Print this page
Sunday, 24 July 2011 07:44

ፎቶግራፎች

Written by  ጌታሁን ሽፈራው
Rate this item
(9 votes)

ከአቢጃን ተነስቶ ካልካታ ከገባ 3ኛ ቀኑን ይዟል፡፡ ይህች በህዝብ የተጨናነቀች ታላቅ ከተማን እንደረገጠ የካልካታ ተወላጅ የሆኑት የ10ኛ ክፍል ህንዳዊ መምህሩ ስለዚህች ከተማ በአድናቆት የተናገሩትን አስታወሰና ቃላቱን በውስጡ አነበነበው ‘KALKATA IS A BIG CITY WHEN YOU THROW A STONE FROM THE SKY IT WILL NOT REACH TO THE GROUND’ (ካልካታ ታላቅ ከተማ ናት ከሰማይ ድንጋይ ብትወረውር ሰው ላይ ነው የሚያርፈው) ያሉት አባባል ትክክል እንደሆነ ተገነዘበ፡፡

አሁን የመጣበትን ጉዳይ ከውኖ ከተማዋን ለቆ ሊወጣ ነው፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ሆድን ጠርቀም አርጐ የሚይዝ ምግብ ተመገበና የሚወስደውን ነገር በጥንቃቄ ወስዶ፣ ወደ ካልካታ አውሮፕላን ጣቢያ አመራ፡፡ ሰፊውንና ረጅሙን የመስታወት በር አልፎ ገባ፡፡
የአዳራሹ መስክ በመንገደኞች ተሞልቷል፡፡ ሰልፍ ያዘና አነስተኛ ሻንጣውን አስፈትሾ ወደ መንገደኞች መቆያ ክፍል ከገባ በኋላ፣ ወንበር ላይ ተቀምጦ የበረራ ፕሮግራም የሚያሳየውን ሰሌዳ ተመለከተ፡፡
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ..በረራ ቁጥር..... በአዳራሹ ውስጥ ያለው የድም ማጉያ ጐልቶ ተሰማ ..ሲንጋፖር፣ ካራቼ፣ ኢስታንቡል፣ ካይሮ፣ አዲስ አበባ፣ አቢጃን፣ ሎሜ በሉፍታንዛ መስመር.... ተጓዦች... በረራ ቁጥር..... ተናጋሪዋ መልእክቱን በተለያዩ ቋንቋዎች አስተላለፈች፡፡
ዴቪድ ከሌሎች ተጓዥ መንገደኞች ጋር ቀለል ያለ የጉዞ ሻንጣውን እንደያዘ መተላለፊያውን ተሻግሮ ወደ አውሮፕላኑ ካመራ በኋላ ወንበሩን በዓይኑ አማተረና ቦታውን ያዘ፡፡
አውሮፕላኑ ጉዞውን እንደጀመረ በእፎይታ ተነፈሰ፡፡
እንዲህ አይነት ረጅም አሰልቺ፣ አደጋ የተሞላበት ጉዞ ሲያደርግ ለ3ኛ ጊዜ ነበረ፡፡ ሆኖም ይህኛው የጉዞ መስመር ትንሽ ረዘም ያለ መስሎ ተሰማው፡፡
ይህን መሰል አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ሊገባ የቻለው ለሚስቱ ባለፈው ከፍተኛ ፍቅር ነው፡፡
ከአራት ዓመት በፊት እርሱ ለአንድ ሳምንት የሰርከስ ትርዒት ለማቅረብ በመጣ ጊዜ ነበር ከባለቤቱ ከኢሌኒ ጋር የተዋወቀው፡፡ የኢሌኒ ማራኪ ቁመና፣ ቸኮላት መልክ፣ ረጅም ፀጉርዋና ዳሌዋ የዴቪድን ቀልብ ከሳቡት ክፍሎችዋ ዋነኞቹ ናቸው፡፡
