ከላይ ብርቱካናማ ቀለም ያለው ሹራብና ጥቁር ቁምጣ የታጠቀው የአዲስ አድማስ ቡድን በውድድር ላይ በተሟሟቀ ዝግጅት፤ በማራኪ የድጋፍ አሰጣጥና በአስገራሚ የተሳትፎ ትኩረት ውድድሩን ካዘጋጀው አካል አድናቆት አግኝቷል፡፡
በእግር ኳስ ውድድሩ ሻምፒዮና የሆነው የአዲስ አድማስ ቡድን ልዩ ዋንጫ፤ የአምስት ሺህ ብር ሽልማትና የወርቅ ሜዳልያ አግኝቷል፡፡ በ2ኛ ደረጃ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቭዠን ድርጅት 3ሺ ብርና የብር ሜዳልያ እንዲሁም ሶስተኛ ደረጃ ያገኘው የ2003 ጋዜጠኞች ቡድን የ2ሺ ብርና የነሀስ ሜዳልያ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ቡድን እስከ ዋንጫ ድሉ ባደረገው ግስጋሴ ሽንፈት አላስተናገደም፡፡ በእግር ኳስ ውድድሩ በአጠቃላይ 6 ጨዋታዎች አድርጐ 5 ሲያሸንፍ አንድ አቻ ተለያይቷል፡፡ በተጋጣሚዎቹ ላይ 21 ጐል አስመዝግቦ 4 ብቻ ተቆጥሮበታል፡፡
በውድድሩ የመክፈቻ ጨዋታ ከሪፖርተር ጋር የተገናኘው የአዲስ አድማስ ቡድን 11 ለ1 በሆነ ሰፊ ውጤት ቢያሸንፍም በተጨዋች ተገቢነት በሪፖርተር በቀረበ ክስ ጨዋታው ተደግሟል፡፡ ከዚያም በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታውን ከአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሐን ጋር አድርጐ አዲስ አድማስ 2ለ0 አሸንፏል፡፡ በአዘጋጆቹ ውሳኔ በድጋሚ በተደረገ ጨዋታ ደግሞ ሪፖርተርን 2ለ1 ማሸነፍ የቻለ ሲሆን የመጨረሻ የምድብ ጨዋታውን ከኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቭዠን ድርጅት ጋር በማድረግ 2 እኩል አቻ ተለያይቷል፡፡ የአዲስ አድማስ ቡድን በነበረበት ምድብ በ7 ነጥብ በኢሬቴድ በግብ ክፍያ ተበልጦ 2ኛ ደረጃ በመያዝ ግማሽ ፍጻሜ ገባ፡፡ በግማሽ ፍጻሜው ከአርቲስቶች ቡድን ጋር የተገናኘው ቡድኑ በፍፁም የጨዋታ ብልጫ 3ለ0 በማሸነፍ ለፍፃሜው ጨዋታ ደርሷል፡፡ በፍፃሜው ጨዋታ አዲስ አድማስ ከኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዚን ድርጅት ለዋንጫ የተፋለመ ሲሆን በአስደናቂ ብቃት 1ለ0 በማሸነፍ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ከዜድኬ ፕሮሞሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን 1ኛው የሚዲያና የኪነጥበብ ባለሙያዎች የእግር ኳስ ውድድር በሻምፒዮናነት አጠናቅቋል””