Saturday, 01 December 2012 14:49

...ፍቺ የሚያሻቸው እንቆቅልሾች...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

• ( EDHS 2005 ..እንዳወጣው መረጃ 65 % የሚሆኑ ሴቶችና 16 % የሆኑ ወንዶች ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ከ18/ አመት እድሜያቸው በፊት የወሲብ ግንኙነት እንደፈጸሙ ተናግረዋል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኤችአይቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ቢሮ (Hapco ኘ2010..መረጃ ከሆነ በብሄራዊ ደረጃ የቫይረሱ ስርጭት 2.2-2.3ኀ ይደርስ ነበር፡፡ EDHS-Ethiopian demographic health survey -2005 - እንደገለጸው ደግሞ በኢትዮጵያ በወንዶችና በሴቶች በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈጸመው ልቅ የሆነ የግብረስጋ ግንኙነት አብዛኛውን የተመዘገበው በከተሞች ነው፡፡ ከዚህም መካከል በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ተቋሞች የሚገኙ ተማሪዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት የአዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን እና ሌሎችንም የትምህርት ተቋማት ማእከል ያደረገ ጥናት ተደርጎ ነበር፡፡ ይህንን ጥናት በሚመለከት ከአዋሳ ዩኑኒቨርሲቲ ዶ/ር ይፍሩ ብርሀኑ መረጃውን እንዲያካፍሉን ጋብዘናቸዋል፡፡ ዶ/ር ይፍሩ ብርሀኑ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡

ኢሶግ/ የኤችአይቪ ቫይረስን ስርጭት በሚመለከት የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለጥናት መነሻ የሆነው በምን ምክንያት ነው? 
ዶ/ር እንደውጭው አቆጣጠር በ2008 እና 2009 በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎቹ ባህርይ አስቸጋሪ ነው...ልቅ የወሲብ ግንኙነት ያደርጋሉ...የተማሪዎቹ ባህርይ ከሌላው ህብረተሰብ የተለየ ነው በሚል ብዙ ወሬ ይሰማ ነበር፡፡ ተማሪዎቹ ከተለያዩ የንግድ ሰዎች እንዲሁም ከቱሪስቶች እና እርስ በእርሳቸውም የሚፈጽሙት የግብረስጋ ግንኙነት ይበልጥ ለኤችአይቪ እንደሚያጋልጣቸው ጭምር በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ሳይቀር በሬድዮና ጋዜጣ ይዘገብ ነበር፡፡ ይህ መረጃ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ጥያቄ ከማስነሳቱም ባሻገር ኤችአይቪ የያዛቸው ተማሪዎች ቁጥርም ከሌላው ህብረተሰብ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ነው የሚል አዝማሚያ እየያዘ መምጣቱ እውነት ነው ወይንስ ? የሚለው ነገር ምላሽ ይፈልግ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት ትክክለኛውን ምላሽ ለማግኘት ጥናት ማድረግ አስፈላጊ ስለነበር በሁሉም የሀዋሳ ዩኒቨርሲት ካምፓሶች እና ሁኔታውን ለማወዳደርና እውነታውን ለማግኘት በተጨማሪም በጎንደር፣ በጅማ ፣በመቀሌ ፣አሮማያ ባሉት ዩኒቨርሲቲዎችም ጭምር ጥናቱ እንዲካሄድ ተደርጎአል፡፡
ኢሶግ/ ጥናቱ የተካሄደው በወሲባዊ ባህርይ ብቻ ነው ?
ዶ/ር ጥናቱ የተካሄደው በዩኒቨርሲቲዎቹ ተማሪዎች ዘንድ ስላለው የወሲብ ባህርይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሚጠቀሙዋቸውን ሱስ አስያዥ እጾች የመጠቀም እንዲሁም አግባብ ያልሆነውን የግብረስጋ ግንኙነት ጭምር የሚመለከት ነው፡፡ ከአዋሳ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ከሁሉም ካምፓሶች ከአንድ ሺህ በላይ ተማሪዎች በተካተቱበት ሁኔታ ጥናቱን በተለያየ ዘዴ በመጠቀም ብዙ ባለሙያዎች በተሳተፉበት ሁኔታ ተሰርቶአል፡፡
ኢሶግ/ ከጥናቱ ምን ውጤት ተገኘ?