በአንድ ሳምንት ቆይታው ሁለቴ የእራት ግብዣ አድርጐለት፣ ቤቷ ድረስ እያደረሰ በኮንትራት ታክሲ ሆቴሉ ያመራ ነበር፡፡ ወደ ሀገሩ በተመለሰ ጊዜ በየሳምንቱ እየደወለ ሲጠይቃት ከርሞ ወደ ሀገሩ እንድትመጣ ፈቃደኝነትዋን በገለፀችለት ጊዜ፣ አባቱን አግባብቶ አስፈላጊውን መሰናዶ አድርጐ በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ጠቅልላ ወደ አቢጃን እንድትመጣ አደረጋት፡፡
ዴቪድ ከባለፀጋ ቤተሰብ መሃል የተገኘ ለቤተሰቡ ብቸኛ ልጅ በመሆኑ ተሞላቆ ነበር ያደገው፤ በወጣትነት እድሜው ከበርካታ ሴቶች ጋር የነበረው ግንኙነትና ያለአግባብ ገንዘብ አባካኝ መሆኑ አባቱን በጣም ያስከፋው ስለነበር፣ አሁን በፍቅር መውደቁን አባቱ ሲሰማ ተደስቶ በጋብቻ እንዲታሰር አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ ጋብቻ እንዲያደርጉ አስችለውታል፡፡
ሆኖም ዴቪድ ከሀገር ሀገር ኢሌኒን ለማስደሰት እየዞረ ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚያባክን፣ ለርሱ ሲል ጊዜና ገንዘባቸውን ማባከን እንደሌለባቸው የተረዱት ሚስተር ኦሊሴ፤ በካንሰር ህመም ተሰቃይተው ከመሞታቸው በፊት ከፍተኛ አክሲዮን ያላቸውንና በዋና ሥራ አስኪያጅነት ይመሩት የነበረውን ኢንሹራንስ ድርጅት ድርሻ ለታናሽ ወንድማቸው ሲሶውን ድርሻ እንዲያስተዳድሩና እንዲመሩ በፍርድ ቤት በመሰየም ሲያዞሩ፣ አንድ አራተኛውን ድርሻ ደግሞ ለዴቪድ በደሞዝ መልክ እንዲከፍለው ያደረጉ ሲሆን፤ ሙሉ ድርሻው በስሙ እንዲዞር አድርገው ነበር የሞቱት፡፡
ዴቪድ ከቀለም ትምህርት ይልቅ በአስደናቂ ትርዒቶችና በሰርከስ ትእይንቶች ይመሰጥ ስለነበር ገና በ15ኛ እድሜ ላይ ሳለ ከአንድ የሰርከስ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ገባ፡፡ ወደ ሃያዎቹ አካባቢ ሲጠጋ በጣም የተዋጣለት ኳስ አንቀላላቢ JUGGLER በመሆን ..ዴቭ THE JUGGLER” የሚል ቅል ስም ሲሰጠው፣ ከጓደኞቹ መሃል እጅግ ደፋር በመሆኑ ብዙዎቹ የማይደፍሩትን ጩቤ መሰል ረጅም ስለት በጉሮሮው በመላክ፣ እስከ ሆድ ዕቃው ድረስ በማዝለቅ አስደናቂ ትእይንቶችን ያቀርብ ነበር፡፡
ሆኖም አባቱ እንዲህ አይነቱን አደገኛ ትእይንት እንዲያቆም ቢመክሩትም አሻፈረኝ በማለቱ ለህይወቱና በማንኛውም ነገር ሊደርስበት ለሚችለው አደጋ ከፍተኛ የሆነ የኢንሹራንስ መድህን ለመግዛት ተገደዋል፡፡
ዴቪድ፤ እናቱ ገና የ11 ዓመት ልጅ እያለ ነው በመኪና አደጋ የሞቱት፡፡ አሁን እድሜው 28 ዓመት ሆኖታል፡፡ ልብ እየገዛ መምጣት እንደጀመረ አባቱ በካንሰር ህመም ተሰቃይተው ሞቱ፡፡
ይህ ከሆነ 10 ወራቶች ተቆጥረዋል፡፡
አሁን የባለቤቱ ኢሌኒ እናት በጭንቅላት ዕጢ ህመም እየተሰቃዩ እንደሆነ ከሚወዳት ሚስቱ ተረድቷል፡፡ እርሳቸውን ለማሳከም ወደ 40ሺ ዶላር ገደማ እንደሚያስፈልግ ሚስቱ ነግራዋለች፡፡ እርሱ እናቱን ልጅ እያለ አጥቷል፤ የኢሌኒን እናት እንደ እናቱ ሊያያቸው ይገባል፡፡
