Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 24 November 2012 13:05

የክሱ ቻርጅ ተተርጉሞ በአማርኛ ይቅረብልኝ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አስቀድሜ የተከሳሽነት ድምፄን ላሰማ!
እነሆ በዛሬ ሳምንቱ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በቁጣ ገንፍለው ድንገተኛ ክስ የመሰረቱብኝ የኬሚካል ኢንጅነሪንግ ባለሙያው ጌታሁን ሄራሞ፤ የክስ ጭብጣቸውን ለማጠናከር 130 የእንግሊዘኛ ቃላትን በመጠቀም፤ አምስት የውጪ አገራት መፃህፍትን በማጣቀስ፤ የአራት ታዋቂ ናቸው ያሉትን የውጪ ደራሲዎች ስም ጠቅሰውና የሁለት ፈላስፋዎችን ስም መርቀው ሙግትህ ትክክል አይደለም የሚል ክስ አቅርበውብኛልና የተከሰስኩበትን ምክንያት ሙሉ በሙሉ ጠንቅቄ እረዳው ዘንድ፣ የክሱ ቻርጁ ሙሉ በሙሉ በአማርኛ ተተርጉሞ እንዲቀርብልኝ አቤት እላለሁ፡፡ በመቀጠል ወደ ፍሬ ነገሩ ልመለስ፡፡

የድህነት ነገር!
የአራት ኪሎና ሌሎች ተመሳሳይ አካባቢዎች መፈረስ ቢያንስ ጉርብትናን ወይም ማህበራዊ ኑሮን ከማፍረሱ አንፃር ተገቢ አይደለም ብለን ልንከራከር እንችል ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን ከዚህ ወጣ ብለን ሰፋ ባለ ምዘና የጉዳዩን ስረ-መሰረት በጥልቀት መመልከትና ተገቢውን ሚዛናዊ ፍርድ ለህሊናችን መስጠቱ ደግሞ የበለጠ ሐቀኛ ተከራካሪ ያደርገናል፡፡ ለምሳሌ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት ለድህነት የተሰጠውን ሰፊ ትርጉም በጥሞና በመመልከት፣ ስለአራት ኪሎዎችና ስለሌሎችም መፍረስ ስለሚጠበቅባቸው አካባቢዎች በዝርዝር እንነጋገር፡፡
ድህነት ብዙ ገፅታዎች አሉት፡፡ በዝቅተኛ ገቢም ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ ድህነት ዝቅተኛ ገቢን ከማግኘት በተጨማሪም አነስተኛ የጤናና የትምህርት ሽፋን፤ የእውቀትና የግንኙነት መነፈግ፤ ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶችን በተገቢው መንገድ መጠቀም አለመቻል፤ በራስ የመተማመን ስሜት መጥፋትና ለገዛ ራስ ከበሬታ አለመስጠት መቻል እነዚህ ሁሉ የሚንፀባረቁበት ሁኔታ ነው፡፡ምሳሌ ከ“አጥቢያ” መፅሃፍ፤ ሸርሙጣ ተብላ የተሰደበች ሴት መልሷ የቆንጆ ወጉ ነው፡፡ (ይሔ ነው እንግዲህ ለራስ ያለ ክብርና በራስ መተማመን ማለት) ለድህነት ትርጉም ስንሰጥ በቁሳዊ ሃብት ማጣት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን የኢኮኖሚ፣ የቴክኒክ፣ የማህበራዊና ፖለቲካዊ እውቀት የማግኘት መብት ማጣትንም ማጠቃለል አለበት፡፡ ባጠቃላይ ድህነት ማለት ችሎታና ብቃትን መነጠቅ ነው!

