Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 01 December 2012 13:19

ምርጫውን fun ማድረግ አይቻልም?

Written by 
Rate this item
(6 votes)

አንድ የአሜሪካ ፖለቲከኛ በምርጫ ተወዳድሮ ውጤት እየተጠባበቀ ነው - የምርጫ ዘመቻ ዋና ማዘዣ ቢሮው ውስጥ ተቀምጦ፡፡ በዚህች ቅፅበት የሚያስበው አንድ ጉዳይ ብቻ ነበር -ምርጫውን አሸንፍ ይሆን ወይስ በተፎካካሪዬ እረታ ይሆን ? በቃ ለጊዜው እቺው ብቻ ነበረች ሃሳቡ (ከስልጣን ሌላ ምን ያስብ?) በዚህ የሃሳብ ማዕበል እየተናጠ ሳለ ነው ድንገት የቢሮው ስልክ ያንቃጨለው፡፡ ፖለቲከኛው በፍርሃት እየራደ ስልኩን አነሳና “ሃሎ” አለ፡፡ (እንዴ … ለምን አይርድ?) ምርጫውን “ተሸንፈሃል” ከተባለ እኮ አለቀለት- ሥልጣን ሱሚ ናት፡፡ ደግነቱ ግን ቀናው(ቺርስ!) ስልኩን ዘግቶ ብቻውን እንደ ህፃን ልጅ ቦረቀ (ስልጣን እኮ ዳግም መወለድ ነው!) ለአፍታ ያህል ደስታውን ለብቻው ካጣጣመ በኋላ እንደገና ወደ ስልኩ አመራ፡፡

የመጀመሪያውን ስልክ የመታው ለሚወዳቸውና ለሚወዱት እናቱ ነው፡፡ “ሃሎ … እማማ” በደስታ እየተፍለቀለቀ ነው የሚያወራው፡፡ “እማማ…ውጤቱ ደረሰ እኮ … ምርጫውን አሸነፍኩ!” አለ እየተቁነጠነጠ፡፡ እናቱም- “የእውነት?!” ሲሉ ጠየቁት- በጥርጣሬ በታጀለ ድምፅ፡፡ በደስታ በርቶ የነበረው የፖለቲከኛው ፊት ከመቅፅበት ጨፈገገ “እማማ ደግሞ--- በዚህ ሰዓት የእውነት ተብሎ ይጠየቃል?” በማለት ስልኩን ጆሮአቸው ላይ ጠረቀመባቸው፡፡ ፈፅሞ እናቱ ሳይሆኑ የምርጫ ተፎካካሪው ነው የመሰሉት፡፡ እናም በዚያች ቅፅበት ጠላቸው፡፡ አያችሁልኝ-- እናት ልጃቸውን አላመኑትም ማለት ነው (ያጭበረብራል ብለው ሰግተው ይሆን?) ፖለቲከኛ ልጃቸውስ ለምን ተናደደባቸው? አሁን “የእውነት?” ማለት ምኑ ያናድዳል! (ምን ያለበት ዝላይ አይችልም አሉ!) 
እኔ የምለው--- እስቲ ከዚህ ቀልድ ምን ተማራችሁ ብትባሉ ምን ትላላችሁ? እኔ የተማርኩት ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎች በመጪው የአዲስ አበባና የአካባቢ ምርጫ “ምርጫውን አሸነፍን እኮ!” ካሉ “የእውነት?” የሚል በጥርጣሬ የተሞላ ጥያቄ ፈፅሞ አላቀርብም፡፡ ይልቁንም “እንኳን ደስ ያላችሁ-ኮንግራ!-ቺርስ!ቪቫ!” በማለት ማሸነፋቸውን በፀጋ እቀበልላቸዋለሁ (ቢያሸንፉም ባያሸንፉም!) ከምሬ እኮ ነው … ሺ ጊዜ “ተጭበርብሯል” ብላችሁ ብትጠረጥሩም ዋጋ ስለሌለው ለምን ትዝብት ላይ ትወድቃላችሁ (ትርፉ ቂም ማትረፍ ነው!)
የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት በኒውዮርክ እምብርት ላይ ከሚገኝ አንድ የታወቀ ባር ውስጥ ተሰባስበው ይገባሉ (ጉዳቸውን አላወቁ!) ወዲያው የባሩ ባለቤት ይሄድና “ምን ፈለጋችሁ?” ይላቸዋል፡፡ “ውሃ ጠምቶን ነው--- ቀዝቃዛ ቢራ አምጣልን ባክህ--- ሁለት ሁለት አድርገው” ሲሉ ያዙታል፡፡
ባለቤቱ የፈለጉትን ሁሉ አዝዘው እስኪጨርሱ ይጠብቅና “አዝናለሁ--- ሪፐብሊካንን አላስተናግድም” ይላቸዋል- የዲሞክራቶች ደጋፊነቱን በሚጠቁም አስተያየት፡፡ አልተከራከሩም፡፡ ሊሄዱ ሲነሱ ግን “እኛም አናስተናግድህም” አሉት የባሩን ባለቤት፡፡ አያችሁ--- ይሄው ነው ከፖለቲከኛ ጋር መቀያየም ትርፉ!
እንግዲህ ከዚህ ቀደም ፖለቲክስ የሚለው ቃል “ደርቲ ጌም” ከሚለው ጋር ተያይዞ ነበር የማውቀው፡፡ ሰሞኑን ግን ትንሽ ከዚያም ገፋ ያደረገ ብያኔ እንደተሰጠው ሰማሁ፡፡ Politics የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል በላቲን ትርጉሙ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? Poli “ብዙ” ማለት ሲሆን tics ደግሞ “ደም መጣጭ ፍጡራን” ማለት ነው ይላል አንድ መረጃ (በአንድ ላይ ሲጣመር ብዙ ደም መጣጭ ፍጡራን እንደማለት ነው!) እኔ እንግዲህ ምን ላድርግ … የቋንቋው ባለቤቶች ናቸው እንዲህ ያሉት፡፡ ክፋቱ ደግሞ Politics የሚለው ቃል የአማርኛ አቻ ፍቺ የለውም፡፡ ስለዚህ ይሄንኑ ቃል ከእነፍቺው ልንጠቀምበት እንገደዳለን ማለት ነው (What a pity!)
አሁን እንግዲህ ወደ ራሳችን ፖለቲካና ምርጫ እንግባ-- (የሰው ቤት ያመሻሹበታል እንጂ አያድሩበትም አሉ) ገና ስድስት ወር ለሚቀረው የአዲስ አበባ አስተዳደር ምርጫ ካለፈው የጥቅምት ወር አንስቶ ውዝግብ መጀመሩ ያሳዝናልም ያስገርማልም (አይ እቺ አገር!) ምናልባት የኢህአዴግም ሆነ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች “መነጋገር እኮ ህገመንግስታዊ መብታችን ነው” ሲሉ ሊወቅሱኝ ይችላሉ (ከእነሱ ብሶ!) እኔ የምለው--- “መነጋገር” እንዲህ ነው እንዴ? “አምባገነን ነው!-- አናምነውም!-- አንደራደርም!-- ሰላም አደፍራሾች ናቸው!--ወዘተ” እንዲህ ያለ “መነጋገር” የት ነው የተማሩት? (የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ተቀጥተው አላደጉም እንዴ?) እሺ ታዲያ ምን ልበል ---በሁለቱም ጎራ ያሉት እኮ ካለመሰዳደብ ሌላ አያውቁም፡፡ በዚያ ላይ “አስታራቂ” ቢመጣ “ሽማግሌ” ፈፅሞ እሺ አይሉም (እኔን ካላመናችሁ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅን ጠይቋቸው!)
ምናልባት ውዝግቡ ገና መጀመሩ ስለሆነ (ስድቡ አልተሟሟቀማ!) ትንሽ ያጋነንኩት ሊመስላችሁ ይችላል፡፡
