ኢስላማዊ ኤግዚብሽኑን ከ25 ሺህ ሰው በላይ ጐበኘው
በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና ተባባሪዎቹ ያዘጋጁትን ኢስላማዊ አውደርእይ መክፈቻውን እና ያለ ትኬት የገቡትን ሳይጨምር ከ25 ሺህ ሰው በላይ እንደጐበኘው አዘጋጆቹ ገለፁ፡፡ ከሐምሌ 27 እስከ ነሐሴ 1 ለሕዝብ ክፍት ሆኖ ለቆየው አውደርእይ ከስድስት ክልሎች በተለይ ከአርጐባ፣ ከሚሌ፣ ጅማ፣ ሐረር እና ቀጥበሬ የመጡ ቅርሶች ቀርበውበታል፡፡ የአውደርእይ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፈይዘል ከማል ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ከአንድ ሺህ ዓመት በላይ ያስቆጠረውን ቁርአን ጨምሮ ከሐይማኖት፣ ከሥነ ሕንፃ፣ ከታሪክ፣ ከባህልና ሌሎች ዘውጐች አንፃር የቀረቡትን ቅርሶች በቋሚነት ለማሳየት ታስቧል፡፡ አውደርእዩ የተዘጋጀበትን ዓላማ ጠይቀናቸውም ..የሙስሊሙ እምነት፣ ባህልና ታሪክ እንዲታወቅ ማድረግ.. መሆኑን ገልው የቅርስ ጥበቃው የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድርሻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡በእስልምና ቅርሶች ላይ ያተኮረ አውደርእይ ሲዘጋጅ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ ነው፡፡