Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 10 September 2011 11:58

2ሺ30 ዓ.ም ትንቢታዊ ልቦለድ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

መስከረም፣ 2030 ዓ.ም
አዲስ አበባ
አራት ኪሎ ጋዜጣ ተሳልጬ (ተከራይቼ) ለማንበብ ተራ በመጠበቅ ላይ ነኝ፡፡ የግል ጋዜጣ እና ጋዜጠኛ ተቀዶና ተሰዶ አልቋል፡፡ የአገሬዉን ህዝብ ለማቅናት ሀላፊነቱ ሙሉ በሙሉ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጫንቃ ላይ ወድቋል፡፡ ይህ ነባር ጋዜጣ የተጣለበትን ሰፊ የሕዝብ አደራ ለመወጣት ወርድና ቁመቱን በእጥፍ ከማሳደጉም በላይ ራሱን እንደ አሜባ በማብዛት አንድም ሦስትም ለመሆን ተገዷል፡፡ ዘመን ፖለቲካ፣ ዘመን ስፖርት፣ ዘመን ልማት - ሦስት ቤተሰብ መስርቷል፡፡ ..በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ጋዜጦች ቁጥር ከአንድ ወደ ሶስት አሻቀበ.. የተባለውም አዲስ ዘመን ራሱን ሦስት በማድረጉ ነው፡፡

ለምሳሌ የዊኪፒዲያ የመረጃ ቋት ..ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የምትገኝ፣ ሰፊ ጋሻ መሬቷን ለአረብ ከበርቴዎች በማከራየት የምትተዳደር ትልቅ አገር እንደሆነች፣ የሕዝብ ብዛቷ ደግሞ 135 ሚሊዮን የሚጠጋ.. መሆኑን ካተተ በኋላ አገሪቱ ሦስት ቴሌቪዥን ጣቢያዎችና ሦስት ጋዜጦች እንዳሏትም ይናገራል፡፡ እነርሱም ኢቴቪ 1፣ አቴቪ 2፣ ኢቴቪ 3፤ ዘመን ፖለቲካ፣ ዘመን ስፖርት እና ዘመን ልማት በመባል ይታወቃሉ ይላል፡፡
አራት ኪሎ ፈርጣማውን ዘመን ጋዜጣን ለማንበብ ከተኮለኮሉት ወጣቶች ከፊሎቹ ክፍት የሥራ ቦታን ከሚጠቁመው 20 ሜትር በ20 ሜትር ከሆነ ሶኒክ ስክሪን ላይ ዐይናቸውን ተክለዋል፡፡ ሶኒክ ስክሪኑ በየሥራ ማስታወቂያው መካከል የወቅቱን መፈክሮች ደጋግሞ ያስነብባል፡፡
ፊታውራሪነት ኢሕአዴግ ዘላለማዊ ፓርቲ ይሆናል!!!..፣ ..የተማሩ ሥራ አጦች መበራከት የዕድገታችን ማሳያ |አንድም እናት በወሊድ አትሞትም፣ እናት ለምን ትሙት፤ አንድም አባት ዲግሪ አያጣም፣ አባት  ዲግሪ ለምን ይጣ!!!.. ..ጠቅላይ ሚኒስትራችን  ከኢትዮጵያ አልፈው አፍሪካን ያቀናሉ!!!.. ..ዲግሪ ለህዝባችን ብርቅ የሚሆንበት ጊዜ አክትሟል!!!.. ..የተማረ ይግደለኝ!!!..፣ ወዘተ የሚሉ መፈክሮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
አራት ኪሎ ያለው ሶኒክ ስክሪን በእርግጥም እረፍት የለውም፡፡ በአካባቢው ከተኮለኮሉት ወጣቶች ከፊሎቹ ያንኑ እስክሪን የሚያክለውን ዘመን ጋዜጣ በአፍጢማቸው ተተክለው ያነባሉ፡፡ ከሁለት ዐስርት ዓመታት በፊት በዚህ ስፍራ ክፍት የሥራ ቦታ የሚነበበው ከብረት በተሠራ የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ እንደነበር አስታወስኩ፡፡ ዕድሜዬ ሀምሳዎቹን ዘለለ ማለት ነው፡፡ ጊዜው እንዴት ይሮጣል!
የጋዜጣ ወረፋዬን እየጠበቅሁ ዐይኔን ወደ ዲጂታል ስክሪኑ በድጋሚ ወረወርኩ፡፡ ከመፈክሮች ቀጥሎ የስራ ማስታወቂያዎች ተነበቡ፡-
..እኔ ዶ/ር ይርጋ አረጋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመካኒካል ኢንጂነሪንግ መምህር ስሆን በትርፍ ጊዜዬ ለልጆችዎ የቤት ለቤት የማስጠናት ሥራ እሰራለሁ፡፡ ለሂሳብ እና ለፊዚክስ ልዩ ትኩረት እሰጣለሁ፡፡ ከኬጂ እስከ ማትሪክ ተፈታኞች ድረስ አስጠናለሁ፡፡ ለልጆችዎ ስኬት ዶ/ር ይርጋ አረጋ ብለው ይደውሉልኝ፡፡ ስልክ ሞባይል 0990487686..