አንድ ቀን አጐቱ ኦቻና ዘንድ ሄደና ከድርሻዬ ላይ የሚታሰብ 40ሺ ዶላር ስጠኝ ብሎ ያጋጠመውን በሙሉ አወያየው፡፡ አጐቱ ኦቻና ግን ሙሉ ለሙሉ እምቢ ባይለውም አንድ የማግባቢያ ሃሳብ አቀረበለት፡፡ ..አንተ በጉሮሮህ አሾልከህ ሆድ ዕቃህ ድረስ ረጅም ስለት ሰደህ ማስቀመጥ ትችላለህ ይህን ተሰጥኦህን ለምን በብር አትቀይረውም፡፡ የተወሰኑ ሀገሮች በመሄድ በሆድህ ውስጥ ዕቃ ቀብረህ ትመጣለህ፤ ከአራት ጊዜ በላይ ያልበለጠ ጉዞ አድርገህ ከ25ሺ ዶላር በላይ ታገኛለህ፡፡ የተቀረውን እኔ እሞላና የህክምናው ወጪ ይሸፈናል.. የሚል ድርድር አቅርቦለት ተስማማ፡፡
የአሁኑ በረራው ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው - ዴቪድ፡፡ አንድ ተጨማሪ በረራ ከዚህ ረጅም ጉዞ በኋላ ይጠበቅበታል፡፡ በረሃብ እየተሰቃየ፣ አደጋ እየተጋፈጠ ...ሦስተኛውን ጉዞ በድል ሊወጣ 10 የሚሆን ተጨማሪ ሰዓት ብቻ ይቀረዋል፡፡ ረሃብና ድካም ቢጠናበትም በፍቅር ሁሉ ነገር ይቻላል ሲል አሰበ፡፡ እስካሁን ለ34 ሰዓታት ያለ ምግብና መጠጥ ተጉዟል፡፡
እቤቱ እንደገባ በእቅፉ ስር አድርጓት፣ ለስላሳ ፀጉርዋን እያሻሸ በከንፈሩ እየዳበሰ ደረቱ ላይ ልጥፍ አድርጐ በስሜት ሰመመን አብሯት ሲዳክር፣ ለእርሷ ብቻ እንደሚኖር ተሰማው፡፡
የበረራ አስተናጋጆች በጋሪ የሚገፉ ምግብና መጠጥ ይዘው መለስ ቀለስ ሲሉ፣ በረሃብ የታጠፈ አንጀቱን እንደቆለፈ፣ ለመብላት እየጐመጀ አለፈው፡፡
አዲስ አበባ የሚወርዱ ተጓዦች ጥቂት ነበሩ፡፡
ከአውሮፕላኑ እንደወረደ ከአጐቱ የተነገረውን መልእክት አስታውሶ፣ ቦሌ ኤርፖርት ውስጥ ካለ ለንደን ካፌ ውስጥ ገባ፡፡
በዚህ ካፌ የምታስተናግድ ቅድስት የተባለች ወጣት አስጠራና፣ ካነጋገራት በኋላ የሞባይል ስልኳን ተውሶ አዲስ አበባ መድረሱን አቢጃን ላለው አጐቱ መልእክት አስተላለፈ፡፡ ከዚያም 50 ዶላር በጉርሻ መልክ ጭምር ሰጣትና ወደመንገደኞች መጠባበቂያ ክፍሉ አመራ፡፡ ለተወሰኑ ደቂቃዎች እንደተቀመጠ ቅድስት የመንገደኞች መጠባበቂያ አቋርጣ፣ ወደ አንድ ክፍል የሞባይል ስልክ እያወራች ስታመራ ተመለከተ፡፡
መልኳ፣ ፈገግታዋና አካሄዷ ሁሉ ቁርጥ ኢሌኒን መስላ ታየችው፡፡
ከ15 ደቂቃ በኋላ ሁለት የፖሊስ ዩኒፎርም የለበሱ ሰዎች እርሱ ወዳለበት ቦታ ሲቀርቡ ተመለከተ፡፡
ሰላምታ ካቀረቡለት በኋላ ለጥያቄ እንደሚፈልጉት ፈቃደኝነቱን ጠይቀው እንደተስማማ አጅበውት ኤርፖርት ውስጥ ካለ አንድ ክፍል ውስጥ ወሰዱት፡፡
አራት በአራት ሜትር ከምትሆን መለስተኛ ክፍል ያለ መቶ አለቃ፤ ..በኢትዮጵያ የአደንዛዥ ዕ መከላከያ ግብረ ሃይል..... በማለት ራሱን አስተዋውቆ በቀጥታ ወደ ጉዳዩ ገባ፡፡
..በመጀመሪያ ስምህን ብትገልልን?..
