Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 10 September 2011 12:00

ታሪክን በስፖንሰር

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ታሪክያለፈውንለመገምገምየሚመጣውን በወጉ ለመተለም     የሚያገለግላል የማኅበራዊ ሳይንስ መስክ ነው፡፡ የታሪክ ተመራማ ሪያን ወይም ጸሐፍቱ በልዩ ልዩ ምክንያቶች በተጽኖ ስር ሊወድቁ ስለሚችሉ ፍጹማዊ ወይም ትክክለኛ ታሪክ ለማግኘት አዳጋች ነው፡፡ ታሪክን ፍጹማዊ ማድረግ ባይቻል እንኳን ፍላጎቱና ገለልተኝነቱ ካለ የተለያዩ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በማጥናት፣ ሚዛናዊነት በመጠበቅ እና ሳይንሳዊ ትንተናዎችን በማካተት የተጽኖዎችን ኃይል ቀንሶ ፍጹማዊ ባይሆንም የተሟላ ታሪክ ማቅረብ ይቻላል፡፡በኢትዮጵያ ከ50 ዓመታት ወዲህ ከተከናወኑት ክንውኖች መካከል በአንድ ወገን ብቻ ወደ 55 ሺህ የሚጠጉ ታጋዮችን ህይወት መስዋት ያደረገው ለ17 ዓመታት የተካሄደውን የትጥቅ ትግል የሚተርኩ መጽሐፍት እየወጡ ነው፡፡

ፊልሞችም እየተሠሩ ነው፡፡ ባለታሪኮቹ የእነዚህን መጻሕፍት ጸሐፊዎች እና ፊልም ሠሪዎች ..ውሻ በበላበት ይጮሃል.. ይሏቸዋል፡፡
በህወሓት የትጥቅ ትግል ታሪክ ዙሪያ የተጻፉት መጽሐፍት፣ የተሠሩት ፊልሞች እና የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች ሚዛናዊነታቸው እና በባለታሪኮቹ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት በትግሉ ሂደት ባለፉ ከፍተኛ አመራሮች ጥርጣሬ ውስጥ ወድቋል፡፡
የታሪኩ ይዘት
ከዓመታት በፊት አጫጭር የታጋዮች ታሪክ በአንድ መድብል ተጣምረው ..ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ.. በሚል ርእስ በተስፋዬ ገብረአብ ተዘጋጅተው ይወጡ ነበር፡፡ ከዛ በኋላ ለረጅም ጊዜ በጣም አልፎከሚወጡት የአንድ እጅ ጣት ቁጥርን ከማይሞሉት መጽሐፍት በስተቀር ለንባብ የበቁ አልነበሩም፡፡
እነ ..ጋላህቲ ሰጊ..፣ ..ፅንዓት..#..መለስ እና የህወሓት የትጥቅ ትግል ታሪክ..፣ ..ጋሀዲ.. (XSk ክፍል 3) በትጥቅ ትግሉ ዙሪያ ከወጡት መጻህፍት ተጠቃሽ ሲሆኑ፤ ከፊልም አጋዚ ኦፕሬሽን እና ሙሴ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የትጥቅ ትግሉን ለመጀመር በየካቲት ወር ወደ ደደቢት ካመራው ቡድን አንዱ የሆኑት አቶ አሰገደ ገ/ስላሴ፤ ..