Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 December 2012 11:19

ያበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም! የጃፓንን ጠባሳ ያየ በውሃ አይጫወትም! የአሜሪካንን ጠባሳ ያየ በንፋስ አይጫወትም!

Written by 
Rate this item
(4 votes)

አንድ የአፈ-ታሪክ ንጉሥ ህዝብ እያጉረመረመና እያደመ ሲያስቸግራቸው እንዲህ ያደርጉ ነበር አሉ፡፡
“እገደል አፋፍ ላይ ትልቅ ድንኳን ጣሉ” ይሉና ያዛሉ፡፡
“ከየት እስከ የት?” ይላቸዋል ባለሟሉ፡፡
“ህዝባችንን የሚይዘውን ያህል አስፍታችሁ ትከሉት”
“የዚያን የሚያህል ድንኳን ከየት እናገኛለን ንጉሥ ሆይ?”
“ቀጣጥላችሁም ቢሆን በሰፊው ስሩልኝ ብያለሁ፤ ብያለሁ፡፡ ይሄን ይሄንን መሥራት ካልቻላችሁ ለምን ሾምኳችሁ?!” ብለው ቱግ ብለው ይቆጣሉ፡፡

ባለሟሎቹ ሁሉ ይሸማቀቃሉ፡፡
አንደኛው ባለሟል እንደምንም ቀና ብሎ፤
“ለመሆኑ ይሄ ለምን አስፈለገን ንጉሥ ሆይ?” ሲል ይጠይቃል፡፡
“የዚህን ህዝብ ዝርያ ማጥፋት እፈልጋለሁ፡፡ አይታዘዝ፣ ልቡ አይታወቅ፣ ያወቀውን አውጥቶ አይናገር፤ ወይ በደንብ አይስቅ ወይ በደምብ አያለቅስ!... መቀጣት አለበት!”
“እንዴት ነው የምንቀጣው?” አለና ጠየቀ ሌላው፡፡
ንጉሡም፤
“የሚበላው በርካታ ምግብ፣ የሚጠጣው ጠጅ፣ ታዘጋጃላችሁ!”
“ለህዝቡ ሁሉ የሚበቃ ምግብኮ የለንም፡፡ ያን ያህል ምግብ ልንሰጠው የምንችል ከሆነማ ህዝቡስ ለምን ያጉረመርምብን ነበር?”
ንጉሡ ተቆጡ፡-
“አንተ ለህዝቡ ነው የቆምከው ለእኔ?! የምልህን በትክክል ካልፈፀምክ ለምን ሾምኩህ ታዲያ?”
ሁሉም እጅ ይነሱና “እሺ ንጉሥ ሆይ እንዳሉን እናደርጋለን!” ይላሉ፡፡
“ከዚያ” አሉ ንጉሡ “ጠጁን ጥምብዝ አድርጐ የሚያሰክር ታደርጉታላችሁ!”
“ለምን ንጉሥ ሆይ?”
“ጥንቢራው እስኪዞር ጠጥቶ ጥምብዝ እንዲል ነዋ!”
“ከዛስ? ንጉሥ ሆይ”
“የድንኳኑን መውጫ በር በገደሉ በኩል ታረጉታላችሁ! ያኔ በገዛ እጁ ገደል ይገባል፡፡ እኛ አበላን አጠጣነው እንጂ አልገፈተርነውም፡፡ ወዶ በላ! ወዶ ጠጣ፤ ወዶ ገደል ገባ!! አለቀ፡፡ እኛን አያስጠይቀንም!”
“እሺ ንጉሥ ሆይ!” እያሉ ተራ በተራ እጅ እየነሱ ወጡ፡፡
የተንጣለለ ድንኳን ተጣለ፡፡
ድል ያለ ድግስ ተደገሰ፡፡
ህዝቡ በገፍ መጣ፡፡ በገፍ በላ፡፡ በገፍ ጠጣ! ከዚያ እወጣለሁ ሲል ወደገደል እየወረደ ይንከባለል ጀመር፡፡
አንድ ብልህ ማየት የተሳነው ሰው ነበረ አሉ በከተማው፡፡ በሴት ልጁ እየተመራ ወደ ድግሱ እየመጣ ሳለ፣ እንዲህ ሲል ልጁን ይጠይቃታል፡-
