Saturday, 24 November 2012 12:05

የምርጫ ሰሞን የፖለቲካ ትራፊክ ይበዛል!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(3 votes)

ሰሞኑን ድምፃቸው ጠፍቶ የከረሙትን ፖለቲከኞች ድምፅ ስሰማ ደስ አለኝ፡፡ (ውዝግብ ባይሆንማ!) ጥሎብኝ የተቃዋሚዎች አንደበት ከተዘጋ ደስ አይለኝም፡፡ ደስ አይለኝም ብቻ ሳይሆን ይከፋኛል፡፡ (ወገን አይደሉም እንዴ?) የተቃዋሚ ደጋፊ ሆኜ ግን አይደለም፡፡ በቃ… የተቃዋሚ ድምፅ ከታፈነ የአገሬ ድምፅ የታፈነ ይመስለኛል (ተሳስቼ ይሆን?) ግን በቃ ምን ላድርግ… ተፈጥሮዬ ነው፡፡ የነፃ ፕሬስ ድምፅ ከታፈነም አይደላኝም… አብዮተኛ ወይም የነፃነት ታጋይ ሆኜ ግን አይደለም… የፕሬስ ድምፅ ከተዘጋ የአገሬ ድምፅ የተዘጋ ስለሚመስለኝ ብቻ ነው፡፡ (አይዘጋም እንጂ የኢህአዴግም ድምፅ ሲዘጋ ቅር ይለኛል) ለዚህ ነው በዚያ ሰሞን አንድ ሁለት ጋዜጦች ሲዘጉ ድብር ያለኝ፡፡

እኔ የምለው… አንዳንድ የመንግሥትና የግል ማተሚያ ቤቶች ቢዝነሳቸውን ትተው የፖለቲካ ፓርቲ የማቋቋም ሃሳብ አላቸው እንዴ? ለምን መሰላችሁ… ጋዜጣ፣ መፅሄት ወይም መፅሃፍ የሚያሳትም “ፖቴንሻል ከስተመር” ሲመጣ የፖለቲካ ጀርባውን ያጠኑና “አናትምም” ይላሉ አሉ፡፡ (ስም አልጠቅስም) ጋዜጣው ወይም መፅሄቱ እኮ በህቡዕ (underground) የሚሰራጭ አይደለም፡፡ የትጥቅ ትግል የሚያካሂድ ድርጅት ልሳንም አይደለም፡፡ አንዱ ደመ-ሞቃት ካድሬ “እንዴት አወቅህ?” ብሎ ሊያፈጥብኝ እንደሚችል ከተመክሮዬ አውቀዋለሁ፡፡ ስለዚህ መልሴን ጣል አድርጌ ልለፍ - እግረ መንገዴን፡፡ እስካሁን ማተምያ ቤቶች አናትምም ብለዋቸው የቆሙ ወይም የተስተጓጐሉ የፕሬስ ውጤቶች ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስት የፕሬስ ስራ ፈቃድ የሰጣቸው ናቸው፡፡ ያለፈቃድ እያተሙ ከሆነማ … ተጠያቂው በብርድ ተሰልፈን የመረጠነው መንግስታችን ነው (“መንግስታችን” ቁልምጫ ነው እንዴ?) 
አንዳንዴ ኢህአዴግ (ፓርቲው ሳይሆን መንግስታችን) በጣም ያስገርመኛል፡፡ እንዴ … ራሱ ፈቃድ የሰጣቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች እኮ ነው “ሽብርተኛ” ምናምን እያለ በአደባባይ የሚፈርጀው፡፡ አሃ… ሽብርተኛ ከሆኑ ፈቃዳቸውን ተቀብሎ በአገሪቱ ህግ መሰረት ይጠይቃቸዋ! በአንድ በኩል ህጋዊነት ሰጥቶ በሌላ በኩል መወንጀል ምን ይባላል? (ህጋዊነትና ህገወጥነትን ማጣቀስ እኮ ነው!) ኢህአዴግ “ወደ ደቡቡ” ስለሆነ ምናልባት አዝኖላቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ክፋቱ ግን ማንም ደግ የሚለው የለም (“ሽብርተኛ” ብሎ ከፈረጁ ወዲያ ደግነት የለማ!)
