ሦስቱ ፀሐፍት ከሃያ ስድስት ፀሃፍት መካከል በዳኛ ውሳኔ የተመረጡ ሲሆን ስልጠና ተሰጥቷቸው በስድስት ወር ጊዜ ጽፈው ያጠናቀቁ ናቸው፡፡ የኮድ ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ዱባለ፤ በኢትዮጵያ የእንግሊዝኛ የሥነ ጽሑፍ ውድድር ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ገልው፣ ሦስቱ መጻሕፍት እያንዳንዳቸው በአምስት ሺህ ቅጅ እንደተዘጋጁና ለዩኒቨርስቲዎችና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በነጻ እንደሚሰራጩና ከነዚህ የተረፉት በተመረጡ መጻሕፍት መደብሮች በዝቅተኛ ዋጋ ለሕብረተሰቡ እንደሚዳረሱ በተለይ ለአዲስ አድማስ ገልዋል፡፡
ከ15-18 ዓመት ያሉ ወጣቶችን ታሳቢ በማድረግ የተጻፉትን የእንግሊዝኛ መጻሕፍት እንደገና የማሳተምና የመሸጥ መብት የደራሲያኑ ሲሆን ይህን ሲያደርጉ ግን ለኮድ ኢትዮጵያና ለበጎ አድራጊው ለሚስተር ቢል በርት እውቅና እንዲሰጡ ከስምምነት መደረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፉአድ ኢብራሂም፤ ኮድ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ሲናገሩ፤ በገጠር ንባብ ለማስፋፋት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ1994 የተቋቋመው ኮድ ኢትዮጵያ ግብረ ሰናይ ድርጅት እስካሁን 1.5 ሚሊዮን መጻሕፍት ያሰራጨ ሲሆን ላቋቋማቸው 82 የማህበረሰብ ቤተ መፃሕፍት መፃህፍት ገዝቶ በማሟላትና አዳዲስ ቤተ መጻሕፍት በማቋቋም ይታወቃል፡፡