Saturday, 27 August 2011 12:52

ኢህአዴግ ተስፋው አድጓል ወይስ በተስፋ ማጣት ውስጥ ነው?

Written by  አባበየሁ ለገሠ
Rate this item
(0 votes)

ንግሥት በገዛ እጁም ሆነ በአሁኑ ወቅት የሁለትዮሽ የውስጥ ጨዋታ ውጤት የሚመስለው መዘበራረቅ ደፍርሶ ይጠራ ዘንድ ያለን ዝንባሌ ያመለክታል፡፡
የሥርዓት ተስፋ መቁረጥ ከተቀናቃኝ ተስፋ መቁረጥ ከፍ ያለ እንደሆነ በቀላሉ ሊታረቁ የማይችሉ ለቁጥር የሚያዳግቱ ክስተቶች ሊስተናገዱ ስለሚችሉ አገሪቱ ይህ ሊያሳስባት ይገባል፡፡
ሥርዓት ተሻጋሪ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች
አስተሳሰብ መነሻው እንደየክፍሉ ነው፡፡ የሚያበቅለው ቅርንጫፍም ሆነ ቅጠሎቹ ባብዛኛው ግንዳቸውን ይመስላሉ፡፡ ልክ እንደ ግስ እርባታ በተለያዩ ቅርፆች ሊበዙም ይችላሉ - አስተሳሰቦች፡፡
አስተሳሰቦችን የሚከተሉት ድርጊቶች ናቸው፡፡ የተለያዩ አስተሳሰቦች ጐጂም ይሁኑ ጠቃሚ በገቢር ሊገለ ይችላሉ፡፡

አስተሳሰቦች ባለቤት አላቸው፡፡ ባለቤቱ ሊቀረ የሚችሉ፣ ወይም ደግሞ ከመጡ በኋላ ግለሰቡን የሚቀር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
በአገር ደረጃ የተለየ የአስተሳሰብን መንገድ በመከተል ሕዝብን ለመጥረብ መሞከርም ሆነ መሥራት የተለመደ ነው፡፡
የትኛውም ሥርዓት ይህን ሊፈጽም ይችላል፡፡ አዲስ እውቀት አይደለም፡፡ እንደ መንግሥት ይህ መንገድ የተለየ ክብደት አለው፡፡ በሁሉም ጉዳይ ተጠሪ ነው፡፡ ለልማቱም ሆነ ለጥፋቱ የመጀመሪያው ነው፡፡ የሚያመነጨው ሀሳብም ሆነ አስተሳሰብ ወቅቱን ለመሻገር የተሰላ ቢሆን ሥርዓት ተሻጋሪነቱን አጥርቶ የመመልከት ግዴታ አለበት፡፡ ጊዜያዊ አስተሳሰብ እና ድርጊት ጊዜውን አልፎ የሚሄድበት ሰፊ መንገድ አለ፡፡ የራስ አካባቢን ማሰብ፣ የወደፊት ዕጣ ፈንታን በጤናማ መንገድ መተለም፣ ኅብረተሰብን ማፍረስ (በማወቅም ሆነ ባለማወቅ) ለለውጥ ከሚያደርገው አስተዋጽኦ ይልቅ አሉታዊነቱ ካመዘነ ይህ እየተስፋፋ ሊሄድና እንደ ሰናይና ተስፋ ሰጪ ሊወሰድ እንደሚችል ማመዛዘን ተገቢ ነው፡፡
የዘመን ቅዝምዝም በሥርዓት ውስጥ የሚፈጠረው ሥርዓቱን ለማዳን ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህ ያለፈ ብልጭታ አለው፡፡ ህዝብን ብቻ ሳይሆን የተመረጡ ግለሰቦችን በተለያዩ ውጥረቶችና ወጥመዶች ውስጥ ለመዝፈቅ ከተሳካ (ሁሉም ላይ እንዳሴሩት አይሳካም እንጂ) ብዙ ወጪ፣ መዋቅር፣ ሸፍጥ እንደሚዘረጋ ይታወቃል፡፡ በዚህ ድርጊት የአገር መሪ፣ የፓርቲ (የገዢም ሆነ የተቀናቃኝ) ሊቀመንበር ይሳተፉበታል፤ ተሳትፈውበታል፡፡
ተቃናቃኞች እጃቸው እንዳለበት ይነገራል - በቅዝምዝሙ! በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ ንፁሀንን ለጥቃት ማመቻቸት ትክክለኛው መንገድ የሚቆረቁራቸው ሥርዓቶችና ፓርቲዎች መገለጫ ነው፡፡
