Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 27 August 2011 13:42

የአባቱ ልጅ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የዜማና ግጥም ደራሲ፣ የሙዚቃ መሣሪያዎች ተጫዋችና ድምፃዊ ከነበረው አባቱ ተፈራ ካሣናከተወዛዋዥ
እናቱ ወ/ሮ አረጋሽ ኩምቴሳ መወለዱ ገና በልጅነት  ዕድሜው ስሜቱ ለሙዚቃ እንዲያዳላ ምክንያት እንደሆነው ይናገራል፡፡ ተወልዶ ያደገበት ፈረንሳይ ለጋሲዮን ለበርካታ የጥበብ ሰዎች መፍለቂያ የሆነና አንጋፋ የሙዚቃ ባለሙያዎች የከተሙበት አካባቢ መሆኑ ደግሞ ስሜቱ የበለጠ ከሙዚቃ ጋር እንዲተሳሰር አደረገው፡፡ ጐረቤታቸው የነበረው አንጋፋው ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠና ወላጅ አባቱ ተፈራ ካሣ የሙዚቃ ሥራ ልምምድ ሲያደርጉ ሁሌም ከሥራቸው አይጠፋም ነበር፡፡

የድም አወራረዳቸውን፣ የዜማ አወጣጣቸውን በተመስጦ እየተመለከተ ማደጉ ለዛሬ እሱነቱ መነሻ ሆኖታል፡፡ ከአመታት በፊት ለአድማጭ ጆሮ ባደረሰው ..እኔስ አባብዬ.. በተሰኘ አልበሙ ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ ሰሞኑን ገበያ ላይ የዋለውና ..እኔ አይደለሁማ.. የተሰኘ አዲስ አልበሙን ተከትሎ ባለፈው ቅዳሜ በአገራችን እምብዛም ባልተለመደ ሁኔታ በመስቀል አደባባይ ልዩ የማስተዋወቅና የአክብሮት ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ የአዲስ አደማስ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ ተገኝታ ከድምፃዊው ግርማ ተፈራ ካሣ ጋር  ቆይታ አድርጋለች፡፡

ከጅማሬህ እንነሳ . . .
ጅማሬዬ ከቤት ነው፡፡ አባቴና ጥላሁን ገሠሠ ቤት ውስጥ የተለየዩ የሙዚቃ መሣሪያዎችን አባቴ እየተጫወተ የድም ልምምድ ሲያደርጉ እያየሁ ነው ያደኩት፡፡ በተፈራ ካሳና በጥላሁን ገሠሠ መካከል ማደግ በራሱ አንድ በእንክብካቤ እንደሚያድግ ችግኝ መሆን ነው፡፡ ከዛ እየቀጠለ ቀበሌ ከፍተኛ እያለ ሄዶ ሙዚቃ ት/ቤት ለመግባት በቃሁ፡፡ እዛ እየተማርኩ ሀገር ፍቅር ቲያትር አርብ አርብ ይዘጋጅ በነበረው ዝክረ ፕሮግራም ላይ መሥራት ጀመርኩ፡፡ ይህም ከህዝብ ጋር እንድገናኝና ሙያውን እንዳዳብር በጣም ረድቶኛል፡፡
የሙዚቃ ሙያ ዝንባሌህን አባትህ ይወድልህ ነበር?    
ገና ስጀምር ፈሞ ፍላጐት አልነበረውም፡፡ እሱ በሙያው ውስጥ የኖረና ለትውልድ ሊተላለፍ የሚችል አቅም ያላቸውን ሥራዎች ቢሠራም ምንም ባለመጠቀሙ እኔ ልጁም የሱን ጐዳና ተከትዬ እንድሄድ አይፈልግም ነበር፡፡ የእኔ ፍላጐትና ዝንባሌ ግን ወደ ሙዚቃው በማድላቱ ምንም ማድረግ ባለመቻሉ ፍላጐቴን ሳይጫን ስሜቴን ተቀብሎ ወደ ሙዚቃ ት/ቤት እንድገባ አደረገኝ፡፡ በህይወት እስከነበረበት የሁለተኛ ዓመት የሙዚቃ ት/ቤት ቆይታዬ ድረስም በጣም ያበረታታኝና ይደግፈኝ ነበር፡፡
አባትህ አንተመድረክ ላይ  ስትጫወት የማየት አጋጣሚ ነበረው?