“ልጄ ወደ ድንኳኑ ስታይ ምን ተመለከትሽ?”
“እረ አባዬ የሚገባ እንጂ የሚወጣ ሰው አይታየኝም”
“በይ እንግዲያው እንመለስ” ብሎ ወደ ቤት ይመለሳሉ፡፡
ድግሱ ሲያልቅ፤ ንጉሡ በደስታ ፍንድቅድቅ ብለው፤
“ለመሆኑ የቀረ ሰው ያለ ይመስላችኋል?” ሲሉ ጠየቁ፡፡
“ያ ማየት የተሳነው ፈላስፋ ብቻ ነው ያልመጣው” አለ አንዱ ባለሟል፡፡
ንጉሡ አዘኑ፤ ደነገጡና፤
“እዚህ አገር ከሚያየው የማያየው ይሻላል ማለት ነው!” አሉ፡፡
***
መሥራት ካልቻላችሁ ለምን ሾምኳችሁ ከሚል አለቃ ይሠውረን፡፡ መሥራት ሳይችሉ ሹመትን ለሹመት ብቻ ብለው ከሚቀበሉም ባለሟሎች ያድነን፡፡ የህዝብን ብሶት የሚፈቱ እንጂ ህዝብን እናስወግድ የሚሉ እንዳይገጥሙን እንፀልይ፡፡ ለህዝቡ ነው ለእኔ የቆምከው? የሚል ሹም ላያችን ላይ እንዳይንሰራፋ ነቅተን እንይ፡፡ የሚያስረዳ፣ ዐይን - የሚገልጥና ለመልካም አስተዳደር የቆመ ባለሥልጣን እንጂ እኔ ያዘዝኩህን ብቻ ፈጽሞ የሚል አይዘዝብን! ገደል እንዳንገባ ገደሉን የሚያጥርና ከመውደቅ የሚያድነን እንጂ “ወዶ ገደል ገባ!” ከሚል ኃላፊ ያድነን፡፡ ከሚያየው የማያየው የሚሻልባት አገር ሳትሆን፤ ልቦና የሰጠው ህዝብ የሚኖርባት አገር ትሆን ዘንድ የልባችን ይሙላልን፡፡
“ሹመት፤ ማዕረግ ሳይሆን የአገልግሎት ቃል ኪዳን ነው” ይላሉ ፈረንጆች፡፡ ብቃትና ዕውቀት ዋና ነገር ነው፡፡ ተዐብዮ - አልባ መሆን ዋናና ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ አሠሪውም ሆነ ሠራተኛው አወቅሁሽ ናቅሁሽ የማይባባሉበት ሥርዓት እንዲኖር የሁላቸውም ጥራት ወሳኝ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል!
ማናቸውም ሹመት የሌላ ሥልጣን መሳለጫ መንገድ ነው ብሎ ማሰብ አገርንም ህዝብንም ይጐዳል - የግል ዕድገትን እንጂ የአገር እድገትን እንዳናስብ ጫና የሚፈጥር እሳቤ በመሆኑ! ባለሙያነት፣ ተዓማኒነት፣ ኃላፊነትን የመሸከም ብቃት ያለው ሹም ኢወገናዊ መሆንን እንደ ታላቅ መልህቅ ሊያስር ይገባል፡፡ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል”ን ተረት ካላደረግነው፤ ድህነት ተረት አይሆንም! ከትላንትና እንማር! አገርን ያጠፋ ህዝብን የጐዳ አያሌ ነገር አይተናል፡፡ ያንን ከወዲሁ ካላሰብንና አርቀን ካላስተዋልን፤
“የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም!”
“የጃፓንን ጠባሳ ያየ በውሃ አይጫወትም!”
“የአሜሪካንን ጠባሳ ያየ በንፋስ አይጫወትም!” የሚለው አባባል ገና አልገባንም ማለት ነው!

Read 4389 times