ሥርዓት ተሻጋሪ አስተሳሰብ በጥሩም፣ በመጥፎም ነው፡፡ መጥፎ አስተሳሰብን መጋባት ለይቅርታ አይመችም፡፡ ጊዜውን ማለፍ በመፈለግ ውጤቱ ምንም ቢሆን ማንኛውንም ድርጊት መፈም የአስተሳሰብ መዳሸቅን እንዲሁም ቀቢፀ-ተስፋን ያመለክታል፡፡
የትኛውም የአገር መሪ፣ የፓርቲ ፕሬዝዳንት፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ (በጥሩም ሆነ በመጥፎ) ጉዳዩ አገሪቱ ከሆነች ሁሌም የመጀመሪያው በእጁ ነው፡፡ በመፍትሔነት የሚዘረጋውም ሆነ የሚያርከፈክፈው ሀሳብና አስተሳሰብ ሥርዓት ተሻጋሪ እንዲሆን ማቀድ አለበት፡፡ ምናልባት ሥርዓትን ማሻገር ሥርዓትን በመገሸር ሊሆን ይችላል፡፡ ሰላማዊነቱ ግን ያጠራጥራል፡፡
አገሪቱ በረጅም የሰላም እጦት የቆረበች ይመስል ይህ አዙሪት እንዲሸታት ማድረግ በአገር ደረጃ አርቆ አሳቢነትን አያመለክትም፡፡
የኢህአዴግ ሁለት መልክ
ኢህአዴግ ከረጅም ዘመናት ጀምሮ የለመደው ጨዋታ አለ፡፡ በአንድ አሉታዊ አስተሳሰብና ድርጊት ሁለት ካርድ ይዞ ይገባል፡፡ ጥፋትን በውክልናም ሆነ በቀጥታ ካስፈመ በኋላ ይህን ከርሱ ውጭ ያሉ የፈሙ አስመስሎ መንቀሳቀስ ይጀምራል፡፡ በዚህ በኩል የራሱን ሰዎች ልኮ የፈመው አጉል ድርጊት ውጤቱ ምን ይመስል እንደሆነ በሌላ በኩል ሌላኛዎቹን የራሱን ሰዎች ልኮ በተለያዩ ስልቶች የማጣራት ሥራ ይሠራል፡፡
የራሱ አባልም፣ ደጋፊም ባልሆኑ ሰዎች ላይ ሁለት መልኩን የሚያረጋግጥ በርካታ ድርጊቶችንና ሐሜቶችን በይፋና በህቡዕ እንደሚፈጽምና ፋይናንስ በማድረግ እንደሚያስፈጽም እርሱም፣ ሌሎችም ያውቃሉ፡፡
ለምሳሌ በቫት የሚከሰሱ ግለሰቦች በአገሪቱ ህግ መሠረት በፍጥነት የዋስትና መብታቸው ሊከበር ይገባል፡፡ ሕጉ መቼ ነው ዋስትናን የሚከለክለው? ይታወቃል፡፡ በዋስትና ወረቀቱ ላይ የተመለከቱትን ግዴታዎች አመልካቹ የማይፈጽም የሚመስል ከሆነ፣ ቢለቀቅ ሌላ ወንጀል ይፈጽም ይሆናል ተብሎ የሚገመት ሲሆን፣ ምስክሮችን በመግዛት (በማባበል) ወይም አስረጂ የሚሆኑበትን ያጠፋ ይሆናል ተብሎ ሲገመት ነው፡፡ ይህን የሕግ ማዕቀፍ በግልጽ መጣስ የሕግ ተርጓሚውን ብቻ ሳይሆን የአስፈጻሚውን ስውር የእጅ ጥላ ሊጠቁም የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ያመለክታል፡፡
በአገሪቱ የተከሰተው የበሬ ሽንትነት አካሄድ የሥርዓቱን መንታ ባህርይ ማሳያ ነው፡፡ በአንድ በኩል ችግሮች የትና በምን መጠን እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በየቀኑ የተለያዩ ወገኖች ይጠቁማሉ፤ ይገልጻሉ፤ ያመለክታሉ፡፡ ጭራሽ የሥርዓቱ ሰዎች በአገሪቱ ነፍስ ዘርተው የሚስተዋሉ ገደቦችን እየነቀሱ፣ በቂ እውቀት እንዳላቸው ቢታወቅም፣ በሌላ በኩል በሁለተኛው መልኩ አንዳችም ሽው ያላለው ይመስል በዝምታው ዛጐል ስር ተከናንቦ ቁጭ ብሏል፡፡ አባላቱ ሁሉ ፈዘውና ደንዝዘው ያሉ ይመስላሉ፡፡
ያውቃሉ ወይስ ይተዋወቃሉ?