አዎ አገር ፍቅር ቲያትር ዝክረ የመጨረሻ መዝጊያ ፕሮግራም ላይ ከተጋበዙ ድምፃውያን መካከል አንዱ እኔ ነበርኩ፤ አባቴም በሥፍራው በክብር እንግድነት ተገኝቶ ነበር፡፡ በዚህ መድረክ ላይ ስዘፍን አይቶኝ አቅፎኝ ስሞኝ አበባ ሰጥቶኛል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ መድረክ ላይ የወጣህበትን ዜማ ታስታውሣለህ?
አዎ የመልካሙ ተበጀ ..ዳህላኬ ታየችኝ.. የሚለው ዜማ ነው፤ ለመልካሙ ታላቅ አክብሮትና ፍቅር አለኝ፡፡
ምን ያህል አልበሞችን አሣትመሀል?
አራት ያህል አልበሞችን አሣትሜአለሁ፡፡ ከእነዚህ መካከል ሁለቱ ከሌሎች ድምፃውያን ጋር  በጋራ ያሳተምኳቸው ሲሆኑ ሁለቱ ግን የራሴ ሙሉ ሥራዎች ናቸው፡፡
በጋራ ከሠራኋቸው መካከል የመጀመርያው ክቡር ዘበኛ እንደገና ሲቋቋም ..የክብር ዘበኛ ቅርስ.. በሚል ከእነ ተዘራ ኃይለሚካኤል፣ እሣቱ ተሰማና አየለ ማሞን የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎች ጋር የአባቴን አልጠላሽም ከቶ እና ኧረ መልሱን ስጪኝ የተሰኙ ሁለት ዜማዎችን ሠርቻለሁ፡፡ ሌላው ከኃይለየሱስ ግርማና ከሂሩት በቀለ (አንጋፋዋ አይደለችም) ጋር በጋራ የሠራሁት ካሴት ነው፡፡ ሌሎቹ ሁለቱ የራሴ ናቸው፡፡
'Xn¤ስ xÆÆü' የሚለው ካሴትህ በወቅቱ እጅግ ተወዳጅ የነበረ ሥራ ነው፡፡ ዘፈኑን የዘፈንከው ለሟች አባትህ ማስታወሻ እንደነበርም በወቅቱ ስትናገር ነበር፡፡ ለመሆኑ ግጥሙ እንዴት ተሠራ?
የዚህ ዘፈን ግጥም ደራሲ ተመስገን ተካ ነው፡፡ ቁጭ ብለን ስሜቴን በደንብ እንድነግረው ጠየቀኝና በማግስቱ ግጥሙን ይዞልኝ መጣ፡፡ በጣም ነበር የተገረምኩት፤ ..እኔስ አባብዬ.. የሚለው ዘፈን ትክክለኛ ስሜቴን የገለፀልኝና ውስጤን የተናገርኩበት ዘፈን በመሆኑ በጣም እወደዋለሁ፡፡
የእውነትና ከልብ የተሠራ ሥራ ስለሆነም ይመስለኛል በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘው፡፡ የዚህ ዘፈን መውጣት በወቅቱ ለእኔ ትልቅ ጉልበት ሆኖኝ ነበር፡፡ ይህ ዘፈኔ ዛሬም ድረስ ለእኔ እንደ ማስተር ፒስ የማየው ዘፈኔ ነው፡፡
አባትህ በግጥምና ዜማ ድርሰት በወቅቱ ስሙ የተጠራ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከሥራዎቹ መሃል ጥቂቶቹን አስታውሰን?          