ወደ ሌላኛው የስክሪን ማስታወቂያ አለፍኩ፡-
..ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያ
ተፈላጊ ባለሙያ፡- ግንበኛ
ተፈላጊ ችሎታ፡- ከህንጻ ኮሌጅ በድንጋይ ጠረባ ሁለተኛ ዲግሪ ያለውና በሙያው አምስት ዓመት እና ከዚያ በላይ የሰራ/የሰራች፣ ወይም ከማንኛውም የግል ኮሌጅ ሶስተኛ ዲግሪ ያለውና በሙያው 25 አመት የስራ ልምድ ያለው /ያላት..
በኛ ጊዜ ድንጋይ ጠረባ የሚባል ትምህርት በዲግሪ ደረጃ ስለመሰጠቱም አልከሰትልህ አለኝ፡፡
ደመወዝ፡- 7 ሺ 7 መቶ ዘጠና
አመልካቾች- የስራና የትምህርት ማስረጃችሁን ዋናውንና ፎቶኮፒዉን እንዲሁም አንድ የምትጠርቡትን ድንጋይ በመያዝ እስከ ጥቅምት 13፤ 2030 ድረስ ላፍቶ በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት ማመልከት ትችላላችሁ፡፡
ሴት ጠራቢዎች ይበረታታሉ፡፡
ሌላ ማስታወቂያ q«l:-
ሙያ፡- ሀኪም
ተፈላጊ ችሎታ፡- የታመሙ ሰዎችን አክሞ ማዳን የሚችል
ከታወቁት የአገሪቱ 73 ዩኒቨርሲቲዎች በህክምና ሙያ የተመረቀ/ የተመረቀችና በሙያው ቢያንስ 18 ዓመት የሰራ/ የሰራች፤
ማሳሰቢያ
አመልካቾች የትምህርትና የስራ ማስረጃቸውን እንዲሁም አክመው ያዳኑትን 15 ሰዎች ለምስክርነት ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ በእንስሳት ሀኪምነት የተመረቁ አመልካቾች ተቀባይነት አይኖራቸውም፡፡
ሙያ፡- ፎርማን
ተፈላጊ ችሎታ፡- በሲቪል ምህንድስና ወይም በአርክቴክቸር ወይም በተመሳሳይ ሙያ ሁለተኛ ዲግሪና ከዚያ በላይ ያለው/ ያላት እና በሙያው 35 ዓመት የስራ ልምድ ያለው/ ያላት፣
ደመወዝ፡- 8 ሺ 8 መቶ ዘጠና
አመልካቾች የትምህርት ማስረጃችሁንና በታማኝነት ሊመሰክሩላችሁ የሚችሉ ሁለት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያስተማሯችሁን መምህራን ይዛችሁ መቅረብ ይኖርባችኃል፡፡ መምህራኖቻችሁ ስለናንተ ከመመስከራቸው በፊት በየኃይማኖታቸው ቃለ መሀላ ለመፈጸም ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡
ማሳሰቢያ
የትምህርት ማስረጃ ብቻውን ዋጋ አይኖረውም፡፡ እንግሊዝኛን በትክክል ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ተወዳዳሪዎች ሁለተኛ ዲግሪ እና ከዚያ በላይ ቢኖራቸውም እንኳ ተቀባይነት አይኖራቸውም፡፡ ድርጅቱ ለማወዳደር የሚገደደው የመጀመርያዎቹን 10ሺ አመልካቾች ብቻ ይሆናል፡፡
ማስታወቂዎቹ  27 አመታትን ወደ ኋላ ይዘውኝ ነጎዱ፡፡ ትዝ ይለኛል ያኔ ገና ከዩኒቨርሲቲ ተመርቄ ሥራ እንዳገኘሁ የተቀጠርኩት በ2ሺ 500 ብር ነበር፡፡ በዚህ ብር ቤት ተከራይቼ፣ ለናቴ የአስቤዛ ሰጥቼ፣ ድራፍት ጠጥቼ ደመወዜ ከወር -ወር አንቀባሮ ያኖረኝ ነበር፡፡ ሊያውም ያኔ ህዝቡ ኑሮ እሳት ሆነ እያለ ማማረር ጀምሮ ነበር መሰለኝ፡፡ እንዴት የአንድ ፎርማን ደመወዝ 8 ሺ ብር ይሆናል? በኔ ጊዜ ብር እና ዶላር እኩል ሊሆኑ ምን ቀራቸው፡፡ አንድ ብር 16 ብር አልነበረም እንዴ የሚመነዘር?  አሁን እዚህ ዙርያዬ ለተኮለኮሉት ወጣቶች ድሮ በ70 ብር ምን የመሰለ ክትፎ እንበላ ነበር ብላቸው ያምኑኛል? ያኔ በደጉ ጊዜ ፡፡ ያኔ በደጉ ዘመን!
