Saturday, 10 September 2011 13:25

ቴዲ አፍሮ አዲስ አልበሙን ከሁለት ወራት በኋላ ይለቃል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

ታዋቂው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን /ቴዲ አፍሮ/ አዲስ አልበሙን ከሁለት ወራት በኋላ በመጪው ህዳር ወር እንደሚለቅ አስታወቀ፡፡የአንጋፋው ድምፃዊ ተፈራ ካሣ ልጅ የሆነው ድምፃዊ ግርማ ተፈራ ..እኔ አይደለሁማ.. የሚል ስያሜ የሰጠውን አዲስ አልበም ምረቃ አስመልክቶ ባለፈው ማክሰኞ በታምሩ ፕሮዳክሽን በጣይቱ ሆቴል ተዘጋጅቶ በነበረው የምረቃ ፕሮግራም ላይ ድምፃዊ ቴዲ አፍሮን፣ ንዋይ ደበበን፣ ሃና ሸንቁጤንና ዳዊት ፍሬውን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ታዋቂ ድምፃውያንና የጥበብ ሰዎች ተገኝተዋል፡፡በዚህ የምረቃ ፕሮግራም ምሽት ላይ ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ..አበባየህ ወይ.. የተሰኘ ተወዳጅ ዜማውን ለፕሮግራሙ ታዳሚዎች አቅርቧል፡፡

በዚህ ወቅትም አዲስ አልበሙን ከሁለት ወራት በኋላ ለአድማጭ እንደሚያደርስ በይፋ ተናግሯል፡፡ በጉጉት ሲጠበቅ የቆየውን አልበሙን የሚለቅበትን ትክክለኛ ቀን ከመናገር የተቆጠበው ቴዲ አፍሮ፤ በመጪው ህዳር አልበሙን እንደሚለቅ ይፋ አድርጓል፡፡
..የአባቱ ልጅ.. በሚል ተዘጋጅቶ በነበረው የአልበም ምረቃ ፕሮግራም ላይ ንዋይ ደበበና ሃና ሸንቁጤ ሥራዎቻቸውን ለታዳሚው አቅርበዋል፡፡ ዳዊት ፍሬው ኃይሉ አምባሰልና ትዝታን በመሣሪያ የተጫወተ ሲሆን ከአንጋፋ ድምፃውያን መካከል ባህታ ገብረሕይወት በመድረክ ላይ ተጫውቷል፡፡
የአዲስ አልበሞች ምረቃ በአሁኑ ወቅት እየተለመደ የመጣ ቢሆንም ይህ ምሽት ግን ከቀድሞዎቹ የተለየ ነው ያሉን አንድ የፕሮግራሙ ታዳሚ፤ ይኼ ሁሉ አንጋፋና ምርጥ ድምፃዊ በአንድ ምሽት ለአንድ ዓላማና የሙያ ባልደረባውን ለማበረታታትና ለማገዝ መሰብሰቡ በጣም አስገርሞኛል ብለዋል፡፡ የምረቃ ፕሮግራሙ አዘጋጅ ታምሩ ፕሮዳክሽን፤ ፕሮግራሙን በዚህ መልኩ በማዘጋጀቱና ታዋቂና አንጋፋ ድምፃውያን ተገኝተው ሥራዎቻቸውን ለማቅረብ እንዲችሉ በማድረጉ ሊመሰገን ይገባዋል ያሉት ታዳሚዎቹ፤ ምሽቱ ለሌሎች የምረቃ ፕሮግራሞች ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

 

Read 5009 times Last modified on Friday, 16 September 2011 06:18