ወዳጆቼ --የጦቢያን ፖለቲከኞች አታውቋቸውም እንዴ? ከ0 ድግሪ ሴንቲ ግሬድ ተነስተው በአስደናቂ ፍጥነት እኮ ነው 100ድግሪ ሴንቲግሬድ ላይ ቂብ የሚሉት! (አሁን ሰላም ናቸው ብላችሁ ዞር ስትሉ እነሱ ልጄ ለድብድብ ሸሚዛቸውን ጠቅልለዋል) ወዲያው ሁሉ ነገር ቀውጢ ይሆናል (እሳት አደጋ የማያጠፋው እሳት ታውቃላችሁ?) በቃ እሱን ነው አገሪቱ ላይ የሚለቁት --- (የጎዳና ላይ ነውጥ፣ እስር ፣ወከባ፣ ስደት፣ ሞት፣ ብቻ ምን ልበላችሁ--- ምርጫ አሉታዊ ግሳንግሶቹን ይዞ ከተፍ ይላል) ያለፈውን የአሜሪካ ምርጫ በዲኤስቲቪ ኮምኩማችሁ “ምርጫ እኮ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ መብቱን “ኤክሰርሳይስ” የሚያደርግበት የስልጣኔ ምልክት ነው” እንዳትሉኝና እንዳታስገርሙኝ---- (ነገሩ እኮ ልክ ናችሁ)-- የምርጫ ዓላማው እሱ ነበር፡፡ ችግሩ ግን የጦቢያ ፖለቲከኞች የራሳቸው የምርጫ “ዴፊኒሽን” አላቸው፡፡ ለዚህ ነው ፖለቲከኞች የሚሉትን ትታችሁ ምርጫ ሲደርስ ጠንቀቅ በሉ የምለው፡፡ አቅም ስለሌለን ነው እንጂ አሜሪካውያን “ሱናሚ” ወይም “ሳንዲ” የተባለው የተፈጥሮ አደጋ ሊመጣ ነው ሲባሉ የሚገቡበት ዓይነት ምሽግ ያስፈልገን ነበር - ልክ ምርጫ ሲጀመር የምንሸሸግበት፡፡ ከዚያ ውጤት ተነግሮ ሁሉም “አንዲትም እናት በወሊድ አትሞትም!” የሚለው የጤና ጥበቃ መፈክር በጣም ነው የሚመቸኝ፡፡ የዚህ ተመሳሳዩ ለምርጫ ቦርድም ሳያስፈልገው አይቀርም፡፡ የቦርዱ መፈክር ምን መሆን አለበት መሰላችሁ--- “በምርጫ አንድም ዜጋ አይሞትም! አይታሰርም! አይሰደድም! አይዋከብም!” የሚል፡፡ ታዲያ መፈክር አውጥቶ ዝም ማለት አይደለም፡፡ መፈክሩን ወደ ተግባር መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ካልተወጣ ምርጫ ቦርድን ፍ/ቤት እናቆመዋለን፡፡ (ተጠያቂነት ማለት ይሄ እኮ ነው)
እንዴ--- ምርጫ በመጣ ቁጥርማ አንሸወድም፡፡ እስቲ በ97 የተሰራነውን ጉድ ወደ ኋላ መለስ ብላችሁ አስታውሱት፡፡ ለዓለም ምሳሌ የሚሆን “ነፃና እንከን የለሽ ምርጫ” ይካሄዳል ሲሉን አመናቸው፡፡ በሬዲዮና በቲቪ ዱላ ቀረሽ ክርክር ሲያደርጉ “እውነትም ዲሞክራሲ!” ብለን ተደመምን፡፡ ከዛስ? ከዛ በኋላ ያለውን ማስታወስ አልፈልግም (ትራጄዲ ነው!) በእርግጥ ያንን ትራጄዲ አሳምረው የፃፉ ፖለቲከኛ ፀሃፍት ተፈጥረዋል፡፡ ምፀቱ ግን ምን መሰላችሁ--- የትራጄዲው ፈጣሪዎች ራሳቸው-- ዘጋቢዎችም ራሳቸው መሆናቸው ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ባሉት ምርጫዎች ግን ይሄን እድል ልንሰጣቸው አይገባም ባይ ነኝ፡፡ ወቸ ጉድ! ራሳቸው ለሰሩት የፖለቲካ ፊልም ራሳቸው ሃያሲ ሆነውላችሁ ቁጭ አሉ፡፡
እንግዲህ ወዳጆቼ --- ዓላማዬ ባለፈ ምርጫ አዲስ ውዝግብ ለማንሳት አይደለም (የእነሱ ቢጤማ አልሆንም!) ግን የሰሩንን እንዳይረሱ ለማስታወስ ነው--- እናም ገና ትንሽ የውዝግብ ፍንጭ ስንሰማ አደብ ልናሲዛቸው ይገባል “ስርዓት ያዙ-- በወጉ ተነጋግራችሁ ችግራችሁን ትፈቱ እንደሆነ ፍቱ--- ያለዚያ ምርጫው ይቀራል እንጂ አገርና ህዝብ አይበጠበጥም!” ለማለት መድፈር የግድ ነው (ለደህንነታችን ስንል) እንዴ--- በራሳችን ስልጣን እኛኑ ይቀውጡናል እንዴ? (ፌር አይደለም!) ይሄውላችሁ --- የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ተቆንጥጠው አለማደጋቸውን በተደጋጋሚ አሳይተውናል፡፡ ቱባ ቱባዎቹ የሁለቱም ጎራ ፖለቲከኞች እድሜያቸው እየገፋ ስለሆነ ከአንድ ምርጫ በኋላ እንገላገላቸዋለን ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ እኔ የምፈራው ግን ምን መሰላችሁ? ለአዲሱ ትውልድ ክፉ ባህርያቸውን አስረክበውት እንዳይሄዱና የፖለቲካው አዙሪት እንዳይቀጥል ነው (መተካካት ቀለጠች!)