ጋላሀቲ ሠጊ.. እና ..መለስ እና የህወሓት የትጥቅ ትግል.. የተባሉት መጻሕፍቶች ማዕከል ያደረጉት መለስ ዜናዊን፤ ..ፅንዓት.. የተባለው መጽሐፍ ደግሞ ስዩም መስፍንን ነው፡፡ እኔ ስለሁለቱም ባለታሪኮች ቢጻፉ ምንም ችግር የለብኝም፡፡ ቅሬታም የለብኝም ነገር ግን ባለታሪኮቹ የራሳቸው ታሪክ ይበቃቸው ሳለ የሌሎች ታሪክ ተደርቦ ሊሰጣቸው አይገባም፡፡ ውሸት ተጨምሮ ሐቅ ሊደበቅ አይገባም፤ ታሪክ ነውና ይዘቱ በእውነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት ባይ ነኝ.. ይላሉ፡፡
ልዩነት ቢኖር እንኳን ታሪክ የሚተላለፈው ለሕዝብ በመሆኑ፤ ታሪክ ጸሐፊ ነን የሚሉ ሰዎች የነበረውን እንደነበረ ሊያስቀምጡ ይገባ እንደነበረ ባለታሪኮቹ ይገልጻሉ፡፡
..የህወሓት የትጥቅ ትግል ታሪክ የተፈጸመ እና የማይቀየር ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ መጽሐፍ የሚጽፉ ጸሐፍትም ሆኑ ፊልም ሠሪዎች ይህን ታሪክ እንደነበር ማስቀመጥ አለባቸው፡፡ በታሪኩ ላይ አስተያየትም ሆነ ግምገማ መስጠት የፈለገ ሰው መስጠት ይችላል፡፡ ታሪኩን ግን መቀየርም ሆነ አዛብቶ ማቅረብ አይቻልም፡፡ እኔ እስካሁን በትጥቅ ትግሉ ዙሪያ የተጻፉትን ጥቂት መጻህፍት እንዳነበብኳቸው ከተሠሩት ፊልሞች ሁለቱን እንዳየኋቸው፣ ታሪኩ እና ግምገማው ተምታቶባቸዋል፡፡.. በማለት ግምገማቸውን የሚያስቀምጡት ከባለታሪኩ አንዱ፣ ለመጀመሪያው የትጥቅ ትግል ወደ ኤርትራ ሣህል ማሰልጠኛ ከተጓዙት ታጋዮች አንዱ የነበሩት እና በኋላም በክፍፍሉ ወቅት ከህወሓት ተገንጥለው የወጡት አቶ አውዓሎም ወልዱ ናቸው፡፡
ከትጥቅ ትግሉ ባለታሪክ አንዱ የሆኑት አቶ ገብሩ አስራት፤ ..በቅርብ ጊዜ ከወጡት ውስጥ ሦስቱም ያነበብኳቸው መጻሕፍቶች ግለሰቦችን ማዕከል ያደረጉ ናቸው፡፡ በመጻሕፍቱ የተጠቀሱት ግለሰቦችም ቢሆኑ በዛ ታሪካዊ ወቅት ከሌሎቹ ያልበለጠ ታሪክ የነበራቸው እንዲያውም አንዳንዶቹ ያነሰ ታሪክ የነበራቸው ናቸው፡፡.. ይላሉ፡፡
አቶ ገብሩ እንደሚሉት ታሪካቸው ጎልቶ የሚጻፍላቸው ባለታሪኮች አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት ናቸው፡፡ በፓርቲው ክፍፍል ወቅት ተለይተው የወጡት ባለታሪኮች ታሪክ እንዲጎላ ስለማይፈለግ አይወሱም፡፡ ድንገት ከተወሱም በጣም በደበዘዘ መልኩ ነው፡፡
