Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 15 December 2012 12:40

አቶ ሬድዋን ስለምርጫ፣ ስለተቃዋሚዎች፣ ስለመተካካት---ምን ይላሉ?

Written by 
Rate this item
(14 votes)

የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ከኢህአዴግ ፅ/ቤት ሃላፊ ከአቶ ሬድዋን ሁሴን ጋር በተለያዩ አነጋጋሪና አወዛጋቢ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረገችው ሰፊ ቃለምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል።
ኢህአዴግ ከመድረክ ጋር ለመነጋገር፤ በቅድሚያ መድረክ የስነ ምግባር ደንቡን መፈረም አለበት ይላል። በሌላ በኩል፤ ደንቡ በፓርላማ ፀድቆ የአገሪቱ ህግ ሆኗል። የፈረመም ሆነ ያልፈረመ ፓርቲ፤ የህጉ ተገዢ ነው፡፡ መድረክ ደንቡን እንዲፈርም ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር ካልሆነ በቀር ትርጉም የለውም ይባላል---

በፓርላማ የፀደቀው ህግ ምን እንደሚል መመልከት ይቻላል። የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ውስጥ መሳተፍ የሚቻለው፤ የስነ ምግባር ደንቡን የፈረሙ ፓርቲዎች ናቸው ይላል - ህጉ። ህጉ በፓርላማ እንደፀደቀ የሚያውቁ ከሆነ፤ ህጉን ማንበብም ይችላሉ፡፡ ኢህአዴግ ያቀረበው ጥያቄ ህጉ ውስጥ ያልተፃፈውን ሳይሆን ህጉ ላይ የተፃፈውን ነገር ነው፡፡ ፈርማችሁ ተቀላቀሉና ውይይት እንጀምር ነው ያልነው፡፡ ለነገሩ አዋጁ ከመውጣቱ በፊትም፣ መድረክ ሁለት ጊዜ ውይይትና ድርድር አልፈልግም ብሎ ረግጦ ወጥቷል፡፡ ፈርመው መወያየት የጀመሩ ፓርቲዎችን፤ “ለኢህአዴግ የተሸጡ አሽከሮች ናቸው” ብሎ በይፋ አውግዟቸዋል፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ጋር የምንወያየው፤ በአቋም ሙሉ ለሙሉ ስለተስማማን አይደለም። የሚያለያዩን፣ የማያግባቡንና የማይታረቁ በርካታ አቋሞች አሉን፡፡ እነዚህን ልዩነቶቻችን ይዘን፣ በጋራ አገር በመገንባት ዙሪያ ላይ፤ ልዩነታችንን አጣጥመንና አቻችለን፣ በየፊናችን የሚደግፈንን ህዝብ ወክለን ለመንቀሳቀስ የምንችልበት አመቺ ሁኔታ መፍጠር ይገባናል፤ በዚህ ጉዳይ ላይ እንዳንወያይ የሚከላከለን ነገር የለም ብለው ነው የገቡት፡፡ መድረክ ግን ወደ ውይይት መግባት አልፈለገም። ውይይቱ ላይ እገሌ የሚባለው ተቃዋሚ ፓርቲ ከገባ እኔ አልገባም ብሎ ወጣ፡፡ ብንፈርምም ኢህአዴግ ስለማይተገብረው አልፈርምም አለ፡፡ አሁን እንወያይ ማለታቸው ችግር የለውም። ነገር ግን፤ ከውይይት መውጣታችን ልክ አልነበረም፤ መስሎን በወቅቱ አድርገነዋል፤ አሁን ስናየው ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘነው እንወያይ ቢባል ምን አለበት? ነጥብ ከማስቆጠር ጋር ባይያያዝ ምን አለበት? ኢህአዴግ በአንድ ወቅት ትክክል መስሎት ያደረገው ነገር፤ ከጊዜ በኋላ ስህተት መሆኑን ካየ፤ እንዲህ መስሎኝ ተሳስቼ ነበር፤ አሁን ትቼዋለሁ ይላል፡፡ ተቃዋሚዎች የትናንት ስህተታቸውን በአደባባይ ለማመን ከተቸገሩ፤ የመንግስት ስልጣን ሲይዙ፤ እንዴት ስህተታቸውን ማመን ይችላሉ? “ተሳስታችኋል” ብሎ የሚጠይቃቸውንስ እንዴት መቀበል ይችላሉ? ካሁኑ ነው መላመድ የነበረብን። ስህተትን በይፋ አምኖ ማስተካከልኮ፤ የተራማጅነትና የለውጥ ፈላጊነት ምልክት ነው። የተሻለ ለመማር የመፈለግ ምልክት እንጂ የሽንፈት ምልክት አይደለም፡፡ ካፈርኩ አይመልሰኝ አይነት አቋም አይጠቅምም።
የኢህአዴግ ዋና ድርጅቶች በባለፈው ሁለትና ሶስት ወራት በነበራቸው ግምገማ በተለይም ኦህዴድ በርካታ አማራጮቹን ገምግሞ እርምጃ የወሰደ ሲሆን ድርጅታቸውን ከማገልገል ይልቅ ለሌሎች ድርጅቶች ሲያጐበድዱ ተገኝተዋል ባላቸው ላይ አቋም መውሰዱ ይነገራል፡፡ እንደ ኢህአዴግ ለአገር መስራት ለሌላ ድርጅት መስራት ተብሎ ሊወስድ ይችላል?
