Saturday, 10 September 2011 11:19

የአዲስ ዓመት እቅዴ - ኢህአዴግ መሆን!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(1 Vote)

የቴሌ “Happy New Year” ከ25 ብር ካርድ ጋር ይሁንልን!
•b2004 ህጋዊና ህገወጥ የቡሄ ጨፋሪዎች ይለያሉ. . .
•2003 የተረት ዓመት ተብሏል. . .

ዘወትር ለአውዳመት በቴክስት ሜሴጅ የ..እንኳን አደረሳችሁ..መልዕክት የሚልክልን ቴሌን    ለመቅደም በማሰብ ይኸው
“Happy New Year” ብያለሁ፡፡     ቴሌ እቺን መቀደም ለማካካስ     ከ..እንኳን አደረሳችሁ..
መልዕክት ጋር የ25 ብር ካርድ     ቢልክልን ሸጋ ይመስለኛል፡፡ (አሪፍ ሀሳብ አይደል?) እኔ የምለው ለቡሄ፣ ለእንቁጣጣሽና ለአሸንዳ የሚጨፍሩ ልጆች ገቢያቸውን አሳውቀው ለመንግሥት ግብር ይክፈሉ የተባለው እውነት ነው እንዴ? እውነት ከሆነ ግን ምርጥ ሃሳብ ነው! እየቀለድኩ እንዳይመስላችሁ - የምሬን ነው፡፡ ለምን መሰላችሁ? ልጆቹ ገና ከአሁኑ ከገቢያቸው ላይ ግብር መክፈል ከለመዱ አዋቂ ሲሆኑ ..ግብር አይደለም ዕዳ!.. የሚለው ቅስቀሳ አያስፈልጋቸውም፡፡ ማንም ሳይቀሰቅሳቸው ግዴታቸውን (ዕዳቸውን) ይከፍላሉ፡፡

እናም ይሄ ተደርጐ ከሆነ ..ምርጥ የ2003 ሃሳብ.. ብየዋለሁ!! ትንሽ ቅር ያለኝ ቡሄ ጨፋሪ ልጆች ካሽ ሪጂስተር ያስገቡ መባል ነው (ወይስ አልተባለም?) ከተባለ ግን ጉዳዩን የሚመለከተው ወገን እንደገና ቢያጤነው መልካም ነው፡፡ እንዴ. . . የልጆቹን የቡሄ ጭፈራ ገቢ ያላገናዘበ እኮ ነው! የገቢ አቅማቸው ካሽ ሬጂስተር ለመግዛት አይፈቅድላቸውማ፡፡ በዚያ ላይ የቡሄ፣ የእንቁጣጣሽ (አበባየሆሽ) እና የአሸንዳ በዓላት በዓመት አንዴ የሚመጡ ስለሆኑ ማሽኑ አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ ወይም ደግሞ በትዕዛዝ የልጆች ካሽ ሬጂስተር ማሠራት ይሻላል - ከቻይና! ከዚያ በአቅማቸው ማሽኑን ገዝተው አዲሱን ደንብ ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ መልኩ ህጋዊ የቡሄ ጨፋሪዎችና ህገ ወጦቹን መለየት ይቻላል፡፡
በነገራችን ላይ አንዳንድ የዘመን ተንታኞች 2003 ዓ.ም. በዓይነቱ ለየት ያለ ዓ.ም. ነበር ይላሉ፡፡ ለምን ይሆን?  
