አንድ አንባቢ በድህረ ዘመናይ ጽሁፍ ውስጥ የደራሲውን ሀሳብ በመደበኛውና በአዘቦት ዘዴ ለመገንዘብና ለመተርጎም ጥረት ባደረገ ቁጥር ውጤቱ ንዴትና ንጭንጭ ሊሆን እንደሚችል ትናገራለች፦”Unlike the phenomenon of readers’ expectations and its facilitation of the process of perception and interpretation, the breaking of generic conventions can have a shocking effect on readers” ለዚህ በማስረጃነት ዳዊትን መጥቀሱ በቂ ነው፡፡
ሌላው በአጥቢያ ልብ ወለድ መጽሀፍ ውስጥ የምናስተውለው የድህረ ዘመናይነት ባህርይ ደራሲው ላለፉት ታሪኮች፣ ወጎችና ልማዶች ከሰጠው ሰፊ ትኩረትና ትረካ ጋር የሚቆራኝ ነው፡፡ ዳዊት ንጉሡ “መንደር ፣ቀዬ፣አድባር፣ምንትስ” እያሉ ማለቃቀስ የዕድገት ጸር እንደሆነ ሊያስገነዝበን ሙከራ አድርጓል፡፡ ደራሲው በተቃራኒው ስለነዚህ ማህበራዊ ጉዳዮች በሰፊው ይተነትናል፡፡ የዘመናዊነት የሁል ጊዜ ነጠላ ዜማ በአዲስነት ላይ ብቻ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ድህረ ዘመናዊነት ግን ወደ ኋላ ተጉዞ የጥንቱን አመለካከት ወደ ዛሬው በመሳብ ወቅታዊና አውዳዊ ትርጉምን ለመስጠት ይሞክራል፡፡ አዲስነት በአሮጌነት፣ አሮጌነትም በአዲስነት ውስጥ ሊኖር ይችላል የሚል ግንዛቤን ያራምዳል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ አንድ ስሙ በውል የማይታወቅ ፀሐፊ ያለውን እንመልከት” Post modern literary work does not pretend to be new and original ,but uses old literary forms ,genres, quotation allusion and other means to recontextualize their meaning in a different linguistic and cultural contexts to show the difference between the past and their meaning in a different linguistic cultural contexts”
በእኔ ዕይታ የአሌክስ መጽሐፍ ዕጣ ፈንታዋ ከድህረ ዘመናዊነት ዕሳቤ ተርታ መሆኑን ለማሳየት ከዚህም በላይ ዋቢዎችን መጥቀስ ይቻላል፤፤ የሚገርመው ግን አንድ ደራሲ መጽሐፉን በሚደርስበት ወቅት ስለ ዕሳቤው ጎራ የጠራ ግንዛቤ ሊኖረው አለመቻሉ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የደራሲው ሀሳብ ፍሰትና ጉዞ በአብዛኛው በጣም ሜካኒካል በሆነው (conscious level) ላይ ሳይሆን በደመነፍስ ደረጃ(unconscious) ሊሆን መቻሉ ነው፡፤ ብዙውን ጊዜ ግን ሃያሲያንና ንቁ አንባቢያን ናቸው ጎራውን ፈትሸው የሚለዩት! ለምሳሌ፦ በአንድ ወቅት በሀገር ፍቅር ትያትር አዳራሽ በአዳም ረታ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ላይ አስተያየት በተሰጠበት መርሃ ግብር ላይ ተገኝቼ ነበር፡፡ በጊዜው አንዲት የሥነጽሁፍ ባለሙያ የአዳም ረታ ጽሁፎች ወደ ድህረ ዘመናይነት ያደላሉ የሚል አስተያየት በሰጠችበት አጋጣሚ፣ አዳም በምላሹ ስለ ድህረ ዘመናዊነት አንድ ሁለት ነገር ጣል የሚያደርግልን መስሎን ነበር! እርሱ ግን ያለው “እኔ ጽሁፎቹን የጻፍኩት አሁን የምትናገሩትን ፍልስፍና እያሰብኩ አልነበረም” ነበር፡፡
በደመ ነፍስ ደረጃ በአዕምሮአችን የማስታወሻ ቋት(Memory bank) ውስጥ የተቀመጡትን እሳቤዎች ጎልጉሎ ማውጣት የዘመኑ የስነ ልቦና ሳይንስ የቤት ሥራ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ የዘርፉ ጠበብት የዛሬ ማንነት መገለጫችን ፣ ሰምና ወርቁ ያለው ከወዲያ እንደሆነ አበክረው እየነገሩን ነው፡፡ ስለዚህም የሥነጥበብ ባለሙያዎች የጥበብ ሥራቸውን በሚከውኑበት ወቅት ለዚሁ አመለካከት ትኩረት መስጠት ግድ ይላል፡፡