ኦህዴድ እንደሱ ይገመግማል ብዬ አላስብም፡፡ ኢህአዴግ ውስጥ ያቆየው፤ ኢህአዴግ ያሰኘው እምነቱ ይሄን ስለማይፈቅድለት ኦህዴድ እንደሱ ይገመግማል የሚል እምነት የለኝም፤ በዚህ ሁኔታም ገምግሟል የሚል መረጃም የለኝም፡፡
ለሌላ ድርጅት ማጎብደድ የሚባል ነገር ከመጀመሪያውም አይኖርም፡፡ ሌላ አንድ አዛዥ የሆነ ድርጅት ስላልነበረ፡፡ አራቱም ድርጅቶች በጋራ ባዋጧቸው እኩል ቁጥር ባላቸው ስራ አስፈፃሚዎች ነው የሚመሩት፡፡ 46 46 አባላት በድምሩ መቶ ሰማኒያ አባላት ያሉት የምክር ቤት ውሳኔ ላይ ነው የሚመሩት፡፡
አንደኛው ጐልቶ የሚወጣበት፤ ሌላኛው ሌላውን ለማገልገል የሚሄድበት አደረጃጀትም አይፈቅድም፡፡ መሠረታዊ እምነቱም አይፈቅድለትም፡፡ ኦህዴድ እንደዚህ ገምግሟል ብሎ መውሰድ ይከብዳል፡፡
ኢህአዴግ የ4 ድርጅቶች ግንባር ነው፡፡ በ1994 ዓ.ም ወደ አንድ ፓርቲነት የማደግ ሃሳብ አንስቶ እንደነበር ይታወሳል፤ አሁን ሃሳቡ የት ደረሰ?
ወደ አንድ ፓርቲ የመምጣት ጉዳይ፤ በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ጠረጴዛ ላይ ያለ ጉዳይ ነው። በሂደትም ሊሆን የሚችል ነው። ግን አንገብጋቢው ጉዳይ፤ ወደ አንድ ፓርቲ የመምጣት ጉዳይ ነው አንልም። በሃሳብ ደረጃ ትክክል ነው፡፡ አንድ ቀን ወደዛ ልንሄድ እንችላለን፡፡ አሁን እናድርግ ካልን የሚከለክለን ነገር የለም፤ ለነገ ብናሳድረውም የሚያጐድል ነገር የለም። የሆነ ጊዜ ላይ ዛሬ እናድርገው ካልን ሊሆን የሚችል ነው፡፡ አደረጃጀት መሣሪያ ነው። መሰረታዊ አቅጣጫዎችንና ፖሊሲዎችን በቀላሉ ለመተግበር የሚያስችለኝ አደረጃጀት የትኛው ነው ብሎ የመምረጥ ጉዳይ ነው። አደረጃጀት ራሱን የቻለ የመነጋገሪያ አጀንዳ አይሆንም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ፤አራቱም ድርጅቶች በሚያስተዳድሯቸው ክልሎች ውጤታማ ስራ እያከናወኑ ነው። የጎደለ ነገር የለም። አንድ ወጥ ፓርቲ ሆነንም ውጤታማ ስራ መስራት እንችላለን። ብዙ የሚያጐድል ነገር የለውም፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው። ቀነ ገድብ እናስቀምጥ ብለን በየወቅቱ እንገመግማለን፡፡ የክልሉንና የማህበረሰቡን የለውጥ ደረጃ እናያለን፡፡ አንድ ወጥ ፓርቲ የምንሆንበት ደረጃ መድረሳችን በየጉባኤው ተገምግሞ ልናደርገው እንችላለን፡፡ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ጋ ስንደርስ፣ በርካታ የገጠሩ ገበሬ ከተሜ ይሆናል ከሚለው አሳብ ጋር በሂደት እያጠናን እንመልሳለን፡፡ ወደ አንድ ፓርቲ መሄድ ስህተት አይደለም፤ በጣም የሚያንገበግብም አይደለም፡፡
ከጥቂት ወራት በኋላ በሚካሄደው የኢህአዴግ ጉባኤ ምን ይጠበቃል፤ የመተካካቱ ሁኔታስ እንዴት ይታያል?