አንድ ሥርዓት ህመሙ ብዙ ሊሆን ይችላል፡፡ አባል መሆን ያልፈለገን ግለሰብ አባል ለማድረግ የተለያዩ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን ከመፈም አንስቶ የሥርዓቱ ሰዎች ግልጽ መረጃና ማስረጃ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ዳተኝነት ይታይባቸዋል፡፡ ነገሮችን በተለሳለሰ መንገድ የማስኬድ ፍላጐት ከሆነ ህዝቡም ሆነ ግለሰቦች፣ በተለይ የአንዳንድ ቤተሰብ አባላት ጤንነት አደጋ ውስጥ እንዲገባ እየተደረገ ባለበት ሁኔታ መለሳለሱ ምን ለመፍጠር ነው?
ክፍተት ባለበት ውንብድና መፍላቱ የማይቀር ነው፡፡ የመንግሥታዊነት ባህርይ እያነሰ ሲመጣ፣ ትናንሽ ትዕቢቶች እያቆነጐሉ ይሄዳሉ፡፡ ሐረግ ያበጃሉ፡፡ ሐረጋቸው እየጠበቀ ሲሄድ የሚጠልፈው ይጨምራል፡፡ በመንግሥትነት ማሰብ እየቀነሰ፣ በቡድንተኝነት መወሰን ሲስፋፋ አገር ተረጋግቶ ማደግ የማይታሰብ ነው፡፡
ኢህአዴግ የድለላ አካሄዱን ማጤን አለበት፡፡ ህዝቡ ያስባል፡፡ ውሸትና እውነቱን፣ ጤነኛ አስተሳሰብን ሳያውቅ ቀርቶ አይደለም፡፡ አንድ አስተሳሰብንና ድርጊትን የሁሉም ህዝብ ፍላጐትና አቋም አድርገው ለማቅረብ የሚነዝሩ አሉ፡፡ የሁለትዮሽ ጨዋታውን የማያግዙ፣ በየትኛውም ዘመን ቢሆን ለዚህ ፈቃደኛ የማይሆኑ፣ ሆነውም የማያውቁትን ለማስቀደም መሞከሩ የበለጠ ወደ ማጡ ከመግባት ሌላ መጨረሻ ላይ ለብቻ መቅረት ነው፡፡
የሥርዓቱ የተወሰኑ ሰዎች የሚያውቁት ነገር ይኖራል ባዮች ቢኖሩም፣ ከተቃራኒዎቹም እንደዚሁ አሉ ማለትን የሚያሰምሩበትም አልጠፉ፡፡ ስለዚህ ይተዋወቃሉ ማለት ነው?
