Print this page
Thursday, 04 August 2011 14:18

አዲስ አድማስ በ2003 በሩጫና እግር ኳስ አሸናፊ ሆነ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

በ1ኛው የሚዲያና የኪነጥበብ ባለሙያዎች የእግር ኳስ ውድድር አዲስ አድማስ ከኢትዮጽያ ሬዲዮና ቴሌቪዚን ድርጅት ጋር ለዋንጫ ተጋጥሞ 1ለ0 በማሸነፍ ሻምፒዮን ሆነ፡፡ የ2003 ጋዜጠኞች ቡድን በተመሳሳይ ከአርቲስቶች ጋር ለደረጃ ያደረገውን ጨዋታ 1ለ0 በማሸነፍ 3ኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡ የአዲስ አድማስ ቡድን በዚሁ ዓመት ታላቁ ሩጫ አዘጋጅቶት የነበረውን የ12 ኪሎሜትር የዱላ ቅብብል ሩጫ ከስምንት ሚዲያዎች ብልጫ በማግኘት አሸናፊ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በዚህም የአዲስ አድማስ ቡድን በሩጫና በእግር ኳስ ከአገሪቱ ሚዲያዎች የላቀ ውጤት በማስመዝገብ አድናቆት አትርፉዋል፡፡


የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ከዜድኬ ፕሮሞሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን ይህን ውድድር በአበበ ቢቂላ ስታድዬም በርካታ ተመልካቾች ታድመውታል፡፡ ከላይ ብርቱካናማ ቀለም ያለው ሹራብና ጥቁር ቁምጣ የታጠቀው የአዲስ አድማስ ቡድን በውድድር ዝግጅትና በደመቀ  የድጋፍ አሰጣጥና በአስገራሚ የተሳትፎ ትኩረት ውድድሩን ካዘጋጁት አካል አድናቆት አግኝቶበታል፡፡
በእግር ኳስ ውድድሩ ሻምፒዮና የሆነው የአዲስ አድማስ ቡድን ልዩ ዋንጫ፤ የአምስት ሺህ ብር ሽልማትና የወርቅ ሜዳልያ ያገኘ ሲሆን ሳይሸነፍ ዋንጫ የበላ ቡድን በኮከብ ምርጫው ይገባው የነበረውን የኮከብ አሰልጣኝና ተጨዋች ምርጫ ሊያሸንፍ አለመቻሉ በታዋቂ ጋዜጠኞች ተተችቷል፡፡ በ2ኛ ደረጃ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቭዠን ድርጅት 3ሺ ብርና የብር ሜዳልያ እንዲሁም ሶስተኛ ደረጃ ያገኘው የ2003 ጋዜጠኞች ቡድን የ2ሺ ብርና የነሀስ ሜዳልያ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ቡድን  እስከ ዋንጫ ድሉ ባደረገው ግስጋሴ ሽንፈት አላስተናገደም፡፡
በውድድሩ የመክፈቻ ጨዋታ ከሪፖርተር ጋር የተገናኘው የአዲስ አድማስ ቡድን 11 ለ1 በሆነ ሰፊ ውጤት ቢያሸንፍም በተጨዋች ተገቢነት በሪፖርተር በቀረበ ክስ ጨዋታው እንዲደገም በአዘጋጆቹ ተወስኗል፡፡ ከዚህ በሁዋላ የአዲስ አድማስ ቡድን በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታውን ከአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሐን ጋር አድርጐ 2ለ0 አሸንፉዋል፡፡  በድጋሚ በተደረገ ጨዋታ ደግሞ ሪፖርተርን 2ለ1 ማሸነፍ የቻለ ሲሆን የመጨረሻ የምድብ ጨዋታውን ከኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቭዠን ድርጅት ጋር በማድረግ 2 እኩል አቻ ተለያይቶ ወደ ግማሽ ፍፃሜ የማለፍ ዕድሉን አመቻችቷል፡፡ የአዲስ አድማስ ቡድን በነበረበት ምድብ 1 ከሪፖርተር ጋር የተደገመውን የመክፈቻ ጨዋታ ጨምሮ ባደረጋቸው 4 ጨዋታዎች 3 ድልና አንድ አቻ ውጤት አስመዝግቦ ምንም ሳይሸነፍ በተጋጣሚዎቹ ላይ 17 ጎል በማስቆጠርና 4 ግብ ብቻ በማስተናገድ በ7 ነጥብ በኢሬቴድ በግብ ክፍያ ተበልጦ 2ኛ ደረጃ በመያዝ ለዋንጫው ድል ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት ወደ ግማሽ ፍፃሜው ሊያልፍ ችሏል፡፡ በግማሽ ፍጻሜው ከአርቲስቶች ቡድን ጋር የተገናኘው ቡድኑ በፍፁም የጨዋታ ብልጫ 3ለ0 በማሸነፍ ለፍፃሜው ጨዋታ በቅቷል፡፡ በፍፃሜው ጨዋታ አዲስ አድማስ ከኢትዮጵያ ሬዲዮናቴሌቪዚን ድርጅት ለዋንጫ የተፋለመ ሲሆን በአስደናቂ ብቃት 1ለ0 አሸንፎ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ከዜድኬ ፕሮሞሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን 1ኛው የሚዲያና