እንደ ኢህአዴግ ሳይሆን እንደ ድርጅት በመተካካቱ ሁኔታ ማን ይውጣ የሚለው ተሰርቶ ይመጣል፡፡ መቀጠል አለበት ያለውን ያስቀጥላል፡፡
መተካካቱን በተመለከተ ስርዓት በመሆኑ በመካከለኛ ጊዜ እንወጣለን ብለው የሚያስቡ ጓዶች ይኖራሉ፤ በአጋማሽ እንወጣለን የሚሉ ሰዎች በቀሪ ጊዜያቸው በሚኖረው ይወሰናል፡፡ ተገደው አይደለም የሚወጡት፤ በፊትም ፈቅደው ነው የወጡት፤ እኛ የመጀመሪያ ረድፍ ላይ ነው የምንወጣው ብለው ነው የወጡት፡፡ አሁን ውጡ የተባሉ የሉም፤ አሁን ልውጣ ብሎ የተከለከለ ካለ መለስ ብቻ ነው፡፡ በመጀመሪያ መውጣት አለብኝ ብሎ ወስኖ አይቻልም ተብሎ የተከለከለ ካለ እሱ ነው፡፡ ሌላው ራሱ ባስቀመጠው ሂሳብ እንዲሄድ ነው የተባለው፡፡
በመጀመሪያ ጊዜ መውጣት አለብን ብለው የወጡ አሉ፤ በመካከለኛው እንወጣለን ብለው የውሳኔ ሃሳብ ያላቸው አሉ፡፡ ስለዚህ በዚህ ሁኔታ ፍሰቱ ይቀጥላል ማለት ነው፤ መሠረታዊ ለውጥ ሳይኖረው ባለው አቅጣጫ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ይሄ በሚቀጥለው ጉባኤ ላይ የሚያልቅ ይሆናል፡፡ አሁን የዕለት ተዕለት መተካካት ነው የሚቀጥለው፡፡ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ታች በተግባር አፈፃፀም ተያይዞ የሚመጣው መተካካት ነባራዊ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
በፖሊሲ ደረጃስ?
በፖሊስ ደረጃም ለሚቀጥለው አስርና አስራ አምስት ዓመት ይወስደናል፡፡ የአቅጣጫ ችግር ስለሌለው ይህን ትክክለኛ አቅጣጫ የበለጠ እንዴት እናፋጥነው፤ እንዴት እናስፋው ይበልጥ ባለቤቶች መጠቀም የምንችልበትን አዳዲስ ስልቶችን እንጨምርበት በሚል ዙሪያ መምከር ይችላል፡፡ የዚህች አገር የእድገቷ ፍጥነት አንዱ መገለጫ የሆነው አቅጣጫው ነው፡፡ የዕውር ድንብር እዚህ ድረስ መጓዝ አንችልም፤ አቅጣጫውን ነክሶ የሚይዝ ፓርቲ ስለመጣ ነው፡፡ እንኳን አሁን ውጤት በመጣበት ይሁንና ይሄን ያህል ውጤት ባልመጣበት ጊዜ በጽንስ ሃሳብ ደረጃ ይታወቅ በነበረው በ95 እና 96 ዓ.ም ቢታይ እንኳን ይሄ ለውጥ መምጣት እንደሚችል መገመት ይቻል ነበር፡፡ አሁን ግን በተግባር መጥቷል፤ ያለፈው ዘጠኝ ዓመት ደብል ዲጂት እድገት ያመጡ አቅጣጫዎች ናቸው፡፡
በዚህ ጉባኤ የአቅጣጫ ለውጥ ባይጠበቅም ተጨማሪ የማሳለጫ፣ ፍጥነት የመማሪያ፣ ስፋት የመጨመሪያ ጉዳዮች ላይ እንወያያለን፡፡ በተለይ ከግብርና፣ ከመልካም አስተዳደር አንፃር መሠረቱ አለ፡፡ አቅጣጫው አለ፡፡ ተቋሞቹ አሉ፡፡ ወድቆ መነሳት አለ፡፡ በልማቱ ልክ አልሄደም የሚል እምነትም አለ፡፡ የልማቱን ጥግ ማፍጠን እንችላለን፡፡
የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በሚመለከት ኢህአዴግ ያወጣቸው ሰነዶች ላይ አንድ ነጥብ አለ፤ የፓርቲና የመንግስት ተቋማት እንዲሁም መዋቅር በግልጽ የተነጣጠሉ መሆን አለባቸው ይላል፡፡ 1ለ5 የሚለው አወቃቀር ግን የፓርቲ ይሁን የመንግስት ተለይቶ አይታወቅም፡፡ የመንግስት ተቋማት በ1ለ5 አወቃቀር የልማት፣ የጤና፣ የፍትህ ሠራዊት እያሉ ያደራጃሉ፡፡ ፓርቲው ደግሞ ለምርጫ ዘመቻ ይጠቀምባቸዋል እና ምን ይሻላል?
