Saturday, 01 December 2012 12:53

ዐጼ አምኅ ሥላሴ “የመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት” Featured

Written by  ባየህ ኃይሉ ተሠማ bayehalu@gmail.com
Rate this item
(2 votes)

በኢትዮጵያ የነገሥታት ታሪክ ውስጥ ዘውድ አሸናፊዎች በጉልበታቸው የሚቀዳጁት እንጂ ከወላጅ ወደ ልጅ የሚተላለፍ አልነበረም በቅርብ ጊዜ ታሪካችን ውስጥ ዳግማዊ ምኒልክ በሕይወት ሳሉ ወራሴ መንግሥታቸውን የሰየሙ ሲሆን ዐጼ ኃይለሥላሴ ደግሞ ዘውድ የሚወረስበትን ሥርዓትና ሕግ አበጅተው ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ ዐጼ ኃይለ ሥላሴ ወራሴ መንግስታቸውን ማንነት ያሳወቁት ዘውድ በደፉበት ዕለት ሲሆን አልጋ ወራሽ እንዲሆን የተመረጠውም ሐምሌ 20 ቀን 1908 ዓ.ም በሐረር ከተማ የተወለደው ልዑል አስፋ ወሰን የተባለው የመጀመሪያው ወንድ ልጃቸው ነበር፡፡

ጃንሆይ ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም ዘውድ ደፍተው “ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” በተባሉበት ሥነ ሥርዓት ላይ ልዑል አስፋ ወሰን ከዚህ በታች የሰፈረውን ቃለ መሐላ ፈጽመው “የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት አልጋ ወራሽ” ተባሉ፡፡ 
ሊቀ ጳጳሱ:- “ላባትህ ለንጉሠ ነገሥቱ፣ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ አገልጋይ ለመሆን
ትፈቅዳለህ?”
ልዑል አስፋ ወሰን:- አባትና እናትህን አክብር የተባለውን ትዕዛዝ ሰምቻለሁና በፍጹም ልቤ እገዛለሁ“
ሊቀ ጳጳሱ:-“እንደ አቤሴሎም ደፍረህ፣ እንደ አዶንያስ ቸኩለህ፤ ካባትህ ፈቃድ ለመውጣት፤ ያልተሠጠህን ለመሻት ከሚመክርህ ጋር እንዳትተባበርና እንዳትከተል አጥብቀህ ትጠነቀቃለህ?”
ልዑል አስፋ ወሰን:- “ካባቱ ፈቃድ የሚወጣ የተረገመና ሞት የሚገባው መሆኑን ሰምቻለሁና ይህን በመሠለው መንገድ አባቴን እንዳላስቀይም እጠነቀቃለሁ”
በጊዜው የ15 ዓመት ወጣት የነበሩት አልጋ ወራሽ፤ ጥር 14 ቀን 1923 ዓ.ም ለሸዋ መሳፍንት የሚሠጠውን መርዕድ አዝማች የተሰኘ ማዕረግ ተቀብለው የወሎ ጠቅላይ ገዢ ሆነው የተሾሙ ሲሆን ግንቦት 1 ቀን 1924 ዓ.ም ደግሞ ከወ/ሮ ወለተ እሥራኤል ሥዩም ጋር ጋብቻ ፈጽመዋል፡፡
አልጋ ወራሹ ባህላዊውን ትምህርት በመኖሪያ ቤታቸው፤ ዘመናዊውን ደግሞ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ በኢጣሊያ ወረራ ዘመን ከጃንሆይ ጋር በእንግሊዝ አገር በስደት በቆዩበት ጊዜ በሊቨርፑል ዩኒቨርስቲ ገብተው የሕዝብ አስተዳደር እና የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርትን አጥንተዋል፡፡