ህወሓት ታሪክ የሚሠራው በሕዝብ ነው፡፡ ታሪክ ሠሪውም ሕዝብ ነው የሚል እምነት ነበረው፡፡ፓርቲው ወደ ሥልጣን ከመጣም በኋላ 17 ዓመታት በትጥቅ ትግል ያለፉትን ሂደቶች ለመጻፍ ኮሚቴ ተቋቁሞ መረጃ መሰብሰብ ተጀምሮ ነበር፡፡ ባልታወቀ ምክንያት ምንም ዓይነት መጽሐፍ ሳያሳትም ተበተነ፡፡   
እንደ አቶ አውዓሎም አገላላጽ ታሪክ እንጽፋለን ብለው ከተነሱት ግለሰቦች አንዳንዶቹ የአንድን ድርጅት ፍላጎት እና ምኞች ከነበረው ታሪክ ጋር አዋህደው ታሪክ አስመስለው ያቀርባሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ የግለሰቦችን ታሪክ በሚጽፉበት ጊዜም የድርጅቱን አጠቃላይ ታሪክ እንዳለ ለአንድ ሰው አሸክመው እውነታውን ሽምጥጥ አድርገው በመካድ፣ ያልነበረውን እንደነበር አድርገው ያቀርባሉ፡፡
አቶ አሰገደ ይህንን በምሳሌ ሲያስቀምጡ፤ ..ለምሳሌ ስለ ስዩም ታሪክ በተጻፈው ..ፅንዓት..፤ አቶ ኪሮስ አለማየሁ የሚባሉ የሁመራ ሀብታም ነበሩ፡፡ የአቶ ስዩም አጎት ናቸው፡፡ እኚህ ሰውዬ መጀመሪያ ከልዑል ራስ መኮንን ጋር ወደ ሱዳን ሄደው ኢዲዩ ነበሩ፡፡ ከዛም የኢዲዩ የጦር አበጋዝ ሆነው እስከ ድሉ ቆይተዋል፡፡ ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ ደግሞ ሁሉን ትተው አዲስ አበባ  ገቡ ታሪኩ ሲጻፍ ግን የህወሓት መስራች ተደርገው ተጠቅሰዋል.. ይላሉ፡፡
ተገንጣዩ ባለታሪክ
ህወሓት ሲከፋፈል የተወሰኑት አመራር ባለታሪኮች፣ ሥልጣንን በእጃቸው ሲያስገቡ ሌሎቹ ከዚህ ውጭ ሆነዋል፡፡ ይህም ታሪኩ ተዛብቶ ለመቅረቡ እንደ ምክንያት ተጠቃሽ ሆኗል፡፡ ..ታሪክ የሚጻፈው በገዢዎች ነው የሚባለውን በሚያረጋግጥ መልኩ መጽሐፍቶቹ እየተጻፉ ያሉት በገዢዎቹ ፍላጎት ነው፡፡ ነባራዊ ሁኔታዎችን መሠረት ያደረጉ ሳይሆኑ አሁን በሥልጣን ላይ ያሉትን መሪዎች ስም በማጋነን፣ ታሪክ በዋነኛነት በእነሱ እንደተፈጸመ አስመስለው ማቅረብ ነው የያዙት.. በማለት አቶ ገብሩ ጸሐፊዎቹን ወገንተኛ ናቸው ሲሉ ይተቿቸዋል፡፡
አቶ አውዓሎም በበኩላቸው ..ፅንዓት.. በተባለው መጽሐፍ የሽሬን ኦፕሬሽን የመራው ስዩም ብቻ እንዲሆን ተደርጎ ተጽፏል፤ እኔ እስከማውቀው ድረስ ግን በወቅቱ በነበረው የሥልጣን እርከን ወታደራዊ አመራሩን የሚመራው አረጋዊ በርሄ (በሪሁ) ነበር፤ ያ ባይሆን እንኳ በዛን ኦፕሬሽን የሁለቱ ተሳትፎ አንድ ዓይነት ነበር፡፡ ይህ የሚያሳየው በፖለቲካው የማይፈለጉ ሰዎች በታሪክም እንዲጠቀሱ እንደማይፈለግ ነው፡፡.. ይላሉ፡፡