ይሄውላችሁ --- ምርጫ የሚካሄደው እኮ ህይወትና ንብረትን ለማጥፋትና ለማውደም አይደለም-- ህይወትን ለማበልፀግና ከፍ ከፍ ለማድረግ ነው-- ወደ ላይ ለማደግ እንጂ ወደ ስር ለመግባት አይደለም-- 10 ዓመት ወደፊት ተጉዙ 20 ዓመት ወደ ኋላ ለመመለስም አይደለም፡፡ እኔ የምለው--- ስንት ህግና ደንብ “በዲሞክራሲ የዳበረ ልምድ ካላቸው አገራት” ሲቀዳ እንዴት ስለ“ምርጫ ” ከእኒህ አገራት ሳይኮረጅ ቀረ?
ይሄን ሁሉ የምለው ለምን መሰላችሁ ---የአገሬ ፓርቲዎች ካለፈ ስህተታቸው እንደማይማሩ ስላወቅሁኝ ነው (በአስማት እኮ አይደለም!) ምናልባት ሽንፈት ይመስላቸዋል ልበል? ወይም ደግሞ ከነአካቴው መማር አይፈልጉ ይሆናል (“ካሁን በኋላ ተምረን ምን ልናመጣ?” በሚል ተስፋ መቁረጥ እንዳይሆን ብቻ) ይሄውላችሁ ---ፖለቲከኞቹ ሲወዛገቡ ራሳቸውን ችለው ቢሆን ኖሮ-- “ኢግኖር” አድርገናቸው ከተለመደው ኑሮአችን ጋር እንታገል ነበር፡፡ ግን ራሳቸውን ችለው አይወዛገቡም፡፡ በግድ የራሳቸው ጣጣ ውስጥ ይዶሉናል-“ለህዝባችን ብለን” በሚል ማምታቻ፡፡ “ለስልጣናችን ብለን” አይሉም እንዴ--(እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር አሉ) ቆይ እነሱ ስልጣን ለሚይዙት እኛን ለምን ያንገላቱናል? ምርጫ በመጣ ቁጥር ብርድና ውርጩን ተቋቁመን የምንመርጠው አነሰን እንዴ? እውነቴን እኮ ነው ---አሁንስ የፖለቲከኞች ነገር አንገሽግሾናል! በቃ---በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጭቅጭቅና ንትርክ የምንሸከምበት እንጥፍጣፊ አቅም እንኳ የለንም፡፡ እንዴ--- የኑሮ ውድነትና ግሽበት ትከሻችንን አድቆታል እኮ፡፡ እናም “እዛው በጠበላችሁ!” እንላቸዋለን፡፡
እኔ የምለው --- እንደው ግን መቼ ነው እዚች አገር ላይ ውዝግብ የሌለበት አሪፍ ምርጫ የምናየው? ምን እንደናፈቀኝ ታውቃላችሁ---ምርጫ በሰላም፣ ምርጫ በመተማመን፣ ምርጫ በነፃነት--- ምርጫ ያለጥላቻ፣ ምርጫ ያለስጋት፣ ምርጫ ያለተፅዕኖ፣ ምርጫ ያለጉልበት፣ ምርጫ ያለማጭበርበር ---መቼ ነው እውን የሚሆነው? ግዴለም ትክክለኛ ቀኑ ተቆርጦ ይነገረንና በትእግስት እንጠብቃለን (ሰባት ዓመት ማየት የተሳነው አንድ ሰው “ነገ ዓይንህ ይበራልሃል” ቢባል “ዛሬን እንዴት አድሬ” አለ አሉ) እኔ የምለው ግን በቃ ምርጫን fun ማድረግ የሚቻልበት “መካኒዝም” የለም እንዴ? እንደአሜሪካ ምርጫ አጓጊ ማድረግ አንችልም? በቃ የሚያዝናና! የሚያስደስት! የሚያጫውት! (የኛ እኮ የትጥቅ ትግል መሰለ!) ለምን መሰላችሁ? እየተዝናናን እንድንመርጥ ነዋ! ፖለቲከኞቹም ተዝናንተው እንዲመረጡ! (የምርጫ ወቅት ስጋትና ውጥረትን ተረት ለማድረግ ስፖንሰር እያፈላለግሁ ነው!)