አባባ ተራዎ ደርሷል አለኝ አንድ ምዝዝ፣ሙዝዝ ያለ ወጣት፡፡ ለካንስ ጋዜጣ ለመሳለጥ (ለመከራየት) ነበር አመጣጤ፡፡ ህዝቡ እጅግ በዝቶ ሁሉንም ነገር ለማድረግ ወረፋ መያዝ አለበት፡፡ የመሰለፍ ባህል ከመንሰራፋቱ የተነሳ የኢትዮጵያ ህዝብ በሦስት ተከፍሏል፡፡ አሰላፊ፣ ተሰላፊ እና አሳላፊ፡፡ ሆቴል ምሳ ለመብላት ደጅ መሰለፍ፣ ጋዜጣ ተከራይቶ ለማንበብ ደጅ መሰለፍ፣ አጭር ሽንት ለመሽናት ረጅም ሰልፍ  መሰለፍ፤ ምኑ ቅጡ፡፡ ምንም እንኳ የሰልፍ ባህል በአገሬው ህዝብ ዘንድ እየዳበረ ቢሆንም መንግሥትን ለመቃወም ግን ሰልፍ አይበረታታም፡፡  
አሁንም አራት ኪሎ ነው ያለሁት፡፡ ሰልፌን ጠብቄ ዶልቼ ከሚባለው የጋዜጣ አሳላፊ (በድሮ ቋንቋ አከራይ) አዲስ ዘመን ጋዜጣ ተከራየሁ፡፡ ጋዜጣ አከራዩንም ጋዜጣውንም ለዘመናት ነው የማውቃቸው፡፡ ዋጋቸው እንጂ እነርሱ አይለወጡም፡፡በእርግጥ አዲስ ዘመን ራሱን ሶስት በማድረጉ ትንሽ ክብደቱ የጨመረ መሰለኝ፡፡ ምናልባት በዘመን ብዛት እጄ ሳስቶም ሊሆን ይችላል፡፡ ጋዜጣው ወፍሮ ነው ወይንስ እጄ ሳስቶ የሚለውን እያሰላሰልኩ ሳለ የጋዜጣ አሳላፊው  ..አባት ቶሎ ያንብቡ፤ ሰልፉ ረዥም ነው.. አለኝ፡፡
ይገርማል! እኔ ወጣት እያለሁም በዚሁ ጋዜጣ ነበር ስራ ፈልጌ የተቀጠርኩት፡፡ ያኔ ጋዜጣውን ለመግዛት 2 ብር፣ አንብቦ ለመመለስ ደግሞ ሀምሳ ሳንቲም ብቻ በቂ ነበር፡፡ እንዴት ጋዜጣ ተሳልጦ ለማንበብ (ተከራይቶ ለማንበብ) 25 ብር ይከፈላል? በዚያ ላይ ጥድፊያው፡፡ ክፉ ዘመን!
እንደኔ ጋዜጣ ተሳልጠው ለማንበብ ሰልፍ የያዙ ሰዎችን እንዲሁም ጋዜጣ አሳላፊውን ዶልቼን እንዳላስቀይም ብዬ የአዲስ ዘመንን የፊት ገጾች በቁሜ ገረፍማድረግ ጀመርኩ፡-
..ምርጫ ቦርድ በአገሪቱ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ መካሄዱ ቀርቶ በየ15 ዓመቱ እንዲካሄድ ወሰነ፡፡.. አንዳንድ የምጣኔ ሀብት ጠበብቶች የምርጫ ቦርድን ውሳኔ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ ነው ሲሉ አሞካሽተውታል፡፡
..ጠ/ሚኒስትሩ በሚቀጥለው ምርጫ ለመወዳደር ፍላጎት እንደሌላቸው ገለጹ፡፡ የኮብልስቶን አንጣፊዎች ህብረት ግን ውሳኔያቸውን ተቃውሞታል፡፡ ህብረቱ ከትናንት በስቲያ ባወጣው የአቋም መግለጫ ጠ/ሚኒስትሩ የጀመሩትን ልማት ሳይጨርሱ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ መወሰናቸው ሀላፊነት የጎደለው ብሎታል፡፡..
ትዝ ሲለኝ ከ27 ዓመታት በፊትም እንዲሁ ነበር፡፡ በቃኝ ሲሉ ፓርቲያቸው አይሆንም ብሎ ያስቀራቸዋል፡፡ አሁን ደግሞ ህዝቡ እርሶ ካልመሩን ብሎ ያስቸግራቸው ጀመር፡፡ ያኔ መወራረስ ይሁን መተካካት የሚባል ዘመቻ ተጀምሮ ሚኒስትሮቻቸው ሁሉ ሲተካኩ፣ ሲተካኩ አለቁባቸው፡፡ እርሳቸውን የሚተካ ግን ከየት ይምጣ፡፡ Ã ሰው ተወልዶ ለአቅመ መምራት እስኪደርስ ዙፋኑ ባዶ ከሚሆን በህዝብ ጥያቄ እስከአሁንም አገሪቱን እየመሩ ነው፡፡ ሥልጣን ልልቀቅ ቢሉ እንኳ የእርሳቸውን ፎቶ ከተሰቀለበት ለማላቀቅ ድፍን አምስት አመት አይፈጅም? የእርሳቸው ፎቶ ያልተሰቀለበት ቦታ እኮ ተፈልጎ አይገኝም፡፡ በያዝኩት የዘመን የፖለቲካ ጋዜጣ ላይ እንኳ በፊት ገጽ ብቻ አምስት የእርሳቸው ምስሎች ታትመውበታል፡፡ ማንኛውም መጽሐፍ ሲታተም በመጀመርያ ገጹ የእርሳቸውን ምስል መያዝ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ የመማርያ መሐፍትም ቢሆን የውጭ ሽፋኑ ላይ የእርሳቸው ፎቶ ካልታተመበት አይወጣም፡፡ አለበለዚያ ተማሪዎች የአገር ፍቅር አይገባቸውም፡፡ የሚል ነው ምክንያቱ ለነገሩ ሰውየው ድሮ ለፎቶ ብዙም ግድ አልነበራቸውም እኮ!  ህዝቡ ነው ያበላሻቸው፡፡