ለመተቸትም ሆነ ለመገምገም የበቁት መጽሓፍቱና ፊልሞቹ ናቸው እንጂ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ወቅትን ጠብቀው በሚሠሩ ዶክመንተሪዎች እንኳን ታሪኩን፤ በወቅቱ የተደረጉ የጉባኤ ስብሰባዎች ለማሳየት በሚሞክሩበት ወቅት ከህወሓት የተለዩትን ታጋዮች ምስል ቆርጠው እስከማቅረብ እንደሚደርሱ አቶ አውዓሎም ያስረዳሉ፡፡
..የአጋዚ ኦፕሬሽን ሲካሄድ በወቅቱ የህወሓት ሚሊቴሪ ኮማንደር አዛዥ ስየ አብርሃ ነበር ኃየሎም ኦፕሬሽኑን እና ወታደሩን ይመራ ነበር፤ ስየ ደግሞ ከበላይ ሆኖ ኦፕሬሽኑን መርቷል፤ የማደናገሪያ ተኩሱን ጨምሮ ሬዲዮኑን ይዞ በኦፕሬሽኑ ዋና ተሳታፊ ነበር፤ ነገር ግን ..አጋዚ ኦፕሬሽን.. የሚለው መጽሐፍ በሚጻፍበትም ጊዜ በፊልሙ ስየ ጭራሽ አልተነሳም፤.. ይላሉ አቶ አሰገደ፡፡
አቶ አውዓሎም ደግሞ ስለዚሁ ኦፕሬሽን ሲያስታውሱ፤ ..አጋዚ ኦፕሬሽን የተመራው በማእከላዊ ውሳኔ ነው ቀጥሎ ሁለተኛውን የሚያስፈጽመው ፖሊት ቢሮው ነው፡፡ ከፖሊት ቢሮው በተዋረድ ወርዶ ጠቅላላ የሚመራው ወታደራዊ ኮሚቴው ነው፤ በንድፉ መሰረት ወታደሮቹን የሚመራው ኃየሎም ነበር፡፡ አጠቃላይ ወታደራዊ ክንፉን የሚመራው ሁሉንም ትእዛዝ የሚሰጠው ግን ስየ ነበር፡፡ እንደውም ከዋናው ቦታው እነኃየሎምን ሊያስተባብር መቀሌ ሔዶ ነበር፡፡ ፊልሙ ላይ ስናየው ግን ስየ አንድም ቦታ አልተጠቀሰም፤ እንደውም እንደ መሪ ወደነ ኃየሎም ለማስጠጋት የተሞከረው እነመለስን ነው፡፡.. ይላሉ፡፡
አቶ ስየ ከህወሓት ስለተገነጠለ፤ ከትረካዎቹም ተገንጥሎ ወጥቷል፡፡ ..ባድመን እንደ ምክንያት.. በሚል ርዕስ የ1991 ዓመቱን የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርነት በሚመለከት የተጻፈ መጽሐፍ፤ በወቅቱ በኢትዮጵያ በጠቅላላ የነበሩ ክልሎች እና ፕሬዝዳንቶች ለጦርነቱ ያበረከቱትን አስተዋኦ ሲዘረዝር የሁሉንም ስም እና ፎቶ ያስቀምጥ እና ትግራይ ላይ ሲደርስ በወቅቱ የክልሉ ፕሬዝዳንት የነበሩትን አቶ ገብሩ አስራትን በመተው ም/ፕሬዝዳንቱን አለቃ ጸጋዬ በርሔን ይጠቅሳል፡፡
..ታሪክ ..ታሪክ.. እንጂ የፖለቲካ አቋም ወይም ጥቅም ማራመጃ አይደለም፡፡ እኔ ይህን መጽሐፍ ከመጽሐፍ አልቆጥረውም፡፡ እኔና ሌሎች በዚህ ሂደት ሚና የነበረን ሰዎች ማካተት ለእርሱ ጥቅም የሚያስገኝለት ስላልሆነ ዘሎታል፡፡ ..ውሻ በበላበት ይጮሃል.. አይደል የሚባለው፤ ይህ ድርጊቱ ደግሞ እራሱኑ መልሶ ያዋርደዋል እንጂ ታሪክን እና የግለሰቦችን ሂደት ሊቀይር አይችልም፡፡.. በማለት የታሪኩ አካል ሆነው  ስማቸው በመጽሐፉ አለመጠቀሱን ትልቅ ነገር አድርገው  እንደማይወስዱት አቶ ገብሩ አስራት ያስረዳሉ፡፡
ስፖንሰር በማን?