ዶ/ር የጥናቱ ውጤት እንደሚያመለክተው ቀደም ሲል ይወራ ከነበረውና ከታሰበው ውጭ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ጥናቱ በተካሄደባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ማለትም በጎንደር... በጅማ... በመቀሌ... ወዘተ የተገኘው ምላሽ ከአዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው፡፡ ወጣ ያለ የግብረስጋ ግንኙነት ባህርይ አለ ከተባለ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ያለው በሌላውም ማለትም ጥናቱ በተካሄደባቸው ዩኒቨርሲቲዎች በሙሉ በተመሳሳይ ሁኔታ የሚፈጸም ነው፡፡ የተገኘውን ውጤት ስንመለከተው ወረቀቱ የአንዱ ውጤት የተባዛ እስኪመስል ድረስ የአንዱን ከሌላው መለየት የማይቻልበት ሁኔታ ነው፡፡
ኢሶግ/ ከጥናቱ ያልተጠበቀ ውጤት የሚባል ምላሽ የተሰበሰበበት ሁኔታ ይኖር ይሆን?
ዶ/ር ያልተጠበቀ ውጤት የሚባለው አብዛኞቹ ተማሪዎች ለአደጋ ...ማለትም ለኤችአይቪ ...ለአልተፈለገ እርግዝና ወይንም ከወሲብ ጋር ለሚያያዙ ሕመሞች የተጋለጡ ተማሪዎች የነበሩ ሲሆን የወሲብ ግንኙነቱን ጀመሩ የሚባሉት 68 % የሚሆኑት የከፍተኛ ደረጃ ተማሪ ሆነው ሲሆን ቀሪዎቹ 12 % የሚሆኑት ደግሞ ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በሁዋላ፣ እንዲሁም 20 % የሚሆኑት በመጀመሪያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ ወሲብ መፈጸም የጀመሩ ናቸው ፡፡ ሌላው የተለየ ነገር ደግሞ ብዙ የሚታሙት ሴቶቹ ተማሪዎች ሲሆኑ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ገንዘብ ለማግኘት ከሀብታም ሰዎች ...ከነጋዴዎች፣ከውጭ አገር ሰዎች ጋር ወሲብ ይፈጽማሉ በሚል ይታሙ የነበሩ ሲሆን የጥናቱ ውጤት ያሳየው ግን በጭራሽ ከዚህ ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡በእርግጥ የወሲብ ግንኙነቱን የጀመሩ ሴቶች አሉ ቢባልም መገለጫው ግን እንደ ሐሜቱ ሳይሆን ይልቁንም የሀብታም ሰዎች ልጆች...ገንዘብ በበቂ የሚላክላቸው... ከከተማ የመጡ ተብሎ ቢለዩ እንደሚሻል ጥናቱ አመላክቶአል፡፡ ለኤችአይቪ ቫይረስ የተጋለጡ ተማሪዎች በአብዛኛውም በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ በነበሩበት ጊዜ በመንግስት ትምህርት ቤት ሳይሆን በግል ትምህርት ቤት ይማሩ የነበሩ እንደሆኑም ጥናቱ አሳይቶአል፡፡ በአንጻሩ በመካከለኛ ወይንም በአነስተኛ ደረጃ የሚኖሩ ቤተሰቦች ልጆች ወይንም ጥሩ ገቢ የሌላቸው እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚዘጋጀውን ምግብ የሚጠቀሙት የተሻለ ባህርይ እንዳላቸው ታይቶአል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በየትኛውም ሀይማኖት ይሁን በእምነት ስርአት ውስጥ ተከታታይ ወይንም እምነቱን የሚከተሉ ከሆኑም ይበልጥ ለአደጋ እንደማይጋለጡ ለማየት ተችሎአል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኤችአይቪን በሚመለከት የተሻለ እውቀት ያላቸው ተማሪዎች ይበልጥ ለአደጋው የተጋለጡ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
ኢሶግ/ ጥናቱ የተሰራው በተማሪዎች ላይ ብቻ ነበር?
