Saturday, 24 November 2012 11:33

ሊፋን ሞተርስ እየተስፋፋ ነው Featured

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(7 votes)

“የኢትዮ ታለንት ሾው” አሸናፊ “ሊፋን 320” ሞዴል ይሸለማል
በሊፋን ሞተርስ የሚገጣጠሙ መኪኖች ተፈላጊነታቸው እየጨመረ በመምጣቱ ኩባንያው የማስፋፊያ ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን በቅርቡ የመገጣጠሚያ ፋብሪካውን ወደ ዱከም እንደሚያዛውር ተገለፀ፡፡
የኩባንያው የፕሮሞሽን ማናጀር አቶ የንኤል ታምራት ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ኢስት ኢንዱስትሪ ዞን ተብላ በምትጠራው ዱከም በ20ሺ ካ.ሜ መሬት ላይ የመገጣጠሚያ ፋብሪካውን እየተገነባ ሲሆን ከ300 በላይ የተለያዩ ሞዴሎች ያሏቸው የሊፋን መኪኖች በጅቡቲና በሞጆ ደረቅ ወደብ በመግባት ላይ ይገኛሉ፡፡

ኩባንያው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የስራ ሰዓቱን ወደ 24 ሰዓት ከፍ እንዳደረገና በቀን የሚገጣጥማቸውን መኪኖች ብዛት በእጥፍ በማሳደግ ከስድስት ወደ 12 ማድረሱን አቶ የንኤል ገልፀዋል፡፡ 
በመጪዎቹ ጥቂት ወራት የሽያጭ ቅርንጫፎቹን ወደ አራት ለማሳደግ እንደዚሁም ሁለተኛውን የጥገናና የሰርቪስ ጣቢያ ለመክፈት ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀም ታውቋል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ የሊፋን የሽያጭ ቅርንጫፎች በሃዋሳና በመቀሌ ከተሞች እንዳሉ የገለፁት ፕሮሞሽን ማናጀሩ፤ አራተኛ ቅንርጫፉን ከሁለት ወር በኋላ በድሬዳዋ እንደሚከፍት ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው የመኪኖቹን መለዋወጫ አቅርቦት ለማቀላጠፍ “ሳትኮን” ለተባለ የግል ድርጅት ፈቃድ መስጠቱ የታወቀ ሲሆን ደንበኞች ከዚሁ ድርጅት ሊፋን መለዋወጫዎችን በሚያቀርብበት ዋጋ መግዛት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
ከህዳር 13 እስከ ጥር 6 ቀን 2005 ዓ.ም ባለው ጊዜ መኪኖች ለሚገዙት ደንበኞች ሊፋን ልዩ የሎተሪ ዕጣ ማዘጋጀቱን የገለፁት አቶ የንኤል፤ ሎተሪው በደቡብ አፍሪካ የሚደረገውን 29ኛ የአፍሪካ ዋንጫ ለሚታደሙ ሦስት ባለዕድሎች የአውሮፕላን የደርሶ መልስ ትኬት ያሸልማል ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በአምባሰል ሙዚቃና ፊልም አሳታሚ እየተዘጋጀ በኢቲቪ 3 ለሚተላለፈው “ኢትዮ-ታለንት ሾው” አሸናፊ ሊፋን ሞተርስ 250ሺ ብር የሚያወጣ “ሊፋን 320” አውቶሞቢል እንደሚሸልም የኩባንያው ፕሮሞሽን ማናጀር ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
የአምባሣል ሙዚቃና ፊልም አሳታሚ ባለቤት አቶ ፍቃዱ ዋሪ በአገራችን ብዙ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች ለማፍራት መሰል ሽልማት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ዛሬ ቅዳሜ የ16ኛ ሳምንት ፕሮግራሙን የሚያቀርበው “ኢትዮ ታለንት ሾው” ከሊፋን የሚያገኘው ሽልማት ፕሮግራሙንም እንደሚያነቃቃና ተወዳዳሪዎቹን እንደሚያበረታታ በመግለጽ “ምስጋና የሚገባው ስጦታ ነው” ብለዋል - አቶ ፍቃዱ ዋሪ ለአዲስ አድማስ፡፡

Read 3871 times