አልጋ ወራሹ በነጻነት ማግስት ወደ ቀደመው የወሎ ሹመታቸው ተመልሰው መኖሪያቸውን በደሴ እና በአዲስ አበባ ከተማ በማድረግ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡
በዚሁ ጊዜ አንዲት ሴት ልጅ ያፈሩበት የመጀመሪያ ትዳራቸውን አፍርሰው፣ ሚያዝያ 30 ቀን 1937 ዓ.ም ከልዕልት መድፈሪያሽ ወርቅ አበበ ጋር እስከ መጨረሻው የዘለቁበትን ጋብቻ መሥርተዋል፡፡
በታህሳስ ወር 1953 ዓ.ም አፄ ኃይለሥላሴ ብራዚልን በይፋ ለመጐብኘት ከአዲስ አበባ ሲነሱ አልጋ ወራሹ እንደወትሮው አልተከተሏቸውም ነበር፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ በጉብኝት ላይ እያሉ የክብር ዘበኛው አዛዥ ጀነራል መንግሥቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግሥት ባካሄዱበት ወቅት በዘዴ ካገቷቸው ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት መካከል አልጋ ወራሹ ቀዳሚው ነበሩ፡፡
በዚህ ጊዜ አልጋ ወራሹ የአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት መውደቁን የሚገልፅ አዋጅ በሬዲዮ ለሕዝብ አሰምተዋል፡፡ ከንግግራቸውም መካከል “…ለራሳቸው ጥቅም እና ለግል ሥልጣናቸው ብቻ የሚታገሉ፤ ለለውጥ እንቅፋት ሆነው እንደ ካንሰር የአሪቱን እድገት የጐተቱ ጥቂቶች ራስ ወዳዶች አሁን ከስልጣናቸው ተወግደዋል… እኔም ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅድልኝ መሰረት ደሞዝ ብቻ እየተቀበልኩ አገልግሎቴን እሰጣለሁ” የሚል ይገኝበታል፡፡
መፈንቅለ መንግሥቱ በእንጭጩ የተቀጨ ቢሆንም ጦሱ ግን በንጉሡና በአልጋ ወራሹ ግንኙነት ላይ መጥፎ አሻራውን ጥሎ አልፏል፡፡ ምንም እንኳ አልጋ ወራሹ መንግሥት የመለወጡን ዜና ያነበቡት በጠመንጃ አፈሙዝ ተገደው ነው ቢባልም ድርጊቱ ግን ጉብኝታቸውን አቋርጠው የተመለሱት አፄ ኃይለሥላሴን ማስቆጣቱ አልቀረም፡፡ በጃንሆይ አስተያየት፣ አልጋ ወራሹ ከ30 አመት በፊት ለዘውዱና ለአባታቸው ለመታመን የገቡትን ቃልኪዳን ከአማፂዎቹ ጋር በመተባበር አፍርሰዋል፡፡
ከዚህ ጊዜ በኋላ በአልጋ ወራሹ ሕይወት ውስጥ አቢይ ክስተት የተፈጠረው ከ12 ዓመት በኋላ ነበር፡፡
ጥር 19 ቀን 1965 ዓ.ም አልጋ ወራሹ በደብረ ዘይት ከተማ በእረፍት ላይ እያሉ የደም ግፊት ሕመም በሚያስከትለው “ስትሮክ” ሳቢያ በድንገት ታመሙ፡፡
የጤና መቃወሱ እንደደረሰባቸው በእንግሊዝ የአየር ኃይል አውሮፕላን ለአስቸኳይ ሕክምና ወደ ስዊዘርላንድ የተወሰዱ ቢሆንም ህመሙ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ስለነበር ግማሽ አካላቸውን ሽባ በማድረግ የተሽከርካሪ ወንበር ቁራኛ ሊያደርጋቸው ችሏል፡፡