አራት ኪሎ በድህነት ትርጓሜ እይታ
አራት ኪሎ ከጉርብትና በፊት ብዙ ልታስቀድማቸው የሚገቡዋት የቤት ስራዎች ነበሯት፡፡ “አጥቢያ” በዓለማየሁ ገላጋይ አማካኝነት ቁልጭ አድርጐ እንዳሳየን፡፡ ለራሳቸው ክብር የማይሰጡ፤ እጅግ አነስተኛ የሆነ የጤና ሽፋን የነበራቸው፤ እርስ በርስ በአንድ አካባቢ ተፋፍነውና ተጨናንቀው የሚኖሩ፤ በኤች አይቪ ኤድስ ከማንም በላይ የረገፉ፤ በትምህርት ተቋማት ቢከበቡም እነርሱ ግን በትምህርታቸው ያልገፉ፤ ችሎታና ብቃታቸውን ተነፍገው ቀኑን ሙሉ ጫት ሲያኝኩ የሚውሉና እንደ አለማየሁ ገላጋይ የ“አጥቢያ” መፅሃፍ አገላለፅ ለምሽቱ አሸሼ ገዳሜ የሚዘጋጁ፤ ዛሬ ፍንትው ብለው በርተው ካየናቸው በኋላ ነገ የማንደግማቸው ዜጐች የሞሉባት አራት ኪሎ ራሷ አፍ በማውጣት “ኧረ ድረሱልኝ ልጆቼንም ታደጉልኝ” ብትልስ ምን ያስደንቃል?
አራት ኪሎ የቤተመንግሥቱ መቀመጫ ከመሆንና የመንግስት ግልበጣም ሆነ በመንግስት ላይ የሚነሳ ተቃውሞ በተፈጠረ ቁጥር ነዋሪዎቿ በጥይት አረር ከመጠበስና በከባድ መሳሪያ ጩኸት ከመደናበር ውጪ ያተረፉት ነገር አልነበረም፡፡ ለአራት ኪሎ ወጣቶችም ዘመናይነቱና ከተሜነቱ ህይወታቸውን ባጭር ቀጨባቸው እንጂ የስኬት ጫፍ ላይ አልሰቀላቸውም፡፡

ከተሜነት
ከተሜነት ሊፈጠር የሚገባው ሰዎች የሚኖሩበት አካባቢ ከከተማው ቅርብ በመሆኑና ባለመሆኑ አይደለም፡፡ ማንም የትም ቢኖር ቁምነገሩ ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በቅርበትና በተሟላ ሁናቴ ማግኘቱ ላይ ነው፡፡ የከተሜነት ትርጉም መጀመሪያ መሰራት ያለበት በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ነው፡፡ ከተሜነት ለከተማዋ ቅርብ በሆነ አካባቢ በመኖር የሚወሰን ቢሆን ኖሮ እንደ አራት ኪሎዎች ማንስ ይጠቀም ነበረ? ሆኖም ግን ህይወት፤ ከተሜዎች አሪፎቹ፣ አራዶቹ ወዘተ… ብለን ለምናስባቸው አራት ኪሎዎች ጀርባዋን ሰጥታቸው ቆይታለች፡፡ ሰብአዊ ክብራቸው ተገስሶ ከሞቱት በላይ ከቆሙት በታች በመሆን ለዘመናት አስከፊ ህይወት ገፍተዋል፡፡ የአራት ኪሎን የዚያን ጊዜዋን የድረሱልኝና ነዋሪዎቼን ታደጉልኝ ጩኸት ዛሬ የአውቶብስ ተራዋ አካባቢ ሰባተኛ ተብላ የምትጠራው ሰፈር እያሰማች እንዳልሆነ ማን ያውቃል? ቺቺኒያስ በዚህ ጉዳይ ምን ትል ይሆን? ወዘተ …
