Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 15 December 2012 15:54

33 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለጠ/ሚሩ ደብዳቤ ሊያስገቡ ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በአዲስ አበባ እንዲሁም በወረዳና ቀበሌ ምርጫ ዙሪያ ለጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ የፃፉት ደብዳቤ ማህተም የለውም ተብሎ የተመለሰባቸው 33 ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ እንደገና የሁሉም ማህተም ያረፈበት ደብዳቤ ለማስገባት እየጣሩ ነው፡፡
የምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ውይይት ተዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም፤ የሚዲያ አጠቃቀም፣ የህግ የበላይነትና የውድድር ሜዳው ለሁሉም እኩል እንዲሆን መደራደር እንፈልጋለን ሲሉ የ33ቱ ፓርቲዎች ተወካይ አቶ አስራት ጣሴ ተናግረዋል፡፡ የኢህአዴግ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሬድዋን፤ የወረዳና የቀበሌ ምርጫ ለታይታ ስለማይመች ተቃዋሚ ፓርቲዎች አይፈልጉትም፤ ለምርጫ ሳይሆን ኢህአዴግ አስቸገረን ብለው ለመውጣት ነው የሚዘጋጁት ብለዋል፡፡

የመድረክ ስራ አስፈፃሚ አባልና የ33ቱ ፓርቲዎች የጋራ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አስራት ጣሴ በበኩላቸው፤ ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ እንዲሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ የሚካሄድ እስርና ወከባ መኖር የለበትም ካሉ በኋላ፤ በህግ የበላይነት ላይ መነጋገር አለብን የምንለውም በዚህ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡
የምርጫ ታዛቢዎችን ከምርጫው እለት 10 ቀን አስቀድመን እንድናስመዘግብ ተነግሮናል የሚሉት አቶ አስራት፤ እንዳለፈው ምርጫ በደህንነትና በኢህአዴግ አባላት ከየቤታቸው እየታፈሱ እንዲታሰሩብን አንፈልግም ብለዋል፡፡ በ2002 ምርጫ ላይ እንደታየው 1ለ5 የተሰኘው ጥርነፋ አሁንም በመጪው ግንቦት የሚካሄደው ምርጫ ነፃና ፍትሃዊ እንዳይሆን እንቅፋት ይሆናል ብለዋል - አቶ አስራት፡፡
ምርጫ በደረሰ ቁጥር ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኡኡታ መጀመራቸው የተለመደ ነው ያሉት የኢህአዴግ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሬድዋን በበኩላቸው፤ ምንም ባልተጨበጠና ባልተፈፀመ ጉዳይ ወደፊት ሊከሰት ይችላል በሚል ሰበብ በምናባቸው በሚፈጥሩት ችግር ውስጥ ይናኛሉ ብለዋል፡፡
የ1ለ5 አደረጃጀት የኢህአዴግ ይሁን የመንግስት ተለይቶ አለመታወቁን በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ሬድዋን ሲመልሱ፤ ኢህአዴግ የራሳቸውን ህይወት ለመቀየር የሚተጉ ዜጐችን ለመመልመል ለልማት እንዲበረቱ ለመገፋፋት የሚጠቀምበት አደረጃጀት ነው፤ የምርጫ ጊዜ ሲመጣም ይሰራል ብለዋል፡፡
ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል የፖለቲካ ነፃነት እየጠበበ መጥቷል የሚሉት አቶ አስራት ጣሴ፤ ዛሬ 33ቱ ፓርቲዎች ምርጫውን አስመልክቶ ውይይት ያደርጋሉ ብለዋል፡፡
የምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ ላይ ብቻ ሳይሆን፤ ለኢህአዴግ ያደላው የምርጫ ሜዳ ለሁሉም እኩል እንዲሆን፤ የህግ የበላይነት እንዲከበር፤ የሚዲያ አጠቃቀም ፍትሃዊ እንዲሆን እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
ለዚህም 13 ነጥቦችን የያዘ የውይይትና የድርድር ጥሪ የሚያቀርብ ደብዳቤ በ33ቱ ፓርቲዎች ተዘጋጅቶ፡፡ ሰኞ ለጠ/ሚር ሃይለማርያም ደሳለኝ ያስገባሉ ብለዋል - አቶ አስራት፡፡
ደብዳቤው ለፓርላማ አፈ ጉባኤ፣ ለሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና ለኢህአዴግ ጭምር እንደሚላክ አቶ አስራት ገልፀው፤ የ33ቱንም ፓርቲዎች ማህተም ለማሟላት ከየክልሉ ማሰባሰብ አስቸጋሪ ቢሆንም አድርገነዋል ብለዋል፡፡

Read 3926 times

Latest from