አልጋ ወራሹ ለሕክምና ወደ ስዊዘርላንድ ከተጓዙ ከአንድ አመት በኋላ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በሕዝባዊ ተቃውሞ እና በኢኮኖሚ ቀውስ ይናጥ ጀመር፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሰ ነገሥቱ ሶስት ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ለመቀያየር የተገደዱ ሲሆን የአልጋ ወራሹ ብቸኛ ወንድ ልጅ የሆነውን ልዑል ዘርዓ ያዕቆብ አስፋ ወሰን ተጠባባቂ አልጋ ወራሽ መባሉን አውጀዋል፡፡
ደርግ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱን ከዙፋናቸው አውርዶ አዲስ መንግሥት መቋቋሙን ሲያውጅ፤ አልጋ ወራሹ በአገሪቱ ፖለቲካና አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ የማይገባ ንጉሥ ይሆናል፤ ሥርዓተ ንግሱም አልጋ ወራሹ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ይፈፀማል አለ፡፡
የአልጋ ወራሹ ግዛት በነበረው በወሎ የደረሰው የረሐብ አደጋ ለዘውድ መንግሥት ውድቀት መንስኤ ከሆኑት ችግሮች መካከል አንዱ እንደነበር ይታወቃል፡፡
በዚህ የተነሳ ደርጉ በጠቅላይ ግዛቱ የአልጋ ወራሹ እንደራሴ የነበሩትን ደጃዝማች ሰሎሞን አብርሐምንና ሌሎች የወሎ ሹማምንት ሰብስቦ አስሯል፡፡ አልጋ ወራሹ በዚህ ጊዜ በኢትዮጵያ ቢገኙ ኖሮ ከታሳሪዎቹ ቀዳሚው እንደሚሆኑ እየታወቀ ደርግ አልጋ ወራሽን አነግሳለሁ ማለቱ “ይምጡና ልሰርዎት” ከማለት የማይለይ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ መስከረም 14 ቀን 1967 ዓ.ም የታተመው “ታይም” ጋዜጣ የአልጋ ወራሹ እንደራሴ በስዊዘርላንድ ለጋዜጠኞች የሰጡትን መግለጫ ጠቅሶ “አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ለመንገሥ ይፈልጋሉ” የሚል ዜና ይዞ ወጣ፡፡ ጋዜጣው አልጋ ወራሹ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስና በአባታቸው ዙፋን ለመቀመጥ ያላቸውን ፍላጐት ለአዲሱ የኢትዮጵያ መንግሥት ማስታወቃቸውንም ጨምሮ ገልጦ ነበር፡፡
የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት አማካሪ ሆነው ለረጅም ጊዜ ያገለገሉት ጆን ስፔንሰር፤ አልጋወራሹን በቅርብ ከሚያውቋቸው ሰዎች አንዱ ናቸው፡፡ ጃንሆይ በ1949 ዓ.ም በአደጋ ያለፉትን ልዑል መኮንን ከአልጋ ወራሹ አስበልጠው መውደዳቸው የሚደንቅ አይደለም በማለት አስፋ ወሰን የሚታወቁት በወላዋይነት ነበር ይላሉ፡፡
ስፔንሰር በአስተያየታቸው “ካወቅኋቸው የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ሁሉ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የፀና አቋም ለመያዝ ዳተኝነት ያየሁበት አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰንን ነበር… አሽከሮቹ የእሱን ደካማነት ተገን አድርገው የግል ሐብት ያግበሰብሳሉ፡፡ ደካማነቱን በመተማመን ነበር የ1953 እና የ1967 ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥቶች በአባቱ እግር ተተክቶ ዙፋኑን እንዲወርስ ሃሳብ ያቀረቡት” ብለው ነበር፡፡
