Saturday, 16 July 2011 13:31

በሴት ዓለም ውስጥ አንድ ወንድ

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(2 votes)

ሰማይና ምድር መንትዮቹ እግዚአብሔር የበሕር ልጆች ናቸው፡፡ እነዚህ የተነጠቀ     መንትዮች ድስትና እፊያውእንደመሰሉ እግዚአብሔር ሁሉን
በውስጣቸው አከማቸ፡፡ እግዚአብሔር ይህን በሰማይና በምድር መካከል የተከማቸ ሀብት ለማሟጠጫ ልጁ፣ ከፍጥረታት ሁሉ ታናሽ ለሆነው ለስድስተኛ ቀን ልጁ ሰጠ. . .እግዚአብሔር ሰውን በስድስተኛ ቀን ..እንደተገላገለ.. የባህር አሶችንና የሰማይ ወፎችን፣ እንስሳትን፣ ምድርን፣ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ ..ግዛ!.. አለው፡፡ ግና እግዚአብሔር ምንኛ ቃሉን አጠፈ? ማጠጫ የመሰለውን ሰው ጥሳ፣ የሥራ ቀኖችን ተላልፋ ሔዋን (በ8ኛ ቀን) ትፈጠር ዘንድ ግድ ሆነ፡፡

ሴት በአቋራጭ የመጣች yእግዚአብሔር የማሟጠጫ ልጅ ናት፡፡ እናም ..ወላጅ ወረተኛው.. የፈጣሪ ልብ ወደዚች ጨቅላ አደላ፡፡ ሰውን ጨምሮ ለርሷ የተፈጠረ ሆነ፡፡ በመሆኑም ለወንድ ከተሰጠው የገሃድ ቃል በስተጀርባ ሴት እርሱን ጨምራ ትገዛ ዘንድ ከስውር ፍቅር የተበጀ ስውር እጅ ተሰጣት.  . .ወንድ ከዚያች ዕለት አንስቶ ምስኪንነቱን የማያውቅ ምስኪን ሆነ፡፡
ወንድ ገና ዘር እያለ የሴት ማህፀን ካላገኘ ንስ አይሆንም፣ ንስ ቢሆንኳ ሴት ካላስፈለጋት ወደ ልጅነት አይተላለፍም፣ ልጅ ሆነ እንበል - ሴት ጡት ካላጠባችው የት ሊደርስ? ጡት ቢጥልም - እህል ውሃ ቢልም - የፆታ ሱስ ያክለፈልፈው ዘንድ ግድ ነው፡፡ ሴት ወንድ ላይ ያገባችው ልጓም ቢረዝም እንጂ አይበጠስም፡፡ ወንድ ኖሮ፣ ኖሮ ሲጎፈይ እንኳ ምርኩዝ እንጨት ሳይሆን ሴት ነው፡፡ በደከመ ጊዜ ታዛው ነች፡፡ ሌላው ቀርቶ ወንድ ሲያጣጥር አልጋው ከሴት የተሠራ ጠፍር ነው፡፡ ቢሞት እንኳ ሽኝቱ ያለሴት ቀዝቃዛ፣ ቀዝቃዛ፣ ቀዝቃዛ ነው፡፡


