Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 10 September 2011 11:20

ልጅህ ሞኝም፣ ጠብደልም አይሁንብህ ብትመክረው አይሰማ፣ ታግለህ አትጥለው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በጥንት ዘመን በፖላንድ አገር የኑሮውድነት በጣም ከፋና አሉ፤ ከባድ የሥጋ እጥረት ተፈጠረ፡፡ ህዝቡ በጣም ተማረረ፡፡ ዝቅተኛው የሠራተኛ መደብ ብዙ ብዙ ጥያቄ እያነሳ ምሬቱንይገልጽ ጀመር፡፡ በዚህ የፖላንድ የሥጋአጥረት ላይ በመመሥረት በርካታ ቀልዶች፣ ተረቶችና ዕንቆቅልሾች እንደጉድ ፈሉ፡፡ እንደማንኛውም አገር፡፡ እንደሚከተለው ያሉ፡-
ከዕለታት አንድ ቀን በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት፣ አለም በሁለት ጎራ ፍርጥም ብላ ተከፍላ በነበረች ጊዜ፤ ባንድ ፊት አሜሪካ፣ በሌላ ፊት ሩሲያ ነበሩ መሪ ተዋንያኑ፡፡ ታዲያ በአንድ የቴሌቪዥን የጥያቄ ፕሮግራም ላይ የመጨረሻውን ማጣሪያ አልፈው ለዋንጫ የደረሱት አገሮች በመወዳደር ላይ ናቸው፡፡ የህንድ ምሁር፣ የአሜሪካ ምሁርና የሩሲያ ምሁር ናቸው የመጨረሻ ተጋጣሚዎቹ፡፡
ጥያቄውን የሚያቀርበው የቴሌቪዥን ፕሮግራም መሪ፤ እንዲህ ሲል ጠየቀ፡-
Why is there a shortage of meat in Poland?
በፖላንድ የሥጋ እጥረት ለምን ኖረ፤ እንደማለት ነው፡፡