እስቲ አስቡት--- ምርጫ የምትለዋ ቃል ስትሰማ ምንድነው ወደ አዕምሮአችን የሚመጣው? ፍርሃት-- ስጋት--ውጥረት--ውዝግብ---ጭቅጭቅ---ንትርክ---መፈራረጅ---መጠላለፍ---መወቃቀስ---መካሰስ---በቃ ይሄው ብቻ ነው (ታሪክ አይካድ!) ይሄውላችሁ እኔና እናንተ የፈለገውን ያህል ብንወተውት የሚሰማን የለም፡፡ ለምን መሰላችሁ --- ፓርቲዎቹ የውዝግብ አባዜ ተጠናውቷቸዋል፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ --- አሁን በአንዳች ተዓምር ሁሉ ነገር ተስተካክሎ ውዝግብ የሌለበት ምርጫ ይካሄድ ቢባል ምን እንደሚፈጠር ታውቃላችሁ? በቃ ፓርቲዎቹ ሁሉ ምርጫው ይደብራቸዋል --- እናም ተራ በተራ ራሳቸውን ከምርጫው ያገላሉ (ራሱ ገዢው ፓርቲ ሳይቀር!) ከዛ እኛ ብቻ እንቀራለን - (መራጮች ብቻ! )
እኔ የምላችሁ ----የዘንድሮ ምርጫ በግንቦት ወር ነው አይደል? ለምን ፓርቲዎቹን አንቀድማቸውም! በምን መሰላችሁ--- በፀሎትና በምህላ! አያችሁ እነሱ አሁን ውዝግቡን ለማጧጧፍና ለማክረር እየተንደረደሩ አይደል-- እኛ ቀድመን “ከምርጫ ጣጣና ውጥረት ጠብቀን--ለጦቢያ ፖለቲከኞች ማስተዋያ ልቦና ስጥልን” እያልን ከልባችን ከፀለይንና ምህላ ከያዝን ማሸነፋችን አይቀርም - በቃ አደብ ይገዙልናል--- እንደውም ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች ለምርጫ ቅስቀሳ ቁሳቁስ እየተዋዋሱ “አንተ ትብስ-- አንተ ትብስ” በመባባል በጦቢያ ታሪክ የመጀመርያውን ሰላማዊ ምርጫ ሊያካሂዱ ይችላሉ! ግን ከቀደምናቸው ብቻ ነው- ከቀደሙን አለቀልን!
ፖለቲካዊ ወጋችንን በቀልድ እንደከፈትነው በቀልድ ብንዘጋውስ …
የአሜሪካ አቃቤ ህግ ጆን አሽክሮፍት በአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ ጉብኝት እያደረጉ ነው፡፡ ለ15 ደቂቃ ያህል ለተማሪዎች ንግግር ካደረጉ በኋላ “አሁን ጥያቄ ካላችሁ መጠየቅ ትችላላችሁ” አሉ፡፡ ቦቢ የተባለው ጩጬ ተማሪ ተነሳና “ሦስት ጥያቄዎች አሉኝ” በማለት ጀመረ፡፡ አሽክሮፍት በመገረም እያዩት እንዲቀጥል ፈቀዱለት “1ኛ- እንዴት ቡሽ ከአልጐር ባነሰ ድምፅ አሸነፉ? 2- ለምንድነው የፀረ-ሽብርተኝነት ህጉን የሲቪል ነፃነትን ለመገደብ የምትጠቀሙበት? 3ኛ- በኢራቅ አለ ተብሎ የነበረው ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ የት ገባ?” ይሄኔ ደወል ተደወለና ተማሪዎቹ ለእረፍት እየተጯጯሁ ከክፍሉ ወጡ፡፡ ከእረፍት መልስ ሚ/ር አሽክሮፍት “ቅድም ውይይታችን ስለተቋረጠ አዝናለሁ፤ አሁን የፈለጋችሁትን ልትጠይቁኝ ትችላላችሁ” አሉ፡፡ ጁሊ የተባለች ትንሽ ልጅ ተነሳችና “አምስት ጥያቄዎች አሉኝ” ስትል ተናገረች - በጣፋጭ አንደበቷ፡፡ ቀጥይ አሏት - አቃቤ ህጉ፡፡ “1- እንዴት ቡሽ ከአልጐር ባነሰ ድምፅ አሸነፉ? 2- ለምንድነው የፀረሽብርተኝነት ህጉን የሲቪል ነፃነትን ለመገደብ የምትጠቀሙበት? 3- በኢራቅ አለ ተብሎ የነበረው ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ የት ገባ? 4- ለምን የእረፍት ሰዓት 20 ደቂቃ ቀደም ብሎ ተደወለ? 5- ቦቢ የት ገባ?”

 

Read 4716 times Last modified on Saturday, 01 December 2012 13:26

Latest from