ያሳለፍነው የ2003 ዓ.ም የተረት ዓመት በመሆን ከሌሎች ዓመታት ራሱን የተለየ አድርጐ በእጅጉ ይለያል እየተባለ ነው፡፡ ነገሩን ብቀበለውም እንዴት? ማለት ግን ጥሩ ነው፡፡ ብዙ ተረት የተተረተበት ዓመት ነበር ለማለት ግን እንዳልሆነ ትረዱኛላችሁ ብዬ እገምታለሁ፡፡ እኔ ማለት የፈለኩት ምን መሰላችሁ? ዓመቱ አያሌ ነገሮችን ተረት ለማድረግ የታተረ ሲሆን በሁሉም ባይሆን እንኳ በጥቂቶቹ የተሳካለት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በታሪክ መዛግብት ውስጥም ..2003 የተረት ዓመት.. በሚል ሊጠቀስ የሚችል ጀብድ የፈፀመ ጉደኛ ዘመን ነው - ሊጠናቀቅ አንድ ቀን የቀረው 2003 ዓ.ም፡፡
በኢትዮጵያ ሚሌኒየም ዋዜማ ምሽት በሚሌኒየም አዳራሽ እውቅ አርቲስቶቻችን በእርግጠኝነት ..ድህነትን ተረት እናደርጋለን.. እያሉ ከእውነትነት ይልቅ የካድሬ ቅስቀሳ በሚመስል ፕሮፓጋንዳ ሲያደክሙን እንደነበር አንዘነጋውም፡፡ ከዚያ በኋላ ያሳለፍናቸውን ሁለት ዓመታት ወደ ኋላ በሃሳብ ባቡር ተንሻተን ስንመለከት ግን ድህነት እንኳንስ ተረት ሊሆን ይበልጡኑ ጡንቻውን አፈርጥሞ ..ተረት አደርጋችኋለሁ.. ብሎእየዛተብን ያለ ነው የሚመስለው፡፡ ከእለት እለት እየባሰበት የመጣው የኑሮ ውድነት፣ የሸቀጦች የዋጋ ንረት፣ ግሽበት (inflation) ወዘተ ድህነትን የሚያፈረጥሙ እንጂ ከቶውንም ተረት የሚያደርጉ ነገሮች አይደሉም፡፡ በርግጥ አርቲስቶቹ ከደሰኮሩት ውስጥ ተረት የሆነ ነገር ግን አልጠፋም፡፡ MN ms§Chù? ..ድህነትን ተረት እናደርገዋለን.. ያሉት ነገር ራሱ ተረት ሆኗል፡፡ ይኸው እኔ እንዲህ ብለው ነበር ብዬ እያስታወስኳቸው እኮ ነው!! - ተረት ሆነ ማለት ይሄው አይደለም እንዴ!
አርቲስቶቹ ቃል እንደገቡልን ድህነት ተረት አልሆነም ብለን አጠንክረን እንዳንወቅሳቸው ግን በዚህ ጊዜ ብለው ቀነገደብ አልሰጡንም፡፡ ስለዚህ ከነአካቴው ተስፋ ቆርጠን አንቀመጥም፡፡ በ20ም በ50ም በ100ም ዓመት ቢሆን ድህነትን ተረት ካደረግን እሰየው ነው፡፡ (ይሄ አባባሌ ጨለምተኛ ከሚል ፍረጃ ያተርፈኛል!)
በ2003 ዓ.ም ድህነትን ተረት የማድረግ ወኔ ቢክደንም ሌሎች በርካታ ነገሮች ተረት እየሆኑ እንደመጡ ወይም ሊሆኑ እየተሰናዱ መሆኑን ታዝበናል፡፡ የማንፈልገው ድህነት ተረት ከመሆኑ በፊት የምንፈልጋቸው ነገሮች ተረት መሆናቸው ቅር ቢያሰኘንም ጉዳዩ ከአቅማችን በላይ ስለሆነ ምንም ማድረግ አልተቻለንም፡፡ ለመሆኑ ተረት የሆኑት ወይም የመሆን አደጋ የተጋረጠባቸው እነማን ናቸው? ምንድንስ ናቸው? 2003 ዓ.ምን በተለየ መልኩ የተረት ዓመት ያሰኘው ምን ይሆን? እስቲ ይሄን የተረት ዓመት አብረን እንቃኘው፡፡