በመጀመሪያ የመለሰው ህንዱ ነበር፡፡ መልሱ ግን ጥያቄው እንዲብራራለት የሚጠይቅ ጥያቄ ነበር፡-
“What is meat?” አለ፡፡ (ሥጋ ማለት ምን ማለት ነው?) ሥጋ የማይበላ ህንዳዊ ስለሆነ የሥጋን ምንነት መረዳት ስለነበረበት ነው፡፡
ሁለተኛው ተራ የአሜሪካኑ ሆነ፡፡ አሜሪካኑም እንደ ህንዱ አገሩ የሌለውንና የማያውቀውን ነገር እንዲብራራለት መጠየቅ ነበረበት፡-
“What is shortage?” ብሎ ነው የጠየቀው፡፡ ደሞ እጥረት ምንድን ነው? ማለቱ ነው፡፡ (በዚያን ጊዜዋ አሜሪካ በአንፃራዊ መልኩ ሲታይ ሁሉ ነገር ..በሽበሽ.. ነበረና ነው፡፡)
በመጨረሻ ተረኛው ሩሲያዊው ሆነ፡፡ እሱም በበኩሉ አገሩ የሌለውን ነገር መጠየቅ ነበረበትና እንዲህ ሲል ጥያቄውን አቀረበ፡-
“What is ‘why’?” ..ለምን?.. ማለት ምን ማለት ነው? ማለቱ ነው፡፡ በዚያን ዘመኗ ሩሲያ ጥያቄ መጠየቅ አይፈቀድም፡፡ በተለይ ..ለምን?.. ብሎ መጠየቅማ ክፉ ቅጣት ያስቀጣል፡፡ ዋጋ ያስከፍል ነበርና ነው፡፡
***
አዲሱን ዓመት፤ የከነከነንን ጉዳይ፣ ያጣነውን ነገር፣ ያልጣመንን ፍሬ-ሀሳብ፣ ያልገባንን ነገር ከመጠየቅ የማንቦዝንበት ያድርግልን፡፡ የፕሬስ ነፃነታችንን ንፁህና ተጨባጭ ያድርግልን፡፡ kself sencorship (‰SN በራስ ከማገት) ይሰውረን፡፡
..ነገር በሆድ ማወቅ
ለትውልድ መርዝ መጥመቅ..
የሚለውን የደራሲ አባባል የሚገነዘብ ገዢ አያሳጣን፡፡ አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ እናከብር ዘንድ ልቡናችንን ይክፈትልን፡፡ ዓለም፤ ለመለወጥ ብዙ ጊዜ ፈጅቶበታል፡፡ የ17ኛው ክፍለ ዘመን የምክንያታዊነት ጊዜ፣ የ18ኛው ክፍለ ዘመን የአብራሄ-ህሊና ጊዜ፣ የ19ኛው ክፍል ዘመን የማርክሲዝም ርዕዮት፣ የ20ኛው ክፍለዘመን የገቢራዊነትና የፍተሻ-ገቢር ወቅት ሁሉ እንደ ዘመነ-ህዳሴ በጨረቃ መልኩ ዓለምን የለወጠ አልነበረም ይሉናል አበው ምሁራን፡፡ እኛም በለውጥ ላይ እንጂ በመነባንብ ላይ ያላተኮረ ዘመነ-ህዳሴ እናገኝ ዘንድ መጪው ዓመት፣ መልካም መዐዛ ያለው ዕጣን የሚጤስበት፣ ለምለም ቄጤማ የሚነሰነስበት፣ የኢኮኖሚ ውድነት የሚቀንስበት፣ ፍትሕ የሚያረብበት፣ የፖለቲካ ችግሮች የሚፈቱበት፣ ሙስናዎች የሚመክኑበት፣ ከውድቀታችን የምንማርበት፣ ከመጠላለፍ አዙሪት የምንወጣበት፣ ከንግድ ምስቅልቅል የምንገላገልበት፣ የአስመሳይን ካባ የምናወልቅበት፣ ምህረት የሚሰፍንበት፣ ከድህነት መዘዞች ለመራቅ የምንዘጋጅበት ይሆንልን ዘንድ ከልብ እንመኝ፡፡ ከልብ እንሞክር፡፡ ከልብ እንጣር፤ እንጋር፡፡
የማኪያቬሊን ምሬተኛ ግጥም!
Io rido, e rider mio non passa dento
Io ardo, e l’arsion mia non par di fore.
I laugh, and my laughter is not within me;
I burn, and the burning is not seen outside.
በቁሙ ሲተረጎም፡-
እስቃለሁ እንጂ፣ ሳቄ ውስጤ የለም
ውስጤ ይቃጠላል፣ ከውጪ አይታይም
የሚለውን፤ በመንግሥቱ ለማ ተስፋ-ለበስ ግጥም ለውጦ፤
ማን ያውቃል?
የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ
ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ
ማን ያውቃል? እንዳለው፣ ለድንጋይስ ቋንቋ
ዛፍ፣ ለሚቆረጥ ዛፍ፤ እንዳለው ጠበቃ. . . የሚል ወጣት ያሻናል፡፡
መጪውን ዓመት በዕውነት አዲስ ከምናደርግባቸው መንገዶች አንዱ፤ ..ለምን?.. ማለት የሚችል ወጣት ለመፍጠር ስንዘጋጅ ነው፡፡ ጠያቂ ትውልድ ለመፍጠር ስናልም ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤትና ማህበረሰቡ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ..አንድም በሣር ሀ ብሎ፣ አንድም በአሣር ተመክሮ.. የታረቀ፣ የተቀጣ፣ የተቃና ትውልድ ከዕውቀትና ከጥረት ምንጭ መጨለፍ ይኖርበታል፡፡ ፖለቲከኛ ከመሆኑ በፊት ሰው እናድርገው እንዲሉ ፈላስፎች፡፡ የመከራ ተሸካሚ ሳይሆን የመከር ሰብሳቢ ወጣት አገርን አዲስ ያደርጋል፡፡
ለውጥ፤ በበረሀ ውስጥ ከሩቅ እያጥበረበረ፣ W` ያለ እንዲመስለን እንደሚያደርገው ..ሚራዥ.. እንዳይሆንብን እንጠንቀቅ፤ ይላሉ ፀሐፍት፡፡ በቅርቡ የሚጨበጠውን ዕውነታ ለተረካቢው ትውልድ ማስጨበጥ አስተማማኝ መሠረት እንደመጣል ነው፡፡ ዕውነተኛ ህልምን ከቅዠት፣ ባዶ ተስፋን ከተጨባጭ ተስፋ፣ ሥነ-ምግባራዊ አደብን ከፖለቲካዊ ትኩሳት፣ መሠረታዊ ዕውቀትን ከለብ ለብ ፋኖነት ለይተው ልጆቻችን እንዲያዩ ለማድረግ እንድንችል መጪው ዘመን ብሩህ ልቡናን እንዲያጎናጽፈን እንመኝ፡፡
..አጓጉል ትውልድ
ያባቱን መቃብር ይንድ.. የሚለውን የአበው ብሂል አንዘንጋ፡፡ አጓጉል ትውልድ እንዳይመጣ የማድረግ ትግሉ በኛ እጅ ነው፡፡ ልጅ ከመሠረቱ ከተኮተኮተ፣ ወጣት በእሸትና በእሳትነት ዕድሜው አንድም በዕውቀት፣ አንድም በግብረ ገብነት ከተገራ፤ ብልህነትንም፣ ልባምነትንም የሚረከብ ትውልድ እርሾ ይሆናል፡፡ አለበለዚያ ..ልጅህ ሞኝም፣ ጠብደልም አይሁንብህ፡፡ ብትመክረው አይሰማ፣ ታግለህ አትጥለው.. እንደሚባለው፤ ሁለት ቤት ጉዳት ያመጣል፡፡ መጪውን የትምህርት ዘመን አንብቦ የሚረዳ፣ ጽፎ የሚዋጣለት፤ ..ትምህርትህን ይግለጥልህ!.. የምንለው ልባም ትውልድ የምናፈራበት ያድርግልን፡፡
..ነብስህ እንደ ሱፍ አበባ፣ ለነገ ፀሐይ ትከፈት
እንደ ጉጉ ወጣት ምኞት፣ ያላየኸውን ናፍቅባት..
የምንለው ወጣት አያሳጣን!
መልካም አዲስ ዓመት!

 

Read 5665 times Last modified on Saturday, 10 September 2011 11:32