አደገኛ ጠጠሮቹ
የተወሰኑ ተቀናቃኞችም ሆኑ ኢህአዴግ እንደ ቁልፍ ጠጠር የሚጠቀሙበት ሴራን በተለይ ማጠላለፍን ነው፡፡
ሁሉም በየፊናው ስለሚያሰርግ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም የተሳሳተ፣ የተፈጠረ፣ የተቀመመ ምክር ስለሚጋቱ በተለይ የራስን ጥፋትና ዝቅጠት ለማምለጥ የሚጫወቱባቸው የተለያዩ ጠጠሮች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ቢጤአቸውን መፍጠር ከመሻት አንጻር፣ ሌሎች ደግሞ በየዋህነት ለአገርም ሆነ ለህዝብ የሚጠቅም ሀሳብ ሲሰነዝሩ ያንን ቦርሸውና ለውሰው ለአሳጭነትና ሌላውን ለመቆርቆርና ለመኮርኮም ይጠቀሙበታል፡፡ በዚህም እነርሱ ብልጥ ሌላው ሞኝ ይሆናል፡፡ በድቃቂ አስተሳሰብ፣ ብል ባነከተው ሰብዕና መኩራራትና ተሰሚ ለመሆን መውተርተር የሀሰት ክብርን የሚያጐናጽፍ ሆኗል፡፡
ሕግ የሚያስፈልገው ጉዳይና ሰው እያለ በማያስፈልገው ላይ ጊዜ ማባከን፣ መታረም ያለ ቢሆንም ማስፈራራትና ማንገላታት፣ የፈጠራ ውንጀላዎችን ማዳመጥና መቀበል፣ ጠንካራ ጥቆማን መሸሽ፣ የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን ሳያስፈልግ ሙያን ብቻ መወጣት የሚፈልጉና በዚህ መለኪያ መሥራት የሚቻልበትን ዕድል አባል ባለመሆን ብቻ መዝጋት፣ አንድን ባለሙያ ለሙያው ቅርብነት ቀርቶ በሕገ-መንግሥቱ በር በኩል አልፈው የማያውቁ መሆናቸው ግብራቸው በሚያረጋግጥባቸው ግለሰቦች መገምገም፣ ከየትም የቃረሙትን ግሳንግስ ይዘው የሚመጡትን ማስተናገድ፣ አጀንዳቸውን አለማጣራት. . . በጠጠርነት የሚያገለግሉ ናቸው፡፡
በወጪ መተጋገዝ ለተቀራረቡና ለቤተ-ዘመድ የተለመደ ነው፡፡ ዋናው ያላቸው ሰላማዊ ግንኙነት ነው፡፡ መግባባትም ሆነ መቀራረብ በየትኛውም ፓርቲ፣ መንግሥት ትዕዛዝ ሊፈም አይችልም፡፡ የግል ጉዳይ ነውና! ለፖለቲካ ፓርቲ ፍጆታ የሚውለን ጠጠር አለማወቅ bአሉታዊnTM ሆነ በአዎንታዊነት ሥርዓት ተሻጋሪ ባህርይን ተላብሶ ነገ በራስ ላይ ሊዘንብም ሆነ ሊያካፋ የሚችልን ስሜት ለመቆጣጠር አያስችልም፡፡
የጠጠሮች ዓይነት ብዙ ናቸው፡፡ በተለይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ተገን ማድረግን ይጨምራል፡፡ መንግሥት ይህን በዝርዝር ቢያውቅም ቤቱ አልገባ ይሆናል፡፡ ነገ ሊገባ እንደሚችል ይወቅበት፡፡
ሥርዓቱ የተሸነፈለት የማተነሽ ባህርይ
ኢህአዴግ የሚፈልገውን ማንኛውንም ሰው በመጀመሪያ በሰላም የሚጠይቀው በቀላሉ የሚገቡትን ነው የሚባለው እውነት ሳይሆን አይቀርም፡፡
ሊያስቸግሩኝ ይችላሉ የሚላቸውን ግን በጉንተላ ነው የሚያናግራቸው፡፡ ቀድሞ በሰላም ለምን አይጠይቅም? ፍርሃት ሊሆን ይችላል፡፡
እምቢ መባልን አለመቀበል! በርካታ የውስጥ ክርክሮችን እያደረገ እንደመጣ የሚነገርለት ፓርቲ፤ የሚፈጽማቸው አንዳንድ ድርጊቶች ግን የተለያዩ ጥያቄዎችን ያስነሱበታል፡፡ ጥያቄዎቹ ሲነሱበት እንደተለመደው የሚመለከተው የማይመለከተው፣ የሚያውቀውን አንዳችም ሽው ያላለው መስሎ መቅረቡ የግሉ ነው፡፡