በቅርቡ በደቡብ ኮሪያ በተካሄደውና አትሌቶቻችን በተሳተፉባቸው የአትሌቲክስ ውድድሮች የተገኘውን ውጤት አይታችሁት የለም? ከአትሌቶቻችን ከወርቅ (አንደኝነት) በቀር አንቀበልም የምንል ህዝቦች ነበርን፡፡ (አሁኑኑ ተረት ሆነ እንዴ?) በአሁኑ ውድድር ግን ሁለተኛና ሦስተኛነት ርቆናል፡፡ bአትሌቲክሱ ወርቅ ማጣታችንን ከወርቅ ዋጋ መናር ጋር የሚያያዙ አንዳንድ ወገኖች ግን በሩጫ የወርቅ ሜዳሊያ ያልተገኘው የወርቅ ዋጋ ስለተወደደ ነው ይላሉ፡፡ እንግዲህ የወርቅ ዋጋ ንረትም በዚሁ ከቀጠለ በወርቅ ማጌጥም ተረት መሆኑ አይቀርም ማለት ነው፡፡ በአንድ ወቅት እኛ ኢትዮጵያውያን በወርቅ እናጌጥ ነበር ተብሎ ብቻ የሚወራለት ማለት ነው፡፡ የወርቁስ ግዴለም ቢበዛ አምሮና ደምቆ መታየት ነው የሚቀርብን፡፡ yአትሌቲክሱ ተረት ለመሆን ማኮብኮብ ግን እጅግ ይጐዳል፡፡ ሰው በእጁ የያዘውን እንዴት ለተረት አሳልፎ ይሰጣል? ለዚህ ጉዳይ በቀዳሚነት ተወቃሹ መንግሥት ነው የሚሉ አንዳንድ ወገኖች፤ መንግሥት ሙሉ ጊዜውን ለልማት መስጠቱ ለአትሌቲክስ ድል ማጣት ምክንያት ሆኗል ይላሉ፡፡
በ2003 ተረት የመሆን አደጋ ከተጋረጠባቸው በርካታ ጉዳዮቻችን አትሌቲክሱ ዋነኛው ነውና መንግሥትም፣ ተቃዋሚም፣ ህዝብም፣ አትሌቱም በዓለም መድረክ ብቸኛ መታወቂያችን የሆነውን አትሌቲክስ ከተረትነት ይታደጉ እንላለን፡፡
ሌላው ተረት ሊሆን ትንሽ የቀረውና በ2003 ሊለይለት በተረት አፋፍ ላይ የሚገኘው የዘፈን አልበም ይመስላል፡፡ አዎ የድምፃውያኖቻችን የዘፈን አልበሞች እየተረሱ ነው፡፡ በተለይ አንጋፋዎቹ አርቲስቶች ከኮፒራይት መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ አልበም ማውጣት እርም ብለው ከተው ጥቂት ዓመታት ቢቆጠሩም በ2003 ነገሩ ተባብሶበት በ100ዎች የሚቆጠሩ የሙዚቃ አሳታሚ ቤቶች ሥራቸውን እስከማቆም ደርሰዋል፡፡ በቀጣዩ ዓመት በዚሁ ከቀጠለ ግን አልበሞች ብቻ ሳይሆኑ አርቲስቶቹም ተረት መሆናቸው አይቀርም፡፡ አልበም ከሌለ አርቲስት የለማ! ንግድ ከሌለ ነጋዴ እንደሌለው ማለት ነው፡፡
ለነገሩ በ2003 ነጋዴዎችም ተረት ሊሆኑ ምንም አልቀራቸውም ነበር፡፡ መንግሥት የዋጋ ቁጥጥር በመጀመሩ ነፃ ገበያ ላይ አደጋ ባንዣበበት ወቅት፣ ንግድና ነጋዴው ተረት ወደ መሆን ደርሰው ነበር፡፡ ከሦስት ወር በኋላ መንግስት የአቋም ለውጥ በማድረጉ ተረፉ፡፡ አሁንም ግን አደጋው ሙሉ በሙሉ አልተወገደም፡፡ መንግሥት በአዲስ የግብር አገማመት ስልት በንግድ ተቋማት ላይ የሚጥለው አስደንጋጭ ግብር ያስመረራቸው ነጋዴዎች፤ ከንግዱ ለመውጣት መገደዳቸውን እየተናገሩ ነው፡፡ አሁንም መላ ካላበጀንለት ነጋዴና ንግድ በኢትዮጵያችን ተረት እንዳይሆኑ ያሰጋናል፡፡ እውነት ግን 2003 ዓ.ም እኮ ጉደኛ የተረት ዓመት ነው፡፡ ስኳርና ዘይት ጠፍተውና ንረው ተረት ሊሆኑ ሲሉ እድሜ ለኢህአዴግ መራሹ መንግሥት በኢትፍሩትና በሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበር በኩል መቸርቸር በመጀመሩ ለትንሽ ተርፈዋል፡፡ ጥሬ ሥጋ መቁረጥም ሌላው የተረት አደጋ የተጋረጠበት ጉዳይ ነው፡፡ ኪሎ ሥጋ ዋጋው ከ100 ብር በላይ ሆኗል፡፡