እነዚህ አካባቢዎች ከተሜ ተብለው እየተጠሩ ሆኖም ግን ነዋሪዎቻቸውን በአንድም በሌላም መንገድ ወደ መቃብር በቀን በቀኑ እየሸኙ ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ አካባቢ ነዋሪዎች እውነተኛውን መሪር የሕይወት ፅዋ እየተጐነጩ፣ ሆኖም ግን ታሪካቸው ለተለያዩ አዳዲስ መፅሃፎችና ፊልሞች መፈጠር ምክንያት እየሆኑ ነው፡፡ (ከመፅሃፍ መሀልየ መሀልየ ዘ ካሳንቺስ፤ የቺቺኒያ ሚስጥሮች፤ የአዲስ አበባ ጉዶች ወዘተ ሼፉና ስሌትን የመሳሰሉት ደግሞ ከፊልም) ታዲያ ከከተሜነት የተረፈው ነገር ይሄ ብቻ ከሆነ፣ የጉርብትናና የሰፈር አድባር መጨረሻው ክፉ ሞት ከሆነ፣ አራት ኪሎ አንድ ጊዜ ብቻም ሳይሆን አስር ጊዜ ብትፈርስም አይበዛባትም፡፡እኔም ብሆን ስድስት ኪሎ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ከአንበሳ ጊቢው ጀርባ ተወልጄ ያደግሁኝ ነኝ፡፡ አራት ኪሎንም ጠንቅቄ አውቃታለሁ፡፡
ለእኔ የልጅነትና የጉርምስና ወቅት ትዝታ ሲባል አራት ኪሎ ባትፈርስና ያንኑ መልኳን ጠብቃ ብትኖርልኝ ምንኛ በወደድኩ፡፡ ነገር ግን ይሄ ቅርስን ጠብቆና ተንከባክቦ የማቆየት ነገር አይደለም፡፡ እያወራነው ያለነው ስለሰዎች ከውሻ ጋ ተመሳስሎ ኑሮ ነው፡፡ አራት ኪሎ የእኔው የእትብት መቀበሪያ ሰፈር ስድስት ኪሎ ትክክለኛ ግልባጭ ነች፡፡ ዛሬ የእኛ ሰፈር ለእኛ እዚያው ተወልደን ላደግንባት ልጆች፣ ከተሜዎች፣ አሪፎች … የሰጠችውን ምላሽ ስመለከት ያለማንም የስነ ልቦና ምሁር ወይንም የማህበረሰብ ጥናት አጥኚ ድጋፍ እኔው እራሴ ከኑሮ በተማርኩት ተሞክሮዬ፣ አዎን እነዚያ አራት ኪሎን መሳዮቹ የሰፈሬ ግልባጮች አሁንም እንዲፈርሱና ነዋሪዎች ወደተሻለ ከተሜነት እንዲለወጡ ምኞትም ፀሎትም አለኝ፡፡ ደግሞም ሰው ሰፈሩን ከለወጠ ከሌላ ሰፈር ሰው ጋር አይኖርም፣ ያውም ኢትዮጵያዊውን ማለት የማይዋጥ ሃቅ ነው፡፡
ስለ ኑሮ ለማውራት የሂስ መመዘኛን ማሟላት ያስፈልጋል?
ኬሚካል ኢንጂነር ጌታሁን ሄራሞ ከመደበኛ ስራቸው ጐን ለጐን ስለሂስ ህየሳ ብዙ ነገር እንደተገነዘቡ ከጠቃቀሱልኝ መፃህፍትና አባባሎቻቸው ለመረዳት አልተሳነኝም፡፡ የአለማየሁን “አጥቢያ” መፅሃፍ የድህረ ዘመናዊነት እሳቤ አለመረዳቴን መናገራቸውም አልጠላሁትም፡፡
ይልቁንስ የእኔ ተሟጋችነት ከኑሮና ከኑሮ አንፃር ብቻ የተፈጠረ፤ ባየሁት በሰማሁት፤ ባነበብኩትና በኖርኩበት ኑሮ ሁሉ የተቃኘ ክርክር መሆኑን ስላልተገነዘቡልኝ መጠነኛ ቅሬታ አድሮብኛል፡፡
ለመሆኑስ ግን አለማየሁ ገላጋይ በ“አጥቢያ”ና በሌሎቹም ፅሁፎቹ የተጐሳቆሉ መንደሮች መፍረስ ተገቢነት የለውም የሚል አይነት እሳቤ ያለውን አስተሳሰቡን ለመሞገት ስነሳ፣ ስለሂስ ጥልቅ ትንተና መስጠትና የትክክለኛ ሂስ አሰጣጥ አስሩ መመሪያዎች የሚሉ አይነት መፃሃፍቶችን ማንበብና ዋቢ መጥቀስ ይጠበቅበኛል እንዴ? ጉድ እኮ ነው!