እንግዲህ አጠቃላይ የጽሁፌ መልእክት አንድን የጥበብ ውጤት ከማሄሳችን አስቀድሞ መሠረታዊ የሂስ መርሆችን መከተል አስፈላጊ ነው የሚል ነው፡፡ ለእኔ የአሌክስ አጥቢያ የልብ ወለድ መጽሀፍ የጉንጭ አልፋ ክርክሮች ስብስብ ሳትሆን እልፍ የሆኑ የማህበራዊ ሳይንስ፣ የኪነ ህንጻና የከተማ ፕላን መሪ ሀሳቦችን ሰብስባ የያዘች መጽሀፍ ነች፡፡ ለምሳሌ አሌክስ በጣም ጥቃቅን የሚመስሉትን ማህበራዊ እንከኖችን (የሐዋሳውን አቦካዶ መጥቀስ ይቻላል) እያገዘፈ ማሳየቱ ጽልመት-ናፋቂ ቢያሰኘውም ለትኩረቱ ትኩረት መንፈግ የለብንም፤፤ እንዲያውም “chaos theory” የሚወግነው ለአሌክስ ነው፡፡ ይህ ንድፈ ሀሳብ “ቻይና ውስጥ የሚስተዋል የትንሿ ቢራቢሮ እርግብግቢት ኒውዮርክ ውስጥ ለኃይለኛ አውሎ ነፋስ መፈጠር መንስኤ ሊሆን ይችላል” የሚል ነው፡፡ እናም የአቦካዶው ጣጣው ከሐዋሳም አልፎ ለኢትዮጵያም ሊተርፍ ስለሚችል የፎቁ እርዝመትና የመንገዱ ስፋት ዘለቄታዊ ደስታን እንዲያጎነጽፈን ከፈለግን፣ ለአቦካዶው ጉዳይ እኩልና ፍትሐዊ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ሰማይ ጠቀስ የኒውዮርክ ህንጻዎች የሚቆረቆር የቻይናዊያን ቢራቢሮ እንቅስቃሴ በአትኩሮት የመከታተል ኃላፊነት አለበት!ቅዱስ መጽሐፉም ቢሆን ጥቂቱ እርሾ ሊጡን ያቦካል ብሎ የለs
በኪነ ህንጻውና በከተማ ፕላን ዘርፍም ቢሆን የአሌክስ መጽሀፍ የያዘችው ዕምቅ ዕውቀት የዋዛ አይምሰለን! ለምሳሌ ገጽ 45 ላይ ሙሉጌታ የተባለው ገጸ ባህሪይ ለጭቃ በተደለደሉ አቧራ የለበሱ ድንጋዮች ላይ ያለ ስህተት እንደሚጓዝ የተገለጸው ኬቪን ሊንች የተባለ አሜሪካዊ የከተማ ፕላነር "The Image Of city" በተሰኘው ድንቅ መጽሃፉ ውስጥ አዕምሮአዊ ካርታ (mental map/Image) እያለ የሚያነሳው ሀሳብ ነው፡፡ ዳዊት ንጉሱ "መንደር ፣ቀዬ ፣ምንትስ" እያለ ያጥላላው ሐሳብ በራሱ በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አሜሪካ ኒውዮርክ ውስጥ እንደ ጄን ጃኮብስ ያሉ የህዝብ መብት ተከራካሪዎች ከ400 ቤቶች በላይ ለመኪና መንገድ ሲባል ያለ አግባብ እንዲፈርሱ ትዕዛዝ በተሰጠበት ወቅት ፍርድ ቤት በመከራከር ያሸነፉት ይህን የመንደርተኝነት ጽንሰ ሐሳብን (neighbourhoodness) ተጠቅመው ነበር፡፡ ጄን ጃኮብስ ዕውቅናን ባተረፈችው መጽሀፉዋ (The life and Death of Great American cities) ውስጥ ጉርብትና ስለሚያበረክተው ማህበራዊ አስተዋጽኦ ልክ እንደ እኛው ዓለማየሁ ገላጋይ አውርታ አትጠግብም! ከአሌክስ አጥቢያ መጽሐፍ ሌላም የምንማረው እውነት አለ፣ እ.ኤ.አ. ከ1970ዎቹ በፊት የከተማ ፕላን ዝግጅት አሳታፊ ያልነበረና በአንድ ሙያ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ነበር፡፡ አሁን ግን በሰለጠነው ዓለም የማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ባለሙያዎች ፣የስና ልቦና ባለሙያዎች፣የታሪክ ባለሙያዎች፣ የህዝብ ተወካዮች ወዘተ ሳይቀሩ በከተማ ፕላን ዝግጅት ወቅት ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰፈር በቂና አሳማኝ በሆነ ልማታዊ ምክንያት እንዲፈርስና ነባር ኗሪዎችም ወደ ሌላ አካባቢ እንዲዛወሩ ሲወሰን ወደ ተፈናቃዮቹ በቅድሚያ የሚላኩት አፍራሽ ግብረ ኃይሎች ሳይሆኑ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ናቸው፡፡ የአሌክስ አጥቢያ መጽሀፍም በውስጧ በሀገራችን የጉርብትናን እሴት በተመለከተ ተመሳሳይ ሥርዓትና ግንዛቤ ይኖር ዘንድ በለሰለሰ ድምጽ ጥሪዋን የምታስተላልፍ አትመስልምs
ወደፊት ጊዜና ሁኔታ ከፈቀደ ከአሌክስ አጥቢያ መጽሀፍ ጋር በተገናኘ ከላይ የተነሱትን ሀሳቦች በስፋት ለመዳሰስ እሞክራለሁ! ግን አንድ ነገር አልረሳሁም….. ዳዊት ንጉሱ ረታን እከስሰዋለሁ!

Read 3672 times