ዶ/ር ጥናቱ በሌላው ማህበረሰብስ ምን ይመስላል ? የሚለውን ለማወቅ ሰፋ ባለ ሁኔታም ተዳስሶአል፡፡ በተለይም በአገር አቀፍ ደረጃ EDHS በየአምስት አመቱ የሚካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው አደገኛ የሆነ የወሲብ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችን በሚመለከት የሚጠቁመው የተሸለ እውቀት ፣የተሻለ ገቢ ፣ጥሩ ስራ ያላቸው ሰዎች እንዲሁም የተማሩ እና ጥሩ ኑሮ የሚኖሩ ለአደጋ ይበልጡኑ ይጋለጣሉ፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ በኤችአይቪ ይበልጡኑ የሚያዙት በከተማ አካባቢ የሚኖሩ እና ሁኔታዎች የተሟሉላቸው መሆኑ የሚያሳየው የባህሪ ለውጥ ለማምጣት እውቀት በራሱ ብቻውን መፍትሔ እንደማይሆን እና የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም መኖርም ከአደጋው እንደማያድን ነው፡፡
ኢሶግ/ ኤችአይቪ የተማረውን ፣ገንዘብ ያለውን ይይዛል ሲባል ያልተማረው እና አነስተኛ ገቢ ያለውስ?
ዶ/ር ጥያቄው በእርግጥ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ኤችአይቪ የደሀ በሽታ ነው ወይንስ የሀብታም? ኤችአይቪ የተማረ ሰው በሽታ ነው ወይንስ ያልተማረ? የሚለው ነገር የሚያወያይ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ኤችአይቪን ብቻም ሳይሆን የአባላዘር በሽታንም ይመለከታል፡፡ የአባላዘር በሽታም ልክ እንደኤችአይቪ የተማረውን ፣እውቀትና ገንዘብ ያለውን እንደሚያጠቃ በጥናት ተረጋግጦአል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ፍቺ የሚያሻቸው እንቆቅልሾች ናቸው፡፡
ኢሶግ/ በኤችአይቪ ቫይረስ በመያዝ ላይ የማንነት ሁኔታ በሌሎች አገሮች ምን ይመስላል?
ዶ/ር በሌሎች አገሮችም የተደረገወ ጥናት የሚያሳየው ብዙም የተለየ ነገር የለውም፡፡ ከአገር አቀፍ ውጭ የ 28/ሀያ ስምንት አገሮችን እውነታ ለማየት ተሞክሮአል፡፡ ሀገሮቹም ከአፍሪካ፣ ከካሪቢያን፣ ከላቲን አሜሪካ፣ ከኤሽያ አህጉሮች የተውጣጡ ናቸው፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ ከሁሉም አገሮች የተገኘው የጥናት ውጤት ተመሳሳይ ነበር፡፡ በሁሉም ሀገሮች በኤችአይቪ የሚያዙት በከተማ የሚኖሩ፣ በገንዘብ አቅም ያላቸው ፣ የተማሩና ግንዛቤ ያላቸው የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ሲጠቃለልም ልቅ የሆነ የግብረስጋ ግንኙነት በማድረግ እና በበሽታው የመያዝ ሁኔታ አንድ ሰው ግንዛቤ ስላለው ወይንም ገንዘብ ስላለው የሚቀንስ ሳይሆን እንዲያውም ተባብሶ የተገኘ ነው፡፡
ኢሶግ/ በወጣቶች ላይ የተደረገው ጥናት ያሳየው የተለየ ነገር አለ?
ዶ/ር በወጣቶቹ በኩል ለየት ያለው ነገር ከ26/ሀያ ስድስት ሀገሮች/ሴት እና ወንድ ወጣቶች መካከል (ከ15-24 አመት) በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ወንድ ወጣቶች ከሴት ወጣቶች አስር እጥፍ በላይ ልቅ የግብረስጋ ግንኙነት እንደሚያደርጉ እና ለተለያዩ የአባላዘር በሽታዎች ኤችአይቪን ጨምሮ የመጋለጥ እድላቸው ከፍ ባለ ሁኔታ እንደተመዘገበ ያረጋግጣል፡፡ እነዚህም ወጣቶች ስራ ካለው እና ጥሩ ገቢ ካለው ቤተሰብ ተወልደው ያደጉ እና በከተማ አካባቢ የሚገኙ ናቸው፡፡
ይቀጥላል፡፡

Read 5536 times