ህዝቡ ሬዲዮ ጣብያ ደውሎ የወደደውን ፕሮግራም እንደሚያስደግመው እኚህን መሪ ስልጣንዎ ይደገም እያለ በየአምስት አመቱ ሰልፍ መውጣት ከጀመረ ይኸው ሀያ ምናምን ዓመቱ፡፡ ሰውየው በዙፋናቸው እነሆ 53 ዓመታቸው፣ እንዳማረባቸው፡፡ በኔ ጊዜ ሰውየው ታግለው ካባረሩት ወታደራዊ መሪ ዕድሜ በላይ አገሪቷን ገዙ ተብሎ ጉድ ሲባል ነበር፡፡ የጃንሆይን ክብረወሰን ይሰብራሉ ብሎ የጠረጠረ ግን አልነበረም፡፡
እኔ በግሌ እወዳቸዋለሁ፡፡ ምራቁን የዋጠ ሰው አገር ሲመራ ደስ ይለኛል፡፡ እርሳቸው ብዙም አልተለወጡም፡፡ ያኔም ጸጉራቸው ሸሽቶ ነበር፣ አሁንም ሸሽቷል፡፡ ያኔም ጎበዝ ተናጋሪ ነበሩ፣ አሁንም ናቸው፡፡ ያኔም አንባቢ ነበሩ፣ አሁንም በመነጽር ያነባሉ፡፡ ትንሽ ድካም ሲሰማቸው ምክትል ጠ/ሚኒስትርና የሴቶች ጉዳይ ሚኒስትርነቱን ደርበው የያዙት ባለቤታቸው ያግዟቸዋል፡፡ ባለቤታቸው ጠንካራ ሴት ናቸው፡፡
ጋዜጣ አሳላፊው ዶልቼ ሲገላምጠኝ ወደ ሁለተኛው ዜና አለፍኩ፡-
..የአዲስ አበባ ልማት አሳላጭ ካቢኔ (በድሮ ቋንቋ መስተዳደር) አራት ኪሎና ልደታ አካባቢ የሚገኙ ኮንዶሚንየም ቤቶችን ለማፍረስ በዝግጅት ላይ መሆኑን ገለጸ፡፡ ነዋሪዎች በበኩላቸው ለልማት መነሳታቸውን የሚደግፉት ቢሆንም ተተኪ ቦታ እንዲሰጣቸው ተማጽነዋል፡፡ የክፍለ ዞኑ (ድሮ ክፍለከተማ ይባል የነበረ) የመሬት ባንክ አስተዳደር ዋና የልማት ዘብ (ድሮ የስራ ሂደት ባለቤት ይባል የነበረ) አቶ ሹኩር አሊ እንደተናገሩት፤ ኮንዶሚንየሞቹ ያረጁ ያፈጁ ከመሆናቸውም በላይ በቂ ጥናት ሳይደረግ ከ27 ዓመታት በፊት መሀል ከተማ ውስጥ መሠራታቸው አግባብ እንዳልነበረ ጠቅሰው፣ የመዲናይቱን ገጽታ ከማሽሞንሞን (ከመገንባት) አንጻር yኮንዶሚንየሞቹ መፍረስ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ለነዋሪዎቹ ከሞጆ ክፍለ ዞን ወጣ ብላ በምትገኝ ጂራ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ዉስጥ ምትክ ቦታ እየተዘጋጀላቸው እንደሆነ ሀላፊው ጨምረው ገልጸዋል፡፡..
ትዝታዬ ተሰልፎ መጣ፡፡ ኮንዶሚንየም በኔ ጊዜ ፋሽን ነበረች፡፡ ኮንዶሚንየም የደረሰው አባወራ ዲቪ እንደደረሰው ሰው ይከበር ነበር፡፡ ዲቪም ኮንዶሚንየምም ድንገት እንዲቆሙ ተደረገ፡፡ ኮንዶሚንየም የኪራይ ሰብሳቢዎች መመሸጊያ ሆኗል ይቁም ተባለ፡፡ ዲቪ አክራሪ ዲያስፖራዎችን መፈልፈያ እየሆነ ነው በሚል ተቋረጠ፡፡ በዚህ ዘመን ከአገር ለመውጣት መቶ ሺህ ብር የኮቴ ቁርጥ ግብር እስከነ ቫቱ መክፈል ግዴታ ነው፡፡ ድሮ የኮቴ ቁርጥ ግብር የሚባል ነገር የነበረ አይመስለኝም፡፡ አንድ ሰው ቪዛ እስካገኘ ድረስ ውልቅ ማለት መብቱ ነበር፡፡ እንዲያውም ..መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ.. የሚል አባባል ትዝ ይለኛል፡፡ ደጉ መሪያችን ነበሩ ይችን ቃል የፈጠሯት፡፡ አሁን ይች ቃል እጅግ ከመለመዷ የተነሳ ..ቻው.. የምትለዋ ቃል ..መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ.. በሚለው ተተካች፡፡ ቻው የቅኝ ገዢና የነፍጠኞች ቃል ናት በሚል እንድትወገዝ ተደረገ፡፡ ለምሳሌ ሁለት ሰዎች ተገናኝተው ካወሩ በኋላ ..በል ጓዴ ደህና ዋል.. በማለት ፈንታ፣ ..በል ጓዴ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ.. ይባባላሉ፡፡
ዶልቼ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ ሳይለኝ ወደ ሌላኛው የዘመን ዜና አለፍኩ፡-
|15¾ው የህዝብና ቤት ቆጠራ ዉጤት ነገ ይፋ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ከ135 ሚሊዮን እንደሚልቅ ይጠበቃል፡፡..