ኢህአዴግ ከህብረተሰቡ ውስጥ የራሳቸውን ህይወት ለመቀየር የሚተጉትን፤ የሚጣጣሩትን ነው መመልመል ያለበት የሚል ነው አንዱ አቅጣጫው፡፡ ኢህአዴግ የሚመራ ከሆነ በአባላቶቹ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ጭምር ነው የሚመራው፡፡ መሪ ነው ሲባል የሆኑ ባለስልጣኖችን መርጦ መምራት አይደለም፡፡
የኢህአዴግ አባል ያልሆነ ሰው ተማሪ ከሆነ ጥሩ ተማሪ መሆን አለበት፡፡ የሚያጠና፤ ለራሱ ያገኛትን እውቀት ለሌላው አካፍሎ መኖር የሚችል ማለት ነው፡፡
መርሁ ይሄ ነው፡፡ ካሉን አባላት ውስጥ ምን ያህል ፐርሰንቱ ይሄን ነገር ያሟላሉ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ እሱን ለማሟላት መስራት ይጠይቃል፡፡ የኢህአዴግ አባል የሆነ ገበሬ በአመት ሁለት እና ሶስት ጊዜ ለማረስ የሚተጋ፣ ልጆቹን ት/ቤት የሚልክ፤ ሲልክም ሴቷን ነጥሎ አስቀርቶ ወንዱን ብቻ የሚልክ ሳይሆን ሁለቱንም የሚልክ፤ ጓሮው ላይ ሽንት ቤት እየቆፈረ በሽታን ለመከላከል ለራሱም ለቤተሰቡም የሚተጋ፡፡ ጓሮ ላይ እያለማ የቤተሰቡን የአመጋገብ ስርዓት ለመቀየር የሚጥር፤ ገቢውን በየጊዜው ለመጨመር የሚታትር መሆን አለበት፡፡ ይሄ ከሆነ ፖቴንሺያሊ ኢህአዴግ ይሆናል፡፡ ስለዚህ እሱን እንመለምለዋለን፡፡ ከመለመልነው በኋላ የጀመረውን ጥረት እንዲያሳድግ እንደግፈዋለን፡፡ ለብቻው ጥሮ ግሮ ሃብታም ቢሆንም ብቻውን የትም አያደርሰውም፡፡ አካባቢው መቀየር አለበት፤ በአንድ ነገር ያቺ አካባቢ መታወቅ አለባት፡፡
በዙሪያው ላሉት ልምዱን እያካፈለ፤ እኔ ተቀይሬያለሁ፤ እናንተም ተቀየሩ እያለ የተወሰነ ሰዓቱን መስዋዕትነት ከፍሎ ጐረቤቱን ለማሳመን መስራት አለበት፡፡ እንስራ እንለወጥ ነው፡፡ ኢህአዴግ ሰነፍ ተማሪ፤ ሰነፍ ገበሬ ምን ያደርግለታል? የድርጅቱ ራዕይ እንዲገባው ያስፈልጋል፡፡ ይሄንን ወደ ሲቪል ሰርቪሱም እናመጠዋለን፡፡ የእኛ አባል የሆነ ሰው ህዝብን ማገልገል አለበት፡፡ ራሱን የዚህች አገር የለውጥ ማዕከል አድርጐ ሊወስድ ይገባል፡፡ ለራሱ ሲንቀዋለል እየዋለ መልካም አስተዳደር እንፈጥራለን የሚል ሰው ኢህአዴግ ሊሆን አይችልም፡፡ በኢህአዴግ ስም ሊነግድ ይችል ይሆናል፡፡ ግን ኢህአዴግ ሊሆን አይችልም፡፡
በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ያለው እንደዚህ የበቃ ነው ወይ ከተባለ አይደለም፡፡ ከድሮ ጀምሮ ስንመለምል ስለመጣን እያጣራን እያበቃን፣ ፊልተር እያደረግን እንሄዳለን፡፡ ሲቪል ሰርቪስ ውስጥም ጥሩ ሰርቷል የሚባለው እሱ ጥሩ ስለሰራ ብቻ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ነኝ የሚል ሰው መ/ቤቱ እንዲቀየር ከፈለገ ራሱ ተቀይሮ ማሳየት አለበት፡፡
በእርግጥ የመ/ቤት ሰው በሙሉ ኢህአዴግ ሊሆን አይችልም፡፡ የተወሰነ ሰው ብቻ ነው ኢህአዴግ ሊሆን የሚችለው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ የፓርቲ አባል ወይም የፖለቲካ ተያያዥነት አይፈልጉም፣ነፃ ሆነው መስራት የሚፈልጉ በጣም ስራ ወዳድ ሰዎችም አሉ፡፡ ዋናው ነገር ኢህአዴግ ነን የሚሉ ሰዎች በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ እንዴት እናገልግል፣ ምን እናሻሽል? ብለው እየገመገሙ እንዲሄዱ ነው፡፡ ፍልስፍናው ይሄ ነው፣ የምርጫ ጊዜ ሲመጣ ይሰራል ወይ ከተባልሽ ይሰራል፡፡ ሊሰራ ይችላል፡፡ ተያያዥ ውጤቶች አሉት፡፡ ለምሳሌ አርሶ አደሩን እንውሰድ፡፡ ትናንት በቅጡ የማያመርት የነበረ ገበሬ፣ ኢህአዴግ ነኝ ያለን ሰው ጫና ፈጥረን፣ አሳምነንና አስተምረን ኑሮው እንዲቀየር ካበቃነው፣ ኢህአዴግ ነው ለስኬት ያበቃኝ ይላል፡፡ ይሄ ምንድን ነው ክፋቱ?