..ዴቪድ ኦሊሴ.. ግራ በመጋባት መለሰ፡፡
..ከየት ነው የተሳፈርከው?..
..ለምንድን ነው የምትጠይቁኝ ምን የተፈፀመ ወንጀል አለ?..
በምን ሊያገኙኝ ይችላሉ ብሎ አሰበና ..ከጉዞ ማህደሬ ላይ ፈልጉ.. አለ፡፡
..ይገባሃል ሚስተር ዴቪድ፤ እዚህ የትራንዚት ቆይታህ እንደሚገባኝ ሁለት ሰዓት አይበልጥም... ስለሆነም ከኛ ጋር ቀና ትብብር ካደረግህ አውሮፕላኑ ሳያመልጥህ ጉዞህን ትቀጥላለህ.. አለ መቶ አለቃው፡፡
..እሺ... ከካልካታ ነው የተነሳሁት..
..ከዚህ ቀደም እዚህ አዲስ አበባ ትራንዚት አድርገህ ታውቃለህ?..
..አዲስ አበባ ውስጥ ትራንዚት ማድረግ ተከልክሏል እንዴ?..
..አይደለም ሚስተር ዴቪድ፤ አንተ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁለት ወር ውስጥ ትራንዚት ስታደርግ ለሦስተኛ ጊዜህ መሆኑ ጥቆማ ደርሶናል፡፡ ...በዚህ ላይ የምትመጣባቸው መስመሮች ተመሳሳይና በአደንዛዥ ዕ ዝውውር የወንጀለኛ መቅጫ ህጋቸው ቀላልና አደንዛዥ ዕ የሚተላለፍባቸው ሀገሮች ናቸው፡፡ ...በዚህ ላይ አንተን ስናጤንህ ታላቅ ድካም የርሃብ ስሜትና የመቅበጥበጥ ሁኔታ ስላየንብህ ነው ያስጠራንህ፡፡ ....በዚህ ላይ ጥቆማም አለብህ፡፡..
..ድካም ያለበትና የሚቅበጠበጥ ተጓዥ ወንጀለኛ ነው ማለት ነው?..
..የለም... የለም ምግብም ሆነ መጠጥ አልቀመስክም... ያ ደግሞ ትንሽ ሆድህ ውስጥ ምናምን ስላለ ሊሆን ይችላል፡፡ ...ስለዚህ ትኩስ ነገር ጠጣና ወደ መጣህበት ተመለስ፡፡.. መቶ አለቃው ትእዛዝ አዘል በሚመስል ቃና ተናገረ፡፡
..የለም... ምንም ነገር አልወስድም ፆመኛ ነኝ፡፡ አመሰግናለሁ..