አንድ ሰው የፓርቲ አባል ሳይሆን መኖር ይችላል፡፡ ከፓርቲ አባልነት ይልቅ ባለመሆን የሚሠራው ሥራ እጅግ ብዙ ነው፡፡ እንዲያውም ጤናማ ፓለቲካ ባለባቸው አገራት የፖለቲካውን ሥራ በቀጥታ የሚሠሩት ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡ መግባባትና መደማመጡ ስላለ ነው፡፡ መንግሥት የሚያወጣቸው ህጎችም ሆኑ ፖሊሲዎች ከነተግባራቸው በመልካም ጐኑ የሚገመቱ ናቸው፡፡ አሁን እዚህ ጋ ቢያጣምሙብኝስ? የሚል ሀሳብ የአገር ሰው እንዲያስብ ማድረግ አያስኬድም፡፡ እዚህ ካልሆነ፡፡
የፓርቲ አባልነት መብት ነው፡፡ ክቡር መብት! ግዴታ አይደለም፡፡ በህይወት ዘመኑ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆነ፣ መሆንም የማይፈልግን ሰው ማንኛውንም ድርጊት በመፈም እንዲገባ ለማድረግ መሞከር ጤናማ ፖለቲካን ለመገንባት አያመችም፡፡ ምናልባት መሸጋገሪያ ካልሆነ በቀር፡፡
አንዳንዴ የብሔር ጠጠርን ለፓርቲ አባልነት ለመጠቀም መሞከር፣ የብሔር ስያሜ መስጠት፣ ይህን ለሚፈልግና ለፈቀደ፣ ይህን ላስቀደመ ሲፈቀድለት፤ ሰውን ላስቀደመ፣ ብሔሮችን ላከበረም ይኸው ሊተውለት ይገባል፡፡ ባለቤቱ ይወስን መባል አለበት፡፡
ሥርዓቱ ፈታኝ ጊዜ አሳልፎ ቢመጣም ለትናንሽ ነገሮች መሸነፉና መገዛቱ ይገርማል፡፡ የሚፈጽማቸው ድርጊቶች ታሪኩን ይዘው የሚጓዙ ናቸው፡፡
በገዢውም ሆነ በተቀናቃኝ አንዳንድ መሪዎች በተለያዩ ግለሰቦች እና ህዝብ ላይ የሚወሰኑ ኢ-ፍትሐዊ ውሳኔዎች መዘዛቸው በቀላሉ የማይተኩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
እልህ ውስጥ ያሉ የተወሰኑ ባለሥልጣናት የእልኸኝነት መነሳሳትን ለሚገባው የእድገት ለውጥ ሲጠቀሙበት ያግባባል፣ ያስማማል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶችና ጐጂ መነሻዎች በተመረጡ ግለሰቦችና ባጠቃላይ ኅብረተሰቡን በኑሮም ሆነ በሌላ መንገድ የሚያጠቁ ባለሥልጣናት የሚመለከታቸውን ከማይመለከታቸው መለየት ሲኖርባቸው ለዚህም ተገቢውን መረጃና ማስረጃ መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡
በዚህ ኅብረተሰብ ውስጥ ለተለያዩ ተልዕኮዎች የተሰባሰቡ ኃይሎች እንዳሉ በተለያየ መንገድ ይሰማል፡፡ ለመልካም መንገድ የሚሰባሰቡትን ባንድ በኩል በማስቀመጥ፣ ለጥፋት የሚተጉትን ብንወስድ የሚያስቡት አጉል መንገድ ገደል ሲበዛው፣ ከምድር ተነስተው የተለያዩ ድርጊቶችን ባላጀቧቸው ላይ እንደሚፈጽሙ ይታወቃል፡፡ ስንፍና ነው! ሰውዬውን ማግኘትና ሀሳቡን መሞገት አንድ ሊሆኑ አይችሉም፡፡
በአሁኑ ወቅት ህዝቡ የጠራ ምስል የለውም፡፡ ተቀናቃኞቹም ተመሳሳይ አውድ ነው የሚታይባቸው፡፡ በየጊዜው ለየት ያሉ ክስተቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ኢህአዴግ በተስፋ ማጣት ባህርይ ውስጥ ነው ያለው ወይስ በእርግጥ ከሚስተዋሉት አስገራሚ ዚግዛጐች አንጻር ተስፋው አድጓል ማለት ይቻላል?

 

Read 2821 times Last modified on Saturday, 27 August 2011 13:02