አባቴ በህይወት እያለ በርካታ ግጥምና ዜማዎችን ደርሷል፡፡ ራሱ ከተጫወታቸው ዘፈኖቹ በተጨማሪ ለእነ ጥላሁን ገሠሠ ሁሉ ዜማና ግጥም ይሰጥ ነበር፡፡ ከእነዚህ መካከል ለማስታወስ ፍቅር ከእኛ እንዳይለየን፣ ያለቀሰ ሲስቅ፣ የሣቀ ያለቅሣል፣ ምን ጥልቅ አድርጐኝ፣ እና ..እንደዋዛ.. የተባሉት ዘፈኖች ጥቂቶቹ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለእድገት በህብረት እንዘምት - ወንድና ሴት ሣንል ባንድነት የተባለው ህብረ ዜማ ግጥምና ዜማ ድርሰቱ ያባቴ ነው፡፡    
ስለ አዲሱ ሥራህ ..እኔ አይደለሁማ.. የሚል ስያሜ ስለሰጠኸው አልበምህ አጫውተን?
አዲሱ አልበሜ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ብዙ የደከምኩበትና የለፋሁበት ጊዜዬን፣ አቅሜንና ገንዘቤን ሁሉ ያለመሰሰት ያወጡሁበት ሥራ ነው፡፡ ቋሚ መኖሪያዬ ለንደን ቢሆንም ለዚሁ ሥራ ከአራትና አምስት ጊዜ በላይ እዚህ ተመላልሻለሁ፡፡ ለስድስትና ሰባት ወራት እዚህ እየተቀመጥኩ ነው የሠራሁት፡፡ በግጥምና ዜማ ድርሰቱ አለምፀሐይ ወዳጆን ጨምሮ ታላላቅ የዘፈን ግጥምና ዜማ ደራሲዎች ተሣትፈውበታል፡፡ ቅንብሩንም አገራችን አሉኝ  ከምትላቸው ታላላቅ የዘመኑ አቀናባሪዎች መካከል አበጋዝ ክብረወርቅ (ሺዎታ)፣ ኤልያስ መልካና አማኑኤል ይልማ ሠርተውታል፡፡ የተዋጣ ሥራ ነው የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ አልበሙን ፕሮዲዩስ ያደረኩት እኔው ራሴ ስሆን አከፋፋዩ ቮካል ሪከርድስ ነው፡፡ በአጠቃላይ በዜማ፣ በግጥምና በቅንብር በጣም የማከብራቸውና በህይወቴ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ብሠራ ብዬ የተመኘኋቸው ሰዎች የተሳተፉበትና ጊዜ ተወስዶ ጥሩ ተደርጐ የተሰራ ሥራ ነው፡፡
በአዲሱ አልበምህ ከቀድሞ የአባትህ ሥራዎች መካከል ያካተትከው አለ?
በአዲሱ አልበሜ ከአባቴ የቀድሞ ሥራዎች መካከል ሁለቱን አካትቻለሁ፡፡ ..ማን ነበር ያላንቺ.. እና ..ጥላኝ እኮ ሔደች.. የተባሉትን፡፡ ሥራዎቹ የቀድሞ ይዘታቸውን ሣይለቁ ባማረ ሁኔታ የተሰሩ ለመሆናቸው እርግጠኛ ሆኜ እናገራለሁ፡፡ አሁን አሁን ሪሚክስ እየተባሉ በሚሰሩ የቀድሞ ሥራዎች ላይ የሚነሱ ችግሮች እነዚህ ሥራዎች ላይ አይታዩም የሚል እምነት አለኝ፡፡
በአዲሱ አልበምህ ላይ ካካተትካቸው የአባትህ ዘፈኖች አንዱ ታሪካዊ ግጥምጥሞሽ አሉት ይባላል፡፡ የትኛው ዘፈን ነው? ምንድነው ታሪካዊ ግጥምጥሞሹ?   
