Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 20 August 2011 11:18

ሉሲ ለለንደን ኦሎምፒክ 180 ደቂቃ ቀራቸው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በለንደን ኦሎምፒክ አፍሪካን ወክለው የሚሳተፉ ሁለት ብሄራዊ ቡድኖችን ለመለየት ከሳምንት በኋላ ደቡብ አፍሪካ ከኢትዮጵያ እንዲሁም ናይጄርያ ከካሜሮን ይገናኛሉ፡፡ አፍሪካን በመወከል በኦሎምፒክ የሴቶች እግር ኳስ የሚሳተፉትን 2 ብሄራዊ ቡድኖች ለመለየት በሚደረገው የመጨረሻ ግጥሚያ አራቱ ቡድኖች 4 የደርሶ መልስ ጨዋታዎችን ያደርጋሉ፡፡ የዛሬ ሳምንት በጆሃንስበርግ የደቡብ አፍሪካ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን የኢትዮጵያ አቻውን ሲያስተናግድ አቡጃ ላይ ደግሞ ናይጄርያና ካሜሮን ይጫወታሉ፡፡

በለንደን ኦሎምፒክ በሴቶች እግር ኳስ 12 ብሄራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ፡፡ እንግሊዝ በአዘጋጅነቷ በቀጥታ አልፋ በታላቋ ብሪትኒያ ቡድን በመወከል ትሰለፋለች፡፡ ደቡብ አሜሪካን በመወከል ብራዚልና ኮሎምቢያ እንዲሁም አውሮፓን በመወከል ፈረንሳይና ስዊድን ማለፋቸውን ያረጋገጡ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በጆሃንስበርግ ለሚያደርገው የማጣሪያው የመጀመርያ ጨዋታ 21 ተጫዋቾችን ይዞ በደብረዘይት እየሠራ ቆይቷል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ተገቢ ትኩረት በበቂ ሁኔታ ያገኘ አይመስልም፡፡ ተጨዋቾችና አሰልጣኙ ማለፍ እንደሚቻል ሙሉ ዕምነት ይዘው ሲሠሩ የቆዩት በፌዴሬሽኑ ተገቢ ነገሮች ሳይሟላላቸው ነበር፡፡ ከውጭ አገር ቡድኖች የዝግጅት ግጥሚያ የማድረግ ዕድል አጥቷል፡፡ በትጥቅ ችግር እየተጉላላ ሰንብቶ ሰሞኑን በአቶ አብነት ገ/ጊዮርጊስ በአሜሪካ የተሠራ ሙሉ ትጥቅ ተለግሶለታል፡፡
የኢትዮጵያ ተጋጣሚ የሆነውና ባናያና በሚል ቅጽል ስም የሚጠራው የደቡብ አፍሪካ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በመላው አገሪቱ በመዘዋወር በርካታ ጨዋታዎች በማድረግና የብቃት ልምምድ በመሥራት በተሟላ የአካል ብቃት እንደሚገኝ በዋና አሰልጣኝ ተነግሮለታል፡፡ በመጨረሻዎቹ ቀናት በተጠናከረ የስነልቦና ዝግጅት ላይ ያተኮረ ልምምዱንም ሰሞኑን በኬፕታውን በሚገኝ ዘመናዊ ማዕከል እያደረገ ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ካለፈው ሁለት ወዲህ በ17 ጨዋታዎች ሳይሸነፍ ቆይቶ ከወር በፊት የመጀመርያውን ሽንፈት 1ለ0 የተረታው በዛምቢያ ነው፡፡
በታሪክ 2 ጊዜ ተገናኝተው እኩል አንድ አንድ ጊዜ ተሸናንፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሉሲ በአፍሪካ ዋንጫ 1 ግዜ ተሳትፎ 4ኛ ደረጃ ያገኘ ሲሆን በፊፋ ወቅታዊ ደረጃ በዓለም 106ኛ በአፍሪካ 15ኛ ነው፡፡ ተጋጣሚው የደቡብ አፍሪካ ባናያና በአፍሪካ ዋንጫ 9 ግዜ ተሳትፎ  አንድ ግዜ 4ኛ ደረጃ ሲያገኝ በፊፋ ወቅታዊ ደረጃ በዓለም 63ኛ በአፍሪካ 4ኛ የተመዘገበ ነው፡፡

 

Read 4408 times Last modified on Saturday, 20 August 2011 11:24

Latest from