ይህ ጉዳይ የዜጐች ጉዳይ ነው፡፡ በዜጐች ጉዳይ ላይ ደግሞ ማናችንም በማናቸውም ደረጃ ላይ የምንገኝና ያገባኛል የምንል ሁሉ (እኔንም ኬሚካል ኢንጂነሩንም ጨምሮ ማለቴ ነው) የበኩላችንን አስተዋፅኦ ልናደርግ ይገባናል፡፡ ከዚህ የማይናወጥ አስተሳሰቤ በመነሳት የአለማየሁ ገላጋይ አስተሳሰብ መቋጫቱ የቱ ጋ ነው? ማለቴ ኢንጂነሩን በድንገት አገንፍሎ በማስነሳት “ዳዊት ንጉሡ ረታን እከሰዋለሁ” በማለት ያዛታቸው ነገር አልተገለፀልኝም፡፡

ዓሳ አትስጠው፤ ዓሳ
አጠማመዱን ግን አሳየው!
ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከድህነት ለመውጣት ከፈለግን ዓሳ የመስጠት ተግባሩን (ምንም እንኳን ለፅድቅም ቢሆን) ቆም አድርገን፣ በዓሳ አጠማመድ ተግባር ላይ ዜጐችን ማሰማራቱ ግድ ይለናል፡፡
ራሳቸውን ቸርችረው ለሚኖሩ የአራት ኪሎ ሴተኛ አዳሪዎች፤ አረቄ እየሸጡ ኑሮን ለሚደግፉ ደካሞች፤ አንዲቷን የቤታቸውን ክፍል አከራይተው እነርሱ ግን ከነልጆቻቸው ቆጥ ላይ በመተኛት ቤቱን የተከራዩት ሴተኛ አዳሪዎች ደንበኞቻቸውን ሲያስተናግዱ እየሰሙ የሚያድሩ ዜጐችን ሁልጊዜ ዓሳ በማቅረብ ብቻ ልንታደጋቸው አንችልም፡፡ ዓሳ አጠማመዱን በማስተማርም ጭምር እንጂ!
ለዚህም ደግሞ በቅድሚያ እነዚያ በ4 ኪሎ በአንድ አካባቢ ተከማችተው በድህነት ሲማቅቁ የነበሩ ዜጐች ድንገተኛ የእሳት አደጋ ቢነሳባቸውም፤ ወይንም ደግሞ አንዳች ተላላፊ የሆነ በሽታ ቢከሰት ሊከላከሉት ከማይችሉበት ከዚያ ለኑሮ እጅግ አደገኛ ከሆነ መንደር ማውጣቱና ወደተሻለ አካባቢ ማስፈሩን አሁንም አፈፃፀሙ ህጋዊነትን እስከተከተለና የነዋሪዎቹን ሰብዓዊ ክብር እስከጠበቀ ድረስ ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ አመዛኝ ነው፡፡
ከዚያ በኋላ ደግሞ ዜጐቹን ዓሳ የማጥመድ ተግባር ላይ እንዲሰማሩ የማስቻል የመንግሥትም ሆነ የሌሎችም የሚመለከታቸው ሁሉ አካላት ሃላፊነት ይሆናል፡፡ መጀመሪያ ግን መቀመጫዬን እንዳለችዋ አንዲት እንስሳ የአራት ኪሎ ነዋሪዎች ዘግይቶም ቢሆን ለሰው ልጆች ክብር ወደሚመጥን አካባቢ መሸጋገራቸውን እንዲያውም የነፍስ አድን ስራ አድርጐ ማየት እንደሚቻል ነው እኔ የምገነዘበው፡፡

ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም
125ኛ የምስረታ በአልዋን ሰሞኑን እያከበረች የምትገኘዋ ዋና ከተማችን አዲስ አበባ፣ ለዘመናት ካንቀላፋችበት በመንቃት በተለይም በመንገድ ግንባታና በኮንዶሚኒየም ቤቶች ልማት ዘርፍ በአይን የሚታዩ መጠነኛ ለውጦችን እያሳየች ነው፡፡ ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውሉ ህንፃዎችም እዚህም እዚያም ብቅ ብቅ ሲሉ አስተውለናል፡፡ ይህቺ የአፍሪካም ጭምር ከተማ ተብላ የምትጠራዋ አዲስ አበባ፣ ምርጫ 97 እግዚአብሄር ይስጠውና ከእንቅልፍ እንድትባንን ረድቷታል፡፡
ሬ መንግስት ከግብርና መር ኢኮኖሚው አይኑን መልሶ ስለከተሞችም ለመስራት ሲንፈራገጥ ስናየው “ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም” በሚል ተስፋ የበኩላችንን በየሙያችን እያበረክትን ብናበረታታ ሃጢያት የለውም፡፡
ይልቁኑስ በትራንስፖርት እጥረት ህዝቡ መንገድ ላይ እዚህም እዚያም እየተሰለፈ እያየንና እውነት አዲስ አበባ መንግስት አላት ብለን እንድንጠይቅ እየተገደድን፤ ሰዎች ውሃና መብራት ካገኘን አመታት ተቆጠሩ ብለው እያማረሩ፤ ሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት ነዋሪውን እያንገፈገፈው፤ ዲሞክራሲና የፕሬስ ነፃነት አይናችን እያየ አጠገባችን ሟሙተው እየጠፉብን ብዙ ልንል ብዙ ልንፅፍ፤ ብዙ ልንከራከር፤ ብዙ ጥብቅና ልንቆም ስንችል መንግስት እየተሳተፈበት ባለበትና በአንፃራዊነትም ሲታይ መልካም ጅምሮች የታዩበትን አሮጌ መንደሮችን የማልማት ስራን የምንቃወምበት መከራከሪያ ጉንጭ አልፋ ከመሆን እንደማይዘል ዛሬም በአቋሜ ፀንቼ በማስረገጥ እናገራለሁ፡
መክሰስና ማሰር… የዘመናችን አባዜ
አብዛኛው ፅሁፋቸው ከመከራከሪያ ነጥቡ ይልቅ በሂስ ስነ ምግባር ላይ ያተኮረው ፀሃፊው ኬሚካል ኢንጂነር ጌታሁን፤ በዘመናችን አባዜ ተጠምደዋል፡፡
በመክሰስና በማሳሰር! እኔን ያልደገፈ ከዚያኛው ወገን ነው የሚለው የጭፍን ድምዳሜ ከባድ ተፅእኖውን አድርሶባቸው አሌክስን ያላግባብ ሃይሰኸዋልና እከስሃለሁ ብለውኛል፡፡ ክሱ ላይ እንግሊዝኛ አበዙበት እንጂ፡፡እንግዲህ ህዝብ ከመሪው ይማራል አይደል? በሆነው ባልሆነው ዜጐችን መክሰስ፣ ማሳሰር፤ ማሳቀቅ፤ ማሸማቀቅ ወዘተ ይህ ሁሉ ዜጐች ከመሪዎቻቸው የሚማሯቸው ነገሮች አይደሉ? ኢንጂነሩም ከዚሁ ተመክሮ በመነሳት፣ እኔን ምስኪኑን ተከራካሪ እከሳለሁ በማለታቸው ጥያቄዬ ተቀባይነት አግኝቶልኝ፣ የክሱ ቻርጅ በአማርኛ ሙሉ በሙሉ ተተርጉሞ እንዲደርሰኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡

 

Read 5675 times Last modified on Saturday, 24 November 2012 13:14