ዴቪድ ፊት ላይ ድንጋጤ መታየት ጀምሯል፡፡
ትኩስ ነገር እንድትጠጣ ትገደዳለህ፡፡ ...ያለዚያ ግን ወስጥሀን በጨረር ለማየት እንገደዳለን፡፡ መቶ አለቃው ፍርጥም ብሎ ተናገረ፡፡
በዚህን ጊዜ ዴቪድ ብድግ ብሎ ተነሳና ..መብቴን እየጣሳችሁ ነው... እከሳችኋለሁ... አይሆንም፡፡ ወደ ኤምባሲዬ እደውላለሁ..... አለ ድምፁ መቆራረጥ ጀምሯል፡፡
..ኤምባሲዎችህ በፍተሻው ይስማሙበታል.. አለ መቶ አለቃው ኮራ ብሎ፡፡
ዴቪድ ለአፍታ ራሱን አረጋጋና ሁኔታውን ለማጤን ሞከረ፡፡
ፖሊሶቹ እንደማይለቁት ተረዳ፡፡ ምግብና ውሃ ከቀመሰ 35 ሰዓታት ሆነውታል፡፡ እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ለማደር ርሃብና ድካሙ አስገድደውታል፡፡ ሆድ እቃው ላይ ያለው ጥቅል የህመም ስሜት ፈጥረውበታል፡፡
ከአንድ ሰዓት በኋላ የጨረር ምርመራ ከአካሄደ በኋላ ቀዝቃዛ ዘይትማ ነገር በፌዴራል ፖሊስ ሪፈራል ህክምና ማዕከል ከጠጣ በኋላ በስስ ላስቲክ የተጠቀለለ 640 ግራም የሚመዝን ክኒን መሰል በሰገራ መልክ ከሆዱ ወጣ፡፡ የላብሯተር ውጤቱ ክኒኑ ኤሜታፊን የሚባል አደገኛ ዕ መሆኑን አስረዳ፡፡
በሳምንት ውስጥ ዴቪድ ኤሜታፊን የሚባል ዕ በሆድ ውስጥ ከቶ ለማዘዋወር ሲሞክር መያዙን አስመልክቶ ክስ ተመሰረተበት፡፡
ክሱ በሚሰማበት ወቅት ዴቪድ በጠበቃው አማካኝነት አባቱ ድንገት መሞቱን፣ ኢትዮጵያዊ ሚስት እንዳለውና የባለቤቱ እናት በጭንቅላት እጢ እንደሚሰቃዩ ጠቅሶ፣ ለህክምና ወጪ ማሟያ ሲል ወንጀሉን መፈፀሙን አምኖ ቅጣቱ እንዲቀልለት አመለከተ፡፡
አቃቤ ሕግ በበኩሉ የተያዘበትን ኪኒንና የሰው ማስረጃዎች እንዳለው ገልፆ፣ ተከሳሹ በተደጋጋሚ ጊዜ በአዲስ አበባ ትራንዚት ያደርግ እንደነበር፤ የጉዞ ማስረጃውን አያይዞ ከባለፀጋ ቤተሰብ የተገኘና የገንዘብ ችግር የሌለበት፤ በቂ ትምህርትና እውቀት እንዳለው ጠቅሶ፣ የባለቤቱ እናትም ምንም የጤና ችግር የሌለባቸው መሆኑን በማስረጃ አስደግፎ በማቅረብ፣ ተከሳሹ ሴሰኝነት የተጠናወተው በመሆኑ ብቻ ወንጀሉን ሊፈም እንዳነሳሳው በማስረዳት፣ ቅጣቱ እንዲከብድበት ሲል ፍርድ ቤቱን ጠየቀ፡፡
ዳኛው ግራና ቀኙን ለአንድ ዓመት ያህል ከሰሙ በኋላ ተከሳሹ የታሰረው ጊዜ ታሳቢ ሆኖ በአምስት ዓመት ኑ እስራት እንዲቀጣ ወስነው ፋይሉን ዘጉ፡፡ ዴቪድ እስር ቤት ሳለ አንድ ጊዜ ባለቤቱ ከአቢጃን መጥታ ስትጐበኘው፣ አልፎ አልፎ በተለያዩ ሰዎች እያስላከች ስንቅና ገንዘብ ታቀብለው ነበር፡፡