ለተቃዋሚዎች ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠብቧል ፤ የተዘጉ ጋዜጦች አሉ…
ተቃዋሚዎች የኢህአዴግ መንገድ ሁሉ የጥፋት መንገድ ነው፣“ውጉዝ ከመአሪዎስ” አይደለም ማለት ያለባቸው፡፡ ኢህአዴግ በጣም ሰርቷል ጥሩ ነው፣ እኛ ግን እናሻሽለዋለን ማለት ነው ያለባቸው፡፡ እስከአሁን ሲያዋጋን የነበረው የመሬት ጉዳይ ነው፡፡ በመሬት ጉዳይ የመድረክ አቋም ምንድነው? ምንም የለም፡፡ አንዱ መሸጥ ማለትማ ወያኔ መሆን ነው፡፡ ሌላው ካልተሸጠ የህዝቡ መብት አልተከበረም ይልሻል፡፡
ግን ሁለቱም መድረክ ናቸው፡፡ ታዲያ ምን አንድ አደረጋቸው? የኢህአዴግ ጥላቻና ምቀኝነት ነው እንደዚህ ያደረጋቸው እንጂ ራዕይ አይደለም፡፡ ራዕይ አንድ የሚያደርግሽ ከሆነ በመፍትሔው ትግባቢያለሽ፡፡
የብሔረሰብ መብት ላይ ብሔረሰቦች የራሳቸውን መብት በራሳቸው የማስተዳደር ጉዳይ ነው፡፡ በዚህች አገር አንዱ የቁርቁሶ ምንጭ ይሄው ነው፤ የውደቀታችን አንዱ ምንጭም ለዚህ የሚሆን በቂ ምላሽ የሚሰጥ ስርዓት አለመፍጠራችን ነው፡፡
አሁን ተፈጥሯል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የመድረክ አቋም ምንድን ነው? በፌደራሊዝም፣ በብሔረሰቦች ራስን ማስተዳደር ጉዳይ ላይ ምንድን ነው የመድረክ አቋም? ምንም የለም፡፡ አንድ አገር የመነሻዋም የመውደቂያዋም ምሰሶ በሆነ ጉዳይ ላይ ያልተግባባ ፓርቲ፣ በሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ላይ የተዋጣለት ፖሊሲ ከየት ሊያመጣ ይችላል፡፡ “ኢህአዴግን እንተወው፡፡ እኛ እስከምን ድረስ ነው የምንግባባው” ብሎ የቤት ስራውን ጨርሶ፣ ከዛ ያለቀለትን መረጃ ይዞ “እኛን ብትመርጡን በዚህ በዚህ መንገድ ነው የምንመራችሁ” ብሎ ነው አንድ ፓርቲ የሚመጣው፡፡ ይሄንን የመሰሉ ፓርቲዎች አይደለም እኛ አገር ያሉት፡፡ በዚህ ሁኔታ ምህዳሩ ጠበበ ለምን ይባላል?