ከዚህ በላይ የህዝቡ ቁጥር ከጨመረ ሰው በሰው ላይ ለመተዛዘል ይገደዳል ብዬ አሰብኩ፡፡ ይህን ያልኩት ያለምክንያት አልነበረም፡፡ አሁን አራት ኪሎ ጋዜጣ እያነበብኩ ያለሁት ስፒል በማታስቀምጥ ቦታ ተሸጉጬ ነው፡፡ስንት ነበርን ድሮ! 80 ሚሊዬን፡፡ አሁን ሳስበው ይገርመኛል፡፡ ልጄ እውነቷን ነው ለካ፡፡ እንዴት 80 ሚሊዬን እያላችሁ አዲስ አበባ ውስጥ አንድ ጋሻ መሬት እንኳ መያዝ አቃተህ? እያለች ነጋ ጠባ የምትወቅሰኝ እውነቷን ነው፡፡ እንዴት ያን ጊዜ ቦታ መያዝ ተሳነኝ? ለኔም እንቆቅልሽ ነው፡፡ ኮንዶሚንየም እንዲደርሰኝ ግን ተመዝግቤ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ ሊደርሰኝ ሲል የኪራይ ሰብሳቢዎች መመሸጊያ ሆኗል ተብሎ ተቋረጠ፡፡ ለነገሩ እንኳንም አልደረሰኝ፡፡ አሁን ከተማዋ ውስጥ መሬት ሲጠፋ ኮንዶሚንየሞች እየፈረሱ ለአረቦች በሊዝ እንዲሸጡ እየተደረገ አይደል፡፡ አፍርሰው ለአረብ ከሚሸጡኝ እንኳንም ቀረብኝ፡፡ ተጽናናሁ፡፡ አረቦቹ ያባቶቼን መሬት ሩዝ በሩዝ አድርገውት ሲያበቁ አሁን ደግሞ ጭራሽ ከተማውን ሙዝ በሙዝ ሊያደርጉት፡፡ አረብኛ ሦስተኛው ኦፊሳላዊ ቋንቋችን መሆኑም ያንገበግበኛል፡፡
wd l¤§ የአዲስ ዘመን ዜና አለፍኩ፡-
..የፈተናዎች ድርጅት የ2ኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና /ማትሪክ/ ለመውሰድ የተዘጋጁ 8 መቶ ሺ ተማሪዎች ፈተናውን ማጥቆር ከመጀመራቸው በፊት የፓርቲ አባልነት ፎርም እንዲሞሉ በጥብቅ አሳሰበ፡፡ ይህን በማያደርጉት ላይ የፈተና ውጤታቸው ሙሉ በሙሉ ሊሰረዝ እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡  ድርጅቱ ትናንት ለልማት ዜና አገልግሎት/ልዜአ/ በላከው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው የአባልነት ፎርሙን መሙላት ተማሪዎቹ ፈተናውን ተረጋግተው እንዲሰሩ ከማስቻሉም በላይ፣ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የተሻለ ተቆርቋሪ ዜጋ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል ብሏል፡፡..
ከዚህ ዜና ስር ደግሞ የሚከተለው ዜና በቀይ ቀለም ተጽፎ አነበብኩ፡፡
..ድርቁ ወደ ረሀብነት እንደማይሸጋገር የራስን መቻል ሚኒስትር መስሪያ ቤት አንደበተ-ብስራት(ቀድሞ ህዝብ ግንኙነት ይባል የነበረ) ኃላፊ ገለጹ..
ይህንን ሳነብ ሳቄ መጣ፡፡ እርግጥ ነው በረሀብ አይሳቅም፡፡ ያሳቀኝ ሌላ ነው፡፡ እንደሚባለው ድሮ ጀምሮ ንጉሱም፣ ነፍሱን ይማረውና ወታደሩ መሪም የአሁኑም ሰውዬ እንደምንራብ ማመን አይፈልጉም፡፡እነርሱ እንዲያምኑ ረሀብ ቤተመንግስት መግባት አለበት፡፡
..ተቋርጦ የነበረውን የብልጽግና ግድብ (ቀድሞ ሚሌኒየም በኋላ ደግሞ ህዳሴ ግድብ በመባል ይታወቅ የነበረ) በአዲስ ዲዛይን ለመስራት እቅድ መያዙን የዉሃና ግድብ ሚኒስትሩ ተናገሩ፡፡ ለፕሮጀክቱ ብድር ለማግኘት በሚኒስትሩ የሚመራ የልዑካን ቡድን በያዝነው ወር መጨረሻ ወደ ደቡብ ሱዳን ያቀናል፡፡..