ዴቪድ በእስር ቆይታው የሚከነክኑት አንዳንድ ነገሮች ቢኖሩም፣ አቃቤ ሕጉ የባለቤቱ እናት ፍፁም ጤነኛ እንደሆኑ መግለፁ ሲያብከነክነው የቆየ ጉዳይ በመሆኑ፣ ከእስር ቤት እንደተፈታ በቀጥታ ያመራው ወደባለቤቱ እናት መኖርያ ቤት ነበር፡፡ የኢሌኒ እናት መኖሪያ ቤት ከ7 ዓመት በፊት አዲስ አበባ እያለ ከሚያውቀው በላይ እጅግ የተዋበ ሆኖ ሲያገኘው፣ የእናትየው ጤንነትም የተሟላና ከራስ ምታት ውጪ ምንም ነገር ሆነው እንደማያውቁ ከአካባቢው መረጃ ለመሰብሰብ ችሎ ነበር፡፡
ሆኖም በነገው እለት ወደ አቢጃን ከመብረሩ በፊት የኢሌኒ እናትን በአካል አግኝቶ ሊጠይቃቸው ወሰነ፡፡
የግቢያቸውን በር አንኳኩቶ ተከፍቶለት እንደገሃ የባለቤቱ እናት ከአቢጃን የመጣ እንግዳ በመሆኑ ብቻ ድንገት ለመጣው እንግዳ መስተንግዶ ለማድረግ ከቤት ውስጥ አስገብተው ሽር ጉድ ማለት ጀምረዋል፡፡
ዴቪድ ለርሳቸው ጤንነት ሲል ወህኒ ቤት 5 ዓመት እንደቆየ ቢረዱ ምን ሊያደርጉለት እንደሚችሉ ለመገመት አላስቸገረውም፡፡ በወህኒ ቤት ቆይታው አማርኛ አቀላጥፎ ለመናገር በመቻሉ ከኢሌኒ እናት ጋር ለመግባባት አልተቸገረም፡፡
ዴቪድ ጤንነታቸው መልካም እንደነበረ ከርሳቸው አንደበት ለመረዳት ችሏል፡፡ ግን ለምን ይህን አደረገች? እያለ ቤቱን ቃኘት ሲያደርግ፣ ሳሎን ውስጥ በፍሬም የተሰቀለ የኢሌኒንና የአንዲት ሴት ፎቶ ተመለከተ፡፡ ከጐንዋ ያለችውን ሴት የት እንደሚያውቃት አሰላሰለና በቀላሉ ለያት፡፡ ፍፁም ከኢሌኒ ጋር የምትመሳሰለው ለንደን ካፌ የምትሰራው ሞባይል ያዋሰችው ቅድስት!
አሁን ልቡ መደንገጥ ጀመረ፡፡ በአግራሞት ወደ ኋላው ማብሰልሰል ያዘ፡፡ አንዳንድ ትእይንቶች እየተቆራረጡ ይመጡበት ጀመር፡፡ እርሱ አዲስ አበባ ገብቶ ስልክ ለምን መደወል አስፈለገው? ይህች ሴት ደግሞ በቀጥታ ወደ ኤርፖርት ፖሊሶች ክፍል ለምን መጣች? ለዚህ መልስ ገና ሌላ ጥያቄና ፈተና ያሻዋል፡፡ በዚህ ጥያቄ ግራ እየተጋባ ሳለ ከጠረጴዛው መስታወት ስር ካለ የፎቶ አልበም ላይ አይኑን ተከለ፡፡ አልበሙን አንስቶ ገና ከመግለጡ በድንጋጤ ይበልጥ ፎቶውን አቅርቦ መመልከት ቀጠለ፡፡ አሁንም ሲገልጥ የበለጠ የሚያስደንቁ ትእይንቶችን ከፎቶው አልበም ውስጥ ተመለከተ፡፡ የገዛ ትንፋሹ ሲሞቀው ልቡ በሃይል ሲመታ፣ ሰውነቱ ሲርድ እልህ፣ ቁጭት፣ ንዴት፣ በቀል፣ ድንጋጤ፣ ብቸኝነት፣ ክህደት፣ ውርደት፣ ሀዘን ተሰማው፡፡ ያየውን ማመን አቅቶት ደጋግሞ እየገለጠ አስተዋለው፡፡
