Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 27 August 2011 13:06

ጠፈርተኛው ሮቦት እንቅስቃሴ ጀመረ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የአሜሪካኑ የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ መረጃዎችን እየሰበሰበ በማቀበል በዘርፉ የሚደረገውን የምርምር ሥራ እንዲያግዝ ከወራቶች በፊት ወደ ዓለም አቀፉ የህዋ ጣቢያ ልኮት የነበረውን ሮቦት ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲነሳ ማድረጉን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡ የስነ ፈለክ ተመራማሪዎችን የሚያግዝ ልዩ ሮቦት እንደሆነ የተነገረለት ..ሮቦናውት.. ምድር ላይ ከሚገኘው የመቆጣጠሪያ ማዕከል በተላለፉለት ተእዛዝ መሠረት ሲስተሙ እንዲበራ ከተደረገ በኋላ ስላለበት ሁኔታ አንዳንድ መልእክቶችን እንደላከ የተገለ ሲሆን ነገሩ በሮቦት ቴክኖሎጂው ዘርፍ የታየ ትልቅ ስኬት ነውም ተብሏል፡፡ እንደ ዓይን የሚያገለግሉት እና መረጃዎችን የሚቃርምባቸው ካሜራዎች ያሉት ይህ ጠፈርተኛ ሮቦት ወደ ምድር ከላካቸው መረጃዎች መካከል ደግሞ በህዋ ጣቢያው ላይ የሚገኘውን የአሜሪካን ቤተ-ሙከራ የሚያሳይ ምስል እንደሚገኝበት ለማወቅ ተችሏል፡፡

የስነ-ፈለክ ተመራማሪዎችን ማገዝ ይችል ዘንድ በሰው መልክ የተበጁ እጆች (እና ጣቶች) ያሉት ይህ በልዩ ሁኔታ ተሠርቶ ወደ ጠፈር የተላከው ሮቦናውት እንደ ሰው የስበት ኃይል በሌለበት ሁኔታ ውስጥ መንቀሳቀስ እንዲችል ተደርጐ የተሠራ ሲሆን በሆዱ ውስጥ ከተገጠመው ዋነኛው የኮምፒዩተር ሲስተም በተጨማሪ በእጆቹ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች የሚመሩ ከሰላሳ በላይ የሚሆኑ ፕሮሰሰሮችም አሉት፡፡ በአሜሪካ ሂውስተን ግዛት በሚገኘው የመቆጣጠሪያ ጣቢያ ያሉ ተመራማሪዎች ደግሞ በያዝነው ሳምንት የሮቦቱን ሲስተም በማብራት ኮምፒዩተራይዝድ የሆነውን ህያውነት የዘሩበት ሲሆን ያንንም ተከትሎ ሮቦናውት መልእክት አስተላልፏል፡፡ ነገር ግን ጠፈርተኛው ሮቦት ሙሉ ለሙሉ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ አለመደረጉ ታውቋል፡፡ ሁለት ሰዓት በፈጀው በዚህ ሙከራ ላይ ሮቦናውት ለረጅም ጊዜ ያለ እንቅስቃሴ ከተቀመጠበት ሁኔታ ተነስቶ እንቅስቃሴ እንዲጀምር ከተደረገ በኋላ ተመልሶ እንዲጠፋ የተደረገ ቢሆንም በመጪው የፈረንጆች መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ግን ሙሉ ለሙሉ መንቀሳቀስ የሚጀምርበት ሁኔታ እንዳለ ነው የተገለው፡፡ ናሳ በጠፈር ጣቢያ ላይ የሚገኘው ይህን ሮቦት ተመልሶ እንዲጠፋና የእሳት መከላከያ ወዳለው የመቀመጫ ቦታው ውስጥ እንዲገባ ያደረገው ደግሞ ሮቦናውት በውስጡ ሊቀጣጠሉ የሚችሉ ነገሮች ስላሉት እንደሆነ ታውቋል፡፡ ሮቦቱ አሁን ባለበት ደረጃ በዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ውስጥ ብቻ ተወስኖ የሚቀመጥ ሲሆን ወደፊት የሚመጡት ሮቦቶች ግን ከዚያ ወጥተው እራሳቸውን ችለው በህዋው ውስጥ ሁሉ መንቀሳቀስ የሚችሉ እንደሚሆኑ ነው የተገለው፡፡
የዚህ ፕሮጀክት ምክትል ኃላፊ የሆኑት ኒኮላስ ራድፎርድ አሁን የታየው ነገር እጅግ የሚያስደስትና አመርቂ ነገር እንደሆኑ የገለ ሲሆን ከዚህ ጋር አያይዘውም ሁኔታው ልክ እንደዚህ ስኬታማ ከሆነ ሮቦቱ በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ላይ በህዋ ጣቢያው ላይ ያለውን የአየር እንቅስቃሴና ሌሎች መሰል ነገሮችን ሁሉ ለመለካት የሚችል ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው ያመለከቱት፡፡

 

Read 8619 times Last modified on Saturday, 27 August 2011 13:08