(ይህ ግድብ እንዲሰራ ወጣት እያለሁ ከደመወዜ የሆነ ያህል ብር ይቀነስ እንደነበር ትዝ አለኝ፤ ብሩ ይቀነስብኝ የነበረው ገና እንደተቀጠርኩ ስለነበረ ነው እስከዛሬም የማልረሳው፤ ጊዜው ግን እንዴት ይሮጣል!) ደግሞ ያኔ ደቡብ ሱዳን ገና ሚጢጢ ድሀ አገር ሆና መወለዷ ነበር፡፡ ከሰሜን ሱዳን ተገንጥላ ነው ይባል ነበር፡፡ አሁን አበዳሪያችን ሆነች፡፡ ጊዜው እንዴት ይሮጣል!
ወደ ሌላኛው የአዲስ ዘመን ዜና xlFkù:-
..አዲሱ 97/3 የትምህርት ፖሊሲ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ሊሆን ነው፡፡
የአገሪቱን የግብርና ባለሙያዎች እጥረት ለመቅረፍ የተዘየደውና 97/3 በመባል የሚታወቀው የትምህርት ፖሊሲ በሚቀጥለው ዓመት በስድስቱም የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ አገሪቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለረዥም አመታት ያሰለጠነቻቸው ተማሪዎች አመርቂ ውጤት ሊያስገኙ ስላልቻሉ፣ በዚህ ዘርፍ የሚሰለጥኑ ተማሪዎች ከጠቅላላው  3 በመቶ ብቻ እንዲሆኑ መወሰኑንና በተቃራኒው በማህበረሰብ ሳይንስና በግብርና ዘርፍ የሚሰለጥኑ ተማሪዎችን ቁጥር ወደ 97 በመቶ ከፍ ለማድረግ በተያዘው እቅድ መሰረት፣ በቀጣዩ ዓመት ስድስቱም ዩኒቨርሲቲዎች ለዚሁ የሚረዳቸውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገልፀዋል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ 73 ደርሰው የነበሩት የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ሰርተፍኬት አባዝቶ ከመስጠት ባለፈ አምራችና ስራ ፈጣሪ ዜጋን በማፍራት ረገድ የረባ ውጤት ባለማምጣታቸው  ቁጥራቸው ወደ 6 ዝቅ እንዲል ባለፈው ዓመት መወሰኑ ይታወሳል፡፡..
በኔ ጊዜ ማስመርያ እና ላጲስ ሳያሟሉ እንኳ ዩኒቨርሲቲዎች ኢንጂነሪንግ አስተምሩ ተብለው ሲገደዱ በደንብ ትዝ ይለኛል፡፡ ያኔ 70/30 ምናምን ነበር የሚባለው፡፡እንደመሰረት ትምህርት ዘመቻ ሁሉ yኢንጂነሪንግ ዘመቻ ተጀምሮ ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ በሆዴ እንደገና መልሰው እኛኑ ይቆጡናል እንዴ! ስል አሰብኩ፡፡ በሆዴ ያሰብኩትን የሰማ ካለ በሚል አራት ኪሎን ገልመጥመጥ አድርጌ አየኋት፡፡ ..ወ/ሮ ብርቱካን ሚደቅሳ ከ27 ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ወደ አገራቸው ለመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ፡፡ መንግስት በበኩሉ የሴትዮዋን ዉሳኔ ጊዜውን የጠበቀ ብሎታል፡፡ ወይዘሮዋ ራሳቸውን ከፖለቲካ ካገለሉ በኋላ ቃሌ የሚል የሻማ ፋብሪካ አቋቁመው በአገራቸው ኢንቨስት ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ወ/ሮ ብርቱካን በወጣትነታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪ የነበሩ ሲሆን ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ዕድሜ ይፍታህ ተበይኖባቸው በምህረት ከእስር መፈታታቸው ይታወሳል፡፡.. በስጨት አልኩለኝ፡፡ ሰው እንዴት ለሕዝብ እንደሻማ ይቀልጣል ተብሎ ሲጠበቅ ሻማ ፋብሪካ ይከፍታል? ብስጭቴን ለማብረድ ዘመን ስፖርትን ማንበብ ጀመርኩ፡- /ላለፉት ሀምሳ አመታት ከመበሳጨት ያተረፍኩት በሽታን ነው፡፡ ነጫጭ ጸጉሮቼን ከራስ ቅሌ ላይ የመነጠርኩት በረባ ባልረባው ስበሳጭ ነው፡፡ ቅል ራስ ስል ራሴን ዘለፍኩት፡፡
የአዲስ ዘመን ስፖርት አምድ /ዘመን ስፖርት/ ምን ይዞ ይሆን? የመጀመርያ ዜና፡-
..የአንድነት መርህ ይከበር አባላት ዘንድሮ አርሴናል 46ኛውን የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ እንደሚያነሳ ተነበዩ፡፡ መኢአድ በበኩሉ ዋንጫው የቼልሲ ነው ይላል፡፡..