..እኔ እንዳየኋቸው አብዛኞቹ ለሚጽፉት መጽሐፍት እና ለሚሠሩት ፊልም የሚጠይቀውን ወጪ የሚያወጡት ከራሳቸው ሳይሆን በስፖንሰርሺፕ ድጋፍ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ስፖንሰር ያደረገው አካል እንዲጻፍ የሚፈልገው ታሪክ በመጽሐፍ ወይም በፊልም ጎልቶ እንዲወጣ አሊያም ታሪክ እንዲዛነፍ ያደርጋል፡፡ ..የእነዚህ ስፖንሰር አድራጊዎች ተጽዕኖም በጣም ከፍተኛ መሆኑን ባየኋቸው ፊልሞች እና ባነበብኳቸው መጽሐፍቶች ላይ ተመልክቻለሁ፡፡.. የሚሉት አቶ አውዓሎም ወልዱ ናቸው፡፡
መጻሕፍቱ በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ገንዘብ ሰጥተው ስፖንሰሩ የፈለገው የሚጻፍበት እንጂ ነጻ ሆነው ታሪክ የሚጽፉ ወይም ሂስ የሚያቀርቡ አይደሉም፡፡ ታጋዮች ህይወታቸውን መስዋት ያደረጉበት ታሪክም ስፖንሰርሺፕ ማፈላለጊያ ሆኗል፡፡ እንደ ..ኤፈርት.. እና ..ማረት.. ያሉ ድርጅቶች አሁን ሥልጣን ላይ ያለውን አመራር የሚያጎሉ፣ ሌላውን የሚያሳንሱ ታሪኮች ከሆኑ ስፖንሰር ያደርጓቸዋል፡፡ በተጨማሪም በርካታ የመንግሥት ድርጅቶች ለእንደዚህ ያሉ ታሪኮች እጃቸው ይዘረጋል፡፡ ጸሐፊዎቹም ሆነ ፊልም ሠሪዎቹ ይህን የስፖንሰርሺፕ ገንዘብ ለመልቀም ሲሉ ታሪክን አጣመው ያቀርባሉ፡፡.. ›ሲሉ አቶ ገብሩ ጸሐፍቱን አብዝተው ይተቻሉ፡፡
መጽሐፍቱና መለስ
አቶ መለስን በሆነ ቦታ ሸንቁሮ ማስገባት ገበያ ያመጣል በሚል ስለሚታሰብ እንደምንም ብለው አንድ ታሪክ ውስጥ እንደሚከቷቸው የቀድሞ የትግል ጓደኞቻቸው ይናገራሉ፡፡ ..የትጥቅ ትግሉ ጀማሪዎች በጥር ወር ወደ ኤርትራ ሣህል ማሰልጠኛ ጣቢያ የሄደው እና በየካቲት ወር ወደ ደደቢት ያመራው ነው፡፡ መለስ በወቅቱ በተፈጠረ ችግር ምክንያት ወደ ሣህል አልመጣም ወደደቢትም አልሄደም፡፡ ጋዜጠኛ ሃይላይ ሃድጎ ..ፅንዓት.. በሚለው መጽሐፍ ስለትጥቅ ትግሉ አጀማመር በጻፈበት ምዕራፍ የመለስን ስም ከጀማሪዎቹ አለማካተት ከበደው፤ ስለዚህ ባወጣ ያውጣው ብሎ ኤርትራ ሣህል ከሄዱት ጋር ቀላቅሎ ባልዋለበት አዋለው፡፡.. በማለት ይገልጻሉ፡፡
..እኔ እንዲህ ሆነናል ብዬ የመለስን ታሪክ አኮስሼ ላሳንሰው አልፈልግም፡፡ መለስ በህወሓት ትጥቅ ትግል ውስጥ ከጊዜ በኋላ የድርጅት አመራር ሆኖ እስከ ደርግ ውድቀት ድረስ ቀጥሏል፡፡ አሁንም በሥልጣን ላይ ነው፡፡ በእነዚህ ረጅም ጊዜያት ተጠቃሽ ሊሆኑ የሚችሉ ጠንካራ ጎኖች አሉት፡፡ መለስ ከሌላ ሰው ጋር ታሪክ የሚሻማበት ምክንያት አይታየኝም፤ የራሱ ታሪክ ይበቃዋል፡፡.. በማለት ጥቃቅን ታሪኮችን አዛብቶ በማቅረብ አቶ መለስን ከዚህ ታሪክ አኳያ ትዝብት ላይ ሊጥሏቸው የፈለጉበት ምክንያት ለአቶ አውዓሎም ሊገባቸው እንዳልቻለ ይገልጻሉ፡፡