ወንድ በስውር ከተሻረበት የገሃድ ቃል በመነሳት ዓለምን ለመጠቅለል ቃትቷል፡፡ የሞንጐሉ መሪ ጃንጂስ ከሐን የዓለም አንድ ሦስተኛን ምድር ጠቅልሏል፡፡ ግዛቴም ብሏታል፡፡ የሮማው ታላቁ አሌክሳንደርም እንዲሁ አድርጓል፡፡ ይህ ሁሉ ግን ለበላይዋ ሴት ቀለብ የተደረገ የዝና ክምችት ነው፡፡ እያንዳንዱ ጦረኛ በልቡ የሚታጠቀው ተጨማሪ የጦር ዕቃ አለው፡፡ ያ የጦር ዕቃ ..ሴት.. ይሰኛል. . . (ይሄንን በሐበሻው ጦረኛ ላጉላው)
አፄ ቴዎድሮስ፣ አፄ ቴዎድሮስነታቸው ከጐጇቸው ውጭ ነው፡፡ ለልጃቸው አባት፣ ለሚስታቸው ባል ናቸው፡፡ አንድ ጊዜ ገብርዬ (የጦር ሚኒስትራቸው) ወደ አፄው ቤት ሲገባ ጌታው በሚስታቸው (በተዋበች) ጥፊ ሲነዱ ይደርሳል፡፡ ገብርዬ ግልፍ ይለውና ..እንዴ! ጌታዬን?!.. ብሎ ጐራዴውን ሲመዝ አፄው መካከል ይገቡና እንዲህ አሉት. .
..ገብርዬ፤ ልብ በል፡፡ እዚህ ዓለም ላይ ሱሪዬን የምታስወልቀኝ እሷ ብቻ ናት፡፡..
..ሱሪ ከማስወለቅ.. በላይ ጀግንነት፤ ..ሱሪ ከማውለቅ.. ያነሰ ተሸናፊነት የት መጥቶ? እናም ሴቶች ምስኪንነቱን በማያውቀው ምስኪን ወንድ ላይ ባለ ስውር እጅ ስውር ጌቶች ናቸው፡፡ ወንድ በማያገባው ለሴቷ ግን ትርጉም ባለው ጉዳይ ጉዳዬ እያለ ደሙን አፍስሷል፣ አጥንቱን ከስክሷል፣ ህይወቱን አሳልፏል. . . ከዚህ ሁሉ በከፋ ከፈጣሪው ተጋጭቷል.
. . .ንጉስ ሰለሞን ስለ እቁባቶች ፍቅር አጓጉልኛ ተራምዶ አምልኮ-አማልክት ቀዬ ገብቷል፡፡ የሰገደው ግን ለግዑዛኑ ጣኦታት አልነበረም፤ በስውር እጃቸው ለዳሰሱት ጌቶቹ ሴቶች እንጂ፡፡ አባቱ ንጉሥ ዳዊትስ ቢሆን? በዓመቱ መለወጫ ነገሥታት ወደ ሰልፍ በሚወጡበት ጊዜ እርሱ ብቻ በምንጣፉ ላይ የቀረው ንጉሥ ዳዊት ከምንጣፉ ሲወርድ የመልካም ጦረኛውን የኦርዮንን ሚስት አየ፡፡ እርሷ ሴት. . . እርሱ ወንድ፡፡ ከርሷ አስቀድሞ ንጉሥ ዳዊት ስለ ስውር ሥልጣኗ ተንበረከከ፡፡ አለያማ እርሱ ንጉሥ እርሷ የአሽከሩ ሚስት አልነበረችምን? ግና ስውር እጅ አለና እርሱ ወደቀ፡፡ እናም አረገዘች፡፡ ዳዊትም ምስጢሩን ለመሸፈን ተጣጣረ፣ ሁሉንም ሞከረ፡፡ ባለመሆኑ ከመጋለጡ አስቀድሞ ኦርዮንን አስገደለ፡፡ ዳዊት ልታይ፣ ልታይ ከሚለው ዓለማዊ ሥልጣኑ የከፋ ስውር እጅ እንዳረፈበት ፈጣሪው አይረዳ ይሆንን? የማይቋቋመው የሴት ኃይል እንደገዛው?
ባይረዳም ግድ የማይሰጣቸው አሉ፡፡ ማክስዌል ሪስ የተባለ እንግሊዛዊ ደራሲ ..ሚስቴ እዚያ ከሌለች ገነት ለእኔ ምኔ ነው?.. ብሏል፡፡ ደፋር ይመስላል፡፡ ግና እንዳያያዙ ተይዞ ነው፡፡ ዓለምን ያለሴት አይቷት ወና ሆናበታለችና ገነትን ቢጠራጠር አይፈረድበትም”” ደግሞምኮ ከሴት የተነጠለች ገነት እንዴት እንደምታጓጓ ግራ የተጋቡ ሰዱቃውያን ይሄንኑ ጥርጣሬያቸውን ለኢየሱስ አንስተውለታል፡፡. ... . .