ዘፈኑ ..ማን ነበር ያላንቺ.. የተባለው ዘፈን ነው፡፡ ታሪካዊ ግጥምጥሞሹ ደግሞ በ1962 ዓ.ም አባቴ ይህንኑ ዘፈን ሲዘፍን ኳየር ይቀበለው የነበረው መሐሙድ አህመድ ነበር፡፡
ከ41 ዓመታት በኋላ ዘፈኑን እኔ ስዘፍነው ኳየር የተቀበለኝ መሃሙድ አህሙድ ነው፡፡ ጐሣዬ ተስፋዬና ማዲንጐ አፈወርቅም ተቀብለውኛል፡፡ እናም ይሔ አስገራሚ መገጣጠም አስገራሚ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ደግሞ እኔ በጣም እድለኛ ነኝ፡፡
የቅጂ መብት አለመከበር በርካታ ድምፃውያን ሥራቸውን ወደ ገበያ ይዘው እንዳይመጡ አግዷቸዋል፡፡ አንተ ይህን ችግር እንዴት አልፈዋለሁ የሚል እምነት ይዘህ ነው ወደ ገበያው የገባኸው?  
የቅጂ መብት አለመከበር አሳታሚውንም፣ ድምፃውያኑንም የነካና ለሙዚቃው ኢንዱስትሪ እድገት ከፍተኛ አሉታዊ ተእኖ ያሳደረ ጉዳይ ነው፡፡ ግን በጣም የለፋሁበት ሥራ በመሆኑ ተሰርቶ አልቆ እጄ ላይ መቆየቱን አልወደድኩትም፡፡
ያለቀ ሥራ ማቆየት ሥራው እንዲያረጅና ወቅታዊ ለዛና ጣዕሙን እንዲያጣ ያደርገዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ አሁን አሁን ህብረተሰቡም በኮፒ ሥራዎች ላይ ከቀድሞ የተሻለ ግንዛቤ አለው፡፡ ደግሞሞ ሁሉንም የሚያደርገው እግዚአብሔር ነው፡፡
በአገራችን እምብዛም ባልተለመደ ሁኔታ የግርማ ተፈራ አድናቂዎችና ወዳጆች በመስቀል አደባባይ ባለፈው ቅዳሜ ተሰባስበው ነበር፡፡ እስቲ ስለ ፕሮግራሙ ምንነትና እንዴት ሊታሰብ እንደቻለ አጫውተን፡፡
የዚህ ፕሮግራም ዋንኛ አስተባባሪ አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ ነው፡፡ እኔ ፈጽሞ ስለ ፕሮግራሙ አላውቅም፤ ሰርፕራይዝ ነው ያደረጉኝ፡፡ ለእኔ የተነገረኝ ቅዳሜ በሶስት ሰዓት መስቀል አደባባይ እንድገኝ ብቻ ነው፡፡ በሰዓቱ ከሥፍራው ስደርስ አካባቢው የእኔን ፖስተር ዙሪያቸውን በለጠፉ መኪኖች ተሞልቷል፡፡ በተዘጋጀልኝ ነጭ መርቼዲስ እንደ ሙሽራ ታጅቤ ከተማውን ስዞር ነው የዋልኩት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተዘጋጁ በራሪ ወረቀቶች ላይ ፊርማዬን የማኖር ሥነስርዓት ሁሉ ተዘጋጅቶልኝ ነበር፡፡
በወቅቱ ታዋቂ አርቲስቶች፣ ስፖርተኞች፣ ታዋቂ ነጋዴዎች ሁሉ ተገኝተው ነበር፡፡ በእውነቱ ለእኔ በጣም ያስገረመኝና ፈጽሞ ያልጠበኩት ፕሮግራም ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ አርቲስቱ እርስ በእርስ መረዳዳት፣ መከባበርና መደናነቅ እንደሚገባው ያሳየ የሚገርም ዝግጅት ነበር፡፡
ለመሆኑ በወቅቱ ምን ተሰማህ?