ትግሉን ወታደራዊ ሥልጠና ከመውሰድ ለመጀመር የዩኒቨርስቲ ተማሪዎቹ በጥር ወር 1967 ዓ.ም ወደ ሣህል ማሰልጠኛ የሚወስዳቸውን ሰው ለመጠባበቅ ኤርትራ ተሰበሰቡ፤ በወቅቱ የኤርትራ ታጋዮች ማታ ማታ አስመራ እየገቡ፣ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር ተኩስ ይለዋወጡ ስለነበር አስመራ የተረበሸች ከተማ ሆና ነበር፡፡ ከጭንቀት በስተቀር ምግብ፣ ውሃ፣ መብራት በከተማዋ አልነበረም፡፡ በዚህ ሁኔታ ታጋዮቹን መጥተው ይወስዳሉ የተባሉት ሰዎች ሊመጡ አልቻሉም፡፡ ሰዎቹ ሲመጡ ያገኙት ሸዊትን እና ዋልታን ብቻ ስለነበር ጥር 18 እነሱን ብቻ ይዘው ይሄዳሉ፡፡ ሌሎቹ ጥር 28 ቀን እንደሚሄዱ መረጃ ስለደረሳቸው በቀጠሮው ቀን ከአቶ መለስ በስተቀር ሁሉም ይሰባሰባሉ፡፡
አቶ አውዓሎም ሁኔታውን ሲያስታውሱ፤ ..በወቅቱ ከእኛ ጋር ይሄድ የነበረውን መለስን በማጣታችን እኔና ከእኔ ጋር የነበሩት ጓዶች በፍርሃት ተውጠን ነበር፡፡ በወቅቱ በነበረው የደርግ አዋጅ በሕቡዕ ተደራጅቶ ለትጥቅ ትግል መውጣት ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ከባድ ስለነበር መለስ ታስሮ ይሆናል በሚል ስጋት ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ወደቅን፤ ቦታም ለመቀያየር ሞክረን ነበር፡፡ ለካ መለስ በዘመዶቹ የሕዝብ ማመላለሻ መኪና ተሳፍሮ አዲኳላ መንደፈራ ሄዷል፡፡..
አቶ አውአሎም እንደሚሉት የወጡት መጽሐፍቶች፣ ይህንን ታሪክ በተለያየ መንገድ አቅርበውታል፡፡ ..እኔ በጊዜው ተራ ታጋይ ነበርኩ፡፡ አመራር ላይ የነበሩት እነ አረጋዊ፣ አጋዚ ነበሩ በወቅቱም ገምግመውታል፡፡ መለስም፤ ..ከነበረው ጭንቀት እና ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ለአንድ አባል መፍትሄ መፈለግ ክፍት ስለነበር እዛ ቁጭ ብዬ ለአደጋ ከመጋለጥ ደደቢት ካሉት ጓዶች ጋር መቀላቀሉ የተሻለ ነው በሚል መነሻ ነው የሄድኩት ብሎ መልስ ሰጥቷል፡፡ በተደረገው ግምገማም የወሰደው እርምጃ እንደመፍትሄ ትክክል እንዳልነበረ ታምኖበት ትክክል ቢሆን እንኳን ለሌሎቹ ጓደኞቹ ተናግሮ መሄድ እንደሚገባው ሂስ ተሰጥቶበት ታልፏል፡፡ እሱ እንዳለው በወቅቱ ከእኛ ተለይቶ ደደቢት ባይገባም ዘግይቶም ቢሆን ተቀላቅሏል፡፡ እንግዲህ እንዲህ ያለውን በጣም ጥቂት እውነት እንኳን እያጣመሙ ነው የሚያቀርቡት፡፡.. ሲሉ ሐፊዎቹን አብዝተው ይተቻሉ፡፡