ኢህአዴግ ያልተሰራ መዓት የቤት ስራ ነው ያለው፡፡ እያንዳንዱን ከአረንቋ ለማውጣት በሄደበት ሂደት ውስጥ ተጨማሪ ድጋፍ ያገኛል፡፡ በዚህ ረጅም ጊዜ ድጋፍ አግኝቶ ቢቀጥል ለምን ወንጀል ይሆናል፡፡
ከ40-70 ዓመት የገዙ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ሃጢያት ሊሆን አይችልም፡፡ ዋናው የሜዳው መጥበብና ያለመጥበብ መመዘኛው፣ ሰው በነፃ ፍላጐቱ የመወሰንና ያለመወሰን መብት አለው ወይ፤ አምኖበት ፈቅዶ ነው ወይ የሚወስነው? ሚዛኑ ይሄው ነው፡፡
የፖለቲካ መድረኩ ጠቧል የተባለው በተዘጉ ጋዜጦች ሳይሆን እነሱም በነበሩበት ጊዜ ነው፡፡ መድረክ ጠቧል ለሚለው ምክንያት ሊሆኑ አይችሉም፡፡ የተዘጉ ጋዜጦችን በተመለከተ የግልም ሆነ የመንግስት በርካታ አሳታሚ አለ፣ በእያንዳንዱ የአሳታሚዎች ስምምነት ውስጥ መንግስት እየገባ አይፈተፍትም፡፡ የእገሌን ካላተማችሁ እያለ ማተሚያ ቤቶችን እጅ እየጠመዘዘ አትሙ ሊል አይችልም - ስህተት ነው፡፡ የሀገሪቱ የንግድ ህግና የኮንትራት ውል በሚፈቅደው መሠረት መስተናገድ የእያንዳንዱ ተቋም ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አሜሪካም ቢሆን እኮ የሚታተመውን ይዘት አይተው፣ የአንተን አላትምም ይላሉ፡፡ ይሄ የትም አገር በአደገውም ያለ የንግድ ስርዓት አካል ነው፡፡ አታሚው የማተም ያለማተም መብት አለው፡፡
ተቃዋሚዎች ቢያሸንፉ፣ ኢህአዴግና አባላቱ ተቃዋሚ ፓርቲ ሆነው መስራት ይችሉበታል? ዝግጁስ ናቸው?
ይሄን እኮ በተግባር አሳይተናል፡፡ የኢትዮጵያ እምብርት የሆነችው አዲስ አበባ ላይ ስንሸነፍ፤ ከማንም በፊት ራሱ ኢህአዴግ ነው መሸነፋችንን የገለፀው፡፡ አዲስ አበባ ላይ ስለተሸነፍን፤ በከተማዋ ታማኝ ተቃዋሚ ሆነን እየደገፍን ለመቀጠል ዝግጅዎች ነን አለ፡፡ ይህንን አስቀድሞ ካሳወቀ በኋላ ነው፤ የት የት እንዳሸነፍን የገለፀው። አዲስ አበባ ላይ ተሸንፎ “ኑና ስልጣን ውሰዱ” ብሎ የለመነ ፓርቲ፤ አሁን በተወሰኑ ወረዳዎችና ቀበሌዎች አልያም በተወሰኑ ዞኖች ቢሸነፍ ውጤቱን በፀጋ ለመቀበል የሚያንገራግርበት ምክንያት የለም፡፡
ለነገሩ፤ ካሁን በፊትም ኢህአዴግ ተሸንፎ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያስተዳድሯቸው ወረዳዎችና ዞኖች ነበሩ፡፡ በደቡብ ክልል በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። ኢህአዴግ የምርጫ ውጤቱን በፀጋ ተቀብሏል። በእነዚህ አካባቢዎች፤ በሂደት ህዝቡ ተቃዋሚዎችን ትቶ ኢህአዴግን ሲመርጥ ደግሞ፤ ኢህአዴግ የማስተዳደር ሃላፊነት ተረከበ። ኢህአዴግ ተሸንፎ ሽንፈቱን መቀበል ካቃተውኮ፤ ኢህአዴግነቱ ያበቃለታል፡፡ እስካሁን የለፋለትና የታገለለት ነገር ሁሉ ከንቱ ይሆናል፡፡ ኢህአዴግ አለኝ የሚለው ስብዕናና ማንነቱ አብቅቶ ሌላ ፓርቲ ይሆናል፡፡ በአዲስ አበባ ምክር ቤት ምርጫ ላይ ኢህአዴግ የተሸነፈ ጊዜ ምን እንዳደረገ ማስታወስ እንችላለን። የከተማ መስተዳድሩን ውሰዱ አለ። ግን በክፍለ ከተማና በቀበሌ ደረጃ የሚካሄዱ ምርጫዎች ነበሩ። የስልጣን ርክክብ አዲስ ልምድ ስለሆነ፤ እንቅፋቶችን ለማስወገድ ሲል ኢህአዴግ የክፍለ ከተማና የቀበሌ መስተዳድርንም አብሮ ለማስረከብ ነበር የወሰነው። በዚሁ አጋጣሚ ኢህአዴግ በአዲስ አበባ ታማኝ ተቃዋሚ ሆኖ ከሂደቱ እየተማረ፤ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ምን ዓይነት ሚና መጫወት እንዳለበት ለሌሎች ለማሳየትና ለማስተማር ነበር ያሰበው።