እንደማስታውሰው ሁለቱ ፓርቲዎች የዛሬ ሀያ ምናምን ዓመት ስልጣን ለመያዝ የሚሠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሆነው ነበር የተመሰረቱት፡፡ የኋላ ኋላ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ይልቅ የእንግሊዝ እግር ኳስ የተሻለ ሰፊ ምህዳር አለው በሚል ፊታቸውን ወደ እንግሊዝ ቅሪላ አዞሩ፡፡ በእርግጥ ያን በማድረጋቸው የብዙ ወጣቶችን ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል፡፡
የአገር ውስጥ S±RT:-
..የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች ማኅበር የአባላቱን ቁጥር 48 ሚሊዬን ማድረሱን ገለጸ፡፡ ፓርቲው ትናንት ስታዲየም አካባቢ በሚገኘው ጽ/ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ከሚቀጥለው የበጀት ዓመት ጀምሮ የቡድኑ አባል ያልሆኑ አባወራዎች የኤሌክትሪክ መስመር ሊቋረጥባቸው እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡ የፓርቲው የሕዝብ ማጥመቅ (ድሮ ሕዝብ አደረጃጀት ይባል የነበረ) ክንፍ ኃላፊ ኢኒስትራክተር ኢሳያስ ታረቀኝ ለልዜአ እንደተናገሩት፤ ዜጎች አገሪቱን ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይል እያገለገለ የሚገኘውን ፓርቲ ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ የማገዝ የዜግነት ግዴታ አለባቸው ብሏል፡፡ የእግር ኳስ ቡድኑን ማገዝ ፓርቲውን ማገዝ ነው፣ ፓርቲውን ማገዝ አገርን ማገዝ ነው፤ አገሩን የማያግዝ ደግሞ ባንዳ ነው ሲሉ ነው የህዝብ ማጥመቅ ክንፍ ኃላፊው ያስጠነቀቁት፡፡ የገዢው ፓርቲ ቡድን ለዘንድሮው የውድድር ዓመት ከታይዋን አዲስ አሰልጣኝ  በ50 ሺ ዶላር ማስፈረሙ ይታወሳል፡፡..  
ዘመን ስፖርት የመጨረሻው ገጽ የሚከተለውን ዜና Y²*L:-
..የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአዲስ አበባ ስታዲየም በተመጣጣኝ ዋጋ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጫወታዎችን በስክሪን ማሳየት እንደሚጀመር አስታወቀ፡፡ የፌዴሬሽኑ ብስራተ ልሳን (ህዝብ ግንኙነት) እንደተናገሩት፤ የአገር ውስጥ ውድድሮች በተመልካች ድርቅ በመመታታቸው ከፊፋ ጋር በመነጋገር ሰባት ዘመናዊ ስክሪኖችን በአዲስ አበባ ስታዲየም በማስተከል፣ የአውሮፓ ውድድሮችን ህዝቡ በቀጥታ እንዲኮመኩም ይደረጋል ብለዋል፡፡ ሁለቱ ስክሪኖች የሚተከሉት በተቃራኒ ቡድኖች የግብ ክልል መረቦቹን በመገንጠል ሲሆን ቀሪዎቹ ከማን አንሼ፣ ሚስማር ተራ፣ ካታንጋና ጥላ ፎቅ ይገጠማሉ፡፡ የፌዴሬሽኑ ብስራተ ልሳን ጨምረው እንደተናገሩት፤ የአበበ ቢቂላ ስታዲየምም ተመሳሳይ አገልግሎት በቅርቡ መስጠት እንደሚጀመርና ይህ ማለት ግን የአገር ውስጥ ውድድሮች ሙሉ በሙሉ ይቀራሉ ማለት እንዳልሆነ አብራርተዋል፡፡ የአገር ውስጥ ፕሪምየር ሊግ በጫካ ሜዳ፣ በጉቱ ሜዳና በክልል ከተሞች እንዲካሄዱ መርሀ ግብር እንደተነደፈ ብስራተ ልሳኑ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡..ጋዜጣውን አጣጥፌ ለአሳላፊው /አከራዩ/ አስረከብኩት፡፡ ዝርዝር ይኖርሃል? ብዬ ድፍን አምስት መቶ ብር ከኪስ ቦርሳዬ አውጥቼ ሰጠሁት፡፡  
አይጠፋም አባት! እያለ ተቀበለኝ፡፡ 475 ብር መለሰልኝ፡፡ ረሃብ ተሰማኝ፡፡ አጠገቤ ከሚገኘው ጆሊ ባር ምሳ ለመብላት የያዝኩት ብር አይበቃኝም፡፡ በዚያ ላይ ወረፋው፡፡ በአስፋልቱ ዳርቻ ታክሲዎች ተደርድረው ታፔላቸው ጎን በሰቀሉት ድምጽ ማጉያ የሚሄዱበትን ሰፈር ስም ይለፍፋሉ፡፡ ለቡ!! ፉሪ!! ፉሪ ለቡ!! ለገጣፎ!!!  ይላል የተቀረጸው ድምጽ ማጉያ፡፡ ድሮ በዚህ መልኩ የሚለፍፈው ሰው ነበር ይባላል፡፡ ሲገርም!!