አጐቱ ኦቻናና ባለቤቱ ኢሌኒ ሲሳሳሙ ሲዝናኑና ሲሳሳቁ፤ ቀለበት ሲያደርጉ የሚያሳይ ፎቶግራፍ ነበር፡፡ ዋና አስረጅ ይሆኑኛል ያላቸውን የተወሰኑትን የኢሌኒ እናት ሳይመጡ ፈጠን ብሎ ከአልበሙ ላይ መዞ አወጣና ከጃኬት ኪሱ ውስጥ ከተታቸው፡፡
አሁን ያልተሟሉ ጥያቄዎቹ በራሳቸው ጊዜ መልሳቸውን ይዘው መጡ፡፡ እንደኔ አይነት ጅልና ሰው አማኝ በአለም ላይ ሊኖር አይችልም አለ፡፡ ለራሱ እየተቆራረጡ የመጡት ትእይንቶች በስርአት እየተደረደሩ መጡለት፡፡
ኢሌኒና አጐቱ በምስጢር እንደሚገናኙ ያውቅ ነበር፡፡ ነገር ግን በርሱ የወደፊት እጣና ብኩንነት ዙሪያ ሊወያዩ እንደሆነ የሰማውን አምኖ ተቀብሏል፡፡ ረጅም የጉዞ መስመር መጠቀሙ በፕላስቲክ የተጠቀለለው ኪኒን ሆዱ ውስጥ እንዲፈነዳና እንዲሞት ታስቦ እንደሆነ ገመተ፡፡
አባቱ ለህይወቱና ለጤንነቱ የገባለት ከፍተኛ ኢንሹራንስ እርሱን ለአደጋ በማጋለጥ እንዲሞት ሲደረግ፣ ባለቤቱ ኢሌኒ እንድትወርሰው፤ ከዚያም አጐቱና ባለቤቱ ሊጋቡ አስበው እንደሆነ ገመተ፡፡
የባለቤቱ እናት ታመዋል መባሉ ለዚህ አደጋ ለበዛበት ረዥም ጉዞ እርሱን አደጋ ውስጥ በመክተት ለሞት እንዲዳረግ ታስቦ መሆኑንም ተገነዘበ፡፡ ይህን ሁሉ አደገኛ ሁኔታ በድል ለመወጣት ዳር ላይ ሲደርስ በእህቷ ቅድስት አማካኝነት ተጠቁሞ የመያዙ ሴራ፣ የነርሱ ውጥን እንደሆነ አሰበ፡፡
እናትየው ዘና እንዲል ገባ ወጣ እያሉ አጫወቱትና ነገ እንደሚመለስ ነግሮአቸው ያቀረቡለትን ቡና ጠጣና አመስግኖ ከቤታቸው ወጣ፡፡
ነገ ጉዞ ወደ አቢጃን ያደርጋል፡፡ ይህን ፎቶግራፍ ያባዛል፡፡ ለኢሌኒና ለአጐቱ ይልካል፡፡ ከርሷ ጋር ፍቺ ይፈማል፡፡ አባቱ የጣሉበት የ5 ዓመት የውርስ ገደብ ይነሳል፡፡ ይህን ሁሉ በቤተሰቡ ጠበቃ አማካኝነት ይፈማል፡፡ እስር ቤቱና ፎቶግራፉ አጠንክረውታል፡፡ አሁን ያሻውን ማግባት ይችላል፡፡ የበርካታ መልካም ሴቶች ግፍ ነበረበት፡፡ አንዷን ይበልጡኑ ከአንጀቷ የምታፈቅረውን ሉቺያን ያገባል፡፡
ከእንግዲህ ያለ ምግብ አደጋ ያለበት ጉዞ አያደርግም፡፡

 

Read 8387 times Last modified on Sunday, 24 July 2011 07:48