እናላችሁ… እዚህችው ሸገር እምብርት ላይ የቢዝነስ ሀሁ (Business 101) ያልገባቸው ማተምያ ቤቶች አሉና ስፖንሰር አፈላልጌ የቢዝነስ አሰራር ዎርክሾፖች ላዘጋጅላቸው አስቤአለሁ፡፡ ለእነሱ አዝኜላቸው እንዳይመስላችሁ!! ለአገሬ ብዬ ነው፡፡ ነፃ ፕሬስ ሲታፈን አገሬ ትታፈናለች አላልኳችሁም፡፡ እኔ ኢህአዴግን ብሆን ግን ጉድ እሰራቸው ነበር፡፡ እንዴ… ኢህአዴግ ከታገለላቸው ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ የሆነውን እኮ ነው የነኩት፡፡ (“ሳንሱር” ሊጀምሩ ምን ቀራቸው?) አሁን እነዚህ ወዳጅ ናቸው ጠላት? እናም እኔ ኢህአዴግን ብሆን የማተምያ ቤት ፈቃዳቸውን እቀበልና የፖለቲካ ፓርቲ ፈቃድ አሽራቸው ነበር! (ያለፊልዳቸው ነዋ የገቡት!) ያኔ እየተቅለሰለሱ የገዥው ፓርቲ ደጋፊዎች መሆናቸውን ይደሰኩሩ ይሆናል፡፡ (ኢህአዴግም ቢሆን ህገ መንግሥት የማያከብር ደጋፊ ምን ይሰራለታል?)
በዚህ አጋጣሚ ለወዳጄ ኢህአዴግ ትንሽ ምክር ቢጤ ጣል ባደርግለትስ… ወደደም ጠላም የጥንቱን የአባልነት መስፈርት መቀየር ሳይኖርበት አይቀርም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለምን ቢባል… ዘመኑ ተቀይሯላ! ለአባልነትና ለደጋፊነት ታማኝነት ብቻ አይበቃም ይላሉ - የፖለቲካ ፓርቲ በመገንባትና በማፍረስ የብዙ ዓመት ልምድ ያላቸው አንድ የፖለቲካ መሐንዲስ፡፡ ሰብእናና ብቃትም ወሳኝ መሆኑን ፓርቲው ማወቅ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግ እኔን ካላመነኝ በሙስና ተዘፍቀው ወህኒ የገቡትን የራሱን ሹመኞች (ታማኝ አባላት) መመልከት ይችላል፡፡ (የፓርቲ ታማኝነት ከሙስና ነፃ አያደርግም!)
ወደቀደመው ጨዋታዬ ልመልሳችሁ… እንዳልኳችሁ የተቃዋሚዎች ድምፅ ሲሰማ ደስ ይለኛል - “አገር አማን!” ይመስለኛል፡፡ እነሱ ትንሽ የሚያስፈሩኝ መቼ መሰላችሁ? የምርጫ ሰሞን ነው! እንዴት አትሉም? ሁሉም ምርጫ ሲቃረብ ጐማና ፍሬናቸው ይበላሻል… በቃ ዜሮ ይሆናል (flat!) ለነገሩ የኢህአዴግም ጐማና ፍሬን ያው ነው (እንደውም ባይብስ!) አያችሁ … በሰላሙ ጊዜ ጐማና ፍሬናቸውን ቢያሰሩት እኮ ለአደጋ አይጋለጡም ነበር፡፡ (ማስተዋል ይሰጣቸው!)
እኔ የምለው … የምርጫ ሰሞን ሁሉም የፖለቲካ ሹፌር ልሁን እንደሚል ታዝባችሁልኛል፡፡ ስለዚህ እኮ ነው ትራፊኩ የሚጨናነቀው፡፡ እናም የፖለቲካ አደጋ ይበዛል፡፡ ልምድ ያለውም ለማጁም የፖለቲካ ሹፌር፤ የማሽከርከር አባዜው ስለሚነሳበት በተለይ የእኔ አይነቱ እግረኛ ለግጭት አደጋ ይጋለጣል፡፡ (ፖለቲከኛ ባይሆንም) በዚህ ወቅት ከተቻለ በርን ከርችሞ ቤት መቀመጥ ይመከራል - ትራፊኩ ቀለል እስኪል፡፡ (ምርጫው እስኪያልቅ ማለቴ ነው)