ከ34 በላይ የሚሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው ረቂቅ ሰነድ የጊዜ ሰሌዳ ላይ የምርጫ ቦርዱን እያማረሩ ነው---
የተቃዋሚዎች ዝግጅት ሁሌም ምርጫ ሲመጣ እንደሚደረገው ዓይነት ነው፡፡ የሚጀምረው ከአኡታ ነው፡፡ በተግባር ከታየውም አልታየውም፤ በተግባር ካልተጨበጠውም ገና ወደፊት ያጋጥሙኝ ይሆናል ተብሎ በምናብ በሚሳሉ ችግሮች ውስጥ የመዋኘት ነው የሚሆነው፡፡ ከእስከዛሬው ስናይ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ለአካባቢ ምርጫ አፒታይት የላቸውም፡፡ ለታይታ አይመችም፤ ዋናዎችን ሰዎችን አይጨምርም፡፡ ከታች ያሉ እግረኞችን ነው የሚያሳትፈው፡፡ ለኢህአዴግ ዋናው እግሩ መቆሚያው የአካባቢ ምርጫ ነው፣ ዋናው እግሩ ሁሉን የሚያንቀሳቅስበት ባለቤቱ ነው፡፡ የልማቱ፣ የዲሞክራሲ፣ የውሳኔ ባለቤት የሆነውን ህዝብ የሚያንቀሳቅስበት ጠንካራ አመራር በወረዳ በቀበሌ ሲኖረው ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር የተበላሸበትም እዛ ላይ በደንብ ማጠናከር ስላቃተው ነው፡፡
ልማቱ የሚፋጠነውም ለዛ ቦታ አቅም ያለው ሰው መፍጠር ከቻልን ነው፡፡ ለተቃዋሚዎች ያ ትርፍ ነው፡፡ ትርፍ ስፍራ ነው፣ ብዙ ሰው እንዲዋደቅለትም አይፈልግም፣ ቁም ነገር አለበት ብሎ የማይሻው ነው፡፡ ትላልቆቹ ሰዎች እዛ መግባት አይፈልጉም፣ ቢገቡም ለታይታ አይመችም፡፡ ብዙ ጊዜ አይሳተፉም፡፡
ከተሳተፉም ኢህአዴግ አስቸግሮናል ብለው ትንሽ አብረውን ተጉዘው፣ የመጨረሻው ቀን ሲደርስ ጥሎ መውጣት ነው የሚሆነው፡፡
ከወዲሁ የአንዳንዶቹን መግለጫ አይተሽ ከሆነ፣ ኢህአዴግ ከ3.6 ሚ በላይ እጩ እንድናቀርብ ያስገድደናል፣ ከታች ያሉ እጩዎቹን በብዛት በማቅረብ አቅማችን ተለጥጦ መድረስ በማንችልበት ደረጃ በመድረስ፣ እንድንዘረር እንድንሸነፍ ነው የሚያደርገው፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ታዛቢና የወረዳ ተወካይ ለማቅረብ በማንችልበት ደረጃ ከታች ያሉ ጣቢያዎች እንዲበረክቱ ተደርገዋል፡፡ ይሄን ከወሰድሽ ለኢህአዴግ የህገ መንግስቱን መንፈስ መተርጐም ነው፡፡ በዲሞክራሲ በዳበሩት አገራት ያለውን ቀጥተኛ ያልሆነ ዲሞክራሲ ይዞ፣ በምርጫ የሚካሄደውን የውክልና ዲሞክራሲ አካቶ ግን ደግሞ ህዝቦች የመወሰን መብት የተነፈጉባት ናት፡፡ እንኳን የራሳቸው ጉዳይ እንዲሆን ሊወስኑ የተወሰነባቸውን ጉዳይ የማወቅ መብት ያልነበረበት አገር ናት፡፡ ዋናው የዚህች አገር ስልጣን ባለቤቶች ህዝቦች ናቸው፡፡ እነሱ ደግሞ የሚገኙት ታች ቀበሌና ወረዳ ነው፡፡ ባደጉት አገሮች ያለው የውክልና ዲሞክራሲ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በተቻለ መጠን ብዙሃኑ ሰው የቀበሌና የወረዳ ምክር ቤቶች በጥልቀት በጉዳዩ ላይ ሊወሰኑ የሚችሉ ስለሚሆኑ ስለማዳበሪያ፣ ስለ ውሃ አቅርቦት፣ ስለ ትምህርት ቤት ነው የሚያወሩት፡፡ በየዕለቱ ቀበሌና ወረዳ የሚወስነው ውሳኔ የሁሉንም ሰው ኑሮ በቀጥታ እና ወዲያው ነው የምትነካው፡፡ እያንዳንዱ ውሳኔ የዕለት ኑሮዋቸውን የሚመለከት ስለሚሆን በተቻለ መጠን ብዙሃኑ ተወክለው ገብተው በየጊዜው መወሰን እንዲችሉ እነሱን እናብቃ ነው፡፡ የውክልና ዲሞክራሲ ሆኖም ሲያበቃ፣ የቀጥታ ዲሞክራሲ ዓይነት ሽፋን እንዲኖረው እናሳድገው ነው፡፡ ህዝብ ረፈረንደም ላይ በቀጥታ ወደ አደባባይ ይመጣል፡፡ በኛ አገር ሁኔታ ግን በየሶስት ወሩ፣አንገብጋቢ የሆኑ ችግሮች ናቸው ብለን ባመንን ጊዜ ሁሉ ህዝቡ እየቀረበ እንዲወስን እንዲወያይ፣ ህዝቦች የመወሰን መብታቸውን የሚያጎለብቱበት ነው፡፡ ለምሳሌ መድረክ በዚህ ሲከሰን ወደ ድሮው ወደ ግሪክ፣ ወደ ጥንቱ፣ ወደ ሶቆራጥስ ጊዜ መልሶናል፡፡ ኋላ ቀር ነው ብለው ነው የሚወስዱት፡፡ ለእኛ ግን የሞት ሽረት የሆነ፣ ህዝቦች የተጠሙትን መብት በየቀኑ እንዲለማመዱት የማብቃት ጉዳይ ነው የሚሆነው - ባለቤቱ እንዲወስን እድል የመስጠት፡፡ ለእነሱ ደግም ወደ ኋላ መመለስ ይሆናል፡፡ ሁለተኛው “በየምርጫ ጣቢያው ወኪል፣ እጩ፣ ታዛቢ ለማቅረብ አንችልም” የሚል ነው መከራከሪያቸው፡፡ እንደዚህ በማድረግ ዲሞክራሲውን አጥቦታል፣ የፖለቲካ መድረኩን ኢህአዴግ አጥቦታል የሚል ነው፡፡ በሌላ በኩል ኦህኮ ይነሳና መድረኩ ባይጠብ ኖሮ፣ ከኦህዴድ በላይ ድጋፍ ያለኝ እኔ ነኝ ይላል፡፡ ከኦህዴድ በላይ ድጋፍ ካለው በየቀበሌው ታዛቢ እጩ ለማቅረብ አይቸገርም ነበር፡፡ ይህን ሁሉ ግን እንደችግር አድርጎ መላው ህዝብ ደገፈኝ ሲል ምን ማለት ነው? የመላው ህዝብ ድጋፍ የ70 እና የ80 የ90% ድጋፍ ማግኘት ማለት ነው፡፡ ህዝቡ ወጥቶ ድምፁን ሰጥቶ፣ ይሄ ፓርቲ ይሆነኛል የሚል ከሆነ፣ ከዛ ውስጥ ሁለት ሶስት ሰዎች እንዴት ለታዛቢነት ይጠፋሉ፡፡
የምርጫ ዝግጅት የላቸውም ቢባል ነው የሚሻለው፡፡ እንደተለመደው “ይሄ ምርጫ ነገር አለበት” በሚል ድክመታቸውን ሸፍነው፣ ሃጢያቱን በሙሉ ለኢህአዴግ አሸክመው እብስ ለማለት ነው የተዘጋጁት፡፡ በጥቅሉ ለምርጫው ተዘጋጅተዋል ብሎ መውሰድ አይቻልም፡፡ በእርግጥ ችግሮችን በጋራ እንፍታ ብለው ለመወያየት የሚፈልጉ ፓርቲዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ቢያንስ ከ22 በላይ ተመዝግበዋል፡፡ ሌሎችም በሂደት የሚገቡበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ እስከ አሁን የመድረክና በሱ ዙሪያ ያሉ ስብስቦች ወደዛ ዝግጅት አልገቡም፡፡ ተምረው ይመለሳሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡
በአሁኑ ጊዜ ሙስና እየተስፋፋ እንደመጣ ይነገራል----እዚህ አገር ላይ እንቅስቃሴ አልነበረም፣ ሃብት አልነበረም፡፡ ባለፉት ዘጠኝ አመታት በጣም በፍጥነት እያደግን ነው፡፡ በዚህም ውስጥ በርካታ እንቅስቃሴ አለ፡፡ ከሚፈጠረው ሃብት አንፃር ካየነው ሙስና ጨምሯል ማለት አይቻልም፡፡ ግንዛቤው ግን አለ፡፡ እኛ የሙስና ምንጮችን እናጋልጣለን፣ እናስተምራለን - ህዝቡ እንዲጠላው እንዲያወግዘው፡፡
ሙስና የሚጠየፍበት ነባራዊ ሁኔታ አልነበረም - በዚህ አገር ላይ፡፡ ሲሾም ያልበላ የሚባል በጥረት ያልተደገፈ፣ በብልጥነት አስተምህሮ ላይ የተመሠረተ አካሄድ ነበር፣ ይሄን መስበር ያስፈልግ ነበር፡፡ ይሄንንም ለመስበር አመለካከቱን ደጋግሞ መውቀጥ መቀጥቀጥ ያስፈልጋል፡፡ በርግጥም የስርዓቱ አደጋ ነው፣ እንታገለዋለን፡፡ ዕድገታችንን የሚፈታተነን አንዱ አደጋም ይሄ ነው፡፡

Read 8110 times Last modified on Wednesday, 19 December 2012 06:52

Latest from