ፈጽሞ ያልጠበኩት ነገር ስለነበር በጣም ነው የደነገጥኩት፡፡ እኔን አክብሮ ውድ ጊዜውን ሰጥቶ ስሜቱን በዚህ መልኩ ሊገልጽልኝ የሚችል የሙያ አጋር አለኝ ብዬ አስቤ ስለማላውቅ በጣም ነው ሰርፕራይዝድ የሆንኩት፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከአቅሜ በላይ የሆነ ዕዳ እንዳሸከሙኝ ነው የተሰማኝ፡፡ በዚህ አጋጣሚ በራሱ ፍላጐትና ተነሳሽነት ይህንን ፕሮግራም በዚህ መልኩ እንዲከናወን ያስተባበረውን አርቲስት ታምሩ ብርሃኑን እጅግ አድርጌ ላመስግነው እወዳለሁ፡፡ ታምሩ በዚህ ሥራው ቀና መሆኑን፣ ወንድምነቱን አለሁ ባይነቱን ነው ያሳየኝ፡፡ ይህ በምንም ነገር ሊመነዘር አይችልም፡፡ በወቅቱ የታምሩን ጥሪ አክብረው በሥፍራው የተገኙትን ሁሉ ከልቤ አመሰግናቸዋለሁ፡፡
ከአዲሱ አልበምህ መውጣት ጋር ተያይዞ ኮንሰርቶችን የማዘጋጀት ዕቅድስ የለህም?
እቅድ አለኝ፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በክልል ከተሞች ሁሉ ኮንሰርት የማዘጋጀት ዕቅዱ አለኝ፡፡
ቋሚ መኖሪያህ የት ነው? የሙሉ ጊዜ ሥራህ ምንድነው?
ቋሚ መኖሪያዬ ለንደን ውስጥ ነው፤ እዛ የሙሉ ጊዜ ሥራዬ ይኸው የሙዚቃ ሥራ ነው፡፡
ለጥላሁን ገሰሰ የተለየ ፍቅርና ቀረቤታ እንዳለህ ይታወቃል፡፡
ጥላሁን ገሰሰና የእኔ ወላጆች ጐረቤታሞች ነበሩ፡፡ ልጅ እያለሁም እኔ በእነጥላሁን ቤት፣ የእሱ ልጆች በእኛ ቤት እንደ ቤተሰብ ነው የምንተያየው፡፡ ስሙን እንኳን ስጠራው ልክ ልጆቹ እንደሚጠሩት ጥላሁንዬ እያልኩ ነው፡፡ የእሱም ልጆች የእኔን አባት የሚጠሩት እኔ እንደምጠራው ነው፡፡ መቀራረባችንና ፍቅራችን እንግዲህ የጀመረው ያኔ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለጥላሁን ገሰሰ ታላቅ ከበሬታና ለሥራዎቹም ከፍተኛ ፍቅር አለኝ፡፡
ታላላቅ መድረኮችን የመሥራት አጋጣሚውንስ አግኝተሃናል? በሙያህ ከአገር ውጪ ሄዶ የመሥራቱንስ...
ኤግዚቢሽን ማዕከል የተዘጋጁ ታላላቅ ኮንሰርቶችን ጨምሮ በየቲያትር ቤቶች በሚዘጋጁ የሙዚቃ ኮንሰርቶች ላይ ከአክሱማይትና ከሌሎች ባንዶች ጋር የመሥራቱን ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ ከአገር ውጪ በአውስትራሊያ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ከተሞች እየተዘዋወርኩ ታላላቅ ሥራዎችን ሠርቻለሁ፡፡
በህይወትህ እጅግ የተደሰትክባቸው ጊዜያቶች?
ብዙ ናቸው፡፡ በተለይ በመጀመሪያው አልበም ላይ ከተካተቱት ታላላቅ ሰዎች ጋር አብሬ መዝፈን መቻሌ ለእኔ የማይታመን ነገር ነበር፡፡ መዝፈን አይደለም አጠገባቸው መቆሙ ለእኔ ከባድ ነበር፡፡ እነተዘራ ኃይለሚካኤል፣ እሳቱ ተሰማና አየለ ማሞን የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎች ናቸው፡፡ ይህ ግዜ ለእኔ ታላቅ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ይህንን ዓይነት የአድናቂና የወዳጅ መሰባሰብና አድናቆት መግለጽ ፕሮግራም ሲደረግልኝ ማየቴ ለእኔ ታላቅ ደስታዬ ነው፡፡ ሥራዎቼን በማድነቅ፣ ለሥራዬ እገዛና ድጋፍ በማድረግ ለዚህ ያበቁኝን ሁሉ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ””

 

Read 5719 times Last modified on Saturday, 27 August 2011 13:53