አቶ አውዓሎም በሌላ ምሳሌ ሲያስረዱም፤ ..መለስ እና የህወሓት የትጥቅ ትግል ታሪክ  በሚለው መጽሐፍ የማዕከላዊው ኮሚቴ ወኪል፤ ከ1968 ዲማ ከሚባለው ከመጀመሪያ ቀን ኮንፍረንስ ጀምሮ በ1969 እንደተጀመረ ተጠቅሶ ነው ተጻፈው፡፡ እኔን በጣም እየገረመኝ ያለው እንዲህ ያለ ታሪክ ሲጻፍ መለስ እንዴት ዝም አለ? የሚለው ነው፡፡ ጸሐፊው መለስን ሳያማክረው፣ ቃለምልልስ ሳያደርግለት፣ በጹሑፉ ላይ አስተያየት ሳይሰጥበት የተጻፈ ነው? አላውቅም፡፡ ፈረንጆቹ አንተን ስለሚመለከት ጉዳይ ተነግሮ ዝም ካልክ እንደተቀበልከው ይቆጠራል ይላሉ፡፡ እኔ ሁኔታውን ከዚህ አንጻር ለማየት ተገድጃለሁ ይላሉ፡፡
የል ዩንኒቨርስቲ ያሳተመውን  “The Ethiopian Revolution war the horn of Africa” በሚል ርእስ በኢትዮጵያ ስለተካሄደው የ30 ዓመት የእርስ በእርስ ጦርነቶች መሃፍ የጻፉት ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ፤ ጄምስ ማፈርሰን (Jams McPherson) የተባለ አሜሪካዊ የታሪክ ምሑር እና ጸሐፊ፤ ..በታሪክ እውነት የምትባል ነገር ብትኖር ኖሮ የታሪክ ምሑራን፣ የታሪክ ጸሐፊዎች፣ የታሪክ ተመራማሪያን ነገ የሚሠሩትን ያጡ ነበር.. በሚል የተናገረውን ጠቅሰው የታሪክ ተመራማሪያን እና ሐፊዎች ላይ በተለያየ ምክንያት በሚፈጠር ተጽዕኖ ትክክለኛ ታሪክን ለማግኘት እንደሚቸግር ይገልጻሉ፡፡
ፕሮፌሰር ገብሩ፤ ..የታሪክ ጸሐፊዎች ወይም ተመራማሪያን በጊዜ (Time) እና በቦታ (Space) ውስንነት የተነሳ፣ በኃይማኖት፣ በጾታ፣ በፖለቲካ እና በመሳሰሉት ነገሮች በሚፈጠርባቸው ተፅዕኖ ምክንያት ፍፁማዊ  ታሪክ ለማግኘት እንደሚያስቸግር ይገልጻሉ፡፡ ..የአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት ከተካሄደ 146 ዓመቱ ነው፡፡ እስካሁን ግን ታሪክ እየተጻፈ ነው፡፡ በእኛም ሀገር በምንም ዓይነት መንገድ ቢሆን ስለ ትጥቅ ትግሉ ታሪክ መጻፉ በራሱ ጥሩ ነገር ነው፡፡ ግርድፉን ከጥሬው እየለዩ የተጣራ እና የተሟላ ታሪክ ማቅረብ ለታሪክ ተመራማሪያን የቀረበ ድግስ ነው፡፡.. በማለት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡
የትጥቅ ትግል ባለታሪኮቹ በበኩላቸው በዚህ አይስማሙም፡፡ የሐፊው ፍላጎት እና ገለልተኝነት ካለ እውነት በማስረጃ እና በምርምር የሚደረስበት ሐቅ ነው፡፡ በመሆኑም ሐፊዎቹ ጥናቶችን በደንብ ካጠኑና መረጃ ከሰበሰቡ ታሪክን እንዳለ ለማስቀመጥ የሚጠበቅባቸው ሚዛናዊነት ብቻ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ የህወሓትን ትክክለኛ ታሪክ ለማስቀመጥ ገለልተኛ የሆነ ታሪክ ሐፊ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ፡፡

 

Read 6117 times Last modified on Saturday, 10 September 2011 12:03