እኔማ ትንሽ የፋይናንስ ችግር ገጥሞኝ ነው እንጂ አደጋውን የሚቀንስ ምርጥ የቢዝነስ ሃሳብ ነበረኝ፡፡ ፈቃደኛ ባለሃብት (Risk – taker መሆን አለበት!) ከተገኘ በሽርክና መስራት እፈልጋለሁ (እኔ በሃሳቤ፤ እሱ በገንዘቡ) ቢዝነሱ በተለይ ገበያው የሚደራው የምርጫ ሰሞን ቢሆንም ሌላ ጊዜም አይሞቅ አይደምቅ ይሆናል እንጂ ጦም አያሳድርም (ያተርፋል ማለቴ ነው) የቢዝነስ ሃሳቡን ልንገራችሁ አይደል? (ፓተንት ስላለኝ ሃሳቤ ይሰረቃል ብዬ አልሰጋም) ይኸውላችሁ … እኔ ማቋቋም የምፈልገው ቢዝነስ “የፖለቲካ አሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም” ነው፡፡
ይሄ ቢዝነስ ዘርፈ ብዙ ትርፍ እንዳለው የገበያ ቅኝቴ ይጠቁማል፡፡ ከሁሉም ደስ የሚለው ደግሞ ከቢዝነሱ የምንጠቀመው እኔና የቢዝነስ ፓርትነሬ ብቻ ሳንሆን አገሩ በሙሉ ነው፡፡ (ኢህአዴግን ጨምሮ) አያችሁ ስልጠናው ያነጣጠረው የፖለቲካ ሹፌሮች ላይ ስለሆነ በምርጫ ሰሞን የሞትና የአካል ጉዳት እንዲሁም የእስርና የመዋከብ አደጋዎች ይቀንሳሉ፡፡ በእርግጥ የፓርቲ ደጋፊዎችም ቀስ በቀስ ሥልጠናውን የሚያገኙበት ሁኔታ ይመቻቻል፡፡ (እግረኞችም ሥልጠና ይፈልጋሉ) የፖለቲካ ሹፌሮች ብቻ ቢሰለጥኑ ደጋፊዎች መንገድ የመሻገር ግንዛቤ ከሌላቸው ዋጋ የለውማ፡፡ ከሰለጠኑ ግን የጐዳና ላይ “ነውጥ” ስጋታችን ይቀንሳል፡፡ አያችሁ… በዚህች ዘዴ “ልማታዊ ባለሃብት” ልሆንላችሁ ነው (“ልማታዊ ባለሀብት” እንዴት ያለ ነበር?) ልማት ላይ የሚሰራ ባለሃብት ነው አይደል (በደምሳሳው!) ኪራይ ሰብሳቢስ? “ጥፋት” ላይ የሚሰራ ባለሃብት እንዳትሉኝ ብቻ… ለእኔ ጥፋት ላይ የሚሰራ “ፀረ-ልማት” ባለሃብት ነው፡፡
እኔ የምላችሁ… በዘንድሮ ምርጫ ተቃዋሚዎች “የመወዛገብ ስታይላቸውን” ቀየሩ አይደል? ሌላ ጊዜ ምርጫ ሲመጣ እኮ ከዋና ተፎካካሪያቸው ከባለ ከባድ ሚዛኑ ኢህአዴግ ጋር ነበር “ይዋጣልን!” የሚሉት፡፡ አሁን ግን ከኢህአዴግ ጋር “ድርድር” አሉና ከምርጫ ቦርድ (የምርጫ ትራፊክ ፖሊስ ብየዋለሁ) ጋር ሊቧቀሱ 34 ሆነው ተቧድነዋል፡፡ ምን እንደፈራሁ ታውቃላችሁ… ተቃዋሚዎችና ኢህአዴግ ግንባር ፈጥረው ምርጫ ቦርድን “ወግድ!” እንዳይሉት (ምርጫ ባስከበረ?)
አንድ ያልገባኝ ነገር ግን አለ፡፡ 34 ተቃዋሚዎች የተቧደኑት ለምርጫው ነው ወይስ ሌላ አላማ አላቸው? (በዙብኛ!) ለእኔማ መብዛታቸው ደስ ይለኛል፡፡ ገበያዬ ይደራላ! ኢንቨስተር ተገኝቶ የማሰልጠኛ ተቋሜን ከከፈትኩ እኮ ቢያንስ 34 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተንጋግተው ይመጡልኛል፡፡ ግን ሁለት ማሳሰቢያዎች አሉኝ፡፡ “ውዝግብና ዱቤ አይፈቀድም!” እውነቴን ነው ሰልጣኞችን በዱቤ አላሰለጥንም! ለምን መሰላችሁ… ከምርጫው በኋላ አብዛኞቹ ፓርቲዎች ወይ ይዘጋሉ አሊያም ይሰደዳሉ ወይም ደግሞ ይታሰራሉ (ሰዶ ማሳደድ አትሉም!) ለኢህአዴግ እንኳ ዱቤ ብሰጥም ችግር የለውም (ከአራት ኪሎ የት ይሄዳል?) በሉ ፓርትነር የሚሆን ባለሃብት ላፈላልግ መሄዴ ነው፡፡ ውጤቱን ሳምንት እነግራችኋለሁ፡፡

Read 3124 times