ሌላው ተረት የመሆን አደጋ ያንዣበበባቸው ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ አንዳንዶች በስደት፣ ሌሎች በእርስ በርስ ውዝግብ፣ በፖለቲካ ምህዳር መጥበብ፣ የኢህአዴግ ጫና በዛብን በሚሉ ሰበቦች ወዘተ ተቃዋሚዎች ከፖለቲካው ንፍቀ ክበብ እየጠፉ የመጡበት ዓመት ነበር - 2003 ዓ.ም፡፡ አዲሱ ዓመት ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ምን ይዞ እንደሚመጣ መተንበይ አዳጋች ቢሆንም ኢህአዴግ አንድ ነገር ካላደረገ ተረት መሆናቸው አይቀርም የሚል ስጋት አለኝ፡፡
ከ97 ዓ.ም የፖለቲካ ቀውስ በኋላ የግል ፕሬሱ ተረት የመሆን አደጋ እንዳንዣበበበት በቂና ግል ምልክቶች አይተናል፡፡ የግል ጋዜጦች ቁጥር ማሽቆልቆል የሚያሳየንም ይሄንኑ ነው፡፡ (ኧረ ተረት ከመሆን ያድነን!)
በአገሪቱ ካሉት የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል አምስቱ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲን የግምገማ መስፈርት አያሟሉም ተብለው እንዲዘጉ መደረጋቸው በብዙዎች ዘንድ የግል ኮሌጆች ተረት እንዳይሆኑ የሚል ስጋትን ፈጥሯል፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ጠ/ሚኒስትሩ በቀን ሦስቴ ..መጉረስ.. ትጀምራላችሁ ያሉንም ነገር ከእነ አባባሉ ተረት እንደሆነ እያየን ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱ እንኳን ሦስቴ ..መጉረስ.. መኖራችንንም እየተፈታተነን ነው፡፡ ለጊዜው እንግዲህ ድህነትን ተረት የማድረጉን ጉዳይ እንርሳው - ተረት ነው፡፡ ይልቅስ እኛው ራሳችን ተረት እንዳንሆን መላ ብንዘይድ የተሻለ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አዲሱ ዓመት ክፉ ክፉውን ከ2003 ከወሰደ ሁለመናችንን ተረት በተረት ሊያደርገን ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አለብኝ፡፡ እናም በ2004 ዓ.ም የመንግሥት ዋነኛ ተግባሩ መሆን ያለበት እኛን (ህዝቡን) ተረት ከመሆን ማዳን (ማትረፍ) ይመስለኛል፡፡ ካልሆነ ግን ራሱ ኢህአዴግም ተረት የመሆን አደጋ መጋፈጡ አይቀርም ባይ ነኝ፡፡ ለምን ብትሉ... እኛ በኑሮ ውድነት ተረት ከሆንን ኢህአዴግ ማንን ሊመራ ነው?
አሁን ለናንተ ብቻ በምስጢር የምነግራችሁ ጉዳይ አለኝ - ኢህአዴግ እንዲሰማ የማልፈልገው ምስጢር ማለቴ ነው፡፡ ነገርዬው የአዲሱ ዓመት እቅዴን ይመለከታል፡፡ ይሄን እቅዴን ኢህአዴግ እንዲያውቅብኝ አልፈልግም፡፡
አትታዘቡኝና... አንደኛው እቅዴ ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ መሆን ነው፡፡ በ2004 ዓ.ም የሚከፈለውን መስዋእትነት ሁሉ ከፍዬ ኢህአዴግ እሆናለሁ የሚል ውሳኔ ላይ ደርሻለሁ፡፡ ደግነቱ ደግሞ ነባር ኢህአዴጐች መስዋእትነቱን ሁሉ ከፍለው ስለጨረሱ ብዙም የሚከፈል መስዋእትነት ያለ አይመስለኝም፡፡ ምናልባት ከእኔ የሚፈለገው ታማኝነት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ታማኝ መሆን ደግሞ ፈሞ አያቅተኝም፡፡ እንደውም ከዛሬ ማታ ጀምሮ ታማኝ የመሆን ልምምድ እጀምራለሁ፡፡ በ2004 ዓ.ም ለምን ኢህአዴግ የመሆን እቅድ የነደፍኩ ይመስላችኋል? ሌላ ምንም ምክንያት የለኝም፡፡ በኑሮ ውድነቱ የተነሳ ብቻ ነው፡፡ እውነቴን ነው ኑሮውን ጨርሶ አልቻልኩትም፡፡ እለት ተእለት የሚንረው የኑሮ ሁኔታ ከአቅሜ በላይ ሆኖብኛል፡፡ ስለዚህ ብቻዬን ያቃተኝን ኑሮ ከኢህአዴግ ጋር ደግሞ ልሞክረው ብዬ አስቤአለሁ፡፡ ከኑሮ ንረቱ ጋር ብቻዬን ከምፍጨረጨር ለሁለት ሳይሻል አይቀርም ብያለሁ፡፡ ምን ትሉኛላችሁ? አንዳንድ ወዳጆቼ ይሄን ሃሳቤን ስነግራቸው እዚያው አብረን ተቀምጠን እንዳለ ተጣልተውኛል፡፡ ከዚህ በኋላም እንደማይታረቁኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ከወዳጆቼ ጋር ተቀያየምኩ ብዬ ግን ቅር የምሰኝ አይደለሁም፡፡ የመስዋእትነቱ አካል እንደሆነ ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ከኢህአዴግ ጋር ስሆን እንደመርግ የከበደኝ ኑሮ እንደሚቀለኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ የኑሮ ውድነቱን እንደምረታ አንዳችም ጥርጥር የለኝም፡፡ ኑሮዬን እንደማሸንፍ ይታወቀኛል፡፡ ከኢህአዴግ ጋር ግንባር ከፈጠርኩኝ የኑሮ ማዕበል ወዲህና ወዲያ እንደማይንጠኝ ልቤ ነግሮኛል፡፡ እናም ከነገ ወዲያ የ2004 አዲስ ዓመት መጥባቱ ሲበሰር እኔም ኢህአዴግ እሆናለሁ!!
በአዲሱ ዓመት ሌላም እቅድ አለኝ፡፡ ለብዙ ዓመት ሥራ ፍለጋ የተንከራተትኩ ምስኪን በመሆኔና አሁንም ሥራ ስላላገኘሁ ..ሥራ አጥ የኢህአዴግ ደጋፊዎች ፎረም.. በሚል ድርጅት አቋቁሜ ለፓርቲው ድጋፍ ለመስጠት አስቤአለሁ፡፡ መቼም ኢህአዴግ ነጋዴዎች ብቻ ናቸው የሚደግፉኝ በሚል እንደማይቃወመኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ድሮ ስሰማ እኮ ፓርቲው በዋናነት ለጭቁኑ ህዝብ የተቋቋመ ነው፡፡ የላብ አደሩ ፓርቲ የሚባል ነገርም የሰማሁ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ በ2004 ኢህአዴግ መሆንና ፎረሙን ማቋቋም ዋነኛ እቅዶቼ መሆናቸው ይታወቅልኝ፡፡ በዚህ ድንገተኛ እቅዴ የምትቀየሙኝ ወዳጆቼ ልትኖሩ ትችላላችሁ፡፡ እኔ በኑሮ ውድነት የተነሳ ተረት ከምሆን የእናንተ ወዳጅነት ተረት ቢሆን ምን ይመስላችኋል? ..ቅድምያ ለራስ ህልውና!.. - የአዲሱ ዓመት መፈክሬ ነው፡፡ መልካም አዲስ ዓመት!! (በተለይ ለኢህአዴግ ሥራ አጥ ፎረም)

 

Read 2499 times Last modified on Saturday, 10 September 2011 11:32