ሰባት ወንድማማች በእኛ ዘንድ ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ሞተ፤ ዘርም ስለሌለው ሚስቱን ለወንድሙ ተወለት፤ እንዲህም ደግሞ ሁለተኛው፣ ሦስተኛው፣ እስከ ሰባተኛው ደረሰ፡፡ ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ሞተች፡፡ ሁሉ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀንሶ ከሰባቱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች.. ጥያቄው ትንሣኤ ሙታንን ተስፋ ያደረገ ወንድ ሁሉ ጥያቄ ነው፡፡ እዚህ ውሃ ቀርቦ ጥማት እንዳለ ሁሉ፣ እህል ቀርቦ ረሃብ ጠኔ እንዳለ ሁሉ ሴት ቀርቦ ስም ያልሰጠነው ግዴታ አለ፡፡ እናስ ለጥማቱ የወተት ወንዘ፣ ለረሃብ መና እንዳለ ሁሉ. . . ማለቱ ነው ያ - ወንድ፡፡ ደግሞምኮ ዘፍጥረት ላይ እነዚያ የገነት እንግዶች መሬትን ሲጐበኙ የተመለከቷቸውን የሰው ልጆች ስለቆነጁባቸው ወርደው ተገናኝተዋቸዋል፡፡ እናም ለዓለም ኃይል የማይመጥኑ ኃያላንን ኔፍሊምን ወለዱ፡፡ እግዚሃር እስኪያጠፋቸው ቀን ድረስ፡፡
ወንድ የተሠራው ከሴቶች ጡብ ነው፡፡ ሰብዕናውን ብንከፋፍለው እናት፣ እህት፣ አክስት፣ የከንፈር ወዳጅ፣ እጮኛ፣ ሚስት. . . የሚባሉ ፍርስራሽ ጡቦችን ነው የምናገኘው፡፡ የሳይኮ-አናሊስስ አጋፋሪ ሲግመድ ፍሮይድ ይሄንኑ ይነግረናል፡፡ ለወንድ እናት የሚስት መክተቻ ስልቻ ናት፡፡ ሚስት ደግሞ እንደተራገፈ ጆንያ ምንም ያልያዘች እናት፡፡ እናም ወንዱ የሴት እጅ እንደተቀባበለው መጨረሻ የመቃብር አፍ ተከፍቶ ያጠናቅቀዋል፡፡ የሴት እጅ ቅብብሎሹ በግማሽ መንገድ ቢቋረጥስ? ወንድ ህይወቱ የጐፈነነ ይሆናል፡፡ ሰዓሊው ቪንሰንት ቫን-ጐህ የሴቶች እጅ መታጣት ሰለባ እንደነበር ታሪኩ ያስረዳል፡፡ የቫንጐህ እናት የከንፈር ወዳጅ ወይም ሚስት ሆና የምትቀበልላት ሌላ ሴት በማጣቷ በተፈጥሮ ግፊት ..ሜዳ.. ላይ አኖረችው፡፡ ቫንጎህ የአክስቱን ልጅ አፈቀረ፡፡ እሷን ነዋ ምርጫ አልባ ዳሰሳው ያገኘው፡፡ አልሆነም፡፡ እንዲህ እንዲያ ሲል መሸበትና አንድ ጊዜ አንድ አካሉን ነጥላ የምትወድ ሴት ተፈጠረች፡፡ ..ጆሮህ ሲያምር.. አለችው፡፡ ያ የወደደችለትን ጆሮውን ቆርጦ በፖስታ ሰጣት፡፡ ምን ያስገርማል? ሁላችን እንዲሁ አይደል የምናደርግ፡፡ በሴቶች ተወደደልን ያልነውን ዓይናችንን፣ አፍንጫችንን፣ ድምጻችንን. . . ባንቆርጠውም አሽሞንሙነን እሱኑ ብቻ ሆነን እንቀርባለን፡፡ ቫን ጎህ ወንድ፣ ወንድ ቫንጐህ፡፡ፍሬደሬክ ኒችም ያው ነበር አሉ፡፡ ስውር ኃይላቸውን ሳይረዳ ሴቶችን ..እርም.. ያለ፡፡ ሌላው ቀርቶ ዛራቱስትራ የተባለውን ገፀ ባህሪውን ..ከሀይቅ ድንፋታ ተወለደ.. ይለዋል፡፡ ከሴት ተጽዕኖ ለማላቀቅ፡፡ ግና ምን ይሆናል ከ..ሴት.. የተገኘው ደራሲ ኒች ከሀይቅ ድንፋታ የተገኘውን ገፀ-ባህርይ ብዙ ምሬት ያናግረዋል፡፡ ..ወደ ሴት ጋ ስትሄድ አኮርባጅህን አትዘንጋ.. ይላል፡፡ ከኑሮ ወጪት የተጨለፈ የሚመስለውን ልምድ እንዲህ ሲል በዚሁ ገፀ ባህርይ አንደበት ያወጣል. . .