በታክሲ መሄዱ ጥቅሙ ስላልታየኝ ቁልቁል ወደ ቤተ መንግስት የሚወስደውን አስፋልት በእግሬ ተያያዝኩት፡፡ በስተግራዬ ድሮ ጀምሮ ታጥሮ የነበረው የአላሙዲን የሸራተን ማስፋፍያ ፕሮጀክት መቆፈር መጀመሩን አስተዋልኩ፡፡ ከአጥሩ ስር አንድ ሽማግሌ የኔ ቢጤ ሰፊውን አዲስ ዘመን ጋዜጣን ከእግራቸው ስር አንጥፈው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ስም ሰፊውን ህዘብ ምጸዋት ይጠይቃሉ፡፡
ስለ እመቤቴ! ስለ ወላዲቷ! ስለ...
îSt¾W §Y y«„T SM አስፈርቶኝ 25 ብር መጸወትኳቸው፡፡ለማኙ በየመሀሉ ሞባይል ስልካቸውን ይነካካሉ፡፡ ጥንት ሞባይል የሀብት መገለጫ እንደነበር ለአፍታ ትዝ ብሎኝ ፈገግ አልኩኝ፡፡ በዚህ ዘመን ፈገግ የምለው በዓመት አንዴ እግዜር ካለ ደግሞ ሁለት ጊዜ ነው፡፡ የአላሙዲንን አጥር ተስታክኬ ከመጸወትኳቸው የኔ ቢጤ ፈንጠር ብዬ አረፍ ደገፍ አልኩኝ፡፡  
ትንሽ እንደተራመድኩ ከአላሙዲ አጥር ስር እንደአላሙዲ ባለጸጋ ለመሆን የሚመኝ አንድ ሸጋ ወጣት መጸሐፍ አንጥፎ ይቸረችራል፡፡ ከእግሩ ስር የችርቻሮ ንግድ ፍቃዱን ዘርግቶታል፡፡ ከንግድ ፍቃዱ ስር መጽሐፍ በየአጥር ስር አንጥፎ ለመቸርቸር የሚያስችለውን የትምህርት ማስረጃ ዘርግቶታል፡፡ ሁለቱንም ፍቃዶች ሳይዙ መነገድ ያስጠይቃል፡፡ ልጁ ፍቃዶቹን ንፋስ እንዳይወስድበት መሰለኝ ድንጋይ ጭኖባቸዋል፡፡ በድጋሚ የረሃብ ስሜት ተሰማኝ፡፡ የቤተመንግስቱን አጥር ተደግፈው የተሰሩ አርከበ ሱቆች ዉስጥ ገብቼ ሻይ በአምባሻ መብላት አማረኝ፡፡ ቤተመንግስት አጥር ላይ እነዚህ ሱቆች መሠራታቸው የሆነ ወቅት ላይ ዉዝግብ ፈጥሮ ነበር፡፡ ጠ/ሚሩ ለልማት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳዩበት ነው እየተባለም ይወራል፡፡ አሻግሬ አጥሩን ተስታከው መደዳውን የተሰደሩ ምግብ ቤቶችን አየሁ፡፡ ሁሉም ተመጋቢ ተሰልፎባቸዋል፡፡ አንድ በላተኛ በልቶ ሲወጣ አሰላፊው ..ተረኛ!.. እያለ ይጣራል፡፡ ተረኛ ተሰላፊ ይገባል፡፡ ምግብ ቤቱ ውስጥ ያለው አሳላፊ በበኩሉ ተሰላፊው ምግቡን አቅርቦ መብላት የጀመረበትን ሰዓት እና ማብቃት ያለበትን ሰዓት ይመዘግባል፡፡እስጢፋኖስ አካባቢ ባሉ ምግብ ቤቶች ወረፋው ቀለል ስለሚል ወደዚያ መሄድ እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ተሻግሬ የቤተ መንግስቱን አጥር ይዤ ቁልቁል ተንደረደርኩ፡፡ በስተግራዬ ታላቁን ቤተ-መንግስት ገላመጥኩት፡፡ በሌላ አነጋገር ጠ/ሚኒስትሩን ገላመጥኳቸው፡፡ ቤተ-መንግስቱን መገላመጥ ሦስት ወር እንደሚያሳስር ትዝ ሲለኝ በፍጥነት አቀርቅሬ መራመድ ጀመርኩ፡፡ በእርምጃዎቼ መሀል ሰውየው እዚህ ቤት ውስጥ መኖር አይሰለቻቸውም እንዴ? አልኩኝ በሆዴ፤ በለሆሳስ፡፡ ድንገት ቅጠልያ የለበሰ አንድ የቤተመንግስት ኮማንዶ ከየት መጣ ሳልል ከአጥሩ ተስፈንጥሮ ወረደና ምን አልክ? አለኝ፡፡አፌም እግሬም ተሳሰሩ፡፡ እንዴት በሆዴ ያሰብኩትን ሊሰማ ቻለ? ክፉ ዘመን!
/መሐመድ ስልጣን በመቀሌ ዩኒቨርስቲ በጆርናሊዝም ዲፓርትመንት ሌክቸረር እና መሐመድ ጋ/ ጠብቂኝ መጽሐፍ ፀሐፊ ነው፡፡/

 

Read 7240 times Last modified on Saturday, 10 September 2011 12:02

Latest from