ጃንሆይ ከሥልጣን ከወረዱ ወዲህ ባለው ጊዜ፣ አልጋ ወራሹ ኑሯቸውን ከጀኔቭ ወደ ለንደን አድርገው፣ የስደተኝነት ህይወትን በእንግሊዝ ሲገፉ የቆዩ ሲሆን ከንጉሳዊ ቤተሰቡ አምባ ለ13 አመታት ያህል አዲስ ዜና ሳይሰማ ቆይቷል፡፡
ከአንድም ሁለት ጊዜ አማፅያን ዙፋን እንደሚወርሱ ቃል እየገቡላቸው ዘውድ አልጨበጥ ያላቸው አልጋ ወራሽ፤ በስደት ባሉበት አገር “ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” ተብለው መንገሳቸው ተሰማ፡፡ መጋቢት 28 ቀን 1980 ዓ.ም በተካሄደው ሥርዓተ ንግሥ ላይ ስመ መንግሥታቸው “አፄ አምኃ ሥላሴ” የተባለ ቢሆን “ንጉሡ” ለባለቤታቸው የ”እቴጌነት”፣ ለልጃቸው ለልዑል ዘርዓ ያዕቆብ ደግሞ የ”አልጋ ወራሽነት” ማዕረግ መስጠታቸው ታውቋል፡፡
በ1981 ዓ.ም አዲሱ “ንጉሠ ነገሥት”ና ቤተሰባቸው መኖሪያቸውን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ አዘዋውረዋል፡፡ የደርጉ መንግሥት ከወደቀ በኋላም በሀገር ቤት “ሞአ አንበሳ” የተሰኘ አፍቃሪ ዘውድ ድርጅት ተመስርቶ፣ አልጋ ወራሹን በዙፋን ላይ ማስቀመጥን አላማው አድርጐ ጥርጊያውን ሲያቀና ቆይቷል፡፡
አልጋ ወራሹ ከአባታቸው ከስልጣን መውረድ በኋላ ያሳዩት ድርጊት ከላይ በስፔንሰር ከተገለፀው አስተያየት ጋር የሚቃረን አይደለም፡፡ ከደርግ ጋር ለመስራት መሞከራቸው፤ እንዲሁም በስደት አገር ያውም የተሽከርካሪ ወንበር ቁራኛ ሆነው “መንገሳቸው” ለዘመናት የቆየ የስልጣን ፍቅር እንደጠናወታቸው የሚያሳይ ሳይሆን አይቀርም፡፡
ወራሴ መንግሥት የሆነ አንድ መስፍን የሚያስፈልገው ብልሃት፣ አርቆ አስተዋይነትና ቆራጥነት ከጐደሉት ያለመውን ለመፈፀም የሚያስችለውን ጉልበት አያገኝም፡፡ በዚህ ረገድ አፄ ኃይለ ሥላሴ ለአልጋ ወራሽነት የመረጡት ልጃቸው እነዚህን ፀጋዎች እንዳልታደለ ያለፉ ታሪኮቹ ግልፅ ምስክሮች ናቸው፡፡
አፄ ኃይለሥላሴ ወደ ስልጣን የመጡበት መንገድ ውስብስብና እንቅፋት የበዛበት አቀበት ነበር፡፡ ወጣትነት ሳያሸንፋቸው በዘዴ እና እርጋታ፣ ደግሞም በእርግጠኝነት እየተጓዙ በመጨረሻ ያሰቡበት ለመድረስ ችለዋል፡፡ ልዑል አስፋ ወሰን ግን በተደላደለ መሰረት ላይ ሆነው በአስተዳደርም ሆነ በአመራር ልቀው በመታየት እውነተኛ አልጋ ወራሽ መሆን ተስኗቸው የዘውድ ስርአት ከጃንሆይ በኋላ ግብአተ መሬቱ ተፈፅሟል፡፡
በመጨረሻም የአንድ ወንድ እና የሶስት ሴት ልጆች አባት የነበሩት ልዑል መርዕድ አዝማች አልጋ ወራሽ በተወለዱ በ81 አመታቸው ጥር 9 ቀን 1989 ዓ.ም በዩናይትድ ስቴትስ አርፈው የቀብራቸው ሥነ ሥርዓት እዚህ አዲስ አበባ በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡

 

Read 16441 times Last modified on Saturday, 01 December 2012 12:57