... . .በጦረኞች ዘንድ እጅግ ጣፋጭ ፍሬዎች ተመራጭ አይደሉም፡፡ ስለዚህም እነዚህ ጦረኞች ሴቶችን አጥብቀው ይወዳሉ፡፡ ምክንያቱም እጅግ ጣፋጭ ከተባለችው ሴት እንኳ የሚገኘው ውጤት መሪር ነውና፡፡.. ኒች አንዳንድ ጊዜ ከሚሰማው ገጠመኙ አንፃር ከታየ ሰውየው በሴቶች ላይ እንዲህ ቢያመር አይፈረድበትም ያስብላል፡፡ ኒች አሟሟቱ በቂጥኝ አባላዘር በሽታ አብዶ ነው ስለሚባል፡፡
ወንድ ዘር ነው፡፡ ..ሴት.. ከሚባል ምድር የተገኘ ተክል፡፡ እዚያው በቅሎ፣ እዚያው አሽቶ፣ እዚያው ወድቆ ዳግም የሚበቅል የዘር አዙሪት፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን ሴት ፈቃዷን ልትሰው ግድ ይላላ፡፡ ለማኝነቱን አውቆም ሆነ ሳያውቅ በሴት እርጥባን የሚኖር ሰንካላ ነው ወንድ፡፡ ጌታም ቢሆን፡፡ በተገፈፈ ክብሩ፣ በተነጠቀ ቃል ኪዳኑ እየተኩራራ አልቦ ስልጣን የጨበጠ፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዋሽንግተን ላይ ላዩን ሲያዩዋቸው ባሪያ አሳዳሪ ነበር፡፡ ነገር ግን በባሪያ ተዳዳሪ አሁን አሁን ሳይንስ እየተንኳተተ የዋሽንግተንን ዘራቸውን ባሮች ውስጥ አገኘው፡፡ ያቺ ..ባሪያ.. ብሎ የጠራት ሴት እናት ምድሩ ነችና ላይወድቅባት፣ ላይበቅልባት አልቻለም፡፡ ይሄ እኛም ሀገር ነበር፡፡ ባሪያ አሳዳሪው ከባሮቹ መርጦ የሚሰግድላትን ባሪያ ..ሴት.. ያበጃል፡፡ እዚያም ወንድ፣ እዚህም ወንድ፡፡ሁሉ የገባው ሊባኖሳዊው ደራሲ ካህሊል ጅብራን ይመስላል፡፡..ሴቶች# የዓይኖቼ መስኮቶች፣ የነፍሴን በሮች ከፈቱልን.. የወንዶች ጥንካሬ ከዚህ እንደሚሳ ጅብራን ንስሀውን ሰጥቷል፡፡ ..ደራሲያን ሆኑ ባለቅኔዎች ስለሴቶች እውነቱን ለመረዳት ይጥራሉ.. ይላል ጅብራን፡፡ ..የሚደንቀው ግን አሁንም ስለሴቶች ልብ የሚያውቁት የለም፡፡ ምክንያቱም መፈተሻ ዓይኖቻቸው የተወለዱት ከመጐምጀት ነውና ላይ ላዩን ከመንሳፈፍና ድክመቷን ከማንጠር ውጭ ጠብ የሚልላቸው የለም፡፡.. ይኸው ነው! የጂብራንን ልቡና ይስጠን!!

 

Read 9905 times Last modified on Friday, 22 July 2011 23:49