የኪነጥበብ ባለሙያዎች የእግር ኳስ ውድድር በሻምፒዮናነት አጠናቅቋል፡፡ በእግር ኳስ ውድድሩ ላይ 8 ቡድኖች የተሳተፉ ሲሆን ከየቡድኖቹ ያነጋገርናቸው አንዳንድ ጋዜጠኞችና ባለሙያዎች በአጠቃላይ ሂደቱ የተለያዩ ቅሬታዎች ቢኖራቸውም በጅማሮው እና በነበራቸው ተሳትፎ እርካታ እንደተሰማቸው ገልፀዋል፡፡ በእግር ኳስ ውድድሩ ከአዘጋጆቹ የውሳኔ አሰጣጥ፣ ከተጨዋቾች ተገቢነት እና ከሜዳ ላይ እሰጥ አገባዎች በተያያዘ ንትርኮች በዝተው ቢታዩም ጨዋታዎችን በአበበ ቢቂላ ስታድዬም በመገኘት በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ሲከታተሉት ሰንብተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ተስፋዬ ኦሜጋ በውድድሩ ላይ ተሳታፊ ከነበሩ ስምንት ቡድኖች ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት የውድድሩን ጅማሮ ከሞላ ጐደል ስኬታማ በማለት የህዝብ ንቅናቄ ለመፍጠር ከሚዲያው ጋር ተያይዘን እንሰራለን ብለዋል፡፡ ውድድሩ በአጭር ጊዜ ተዘጋጅቶ በመካሄዱ በየቡድኖቹ በቂ የአካልና የስነልቦና ዝግጅት እንዳይደረግ ተጽእኖ ነበረው፡፡ የውድድሩ ህገ ደንብና ስርዓት በቂ ምክክር ስላልተደረገበትና ተሳታፊዎችን ያግባባ አለመሆኑም ለውዝግቦቹ መንስኤ ሆኗል፡፡ ኮሚሽነር አቶ ተስፋዬ ኦሜጋ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ይህን በመሰሉ ዝግጅቶች የህዝብ ንቅናቄ ለመፍጠር በተያዘው ዓላማ የልማትና የዕድገት አቅጣጫ  ለመቀየስ እንዲሁም የከተማ መስተዳድሩ በስፖርቱ ዘርፍ ማሳካት የሚፈልጋቸውን ግቦች ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ለመስራትና  ለማስተጋባት አመቺ መድረክ ለመፍጠር ፍላጐት መኖሩን ገልፀዋል፡፡
የአወዳዳሪው አካል የተነሳበትን ዓላማ ሊያንፀባርቅ ይገባል ያለው ደረጀ ጠገናው ከሪፖርተር ሲሆን አርአያና ፈር ቀዳጅ ለሆኑ አንጋፋ ጋዜጠኞች የሚሆኑ ውድድሮች ቢዘጋጁ በማለት ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ አስተያየቱን የሰጣው የ2003 ጋዜጣኞች ቡድን ተሰላፊ የነበረው ጋዜጣኛ ጌቱ ውቤ ከቃልኪዳን መሄት ነው፡፡ የሸገር ኤፍ ኤም 102.1 የስፖርት ጋዜጠኛ የሆነው ፋሲል ረዲ ተቋማቸው በውድድሩ የተሳትፎ ፍላጐት ቢኖረውም ጋዜጠኞች በአፋጣኝ ስራዎች በነበሩበት እና ለፊልድ ስራዎች በወጡበት ጊዜ በመካሄዱ ተሳትፎ ሳይኖረን ቀርቷል ብሏል፡፡ ውድድሩ ጋዜጠኞች ተቀራርበው እንዲሠሩና ህብረታቸው እንዲጠናከር የሚያደርግ መሆኑን አምናለሁ ያለው ፋሲል ረዲ ወደፊት በሚዘጋጀው ውድድር የመሳተፍ ፍላጐት እንዳለን በዚህ አጋጣሚ እገልፃለሁ ብሏል፡፡    
የኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋዜጠኛ መኳንንት በርሔ ቡድናቸው ስለነበረው ተሳትፎ በሰጠው አስተያየት ውድድሩ አሪፍ እንደነበር ገልፃ፤ በየግጥሚያው በሜዳ ላይና ከሜዳ ውጭ በሆነ ባልሆነ የመነታረክ አላግባብ የመነጫነጭ የመጣላት ተግባር በአንዳንድ ጋዜጠኞች መስተዋሉ ልክ አይደለም ስርዓትን ከምናስተምር ባለሙያዎች ይህ አይጠበቅም በተሳትፏችን ዲሲፒሊን መጠበቅ አለበት ሲል መክሯል፡፡
በአርቲስቶች ቡድን ተሰላፊ የነበረው ተዋናይ ፍቃዱ ከበደ  በበኩሉ የውድድሩን ተሳትፎ ደስ ይላል ብሎ ገልፆታል፡፡ ለጨዋታው ድምቀት ሲባል ቡድኖች በትክክለኛና ተገቢ በሆነ ተጨዋች ቢሳተፉ ጥሩ ነበር ያለው ፍቃዱ፤ ጋዜጠኞች እና ተዋናዮች እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚችሉ የስፖርት ቤተሰቡ ማየቱ ትኩረት የሚያስገኝ ነው ብሏል፡፡ ሚዲያ ካፕ ተጀምሯል ሲባል እኔ ትወና ውስጥ ነው ያለሁት በእኔ ዘርፍ ያሉትን ስንጠየቅ አልሰማንም ይሉኝ ነበር የሚለው ፍቃዱ ከተዋናይ ያለሁት እኔ ብቻ ነኝ፡፡ በእኛ ቡድን ብዙዎቹ ሙዚቀኞች ናቸው፡፡ ወደፊት በቂ ቅስቀሳ ተደርጐ ተዋናዮች፣ ደራሲዎችና የፊልም ባለሙያዎች ቢሳተፉበት ደስተኛ ነኝ ሲል ተናግሯል፡፡

 

Read 5150 times Last modified on Thursday, 04 August 2011 14:30