የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋንና የተቃዋሚ ፓርቲ አባል አንዷለም አራጌን ጨምሮ የ24 ተከሳሾችን ጉዳይ በቅርበት ሲከታተሉ መቆየታቸውን የጠቀሱት የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናት፤ በተከሳሾቹ ላይ የተሰጠው ብያኔ ከሰብዓዊ መብት መርህ ጋር የሚጣጣም አይደለም ብለዋል፡፡
የፓርላማ አባላቱ በአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ከሚመራው መንግስት ጋር ግንኙነት በሚፈጥሩበት ሁኔታ ላይ ተከፋፍለው የነበረ ቢሆንም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ቀውስን ለማስወገድ የአገሪቱ አፋኝ ህግ መከለስ አለበት በሚለው ላይ ለመስማማት ችለዋል ተብሏል፡፡
በ24ቱ የሽብርተኝነት ተከሳሾች ላይ ስለተሰጠው የፍርድ ብያኔ አስከፊነት የተናገሩት በአውሮፓ ህብረት ምክትል ፕሬዚዳንትና የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ ካትሪን አሽተን፤ ለህጋዊ የፍርድ ሂደቱ እውቅና በመስጠትና እያንዳንዱ ሀገር ዜጐቹን ከሽብርተኝነት ለመከላከል ያለውን ሉአላዊ መብት በመገንዘብ፣ የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ዲፕሎማት በሰጡት መግለጫ “በፀረ - ሽብርተኝነት ህጉ ውስጥ የሽብርተኝነት ወንጀሎችን በተመለከተ የተቀመጠው ድንጋጌ ግልጽነት ስለሚጐድለው በኢትዮጵያ ህገመንግስት የተከበሩትን ሃሳብን የመግለጽና የመደራጀት መብትን ይጐዳል” ብለው እንደሚሰጉ ተናግረዋል፡፡